Saturday, 05 October 2024 20:43

በአዋሬ የታየው የመልሶ ልማት ትግበራ

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(3 votes)

 ”ምነው እናታችን በሕይወት ኖራ ይህን ባየች!”

ከ7 ዓመት በፊት፤ ከአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት በስተምሥራቅ በሚገኘው መንደር ወስጥ፤ ለ4 ዓመት ያህል የግለሰብ ቤት ተከራይቼ ኖሬያለሁ፡፡ በዚህ ምክንያት በተለይ አዋሬ ገበያን በቅርበት አውቀዋለሁ፡፡ ‹‹ሙደሲር ጮርናቄ›› ሻይ ቤትን ጨምሮ በቅርብ የማውቃቸው ሰዎችም ነበሩ፡፡ ቅዳሜ መስከረም 4 ቀን 2017 ዓ.ም ጠዋት 5 ሰዓት አካባቢ ወደ አዋሬ ሄጄ፤ በወዳጄ አቶ ዳዊት ሱቅ አረፍ ባልኩበት ያየሁት ነገር ቀልቤን ሳበው፡፡ በዕለቱ ‹‹እንኳን ደስ አለህ/ አለሽ›› እየተባባሉ የሚተቃቀፉና የሚጨባበጡ ብዙ ሰዎች ነበሩ፡፡  
የአዋሬ ገበያ ለዳግም ልማት ሲፈርስ፤ ከስራ ቦታቸው ተፈናቅለው ከነበሩት ውስጥ፤ 70 የሚደርሱ ነጋዴዎች በአዳዲሶቹ ሕንፃዎች ላይ ሱቅ በዕጣ ያገኙበት ዕለት ስለነበር ነው፤ ደስታ የተሰማቸው ሰዎች ተበራክተው የታዩት፡፡ በመጀመሪያው ዙር በዕድሉ ተጠቃሚ የነበረውና በልብስ ስፌት ሙያ ላይ ተሰማርቶ የሚገኘው ዳዊት እንዳጫወተኝ፤ የዕለቱ መርሐ ግብር ሁለተኛው ሲሆን፤ አዋሬ ገበያ ለዳግም ልማት ፈርሶ፤ በአካባቢው አዲስ በተሠሩት ሕንፃዎች ላይ 400 ለሚደርሱ ነዋሪዎችና 200 ለሚሆኑ ነጋዴዎች ምትክ ቤትና ሱቅ ተሰጥቷቸዋል፡፡
አንድ መቶ ዓመት ዕድሜ ከነበረው ከሥላሴ ገበያ ቀጥሎ፤ ረጅም ዘመናት ካስቆጠሩ የአዲስ አበባ ገበያዎች አንዱ የነበረው፣ ‹‹ጎስቋላው›› አዋሬ ገበያን በቅርበት ለሚያውቅ ሰው፤ አሁን የሚታየው ነገር ‹‹ተአምር ነው !›› የሚያሰኝ  ነው፡፡ ሰፊ ከሆነው የአዋሬ መንደር አንጻር አጠቃሎ ድምዳሜ መስጠት ቢያስቸግርም፤ ገበያውን ማዕከል አድርጎ አሁን ተግባራዊ የሆነው የልማት ስራ ግን በአካባቢው ላይ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣቱ የማይካድ ነው፡፡  
የገበያው መሥራቾች ወደዚህ ሠፈር ከመምጣታቸው በፊት፤ 4 ኪሎ በበአለወልድ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ፣ ‹‹በሥላሴ ገበያ›› ነበር የሚገኙት፡፡ በ1920ዎቹ አካባቢው ለልማት ተፈልጎ ነጋዴዎቹ ሲባረሩ ለሁለት ተከፋፍለው፤ ከፊሎች በንግሥት ዘውዲቱ ዘመን ማረሚያ ቤት ወደነበረው (በኋላ ፖሊስ ጋራዥ) አካባቢ ሲሄዱ፤ ሌሎቹ ወደ አዋሬ መጥተው ሰፈሩ፡፡
ለገበያው ብቻ ሳይሆን ለአካባቢውም መጠሪያ የሆነው፤ አዋሬ የሚለውን ስያሜ ‹‹አቧራማ›› ከነበረ ስፍራ ጋር በተያያዘ እንዳገኘ ይነገራል፡፡ ገበያው የመጀመሪያ ማረፊያው ከነበረው ‹‹አቧራማ ሜዳ›› (አሁን በጀርመኗ ላይፕዚግ ከተማ ስም የተሰየመው አደባባይ)፣ ወደ ታች ወርዶ ግንፍሌ ወንዝ ስር በመስፈር ለብዙ ዓመታት አገልግሎት ሰጥቷል፡፡ ገበያው በመጨረሻ ዘመኑ ይታይበት የነበረው ጉስቁልና በቃላት ለመግለጽ የሚያስቸግር ነበር፡፡ በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ለፓርላማ የሚወዳደሩ አንድ ዕጩ፣ ‹‹ገበያውን ማልማት›› የቅስቀሳቸው አንድ አካል የነበረ ቢሆንም፤ ለፓርላማ ማሸነፍ ስላልቻሉ ህልማቸው የውሃ ሽታ ሆኖ እንደቀረ ይነገራል፡፡
በቀደመው ዘመን ‹‹የገረድ መፈንጪያ›› የሚል ዝና የነበረው አዋሬ ገበያ፣ በኋላ ላይ ‹‹የአይጥ መፈንጫ›› ሆኖ ነበር፡፡ መገበያያ ብቻ ሳይሆን መኖሪያም ጭምር ሆነው የሚያገለግሉ የቆርቆሮ ሱቆች የሚበዙበት ስፍራ ስለነበር በተደጋጋሚ ለእሳት አደጋ ተጋልጧል፡፡ በተለይ ክረምት ላይ ግንፍሌ ወንዝ ከበስተኋላቸው የሚያፏጭባቸው ባለሱቆችና ነዋሪዎችም ብዙ ዓመታት በስጋት አሳልፈዋል፡፡
ከሰሜን አዲስ አበባ ተነስቶ ዑራኤል ሲደርስ ከቀበና ጋር የሚቀላቀለው ግንፍሌ ወንዝ፤ ከሚያቆራርጣቸው መንደሮች አንዱ አዋሬ ነው፡፡ ግንፍሌ ወንዝ በአዋሬ አካባቢ አሁን ተግባራዊ የሆነለት ስኬታማ ስራ፤ ከ10 ዓመት በፊት የአዲስ አበባ ፅዳት አስተዳደር ቢሮ፣ ለአዲስ አበባ ወንዞች በእቅድ ደረጃ ይዞት የነበረው ሀሳብ ነው፡፡ ቢሮው የአዲስ አበባ ወንዞችን ከነዋሪዎች በ300 ሜትር ርቀት የመከለል እቅድ ነበረው፡፡ ለዚህም ተግባራዊነት ራስ መኮንን ድልድይ አካባቢ ነዋሪዎችን ከወንዙ ዳር በማንሳት አንድ የመናፈሻ ስፍራ አልምቶ ነበር፡፡
የአዋሬ ገበያ ልማት እንዲህ ዓይነት እቅድና ሀሳቦች እውን እንዲሆኑ ከማስቻሉም በላይ፤ የመኪና ማቆሚያ ፓርክ፣ የሕፃናት መዝናኛ ስፍራ ለአካባቢው ማህበረሰብ አስገኝቷል፡፡ በ1983 ዓ.ም ‹‹የደርግ ሰራዊት ሲበተን›› ወደ አካባቢው መጥተው ‹‹ጥይት ቤት›› አጥር ስር ጨረቃ ቤት ሰርተው ይኖሩ ለነበሩትም የተሻለ ቤት እንዲያገኙ አስችሏል፡፡ ለአዋሬ ምንዱባኖች ፓስቴና ጮርናቄ ከሻይ ጋር በቅናሽ ያቀርብ የነበረው ‹‹ሙደሲር ሻይ ቤት››፣ ወደ ሕንፃ ተዘዋውሮ ወደ ካፍቴሪያነት አድጓል፡፡ እናቱ ብዙ ዋጋ ከፍለው ባቆዩለት የቆርቆሮ ሱቅ ስራ ጀምሮ፤ አሁን በምትክነት ባገኘው ሱቅ የልብስ ስፌት ሙያውን ማስቀጠል የቻለው አቶ ዳዊት፤ ‹‹ምነው እናታችን በሕይወት ኖራ ይህን ባየች›› ብሏል፡፡
ቅዳሜ መስከረም 4 ቀን 2017 ዓ.ም በድንገት ተገኝቼ በአዋሬ ያየሁት ነገር የሩቅና የቅርብ ሁለት ትዝታዎቼን እንዳስታውስ ምክንያት ሆኖኛል፡፡ አንደኛው የዛሬ 20 ዓመት ለአዲስ አበባ ከተማ የመኖሪያ ቤት ችግር፤ የጋራ መኖሪያ (ኮንደሚኒየም) ሕንፃዎችን መገንባት ዘላቂ መፍትሔ እንደሚያስገኝ ተነግሮ፤ እንቅስቃሴ ከተጀመረለት መርሐ ግብር ጋር በተያያዘ በወቅቱ የቀረበው ዕቅድና ማብራሪያ ነው፡፡
እቅዱን ድንቅና አጓጊ ካደረጉት ነገሮች መሐል፤ በተለይ የተፋፈጉ የቀበሌ መኖሪያ ቤቶች ባሉባቸው የአዲስ አበባ ሠፈሮች፤ ማንም ነዋሪ ከኖረበትና ከለመደው አካባቢ ሳይፈናቀል፤ በመልሶ ማልማት ይተካካል የሚለው አንዱና ዋነኛው ነበር፡፡ በዚህ ዓላማና እቅድ መሠረት፤ በ1996 ዓ.ም በመሐል አዲስ አበባ መንደሮች ተገንብተው ለነዋሪዎች የተላለፉ የኮንደሚኒየም መኖሪያ ሕንፃዎች ነበሩ፡፡
በዚህ መሐል ከ1997 ዓ.ም ሦስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ‹‹ትርምስ›› ሰለባ ካደረጋቸው ነገሮች መሐል፤ ለከተማዋ የመኖሪያ ቤት ችግር ዘላቂ መፍትሔ ያስገኛል የተባለለት ፕሮጀክት አንዱ ነበር፡፡ ሚያዚያ 29 ቀን 1997 ዓ.ም ኢሕአዴግን ‹‹ደግፎ››፤ ሚያዚያ 30 ቀን 1997 ዓ.ም በተቃራኒው የቆመው ‹‹ሕዝብ›› እንዲቀጣ ከተደረገባቸው ነገሮች አንዱ፣ ከኮንደሚኒየም መኖሪያ ቤቶች ጋር ተያይዞ የሚተገበር ሆነ፡፡
የአዲስ አበባ ነዋሪ ከዚያ ቀደም ስማቸውን እንኳን ሰምቶ የማያውቃቸው መንደሮች ለኮንደሚኒየም ሕንፃ ግንባታ የተመረጡት ከዚያ በኋላ ነበር፡፡ የጋራ መኖሪያ ሕንፃዎቹ ከተገነቡም በኋላ የመሐል አዲስ አበባ ነዋሪዎችን ‹‹በተጠና መልኩና ታስቦበት በተለያየ አቅጣጫ እንዲበተኑ ተደርጓል›› የተባለውም ያንን ተከትሎ ነበር፡፡ ለ‹‹በቀል›› የታሰበው ጉዳይ ሌላ ‹‹በደል›› ማስከተሉ የቀሰቀሰው ቁጣ እያደገ መጥቶ፣ ለመጋቢት 2010 ዓ.ም ለውጥ የራሱን አስተዋጽኦ አደረገ፡፡
መልካምና ድንቅ የነበረው ሀሳብ መስመሩን ስቶ እንዲሄድ ከተደረገ በኋላ፤ ሌሎች ችግሮች እንዲፈጠሩም ምክንያት ሆኗል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ የመኖሪያ ቤት ችግር ከመቀረፍ ይልቅ እየተባባሰ ስለመጣ፤ በመዲናይቱ 5ቱም በሮች የጨረቃ ቤቶች ግንባታ እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ የሸገር 5 ከተሞች ከተመሠረቱ በኋላ፤ ጨረቃ ቤቶቹን ከማፍረስ ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ውዝግብ ምን ይመስል እንደነበር ነጋሪ የማያሻው የቅርብ  ትዝታችን ነው፡፡
በቅርቡ አዋሬ ገበያን ማዕከል አድርጎ የተሰራው የልማት ስራ፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ነባር ነዋሪዎችንና ነጋዴዎችን ወደነበሩበት መመለስ እንዳስቻለው፤ የ1996 ዓ.ም የልማት እቅድም፤ ከበቀልና ቂም በፀዳ መልኩ፤ እንደታሰበውና እንደተወጠነው ቢተገበር ኖሮ፤ የመኖሪያ ቤት ችግርን ከመቅረፍም በዘለለ፤ በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በማህበራዊ ጉዳዮች በርካታ ጥቅሞችን፤ ለአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱና ሕዝቧ ባስገኘ ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ በአዋሬ ለአንዲት እናት ቤት በማደስ የጀመሩት ስራ ተስፋፍቶና አድጎ፤ በልማት ስራው መጪው ትውልድ ብቻ ሳይሆን ዛሬ ያለውም ሕዝብ (ያውም ከነበረበት አካባቢ ሳይፈናቀል) ተጠቃሚ የሚሆንበት ‹‹ታሪክ ተሠርቷል››፡፡ ቀጥሎ የሚመጣው ጥያቄ በአዋሬ ገበያ ላይ የታየው አዎንታዊ ለውጥ ወደ ሌሎች እንዴት ሊጋባ ይችላል የሚለው ይሆናል፡፡
ከተጠቃሚነት አንጻር አቶ ዳዊት፤ ‹‹ምነው እናታችን በሕይወት ኖራ ይህን ባየች›› እንዳለው፤ በተቃራኒው በልማት ሰበብ ተጎዳን የሚሉ ደግሞ ‹‹ወላጆቻችን ይህንን ጉድ እንኳን በሕይወት ኖረው አላዩ›› ሲሉም ይሰማል፡፡ እንዲህ አይነት ክፍተትና ልዩነቶችን ሙሉ ለሙሉ መድፈን ይቻላል ብሎ መገመት ቢያስቸግርም፤ የተጠቃሚዎችን ቁጥር አብዝቶ የተጎጂዎቹን ቁጥር ለማሳነስ ግን፤ በአዋሬ የታየው የመልሶ ልማት ትግበራ ወደ ሌሎች እንዲተላለፍ የሚያስመኝ ነው፡፡   
***
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 675 times