Saturday, 12 October 2024 13:04

የባህር ዳርቻ ወፍና የባህር አሣ ሲታገሉ፣ አሣ አጥማጅ ይጠቀማል

Written by 
Rate this item
(7 votes)


        ከሊዮ ቶልስቶይ ተረቶች ውስጥ እንዲህ የሚል ይገኝበታል፡፡
አንድ ንሥር በዛፍ ላይ  ጎጆ ትሠራለች፡፡ እዚያም  ውስጥ ጫጩት ትፈለፍላለች፡፡ አንዲት አሳማ ደግሞ ግልገሎቿን ይዛ ዛፉ ሥር ትቀመጣለች፡፡ ንሥሩዋ ሩቅ በርራ አድና ልጆቿን ትቀልባለች፡፡ አሳማዋ ዛፉ ስር እየኖረች እጫካው ውስጥ እየገባች፣ እያደነች ውላ ማታ ለልጆቿ ምግብ ታመጣላቸዋለች፡፡ በዚህ ዓይነት ንስርና አሳማ እንደ ጎረቤት እየተማመኑ፣ እየተዋደዱ፣ አንዳቸው አንዳቸው ላይ ክፉ ላያስቡ ተስማምተው መኖራቸውን ይቀጥላሉ፡፡ በመሰረቱ ንሥርና አሳማ በተፈጥሯቸው አንዳቸው ያንዳቸውን ግልገል ካገኙ የማይምሩ፣ ተፃራሪ ፀባይ ያላቸውና ሊጠፋፉ የሚችሉ ናቸው፡፡ አንድ ቀን አንዲት አሮጊት ድመት ወደ ሁለቱ ሠፈር መጣች፡፡ የንሥሯንም ጫጩቶች፣ ጡት የሚጠቡትንም  የአሳማዋ ግልገሎች ፣ ልትበላቸው አሰበች፡፡
ወደ ንስሯ ሄዳ፤
“ንሥር ሆይ፣ ለምግብና ለአደን ብለሽ ከእንግዲህ ሩቅ መንገድ እንዳትሄጂ፡፡ ይቺ አሳማ የምትተኛልሽ አይምሰልሽ፡፡ መጥፎ ተንኮል እያሰበችብሽ  ነው፡፡ የዛፉን ሥር እየበጣጠሰችው ነው፡፡ እንደምታይው በየቀኑ የሥሩን አፈር እየማሰች ነው፡፡” አለቻት፡፡ ንሥሯም ስለ ምክሯ አመሰግናት ተለያዩ፡፡
ቀጥላ ደግሞ ወደ አሳማዋ ዘንድ ሄዳ፤
“አሣማ ሆይ፣ ዘንድሮ ጥሩ ጎረቤት አልተዋጣልሽም፡፡ ትላንት ማታ ንሥሯ ለጫጩቶቿ እንዲህ ስትል ሰማኋት፡፤ ወዳጄ ስለሆንሽ ሆዴ አልችል ብሎኝ ልነግርሽ መጣሁ አለች፡፡ አሳማም፤ “ምን አለችኝ እባክሽ?” ብላ  በጉጉት ጠየቀች፡፡
ድመትም፣ “ምን ስትል ሰማኋት መሰለሽ፣ ልጆቼ፤ ከእንግዲህ አትራቡም፡፡ እንዲያውም ጥሩ ጥሩ ግልገል አሳሞች እያመጣሁ እቀልባችኋለሁ፡፡ አይዟችሁ፣ ይህቺ አሳማ የምንኖርበት ድረስ መጥታ ግልገሎቿን መሬት ላይ አፍስሳልናለች፡፡ እናታቸው ራቅ ብላ ስትሄድ ቆንጆ ቆንጆ ግልገሎቿን እያመጣሁ አበላችኋለሁ” አለች፡፡
ከዚህ  ቀን ጀምሮ ንሥር ወደ ሩቅ ቦታ እየሄደች ማደኗን አቆመች፡፡
አሳማዋም ከዚህ ቀን ጀምሮ ወደ ጫካ መሄዷን አቆመች፡፡
የንሥርም ጫጩቶች፣ የአሳማም ግልገሎች ከቀን ወደ ቀን ለረሀቡ እየተጋለጡ ሄዱ፡፡ ውሎ አድሮ፣ የንሥር ልጆች  አንድ በአንድ ከዛፍ ላይ እየተፈነቸሩ ይወድቁ ጀመር፡፡ የአሳማም ግልገሎች  እናታቸው ለመኖሪያ በማሰችው ጉድጓድ ውስጥ ሞተው ይገኙ ጀመር፡፡ አሮጊቷ ድመት የሞቱትን ጫጬቶችና ግልገሎች እያፈራረቀች የተመጣጠነ ምግብ ማለት ይሁ ነው እያለች እየተመገበች ፌሽታ ስታደርግ ከረመች፡፡
ንስርና አሳማ ሲያለቅሱ ሰነበቱ፡፡
***
ከላይ  ዛፉ ከታች መሬቱ ለመኖሪያ ካልተመቸ አገር አማን አትሆንም፡፡  የህዝብ ኑሮ አስተማማኝ አይሆንም፡፡ በዜጎች መካከል መተማመን አይኖርም፡፡ አንድም ፍትሃዊነት እየጠፋ “በጨው ደንደስ በርበሬ ተወደስ ይሆናል፡፡” አንድም ደግሞ ቃልኪዳን ፈርሶ፣ የተደላደሉበት ተንሸራትቶ “ያመኑት ፈረስ ጣለ በደንደስ” ይሆናል፡፡
ከላይ በተረቱ እንዳየነው፤ ተቻችለውና ተስማምተው ለመኖር የሚችሉትን በማናቆር እንጠቀማለን ለሚሉ አለመመቸት ተገቢ ነው፡፡
እጅግ የከረሩ አቋሞች የሚያመጡትን  ጉዳት እንዳንዴ ከህዝብና ከአገር  ጥቅም አንጻር ማየት ተገቢ ነው፡፡ በፓርቲዎች ደረጃ ሲታሰብ፣ የኔ ልማት የሌላው ጥፋት የሚል  እሳቤ ብዙ አያራምድም፡፡ በአገረኛው አባባል፣ “ሞትሽ እውነት በሆነና ልጅሽን ማሳደጉ እኔን በቸገረኝ፣ አለች ጣውንት” እንደተባለው ማለት ነው፡፡
በዓለም ላይ እንደታየው ብዙ  ለሥልጣን የሚታገሉ የፖለቲካ ሃይሎች፣ ሁኔታዎች በውጥረት ሲሞሉ ምክንያታዊ መሆናቸው እየላላ፣ በአጭር ጊዜ መፍትሔ ላይ ብቻ ይተማመናሉ፡፡
ይኸውም አብዛኛው ስሜታዊነትና ጉልበተኝነት የተሞላ ሆኖ ነው የሚገኘው፡፡ ይሄ በፈንታው ሰላም ያሳጣናል፡፡ አንድ ፀሀፊ ስለ ተሳትፎአዊ ዲሞክራሲ ሲጽፍ፤፡ “በጥረት ህዝብን ማሳተፍ የመቻሉን ያህል በጉልበት የተሳትፎውን ፍሬ መከልከል ከቶ አይቻልም፡፡ እንለው  በሀገራችን ዲሞክራሲያዊ  ንፍቀ-ክበብ እንዳይጨልም ማድረግ ወሳኝ ነገር ነው፡፡”
በየትኛውም መልኩ ሰላምንም፣ ዲሞክራሲንም ማጣት አገራችን ዛሬ ልትቋቋመው የማትችለው ዕዳ ነው፡፡ የተረገመ እግር በቅሎም ጫማም ይነሳዋል እንደሚባለው ሊሆን ነው ማለት ነው፡፡
 “ከቶውንም ትላንት የነበረውን ምርጫም ሆነ ፖለቲካ አካሄድ ዛሬ ዛሬ ለምንሠራው ሥህተት መሸፈኛ አሊያም መፀፀቻ የምናደርገው እስከመቼ ነው? ግትርነት፣ ጉልበትና ስሜታዊነት ባላንጣ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ የራስን ወገን እንደሚያሳጣ ቀደምት ፀሐፍት ይናገራሉ፡፡”
ሼክስፒር እንዲህ ይጠይቀናል፡-
 “እልህ እስከምን ይዘልቃል፡፡
የት ድረስ ነው ግትር ጽንፉ
በባላንጣው ሰበብ ምክንያት፣
የራሱን ወገን ማርገፉ?...”
ዲሞክራሲም ስንል በህዝብ መካከል የፖለቲካ ጉልበት የሆነበት ግን የህዝብ ተዓማኒ አገልጋይ የሚኮነንበት፣ አትበጀንም ሲል ህዝቡ በቃኸኝ፣ አትወክለኝም ሊል የሚችልበት የሲቪልና የፖለቲካ መብት  እንዲከበር የሚደረግበት፣ ህዝብ ህጋዊና ህገ-ወጥ የሆነውን ነገር በውል አውቆና መብቱን ተረድቶ ሊያስከብር የሚነሳበት፣ መነሳቱም እንደ ወንጀል  የማይቆጠርበት፣ የማይሰጥ- የማይነጠቅ ነፃነት የሚቀዳጅበት ማለት ነው፡፡ ይህንን ስንልም ዲሞክራሲው ምሉዕ ይሆን ዘንድ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶችንም ያካተተ መሆኑን ከቶም ሳንዘነጋ ነው፡፡
ወደ ሰላምና ዲሞክራሲ የሚያራምደንን ምርጫ አንድ እርምጃ ብለን ----- የምርጫው ዘላቂ ውጤት፣ የድጋሚ ምርጫው ውጤት ቁጥርና አግባብ ያለው ቆጠራ እንዲሁም የታዛቢዎቹ እውነተኛ ውሳኔ፣ የስሞታዎች የተጣራ ውጤት ወዘተ ተደምረው ነው ፍሬ የሚገኘው፡፡ ሁሉም ተፎካካሪ ወገኖች ትልቁን ሃገራዊ ስዕል፣ ዘላቂውን የህዝብ ጥቅም ቀዳሚ አድርገው ካስተዋሉ ነው፡፡ አለበለዚያ ቻይናውያን እንደሚሉት፤ “የባህር ዳርቻ ወፍና የባህር አሳ ሲታገሉ አሳ አጥማጅ ይጠቀማል፡፡”




Read 1644 times