እስራኤል ከአስከፊ ውድቀት አገግማ ማንሰራራት ትችል ይሆን? የአይነኬነት ዝናዋን መልሳ ማደስስ ትችላለች? እየተሟሟተች ነው። በቅርቡ በሂዝቦላ የመገናኛ መሳሪያዎች ላይ የፈጸመችው ስውር ጥቃት እንደ ምሳሌ ሊጠቀስ ይችላል። በሺ የሚቆጠሩ የሂዝቦላ መሪዎችና አባላት ላይ በተመሳሳይ ሰዓት የፍንዳታ ጥቃት አድርሳለች። እነዚህ የእስራኤል ስውር እጆች፣ እስራኤልን ከጥፋት ማዳን ይችላሉ? ወይስ ተጠራርጋ ወደ ባሕር እንዳትገባ ያሰጋታል?
የሐማስ፣ የሂዝቦላና የኢራን ፍላጎት እንደዚያ ነው - እስራኤልን ለማጥፋት። መቼም ዛቻቸው ባዶ ጩኸት እንዳልሆነ በተግባር አስመስክረዋል። እንደ ሐማስ እስራኤልን አምርሮ ያደማና ያሳመመ ሌላ ኀይል እስከ ዛሬ አልታየም።
እስራኤል “የአይነኬነት ስሟን ለማደስ እየተሟሟተች ነው” ይባላል። በእርግጥም “አይነኳትም፤ የነኳትን አትምርም” የሚባልላት አገር ነበረች - እስራኤል። አይደፈሬ ዝናዋ የዛሬ ዓመት ተሰበረ። ለዚያውም በትልቅ አገር ወረራ አይደለም የተጠቃችው - በታጣቂ ቡድን እንጂ። ክፉኛ ተደፈረች። እንደ አዲስ ከተመሠረተችበት ጊዜ ወዲህ በታሪኳ እንዲያ ዐይነት ውድቀት ገጥሟት አያውቅም።
በአንድ ቀን ውስጥ 1200 ሰዎች ሞተዋል። 250 ሰዎችም በሐማስ ታግተው ተወስደዋል። እውነትም፣ እስራኤል በታሪኳ ታይቶ በማይታወቅ እልቂት ነው የተመታችው።
በሐማስ ጥቃት ማግሥት ደግሞ የሂዝቦላ የሮኬት ውርወራ ተደረበባት።
ከእንግዲህ ማን ይፈራታል? ተባለች። ገፍተን ገፍትረን ወደ ሜዲትራንያን ባሕር እንጥላታለን እያሉ ተዘባበቱባት። እስራኤል በሐማስ እጅ ደምታለች ብቻ ሳይሆን ተዋርዳለችም። በቀላሉ የማይጠገን “የስም ቅጭት” ደርሶባታል።
ከዓመት በኋላስ? አሁን አሁን የተሰበረ ስሟን፣ የተደፈረ ዝናዋን መልሳ ለመገንባት እየሞከረች ነው - በተለይ በሂዝቦላ ላይ በፈጸመቻቸው ጥቃቶች አማካኝነት።
በእርግጥ የእስራኤል ጦር በሐማስ ላይም ከባድ ጥቃት አድርሷል። በአሜሪካና በአውሮፓ መንግሥታት ግምት፣ ከ30 ሺ የሐማስ ታጣቂዎች መካከል ግማሽ ያህሉ በጦርነት ሞተዋል። የሐማስ ነባር የጦር መሪዎችም በአብዛኛው አላመለጡም። ከስምንት ዋና ኀላፊዎች መካከል አምስቱ ተገድለዋል።
የሐማስ ዋና መሪ የነበሩት እስማኤል ሃኒዬ ላይ የተፈጸመው ግድያ ግን ይለያል። ለኢራን ፕሬዚዳንት በዓለ ሲመት ተጋብዘው በሄዱበት በቴህራን ከተማ ነው የተገደሉት - በኢራን ምድር። ዓለማቀፍ የዜና ተቋማት እንደዘገቡት ከሆነ፣ የሐማስ መሪ በቴህራን የክብር አቀባበልና መስተንግዶ ተደርጎላቸዋል። ምቹ የማረፊያ ቦታም ተሰጥቷቸዋል - ከፍተኛ ወታደራዊ ጥበቃ ሥር የሚተዳደር የማረፊያ ቦታ ነው።
እና በየት በኩል አልፎ የእስራኤል ጥቃት ደረሰባቸው? የእስራኤል እጅ እንዴት እስከ ኢራን ድረስ ዘልቆ ገባ? እንዴትስ ኃይለኛውን ወታደራዊ ጥበቃ በስውር አልፎ የሐማስ መሪ ለመግደል ቻለ?
መጀመሪያ ላይ የተሰማው ግምት፣ የሐማስ መሪ የተገደሉት በሚሳኤል ሊሆን ይችላል የሚል መላምት ነው። በምርመራ ከተጣራ በኋላ እንደተገለጸው ከሆነ ግን፣ የሐማስ መሪ የተገደሉት በሚሳኤል አይደለም። ለረዥም ጊዜ ተጠምዶ በቆየ ፈንጂ ነው የሞቱት ተብሏል።
ተጠምዶ የቆየ? ለረዥም ጊዜ?
ወደ ኢራን ሲሄዱ የት ቦታ እንደሚያርፉ ይታወቃል ማለት ነው። ፈንጂ በድብቅ አስገብቶ ማጥመድ የሚችል ውስጥ አዋቂም ያስፈልጋል ማለት ነው። ከዚያ በኋላም፣ ሰውዬው ወደ ቦታው መግባታቸውን ማረጋገጥና ፈንጂውን መለኮስ የሚችል ሰው መኖር አለበት። ወይም ደግሞ የርቀት የስለላ ቴክኖሎጂ - የሞባይልና የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ።
የሞባይልና የኢንተርኔት ቴክኖሎጂዎችን በመጥለፍ ደግሞ፣ የእስራኤል የስለላ ተቋማት በቀዳሚነት ስማቸው ይጠቀሳል። በዓለማቀፍ ደረጃ የሞባይልና የኢንተርኔት ጠለፋ ለመከላከል በቅርብ ዓመታት የተመሰረቱና ስኬታማ ለመሆን የበቁ በርካታ ኩባንያዎችም ይህን ይመሰክራሉ። ከስኬታማዎቹ ኩባንያዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ ሲታዩ፣ በእስራኤል ወታደራዊ የስለላ ተቋም ውስጥ በሰሩ ወጣቶች የተቋቋሙ ናቸው።
እስራኤላውያን ወጣቶች ለሁለት ዓመት በወታደርነት የማገልገል ግዴታ አለባቸው። በዚያ አጋጣሚም ነው በርካታ ወጣቶች እንደ ዝንባሌያቸው ሁኔታ በሞባይልና በኢንተርኔት የወታደራዊ ስለላ እንዲያካሂዱ የሚሠለጥኑት። ከጥቂት ዓመት በኋላ ከውትድርና ሲላቀቁ፣ ወደ አገረ አሜሪካ ሄደው የስለላ መከላከያ ቴክኖሎጂ እየፈጠሩ ኩባንያ ያቋቁማሉ፤ በርካቶችም ተሳክቶላቸው ቢሊዮነር ሆነዋል።
ለነገሩ፣ በየትኛውም ቦታና በማንኛውም ጊዜ ሞባይል ስልኮችን ለመሰለል የሚያስችል ልዩ ዘዴ በመፍጠር የዓለም መነጋገሪያ ለመሆን የበቃው ኩባንያ የየት አገር ኩባንያ እንደሆነ ይታወቃል - የእስራኤል ነው። የስለላ ዘዴው እስከዛሬ ምሥጥሩ አልታወቀም። ኃይለኛ ዘዴ እንደሆነ ግን ተመስክሮለታል። የሞባይሎች “ስዊችድ-ኦፍ” ቢሆኑም እንኳ፣ ከስለላው አያመልጡም። ከርቀት ሆኖ እንዳሻው ይቆጣጠራቸዋል።
ይሄ ሁሉ ሲታሰብ፣ በሞባይልና በኢንተርኔት የስለላ ዘዴ፣ የሐማሱ መሪ እንቅስቃሴ በየሴኮንዱ መከታተል፣ መቼና የት እንደሆኑ ማወቅ፣ ከርቀት ፈንጂ መለኮስና ማፈንዳት ለእስራኤል ላይከብድ ይችላል።
የግምት አነጋገር ይመስላል። የሂዝቦላው አንጋፋ መስራችና መሪ፣ ለሐሰን ናስረላህ ግን፣ ጉዳዩ የግምት ጉዳይ ሆኖ አልታያቸውም። እስራኤል በሞባይልና በኢንተርኔት የምታካሂደው ስለላ፣ ከአደባባ እስከ ጓዳ አገር ምድሩን ሁሉ ያዳርሳል የሚል እምነት ነበራቸው - ሐሰን ናስረላህ። ለዚህም ነው ባለፈው ዓመት የካቲት ወር፣ ለሂዝቦላ መሪዎችና አባላት አዲስ ማሳሰቢያ ያስተላለፉት።
የሂዝቦላ መሪዎችና መኮንኖች የመገናኛ ቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸውን ካልቀየሩ፣ የእስራኤል የስለላ ኢላማ ይሆናሉ። ከዚያም የሚሳዬል ኢላማ ይሆናሉ። ሚሳዬል ሞባይላቸውን ተከትሎ ይመጣባቸዋል።
እናም ሞባይል ከመጠቀም ይልቅ፣ “ፔጀር” የተሰኘውን የቀድሞ የመገናኛ ቴክኖሎጂ መጠቀም አለብን ብለው ነበር - ሐሰን ናስረላህ። ፔጀር ዛሬ ዛሬ እየቀረ የመጣ ቴክኖሎጂ ነው። “ምልክት ማድረጊያ” ነው ማለት ይቻላል። በሞባይል “ምልክት አድርግልኝ” ይባል የለ! ከዚህ ብዙም አይበልጥም - የፔጀር አገልግሎት። መልእክት መቀበል እንጂ አያስተላልፍም፤ መልእክት አይቀባበልም። እናም ለስለላ ብዙም የተጋለጠ አይደለም። መቼ ከየት ወደ የት እንደተንቀሳቀስክ በስለላ እየተከታተሉ ማወቅ አይችሉም - ፔጀር ብቻ ከያዝክ።
የሆነ ሆኖ የሂዝቦላ መሪ ሐሰን ናስረላህ ባስተላለፉት ማሳሰቢያ መሠረት፣ ለድርጅቱ መኮንኖችና አባላት በሺ የሚቆጠር “ፔጀር” ተገዝቶ መጣ። ተመርምሮ ገባ።
ያ ሁሉ ፔጀር፣ “በእስራኤል የስለላ ተቋም” አማካኝነት የተመረተ እንደሆነ ማንም አልጠረጠረም። በታይዋን ኩባንያ የተፈጠረ ቴክኖሎጂ፣ በአውሮፓ ኩባንያ የተመረተ ፔጀር ተብሎ ነው የተዘጋጀው። ሂዝቦላ ፔጀሮቹን ገዝቶ አስገባ። በሺ ለሚቆጠሩ መሪዎችና አባላትም አከፋፈለ።
ፔጀሮቹ ውስጥ ከቁጥር የማይገባ ተቀጣጣይ ፈንጂ በድብቅ ተገጥሞለታል። ከ3 ግራም ያልበለጠ ፈንጂ። ማንም አላየውም።
የዛሬ ሦስት ሳምንት በተመሳሳይ ሰዓት በሺ የሚቆጠር ፔጀር ከሂዝቦላ አባላት እጅና ኪስ ውስጥ ሲፈነዳ ነው ጉድ የተባለው። በማግስቱ ደግሞ በርካታ የሬድዮ መገናኛ መሳሪያዎች በአገረ ዮርዳኖስ በተመሳሳይ ሰዓት ፈነሱ - የሂዝቦላ መገናኛ ሬድዮዎች።
1500 ገደማ የሂዝቦላ አባላትና መሪዎች በእነዚህ ተከታታይ ፍንዳታዎች እንደተጎዱ ሮይተርስ ዘግቧል። 30 ሰዎች ሞተዋል። በቅርብ ርቀት የነበሩ ከአንድ ሺ በላይ ሲቪል ሰዎችም ተጎድተዋል። እንዲያውም ከሟቾቹ መካከል ሁለቱ ሕጻናት ናቸው።
የሂዝቦላ አባላት በእስራኤል የስለላ መረብ እንዳይጠመዱ፣ የእስራኤል ኢላማ ውስጥ እንዳይገቡ ለማዳን ነበር ብዙ ሺ ፔጀር ተገዝቶ የመጣው - በሂዝቦላ መሪ አሳሳቢነት። ግን በሺ የሚቆጠሩ አባላትን ኢላማ ውስጥ የሚያስገባ ወጥመድ ሆኖ አረፈው።
ከ10 ቀን በኋላ ደግሞ የሂዝቦላው መሪ ሐሰን ናስረላህ የእስራኤል አየር ኃይል የሚሳዬል ኢላማ ሆነዋል።
ለጊዜው የእስራኤል ጦርና የስለላ ተቋም ሂዝቦላን አብረክርከውታል። ነገር ግን የሂዝቦላ መሪ ተገደሉ ማለት ሂዝቦላ ሞተ ማለት አይደለም። ሐማስ ግማሽ በግማሽ ሞተዋል ማለት፣ ሐማስ ተቀበረ ማለት አይደለም። እንደገና ለማንሰራራት፣ ያን ያህል ጊዜ ላይፈጅባቸው ይችላል።
እስራኤል እንደዚያ እየተሟሟተች ትርፉ ምንድነው? ለጊዜያዊ ድል ብቻ ነው? እንደገና ይሄው ዑደት ከጥቂት ወራት ወይም ከጥቂት ዓመታት በኋላ ተመልሶ እስኪደገም ድረስ? ትልቅ ኪሳራ ትልቅ ውድቀት ነው። እንደዚያ ከሆነ፣ የአይነኬነት ስምን የሚያድስ አይሆንም።
በእርግጥ፣ ሐማስ፣ ሂዝቦላና ኢራንም፣ ከጊዜያዊ ድል ያለፈ ትርፍ አግኝተው አያውቁም።
በእስራኤል ላይ ብርቱ ምት አሳርፈዋል። አይደፈሬ ዝናዋን ሰብረዋል። ግን ምን ጥቅም አገኙበት። እስራኤልን ጎድተዋል። ግን ለእነሱ ምን ትርፍ አመጣላቸው። እልቂት ነው ያተረፉት።
በእስራኤል ላይ ያንን ብርቱ ጥቃት ያቀዱና የፈጸሙ የሐማስና የሄዝቦላ መሪዎች፣ የኢራን ጄነራሎች በአብዛኛው በእስራኤል ጥቃት ሞተዋል። በሺ የሚቆጠሩ የሐማስና የሂዝቦላ ታጣቂዎችም ተገድለዋል። ምንድነው ትርፋቸው?
አሳዛኙ ነገር፣ በታጣቂዎች ላይ ከደረሰው ጉዳት ይልቅ በሲቪሎች ላይ የደረሰው ጉዳይ ይበልጣል። ጋዛ ውስጥ በከ20 ሺ በላይ ሲቪሎች ሞተዋል። ከ50 ሺ በላይ ቆስለዋል። አብዛኛው ሰው፣ የቅርብ ቤተሰብ ሞቶበታል። ይህም ብቻ አይደለም።
የ2.2 ሚሊዮን ሰዎች መኖሪያና የሐማስ ግዛት የሆነችው ጋዛ ግማሽ በግማሽ ፈርሳለች። ሕንጻዎቿ የፍርስራሽ ክምር ሆነዋል። ጋዛ ላይ የተከመረው ፍርስራሽ 370 ሚሊዮን ኩንታል ነው ይላሉ - በቁጥር ሲገልጹት። ለእያንዳንዱ ነዋሪ 170 ኩንታል ፍርስራሽ ማለት ነው። ፍርስራሹን ከከተማ ለመሰብሰብ 14 ዓመት ይፈጃል ይላሉ። በሚሊዮን የሚቆጠር የጭነት መኪኖች ምልልስ ያስፈልገዋል።
ከመኖሪያ ቤቱ ያልተፈናቀለ ሰው ማግኘት ይከብዳል። ብዙዎቹ መፈናቀላቸው ብቻ ሳይሆን በስደት ከተጠለሉበት ድንኳን እንደገና ተፈናቅለዋል - ከአንዴም ሁለት ሦስቴ።
ምናለፋችሁ! ሁሉንም እያደማና እያወደመ አንድ ዓመት የደፈነው የእስራኤልና የሐማስ ጦርነት፣ በግልግል የማይበርድ ማጣፊያ የማይገኝለት የመጠፋፋት አዙሪት ሆኗል። እንዲያውም እየተስፋፋ ነው።