አንድ ኤርትራዊ እዚያው ኤርትራ ቤተ መንግስት ስብሰባ ላይ አንድ ሐሳብ አመጣ፡፡ ይኼ የኤርትራ ሕዝብ ኢትዮጵያዊ ነኝ ይላል፡፡ ኢትዮጵያን ይወዳል፤ ሆኖም ኢትዮጵያን አያውቅም፡፡ እናም እስቲ ገበሬውንም፣ ሠራተኛውንም ተራ ተራ አስገብተን፣ ወደ መሃል ሀገር ወደ ደቡብም፣ ወደ ሰሜንም፣ ወደ ምዕራብም እየወሰዳችሁ፣ ኢትዮጵያ ሀገሩ ምን እንደምትመስል አሳዩ፡፡ የሚል ሐሳብ አቀረበ፡፡ ኋላም አራት መቶ አምስት መቶ ሰው በአንድ ጊዜ እያሰባሰብን፣ አሩሲ፣ ሲዳማ፣ ወለጋ በሙሉ ኢትዮጵያ ሀገሩንም ሰውንም እያሳየን፣ እንደ ትውውቅም እንደ ልምድ ልውውጥም የማድረግ ሙከራ አደረግን፡፡ በሌላ ጊዜ ኤርትራ ስሄድ ሰበሰብኩኝና፤ “እንዴት አገኛችሁት ሀገራችሁን?” ብዬ ጠየቅሁ፡፡ በመጀመሪያ በከፍተኛ ጭብጨባ ድጋፋቸውን አሰሙ፡፡ በኋላም አመስግነው ሲያበቁ፤ “በእርግጥም ኢትዮጵያን አናውቃትም” አሉ፡፡
ኤርትራ ጥሩ ሀገር አይደለም፤ ትንሽ ሀማሴንና ከረን አካባቢ ካልሆነ በቀር ለም አይደለም፡፡ ሳር የለም፤ ሜዳ የለም፡፡ በምጽዋ እሳት የሆነ አሸዋ ነው ያለው፡፡ ቆላው አቧራና ሜዳ ነው፤ ሌላው ደግሞ የድንጋይ ተራራ ነው፡፡ አየሩ ሁለት ነው፤ እርር ንድድ ያለ ቆላ እና እላይ ያለው ደጋ፡፡ ደጋው መሬቱ ወጣ ገባ፣ ድንጋያማ ስለሆነ፤ መሬቱ ለእርሻ ይኼን ያኽል የሰጠ አይደለም፡፡ ዝናቡ በቋሚነት እንዲኽ ነው ተብሎ የሚያስተማምን አይደለም፡፡ ደጋው ነፋሻማ ነው፣ አልፎ አልፎ ባልታመነ መልኩ ኃይለኛ ዝናብ ይዘንባል፣ ሌላ ጊዜ ጨርሶ ይጠፋል፡፡ ቆላው ግን በአመዛኙ ዝናብ የለውም፡፡ ስለዚኽ ቆላው በከብት አርቢነት ነው የሚኖረው፡፡ ፍየል፣ በጎች፣ ግመሎች እነዚኽን ነው የሚያረባው፡፡ አብዛኛው ሕይወቱና የንግድ ግንኙነቱ ከሱዳን ጋር ነው፡፡ ከመሃል ሀገር ጋር ያለው ግንኙነት ውሱን ነው፡፡
የትግራይ አማጽያን ከመጀመሪያው አንስቶ የቋንቋና የመልከዓ ምድርን ተቀራራቢነት በማስላት ከኤርትራ አማጽያን ጋር ለመለጠፍ ጥረት አድርገው ነበር፡፡ ኤርትራውያን ግን “ጥያቄያችን ከትግሬ የተለየ ነው” በማለት የትግራይ አማጽያንን አላቀረቧቸውም፡፡ በመጀመሪያ ነገር፣ በኤርትራ ከጣሊያኖቹ ጋር ብዙ በመኖር ከሞላ ጎደል የክልላዊ የሆነ ብሔርተኝነትና ናሽናሊዝም ጎልብቷል፡፡ እውነቱን ለመናገር፣ በጊዜው በነበረው ኤክስፖዠር አኳያም በንቃተ ህሊና ኤርትራውያኑ የተሻሉ ነበሩ፡፡ ወትሮም ካላቸው የተዋጊነት ጸባይ ጋር ንቃተ-ህሊናቸው ከፍ በማለቱና ለምንድን ነው የምንዋጋው? የሚለውን ጠንቅቀው ማወቃቸው አድቫንስ እንዲያደርጉ አደርጓቸዋል፡፡
የትግራይ ፖለቲከኞች ምንድን ነው ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ወደ ኤርትራ ወገን የሚስባቸው? እንዴትስ ሆኖ ነው እነርሱ ከኤርትራ ጋር ሊቀላቀሉ የሚችሉት? ኤርትራ ሌላ፤ ትግራይ ሌላ! ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ ቢሆን ሌላውን ይዞ ሲዋጋ ቆይቶ እንደ ተቀሩት የኢትዮጵያ ግዛቶች እነርሱንም ጥሎ ነው የወጣው፡፡ ከኤርትራው ጋር ስናስተያየው፣ ትግራይ በምንም ምክንያት ከኢትዮጵያ የሚገነጠልበት ምክንያት የለም፡፡
ከእዚያ በላይ ኤርትራውያን እርስ በእርስ ስለሚተባበሩ፣ እነርሱን (የትግራይ አማጽያንን) እንደ በለጧቸው ሁሉ እኛንም ብዙ እንዲያስከፍሉን አቅም ሆኗቸዋል፡፡ በሌላ በኩል፤ የትግራይ አማጽያን (ወያኔዎች) በብሔርተኝነት፣ አማራን በመጥላት፣ ታሪክ እየቆጠሩ “ጥንት እኛ ነበርን አክሱምንና ሌላን ሌላን የገነባን፣ ያለንን ሥልጣንና ኃያልነታችንን የነጠቀን አማራ ነው” የሚል አጓጉል ነገር በህብረተሰብ ውስጥ ለመርጨት ይጥሩ ነበር፡፡
የኤርትራ አማጽያን መጀመሪያም በንጉሡ ዘመንና በለውጡ ሂደት ወቅት ሠራዊታችን ተመናምኖ፣ ተዳክሞ በነበረበት ጊዜ እየገፉ እየገፉ ብዙ አስከፍለውን ነው አስመራን የከበቡት፡፡ እንደሚታወቀው ሁለቱም አንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች ናቸው፡፡ ሁለቱም አምሳያ ቢሆኑም በየራሳቸው የመኖሪያ ክልል የሚኖሩ ሕዝቦች ናቸው፡፡ ከዚኽም በተጨማሪ በየትም አካባቢ ሊፈጠር እንደሚችለው በታሪክ፣ በኑሮና፣ በህይወት ዘይቤ ሁለቱ የተለያዩ ናቸው፡፡ ይኼም ሁኔታ በአብዛኛው ከጊዜ በኋላ በውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነትና በወረራ የተፈጠረ ነው፡፡ የሰሜኑን ክልል ጣልያኖችም፣ ግብፆችም፣ ዐረቦችም እየተመላለሱ ብዙ ችግር የፈጠሩበት ሆኖ የኖረ በመሆኑ፣ ያ ሁኔታ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ልዩ ልዩ መልክ ከማላበሱ ባሻገር፣ በክልሉ ከፍ ያለ የውጊያ ልምድ ሰጥቷል፡፡ የአካባቢያዊነት ስሜትንና የብሔርተኝነትን ባኅርይ ፈጥሯል፡፡ ለዚህ ሁሉ ምክንያት በዚያም ሆነ በዚህ በኩል “አንበገርም ሀገር አናስወርርም” ከሚል መከላከል፣ የረጅም ጊዜ የተዋጊነት ሥነ-ልቦና ተገንብቷል፡፡
በአልበገርም ባይነት ለብዙ ሺህ ዓመታት ተከባብረን፣ ኋላ ላይ ተሸንፈን ሰሜኑ (ኤርትራ) በጣሊያኖቹ ቁጥጥር ሥር ሲውል፣ በስድሳ ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከጣሊያኖቹ ጋር በመኖር አዳዲስ ሁኔታዎች ተፈጠሩ፡፡ ይሄም ሁኔታ በእነዛ ዓመታት አንደኛ፣ ከኢትዮጵያዊነት ይበልጥ በተለየ መልኩ ኤርትራዊ ብሔርተኝነት ተገንብቷል፡፡ ሁለተኛ፣ “ኢትዮጵያ ለጠላት ባትሰጠን ልትከላከልልን ሲገባ፣ ኋላም ምኒልክ ሊዋጋና ጣሊያንን ማባረር ሲችል፣ ለጣሊያን ሸጦናል” ብለው ያምናሉ፡፡ ይሄንን ሐሳብ ከመሃል ሀገር ሰዎችም አንዳንዶች ይጋሩታል፡፡
በግሌ ግን ይሄን ሐሳብ ተንተርሼ ለመፍረድ አስቸጋሪ ይሆንብኛል፡፡ እርግጥ ነው በዚያ ጊዜና ቦታው ላይ የለንም፡፡ በራሱ አህያና አጋሰስ የራሱን መሳሪያና ጥይት ይዞ፣ በሶና ቆሎ እየበላ ያን ሁሉ ነገር የሠራ ሠራዊት፣ ከእዚያ ተነስተህ ሂድና እንደ ገና አስመራና ምጽዋ ተዋጋ ቢባል፣ በጦርነት ጊዜ ያለውን ችግር ስለማውቅ፣ በእውኑ “ምኒልክ ሲቻላቸው ነው ሳይፈልጉ የቀሩት” ብሎ ለመፍረድ እቸገራለሁ፡፡
ብዙ ሰዎች ግን “ይቻላል፤ ጣሊያን ተፍረክርኮ እየሸሸ ነው፤ ቢከተሉት እስከ ባህሩ ድረስ አይቆምም፡፡ ከዚያ በኋላ አካባቢው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከውጭ ወራሪዎች ነጻ ይሆን ነበር” ይላሉ፡፡ “ያ የተተወ ሁኔታ እንደገና መልሶ ተደራጅቶ አርባ ዓመት አድብቶ ኢጣሊያ በ1928 ኢትዮጵያን ወረረ፡፡ ይሄ የምኒልክ ጥፋት ነው” ብሎ የሚያምን ከመሃል ሀገር ብዙ ሰው አለ፡፡ ኤርትራውያኑ ደግሞ “ሆን ብሎ ነው፣ ለመሳሪያ ነው የሸጠን” ብለው ያምናሉ፡፡
በነገራችን ላይ፣ ወታደሩም ውስጥ ሲቪልም ውስጥ እንደ ቀልድ እንደ ፌዝ፤ “እናንተ የመውዜር ሽያጮች” እየተባለ ይፎተት ስለነበር፣ ኤርትራውያኑ “ተሸጠናል” ነበር የሚሉት፡፡ ምኒልክ በደቡብና ምዕራብ ያን ያህል ተጋድሎ አድርገው ሀገሩን ሲያድኑ፣ ቀይ ባህርንና ኤርትራን የመሰለውን ሀገር ሸጠዋል (እየቻሉ ሳይከላከሉ ቀርዋል) መባላቸው ለማመን ያስቸግረኛል፡፡ “የዚህ ጉዳይ ብልቱ ምንድን ነው?” ብሎ መጠየቅ ከሁላችንም የሚገባ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ ሻዕቢያ እና የሰሜኑ አማጽያን፣ ይሄን “ተሸጠናል” የሚለውን የተንኮል ፕሮፓጋንዳ፣ የሕዝብን ልብ ለማስሸፈት ከተገቢው በላይ አስተጋብተውታል፡፡ በመካከላችን ልዩነቱ እንዲሰፋ የሚፈልጉ ወገኖች ጥላቻውን ለማክረር ይኼንን ሬቶሪክ ተጠቅመውበታል፡፡ ሕዝቡ ውስጥ በሚገባ እንዲሠራጭ አድርገውታል፡፡ አዲስ የተወለደው ወጣቱ ሁሉ ሳይመረምረው ውጦታል፡፡ ሁሌም ቢሆን የሀገራችን ዋና ችግር ይኼው ነው፡፡
በኤርትራ የጣሊያኖች ጣልቃ ገብነት ባይከሰት፣ ከላይ ያነሳነው በአካባቢው የተፈጠረው ስሜት ባይመጣ ኖሮ፣ ያ ሀገር የስልጣኔዎቻችን በር፣ የመጀመሪያው የመንግሥታችን ማዕከል ከመሆኑ አንጻር ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ሁሉ የተሻለ የኢትዮጵያዊነት ስሜት መፍጠር የነበረበት ቦታ ነበር፡፡ ነገር ግን ያ ሳይሆን ቀርቶ የተቀረነው ትውልድ ሁሉ ስንት ከፈልንበት?... ስንት?!… እኔ እንጃ… የኢትዮጵያ ሕዝብ የከፈልነውን ዋጋ በቅጡ የሚያውቀው አይመስለኝም፡፡ ስንቱ ደማ!? አስራ ሰባት ዓመት ሀገር በማልማትና ብዙ ግንባታ በመሥራት ፈንታ፣ ሁል ጊዜ ሥራችን ጦርነት ነው፣ መሞት ነው፤ መግደል ነው፡፡
(ከይታገሱ ጌትነት ገበየሁ ”መንግሥቱ ኃ/ማርያም፤ የስደተኛው መሪ ትረካዎች”፤ ከገጽ 126-129 የተቀነጨበ)
Published in
ማራኪ አንቀፅ