በዓለም አቀፍ ደረጃ መስከረም 16 (September 26) በኢትዮጵያ መስከረም 23 (October 3) ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ ቀን (contraception day) ተከብሯል። ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ (የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት) ለሁሉም የማህበረሰብ ክፍል የቀረበ የህክምና አገልግሎት እንደሆነ ይታወቃል። ይህ አገልግሎት ከሚሰጥበት የህክምና ተቋማት ውስጥ የጤና ጣቢያዎች ይጠቀሳሉ። እናም ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ ቀንን መነሻ በማድረግ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ኮ/ቀ/ክ/ከ ወረዳ 9 ጤና ጣቢያ አመራን። በጤና ጣቢያው የቤተሰብ እቅድ፣ የማህፀን ካንሰር እና የአፍላወጣቶች ቡድን መሪ ከሆኑት ነርስ ሙሉእመቤት ጫኔ ጋር ስለ ቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ያደረግነውን ቃለመጠይቅ እነሆ ለንባብ አቅርበናል።
በወረዳ 9 ጤና ጣቢያ ሁሉም አይነት የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ይሰጣል። ይህ አገልግሎት የመውለጃ እድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ሴቶች የሚሰጥ ነው። እንዲሁም ወንዶችም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ናቸው። እንደ ነርስ ሙሉ እመቤት ጫኔ ንግግር አገልግሎቱ የሚሰጠው በቤተሰብ እቅድ አገልግሎት በሰለጠኑ እና ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች ብቻ ነው።
በወረዳ 9 ጤና ጣቢያ የሚሰጡ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት አይነቶች
የሚዋጥ እንክብል (ለማታጠባ እና ለምታጠባ እናት)
በመርፌ የሚሰጥ (የ3 ወር)
በክንድ ቆዳ ስር የሚቀመጥ (የ3 እና የ5 ዓመት)
በማህፀን የሚቀመጥ (የ12 ዓመት)
የወንድ ኮንዶም
ነርስ ሙሉ እመቤት ጫኔ እንደተናገሩት ለ12 ዓመት የሚያገለግል በማህፀን የሚቀመጥ (ሉፕ) ለመጠቀም ወደ ጤና ጣቢያ የሚሄዱ ሴቶች የማህፀን ጫፍ የቅድመ ካንሰር የምርመራ አገልግሎት (ካልተፈለገ እርግዝና መከላከያ በተጨማሪ) ያገኛሉ። እንዲሁም የኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ ተጠቂ የሆኑ ሴቶች ካልተፈለገ እርግዝና መከላከያ አይነቶች ውስጥ 2 አይነት እንዲጠቀሙ ይደረጋል። ለዚህም እንደምሳሌ የጠቀሱት ከሚዋጥ ወይም በክንድ ቆዳ ስር ከሚቀመጥ ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ ጋር ኮንዶም መጠቀምን ነው። ይህም የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ የሚደረግ ነው ብለዋል የህክምና ባለሙያዋ። እንዲሁም በጤና ጣቢያው የሚሰጠው የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ሙሉበሙሉ ከክፍያ ነፃ መሆኑን የህክምና ባለሙያዋ አክለው ተናግረዋል።
የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት እንዱሁም ሌሎች የህክምና አገልግሎቶችን የሚጠቀሙ ተጠቃሚዎች በተለያየ የኑሮ እና የትምህርት ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው። ስለሆነም ሁሉንም ያማከለ እና ተደራሽ የሆነ አገልግሎት ለመስጠት የሚሰሩ ስራዎች ምንድናቸው ስንል በአአ ከተማ በኮ/ቀ/ክ/ከ ወረዳ 9 ጤና ጣቢያ የቤተሰብ እቅድ፣ የማህፀን ካንሰር እና የአፍላወጣቶች ቡድን መሪ ለሆኑት ነርስ ሙሉእመቤት ጫኔ ጥያቄ አቅርበናል። ነርስ ሙሉእመቤት ጫኔ “ህብረተሰቡ ጋር በመሄድ፣ ከወሊድ በኋላ እና ለልጅ ክትባት ለሚመጡ እናቶች ትምህርት እንሰጣለን” በማለት ምላሽ ሰተዋል። ማህበረ ሰብ በሚገኝበት አከባቢ በመሄድ የሚሰጠው አገልግሎት በሳምንት ውስጥ 3 ወይም 4 ቀናት መሆኑን ባለሙያዋ ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ በኮ/ቀ/ክ/ከ ወረዳ 9 ጤና ጣቢያ በ1 ወር ውስጥ እስከ 110 ወይም 120 የሚሆኑ እናቶች የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ነርስ ሙሉ እመቤት ጫኔ ተናግረዋል። “በፊት ከነበረው የተሻለ ነው” ብለዋል ሙሉእመቤት ጫኔ። እንዲሁም “በፊት የአጭር ጊዜ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተጠቃሚ ብዙ ነበር። ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ግን የረዥም ጊዜ ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ አገልግሎት ህብረተሰቡ የተሻለ ተጠቃሚ ሆናል” በማለት ተናግረዋል። እንደ ህክምና ባለሙያዋ ንግግር በክንድ ቆዳ ስር የሚቀመጥ እና በማህፀን የሚቀመጥ (ሉፕ) ያልተፈለገ የእርግዝና መከላከያ ላይ የተጠቃሚዎች ፍላጎት እየጨመረ ነው። ለዚህ ለውጥ ለህብረተሰቡ በህክምና ባለሙያዎች አማካኝነት የሚሰጠው ትምህርት፣ ስልጠና እና የምክር አገልግሎት ቀዳሚውን ድርሻ ይዟል።
በመንግስት የህክምና ተቋማት የተገልጋዮች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል። እናም ሌላኛው ለነርስ ሙሉ እመቤት ጫኔ ያቀረብንላቸው ጥያቄ “ጤና ጣቢያው ያለው የተጠቃሚዎች ብዛት (ፍላጎት) እና የአገልግሎቱ ተደራሽነት (አቅርቦት) መካከል ያለው ሁኔታ(ልዩነት) ምን ይመስላል” የሚል ነበር። “እስካሁን እጥረት ገጥሞን አያውቅም። አሁን ግን ለ3 ዓመት የሚያገለግል በክንድ ስር የሚቀመጥ ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ የለንም። ይህ ችግር እንደ ሀገር ይመስለኛል። ከዚህ ውጪ ሌላ እጥረት የለብንም” የሚል ምላሽ ሰተዋል። እንደ ህክምና ባለሙያዋ ንግግር በክንድ ቆዳ ስር የሚቀመጠው ለ3 ዓመት የሚያገለግለው ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ ከ5 ዓመት በክንድ ቆዳ ስር የሚቀመጥ ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ ጋር ተመሳሳይ ነው አሰራሩ። ስለሆነም የ3 ዓመት ለሚፈልጉ እናቶች የ5 ዓመት እንዲሁም የ12 ዓመት በማህፀን የሚቀመጥ ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል። አንዲት ሴት የትኛውንም አገልግሎት በፈለገችው ወቅት ማቋረጥ ስለምትችል የዓመት ልዩነት መኖሩ ችግር አይፈጥርም።
በአዲስ አበባ ከተማ በኮ/ቀ/ክ/ከ ወረዳ 9 ጤና ጣቢያ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ስትጠቀም ያገኘናት አንዲት እናት በአገልግሎቱ ላይ ያላትን ሀሳብ አካፍላናለች። ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገችው ይቺ እናት ወደ ጤና ጣቢያው የሄደችው ሶስተኛ ልጇን ከወለደች ከ4 ወራት በኋላ ነው። በክንድ ቆዳ ስር የሚቀመጠውን የ3 ዓመት ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ ለመጠቀም። ይቺ እናት ከዚህ ቀደም (የመጀመርያ ልጇን ከወለደች በኋላ) በክንድ የሚቀበር ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ ተጠቅማለች። ነገር ግን በወቅቱ የህመም ስሜት ፈጥሮብኛል በሚል አገልግሎቱን አቋርጣ ነበር። “ከሌላው ይሄ ይሻላል ብዬ ነው የመረጥኩት። ሌላው ህመም ይኖረዋል ሲባል ስለሰማው ይሄን ልሞክረው ብዬ ነው። ካልሆነ ማስቀየር ይቻላል” በማለት ከዚህ በፊት የተጠቀመችውን አገልግሎት በድጋሚ ስለመረጠችበት ምክንያት ተናግራለች። ይቺ እናት በቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ላይ በዙሪያዋ ያሉ ሰዎች የተለያዩ እሳቤዎች እንዳላቸው ተናግራለች። “አንዷ ጓደኛዬ በማህፀን ሉፕ አስቀብራ የተቀበረው ከቦታው ጠፋ ብላኛለች። እና የተወለደው ልጅ ላይ ሉፑ ችግር መፍጡሩን ሰምቻለው” በማለት ከሰማቻቸው እና ምርጫዋ ላይ ተፅእኖ ከፈጠሩባት ጉዳዮች ውስጥ አንዱን አካፍላናለች።
ነርስ ሙሉ እመቤት ጫኔ ተጠቃሚዎች አገልግሎቱን ሲጠቀሙ ተጓዳኝ ችግር (Side effect) ካጋጠማቸው የህክምና ባለሙያ በማማከር ህክምና ማግኘት እንደሚችሉ ተናግረዋል። ነገር ግን በጤና ጣቢያው ያገኘናት እናት ሀሳብ እና መሰል የተሳሳቱ ግንዛቤዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል። ከተሳሳቱ ግንዛቤዎች መካከል በማህፀን የሚቀመጥ (ሉፕ) ይበራል (ቦታውን ለቆ ይሄዳል) እና ወደ ጭንቅላት ይሄዳል። እንዲሁም በክንድ ቆዳ ስር የሚቀመጥ እጅ ይቆርጣል የሚል እሳቤዎች ተጠቃሽ ናቸው። ነርስ ሙሉ እመቤት ጫኔ አገልግሎቱን ከሰጧቸው ታካሚዎች መካከል በክንድ ቆዳ ስር ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ የተጠቀመች አንዲት ሴት እጅ ይቆርጣል የሚል ስጋት አድሮባት ህክምናውን ለማቋረጥ ከክፍለ ሀገር ወደ አዲስ አበባ ከባለቤቷ ጋር ተመልሳ መምጣቷን ተናግረዋል። ነገር ግን ግንዛቤው ልክ አለመሆኑን ስትረዳ አገልግሎቱን ሳታቋርጥ ተመልሳ ሄዳለች ብለዋል ነርስ ሙሉእመቤት ጫኔ። በተጨማሪም ያልወለደች ሴት የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተጠቃሚ ከሆነች ልጅ ለመውለድ ልትዘገይ ትችላለች የሚለው ግንዛቤ የተሳሳተ መሆኑን የህክምና ባለሙያዋ ተናግረዋል።
የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ምንም እንኳን በይበልጥ ሴቶችን ታሳቢ ያደረገ ቢሆንም አገልግሎቱ ወንዶችንም ያማከለ ነው እንዲሁም የሚሰጠው ጥቅም ለሁለቱም ፆታ (ለወንድ እና ሴት) መሆኑ ግልፅ ነው። ነርስ ሙሉ እመቤት ጫኔ በወረዳ 9 ጤና ጣቢያ ወንዶች (የትዳር አጋር) የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ላይ በተወሰነ መልኩ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። ነገር ግን በሚፈለገው መጠን ጥንዶች በጋራ ማለትም ወንዶች ተሳታፊ ሆነው የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተጠቃሚ አይደሉም።
በትዳር ውስጥ ከሚገኙ ወይም ልጅ ከወለዱ እናቶች በተጨማሪ በጤና ጣቢያው እድሜያቸው ከ15 እስከ 24 ዓመት የሚሆኑ አፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተጠቃሚ ናቸው። በህክምና ተቋሙ ለአፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች ብቻ የተዘጋጀ የተለየ አገልግሎት መስጫ ክፍል እና ባለሙያ መኖሩን ነርስ ሙሉ እመቤት ጫኔ ተናግረዋል።
በአአ ከተማ በኮ/ቀ/ክ/ከ ወረዳ 9 ጤና ጣቢያ የቤተሰብ እቅድ፣ የማህፀን ካንሰር እና የአፍላወጣቶች ቡድን መሪ የሆኑት ነርስ ሙሉእመቤት ጫኔ በየትኛውም በመውለጃ እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሴቶች እና ወንዶች ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ እንዲጠቀሙ እንዲሁም ስለ አገልግሎቱ ባለድርሻ አካላት እና የመገናኛ ብዙሀን ትኩረት ስተው ለህብረተሰቡ ትምህርት እንዲሰጡ መልእክት አስተላልፈዋል።
Saturday, 12 October 2024 13:05
ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ
Written by ሃይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Published in
ላንተና ላንቺ