Tuesday, 01 October 2024 08:42

ከድሬዳዋ መገንጠያ እስከ ጂቡቲ ድረስ ያለው መንገድ ብልሽት ገጥሞታል ተባለ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በብልሽቱ ምክንያት ተሽከርካሪዎች ለዕንግልት እና ተደራራቢ ወጪዎች መዳረጋቸው ተጠቁሟል

ከድሬዳዋ መገንጠያ እስከ ጂቡቲ ድረስ ያለው 200 ኪሎሜትር መንገድ ብልሽት “ገጥሞታል” ተብሏል። በዚህም ሳቢያ ተሽከርካሪዎች ለዕንግልት እና ተደራራቢ ወጪዎች መዳረጋቸው ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ብርሃኔ ዘርዑ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፣ ከድሬዳዋ መገንጠያ ቢኬን እስከ ጂቡቲ ወደብ መግቢያ ድረስ ለብልሽት ከተዳረገ ከሰባት ዓመት በላይ እንደሆነ አመልክተዋል። አክለውም፣ በዚሁ መስመር ላይ እየተሰሩ ያሉ መንገዶች ቢኖሩም ለአገልግሎት ክፍት አለመሆናቸውን ጠቅሰዋል።

“በዚህ የተነሳ እየሄድን ያለነው በተለዋጭ መንገድ ነው።” ያሉት አቶ ብርሃኔ፣ ተሽከርካሪዎቹ የሚጓዙት በጋላፊ መስመር መሆኑን ገልጸዋል። “ይሁንና ይህ መንገድ የመኪና መለዋወጫን የሚያበላሽ፣ ጊዜን የሚወስድ እና ተሽከርካሪዎች እንዲወድቁ የሚዳርግ ነው” ብለዋል።

ለአሽከርካሪዎች የሚሰጠው የጉዞ ፈቃድ በጋላፊ መስመር በኩል በመሆኑ፣ አሽከርካሪዎቹ በደወሌ መስመር በኩል ያለፈቃድ በማሽከርከራቸው ምክንያት ከ5 ሺህ እስከ 10 ሺህ ብር ድረስ መቀጮ እንደሚከፍሉ ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።

ነገር ግን በጋላፊ መስመር ከማሽከርከር ይልቅ መቀጮ እየከፈሉም ቢሆን ሾፌሮች በጋላፊ በኩል ማሽከርከሩን “ይመርጣሉ” በማለት የሚያስረዱት አቶ ብርሃኔ፣ “ምክንያቱም አንድ መኪና በዚያ መስመር ላይ ከወደቀ ወዲያው ከመንገድ እንዲነሳ አይደረግም። እንዲያውም ተጨማሪ መኪናዎች እስኪወድቁ ድረስ ነው የሚጠበቀው። የጂቡቲ የዕቃ ማንሻ ማሽን (ክሬን) እስኪመጣ ድረስ ይጠበቃል። ምክንያቱም የኛ ክሬን እንዲገባ አይፈቀድም። በተደጋጋሚ የራሳችንን ክሬን ለማስገባት ብዙ ጊዜ ጠይቀናል። ምላሽ ግን አልተሰጠንም” ሲሉ ተናግረዋል።

ይህን ተከትሎ ለክሬን እና ሌሎች ወጪዎች ከ400 ሺህ እስከ 800 ሺህ ብር ድረስ ክፍያ እንደሚጠየቅ ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል። በተጨማሪም፣ ክሬኖቹ አሮጌ ከመሆናቸው የተነሳ ለብልሽት ከተዳረጉ እንደገና ተጠግነው እስከሚመጡ ድረስ አንድ ወር እንደሚፈጅ ነው አቶ ብርሃኔ የሚያነሱት።

እንዲሁም በመንገዱ ብልሽት ምክንያት ሾፌሮች ለኩላሊት እና ሌሎች መሰል በሽታዎች እየተጋለጡ እንደሚገኙ የተናገሩት አቶ ብርሃኔ፣ “ችግሩ ከአቅማቸው በላይ የሆነባቸው የከባድ መኪና ሾፌሮች የስራ ዘርፋቸውን እየቀየሩ ወደ ራይድ ታክሲ አሽከርካሪነት ፊታቸውን እያዞሩ ነው” በማለት አብራርተዋል።

ፕሬዝዳንቱ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ለመንገዱ ብልሽት በቂ ትኩረት እንዳልሰጠው የገለጹ ሲሆን፣ መንገዱ የአገሪቱ የገቢ እና ወጪ በር መሆኑን አውስተው፣ “ከተሽከርካሪ ጥገና እና ከሌሎች ወጪዎች ጋር በተያያዘ እንደአገር ዋጋ እያስከፈለን ነው። ‘ወይ መንግስት ያድሰው፣ ወይም እኛ ገንዘብ አዋጥተን እንዲታደስ እናድርገው’ እያልን ነው። እኛ ማሳሰብ የምንፈልገው ከፍተኛ ባለስልጣናት ጉዳዩን በጥልቀት እንዲያጤኑት ነው።” ብለዋል።

አቶ ብርሃኔ አያይዘውም፣ በፀጥታ ችግር ሳቢያ ሾፌሮች ለዕገታ፣ በክልሎች አለአግባብ ለሚጠየቅ ክፍያ፣ ለመንገድ መዘጋትና ሌሎችም ችግሮች ከፍተኛ አደጋ እንደሚዳረጉ አመልክተው፣ እርሳቸው የሚመሩት ፌዴሬሽን ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው ድንጋጌዎች መሰረት ሰላማዊ ኢንዱስትሪ መስፈኑን ማረጋገጥ ዋነኛ ዓላማ መሆኑን በማስታወስ፣ የአሰሪው መብት እንዲከበር ጥሪ አቅርበዋል።

Read 812 times