እስቲ ዝም ብለን እንፈላሰፍ፡፡
እስቲ ዝም ብለን በጥያቄዎች ጨዋታ ትርጉም እንማስን…
እስቲ ላሁን ብቻ ነገሩ ሁሉ የተምታታበት ፈላስፋ እንሁን…
እንሁን…ላሁን ብቻ
…ምንድን ነው ይሄ ሁላ ነገር? ምንድን ነው ይሄ ምድር የተባለ ክምር አለት? ደግሞ በላዩ ላይ ሰዎች የቁጥሩ ብዛት እንደ ምድር አሸዋ ተበትኖ፣ ያለ የስነ ፍጥረት ጋጋታ? ከዚያ ደግሞ የሚበላሉ፣ የሚገዳደሉ፣ የሚዋለዱ፣ ከዚያ ይበዛሉ ከዛ…ራሳቸው እና ተፈጥሮ በሰጠቻቸው መሳሪያ የሚቀናነሱ ፍጥረታት የተከመሩባት…መዓት ጋጋታ?
ግዴለም ትንሽ ተከተሉኝ…
ሁሌ ፈጣሪን ብጠይቀው ብዬ የማስባቸው ጥያቄዎች አሉኝ፡፡ እኔ ላንተ ምንድን ነኝ? ምን ልጠቅምህ ምን ላበዛልህ አሰብከኝ? በምን ጉድ ነው ሳላይህ ሳልሰማህ ላምንህ የቻልኩት? እንዴት ደርሼብህ እንዴት ገባኸኝ? (ይሄን አይነቱን ጥያቄ ማንነቴን በማስስበት ወቅት ላይ ለራሴ እጠይቀዋለሁ?)
ምንነቴ ውስጥ ነው የፈጠርከኝ ያለኸው? ታዲያ ይሄ ሁላ የሚታየኝን የተፈጥሮ ትርምስ አይቼ ላልጨርስ እውስጡ እንዴት ህጎች ጨመርክበት? አሁን ተወርውሬበት የመጣሁበት ምድር ካንተ የተሰጠኝ ስጦታ ነው ወይስ እርግማን? የት ድረስ ነው ምድርን የሰጠኸኝ? ወይስ ምንም ነገር እያየሁ አይደለም? ወይስ አይኖቼ ገና አልተገለጡም? ወይስ ይበቃሀል ብለኸኝ ነው? ሰው መሆኔ ላንተ ትርጉሙ ምንድን ነው? እንደ እኔ ተመሳሳይ ነው? የፈጣሪ ተፈጥሮ ምን አይነት ነው? ሙሉ ለሙሉ ፈጣሪዬን አውቄው ካልጨረስኩት እንዴት አድርጌ እንደምወደው እንዴት አውቀዋለሁ?
ፈጣሪዬን መጠየቅ ያምረኛል፡፡
አንዳንድ ቀናቶች አሉ፡፡ በተቀመጣችሁበት ድንገት ባዶ ትሆናላችሁ፡፡ ባዶ ፍላጎት…ባዶ ስሜት…ባዶ መተንፈስ…ባዶ ሀሳብ… እንደው ድንገት ባዶ ብቻ፡፡ እሱን “ባዶ” የምሆንባቸው ቀናቶች አሉ፡፡ እነዛ ቀናቶች ብዙ አይነት የሀሳብ ቅርፆችን ይዘውልኝ ይመጣሉ፤ ባዶነት ውስጥ ያለውን ረቂቅ ፀጥታ ማድመጥ እስከቻልኩት ድረስ እጅግ ተሰባብረው የሚወረወሩ የሀሳብ ጦሮችም በዛው ልክ ሰብዕነቴ ድረስ እያመሙ መጥተው ሸርክተውኝ የሆነ የጊዜ ቋት ውስጥ ይሰወራሉ፡፡
እዛ ባዶነት ውስጥ …
ድንገት ያልተገኘሁ ግን በዚህ ፅንፍ አልባ አለም ላይ እጅግ ያነስኩ ፍጡር እንደሆንኩ ይሰማኛል፡፡ እንዴትም አድርጌ ህይወትን ብኖረው ምንም ይዤው የምሄደውም የምኖረውም ቁም ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ እዛ ባዶነት ውስጥ የባለቤትነት ስሜት አይሰማሽም፤ ተሸንፎ እንደሚያቃስት እና መውደቁን ማንም ያልሰማለት አይነት የወደቀ ቅጠል ነሽ፤ ህይወት ውስጥ ተወትፈህ የተገኘህ ትርፍ ፍጥረት የሆንክ ይመስልሀል፡፡
ሀሳብ ዝም ብሎ አይወለድም…የራሱ ህግ አለው፡፡ የሚኮረኩሩትን አምስቱን የስሜት ህዋሳት እያደመጣቸው ወጉን የጠበቀ ታሪክህን ይተርክልሀል፡፡ የማትሸሸው ራስህን ሳትወድ በግድህ ታዳምጠዋለህ፡፡ አንዳንዴም እሱ ማነው? እኔ ማነኝ? ትላለህ፡፡ ዞሮ ዞሮ ራሴ ነኝ ብለን ትቀጥላለህ፡፡ ይህ እኔነትህ ያየውን የሰማውን በአንጎልህ ሴሎች ውስጥ ቃላት ተሸክሞ ሲሯሯጥ አድነህ ማቆም አትችልም፡፡ የምትችለው ማዳመጥ ነው፡፡
ስለዚህ ምንም አይነት ሀሳብ አዕምሯችን ቢያፈልቅ በኛው ሰበብ የተበጁ የህይወት እና የእውቀት ማዕድ ፊት ቀርቦ ያገኘውን በልቶ የበላውን በራሱ ቅርፅ እኛው ላይ መልሶ ወርውሮብን እንደሆነ ይገባናል፡፡ በመሀል ህይወትህ እና አንተ አላችሁ፡፡
አሁን ባዶነትን እና መሆንን አፋልሞ መልስ የሚያመጣልንን የፍልስፍና ጨዋታ የሚያስጀምረው ሀሳብ ጋር ቀረብ ብለን እየተወዛገብን ትርጉሞችን በህሊናችን ብዕር ነፍሳችን ላይ ለመሞነጫጨር የሚያመቸን የሀሳብ በር ጋር ደርሰናል፡፡
ሆኖም ቀደም ብዬ እንደተናገርኩት ለዛሬ እነዚህን ውስብስብ የሀሳብ ገመዶች በላያቸው ላይ ጥያቄዎች እየነሰነስን ወይ እንዲቀሉልን ካልሆነም ብትንትናችንን አውጥተውልን እንደአዲስ እንዲፈጥሩን በማድረግ ጉዟችንን እንጀምራለን፡፡
አሁን ዝም ብለን እንፈላሰፍ…ውስብስብ ያሉ፣ ቅርፃቸውን ራሳቸው ፈላልገው የሚገጠጥሙ የጥያቄዎች ጋጋታ ማዝነብ እንጀምር፡፡
ሰው እኔ ሲል ምን ለማለት ፈልጎ ነው? የቱ ድረስ ነን እኛ? እኔነት ውስጥ ያለው እኔነታዊ መስፈርት ማነው ሊነግረን የሚችለው? ነገርየው የሚነገር ነው ወይንስ በሀሳብ ጡንቻ ከተሸሸገበት ተጎትቶ የሚወጣ ነው? ማነው እያሰበ ያለው አሁን? እኔ ከሆንኩ ደግሞ አሳቢው… ለምንድን ነው ማሰብ ለማቆም ስሞክር ጭንቅላቴ ማሰብ ማቆም የማይችለው? ማነው ጭንቅላቴ ውስጥ ሆኖ እያሰበ ያለው? መውደድ ምንድን ነው? መጥላት ውስጥ ያለን እርካታ የትኛው የሞራል ፍልስፍና ነው መመለስ የሚችለው? ራስን ማጥፋት የነፃ ፍቃድ ውጤት መሆኑን እንዴት እናውቃለን? ባንሞት ምን ሊፈጠር…የትኛው የተፈጥሮ ስርዓት ሊዛባ ነው እንዲህ እየረገፍን ያለነው? ሞታችንን እኛ ካልፈለግነው ፈጣሪ ለምን እንደሌላው ጥያቄዎቻችን ይህንንም መፍትሄ አይሰጠንም? ሞቼስ ቢሆን እና ዘላለምን ባልፈልግ…ምንምነትን ብናፍቅ የፈጠረኝ ይፈቅድልኛል? ለምን ብላችሁ አትጠይቁ የተባሉት አማኝ ሀይማኖታዊያን እንዴት አድርገው ነው ማመን የቻሉት?
አሁንም እንጠይቅ…
ባለቀለት የተፈጥሮ ስርዓት ውስጥ ውስብስብ ሀሳቦችን የምናስብበት ንቃተ ህሊናችን ጥቅሙ ምንድን ነው? ምንም ላያመጣ፣ ምን ሊሰራ ጭንቅላታችን ውስጥ ተሰንቅሮ እዳ ይሆንብናል? እንዴት ሰው ሰራሽ የሆነው ቋንቋ… ከቦን ያለውን እና የማናየውን ፍጥረተ አለም ሊያስረዳው ቻለ? ያልተፈጠረን ነገር ከተፈጠረ ነገር እንዴት ልንለየው እንችላለን? ምንምነትን መተርጎም እንችላለን ወይስ የመጠየቁም ሆነ የመመለሱ አቅም ላይ አልደረስንም? ዩኒቨርስ ጥጉን ስቶ በሰፋ ቁጥር እኔ ህይወት ውስጥ የሚያመጣው ለውጥ አለ? ጊዜ መች ተጀመረ? የመጀመሪያው ቦታ የት ነበር? አንድ ሀይማኖተኛ ሰው አንድን ሳይንቲስት ቢግ ባንግን ማን ፈጠረው ብሎ ቢያስጨንቀው እናም ሳይንቲስቱም መልሶ ያንተን ፈጣሪ ማን ፈጠረው ቢለው የትኛው ጥያቄ ወጉን ጠብቆ ተጠየቀ? ፈጣሪ ከየት ነው የመጣው? ለፈጣሪ ለመጀመሪያ ጊዜ ፈጣሪ መሆን ማለት ምንድን ነው? ፈጣሪ እንደ እኛ የማያስብ ከሆነ እንዴት አድርገን ነው እኛ እንደ እሱ ማሰብ የምንችል መስሎ የተሰማን? ሀይማኖት እድሜውን ያራዘመው ይህን የማይመለስ ጥያቄ ለምዕመን ህሊና በተመረጡ ቃላት ማቅረብ ስለቻለ ነው?
እንቀጥል…
አብዛኛው ትምህርት ቤት የሚሄድ ሰው ለምን የሰው ልጅ እንደተፈጠረ፣ በቁሱ አለም ላይ መንፈሳዊው አለም ምን ያህል ጣልቃ ገብቶ እንደሚሰራ፣ ከሚመለከተው የፖለቲካል እና ማህበራዊ መስተጋብር በላይ ሄዶ የህይወትን ጥልቅ ሚስጥራዊ ህጎችን እንዴት መረዳት እንደሚችል፣ ከየት ተሰዶ እና እንዴት ወደዚህ ህልውና ውስጥ እንደተቀላቀለ፣ ለምን እንደመጣ እና ወደ የት እንደሚሄድ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም፡፡
በዚህ የአስተሳሰብ ጣራ ውስጥ ሰንብቶ እንዳለ እያወቅን፣ እነዚህን መሰረታዊ የሰው ልጅ ጥያቄዎች መመለስ እንደማይችል እየተረዳን ዲፕሎም፣ ዲግሪ፣ ማስተርስ፣ ዶክትሬት…እያልን ስም እየቀጣጠልን እንሰጠዋለን፡፡ይህም አይናችን እያየ ተንዶ የማይፈርስ የማህይምነትን ግዛት አብረን ስንገነባ እንከርማለን፡፡ የእውቀትን ከፍታ፣ የጥበብን ስፋት አጠገባችን ባለው የግል እውነታችን ብቻ ግብዓት እንዲሆን በማድረግ አድማሱን እናጠበዋለን፡፡ ሀሳቡን ማሰብ ሲከብደን አስቦልናል ያነው አንድ ግለሰብ ጭንቅላት ውስጥ ገብተን ግማሹን እድሜያችንን በዛ ፈላስፋ ወይም አሰብኩልህ ባይ ባልነው ምህዋር ውስጥ ስንጦዝ እንከርማለን፡፡ አዲስ እና መሳይ ሀሳብ ሲቀርብልን ያለፍነውን እውነት እንዳይድን አድርገን ገለን ለአዲሱ እምነታችን ማዘጥዘጥ ባህላችን አድርገነዋል፡፡ እንዲህም ኖረን ኖርን እንላለን፡፡
ወይስ ሞት ገና አልገባንም? ሞት ግን ምንድነው? እስካሁን ያየህውን እና የተነገረሽን ትርጓሜ ወዲያ አድርገን እስቲ እናሰላስል? ልክ መተንፈስ ብቻውን ህይወት እንደተባለው አለመተንፈስ ብቻ ነው ሞት? ሞትን ከፈጣሪ እና ከሰው ማነው ቀድሞ ማሰብ የጀመረው? በምድር ላይ ለፍተን፣ ተግተን፣ ጥረን እና ግረን ….ኖረን …ኖረን…ኖረን…ድንገት ምንም እንዳላደረገ ሰው ….እንደው ድንገት ደርቀን መገኘት ማለት ምን የሚሉት ነው? ባናሞት ምን ሊፈጠር? ተመርጬ ተፈጥሬ ገና ህይወትን በወጉ ሳልመሰጥር ድንገት ከህልውና ብድግ ብደረግ ተጠቃሚው ማነው? ታዲያ ለምን አፈቅራለሁ? ታዲያ ለምን መውደድ ውስጥ ያለውን ደስታ እየተከተልኩ እስቃለሁ? ለምን የዛች የደስታ መሰላሌ ላይ ስሆን እና ከፍታዬ ድረስ ስከንፍ ስለምን ያኔ ሰዓት ላይ ሞት አልታይህ አለኝ? ወይስ ሞቼ ደግሜ ደጋግሜ በአዲስ ንቃት የምወለድ …በመርሳት እና በመሆን መካከል የምባዝን ሞት ያደከመው ንቃት ብቻ ነኝ? መሞት ርቀት አለው? ርዝመት አለው? አብሮኝ ነው ከውልደቴ ጋር እኩል እየተነፈሰ እየተፈጠረ ያለው? ስለዚህ እኔ ነኝ ሞትን ወደ ምድር ያመጣሁት ማለት ነው? ወይስ ሞት በህይወት ፈረስ እያስጋለበ ነው ለተራ እና አጭር ጉብኝት ብሎ ምድር ላይ የወተፈኝ?
አንዳንዴ አንዳንድ የተፈጥሮ ስርዓቶች ግራ ግብት የሚሉኝ ነገሮች አሏቸው፡፡ ለምሳሌ…
እኛ ከምንረዳው በላይ የሆነ ነገር ሊፈጠር ይችላል? ይህ ሁሉ የፍጥረት መዓት ለኛ ነው? እኛ እንድንረዳው ብቻ ነው? ስለ አንድ ነገር እንዴት አድርገን እርግጠኛ የሆነ መልስ መስጠት እንችላለን? እውነቴን እኮ ነው ሁሌ መረጃ እንፈልጋለን፣ ሁሌ እንጠይቃለን፣ ሁሌ እናወዳድራለን፣ ሁሌ ተስፋና ምርጫ በውስጣችን አለ፡፡ ታዲያ እውነት የቱ ጋር ሆና እየጠበቀችን ነው? ወይስ እኛ ነን ለእውነት እውቅና የምንሰጣት? ወይስ መጀመሪያም እውነት የሚባል ነገር የለም…እውነትን እኛ ነን የፈጠርነው ማለት ነው?
ለዛም ነው “እኔ” ስንል ምን ማለታችን ነው እያልኩ ደጋግሜ የምጠይቀው?
ጠይቁ፡፡
ነፍሳችሁ የሚሄድበት ድረስ ሰዳችሁት ለጥያቄያችሁ ወይ የተሻለ ጥያቄ ወይ ደግሞ መልስ የሚመስል ጥያቄ እስክታገኙ ድረስ ጠይቁ፡፡
በመጠየቅ ውስጥ ያለው ጉልበት እና ለሁሉም መልስ አለኝ በሚለው እርግጠኝነት መሀል ያለውን …ብቻውን ጭንቅላታችሁ ውስጥ የሚያስበውን እኔነታችሁን ቀን ወጥቶላችሁ ፊት ለፊት እስክታገኙትና እውነታችሁን የግላችሁ እስክታደርጉ ድረስ ጠይቁ፡፡
የጠየኩትን ሁላ ይመልስልኛል፣ ትመልስልኛለች የምትሉም ሀይማኖታዊያንም ጭምር ፀሎታችሁ ውስጥ የገንዘብ አምጣ (አምጪ) ጎሎኛል ጥያቄያችሁን አንድ ግዜ ገታ አድርጋችሁ ልጅ ልጆቻችሁ የሚድኑበትን መሰረታዊ የህልውና ጥያቄ ጠይቃችሁ ትውልዱን ወደ እውነት አስጠጉት፡፡
የትምህርት ቤት አሰተማሪዎችም ሆናችሁ ተማሪዎች የምታስተምሩትን እወቁት፣ ለምትገነቡት ትውልድ ጥንቃቄ አድርጉ፡፡ ከፈጣሪ ቀጥሎ አምኗችሁ ለሚያደምጣችሁን ተማሪ ተጠንቀቁለት፡፡
ተማሪዎችም ብትሆኑ ስራችሁ መማር እንደሆነ አምናችሁ የሰማችሁትን ለመተርጎም ለራሳችሁ ጊዜ ስጡ፡፡
ምናልባት ምንም አይነት ጥያቄ ላይኖር ይችላል፡፡ ምናልባት የጠየኩ መስሌኝ በመልሶች እየታጠንኩም ሊሆን ይችላል፡፡ አማራጩ የዘላለምን ያህል ሰፊ ነው፡፡ ሆኖም አንዲት የፈተነችኝ ጥያቄ አቅርቤ መሰናበቱን መረጥኩት፡፡
ፈጣሪ ሊሸከመው የማይችለውን ድንጋይ መፍጠር ይችላል?
መልስ ካላችሁ ለዚህች ጥያቄ ብቻ ድረሱልኝ?
መልካም የፍልስፍና ጊዜ፡፡
Tuesday, 15 October 2024 00:00
ሰው (እኔነት እና ምንምነት) (ፍልስፍናዊ ወግ)
Written by ኪሩቤል ሳሙኤል
Published in
ጥበብ