ከሞቱ በኋላ ከፍተኛ ተከፋይ የሆኑ ዝነኞች!
• ማይክል ጃክሰን ዓምና 115 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝቷል
እኛ አገር ሰውየው ወይም ሴትየዋ በህይወት እያሉ የቱንም ያህል ተወዳጅና ዝነኛ ቢሆኑም እንኳን፣ ከሞቱ በኋላ ሁሉም ነገራቸው የሚያከትም ይመስላል - ሃብታቸውም ዝናቸውም ስማቸውም፡፡ በተለይ አርቲስቶቻችን ታመው አልጋ ከያዙ የችግር ቁራኛ ይሆናሉ፡፡ ለህክምና የገንዘብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በማይድን በሽታ ተይዘው እስከ ወዲያኛው ካሸለቡ ደግሞ ቤተሰቦቻቸው ክፉኛ ይቸገራሉ፡፡ የአሁኖቹ ትንሽ ሳይሻሉ አይቀሩም፡፡ የድሮዎቹ ግን ለሙዚቃ ፍቅር ህይታቸውን ጭምር ነው የሰዉት ማለት ይቻላል፡፡ ይሄ እንግዲህ አንድም የሙዚቃ ኢንዱስትሪው ያለማደጉ ያመጣው ውጤት ነው፡፡
ዛሬስ የሃገራችን የሙዚቃ ኢንዱስትሪው እንዴት ነው? የቱ ኢንዱስትሪ? እንዳትሉኝ ብቻ፡፡
የሰለጠኑት አገራት ሁኔታ በዚህ ረገድ ከእኛ በእጅጉ ይለያል፡፡ የውጭዎቹ ዝነኛ አርቲስቶች እንኳንስ በህይወት ሳሉ፣ ሞተውም እንኳን ገቢያቸውና ሃብታቸው አይሞትም፤ እንዲያውም ከዓመት ዓመት እያደገ ነው የሚመጣው፡፡
ፎርብስ እንደሚያመለክተው፣ በአሜሪካ በርካታ በሚሊዮኖች የሚሰላ ዓመታዊ ገቢ የሚያገኙ ሟች ዝነኛ ሰዎች አሉ፡፡ “ከፍተኛ ተከፋይ የሆኑ ስምንቱ የሞቱ ታዋቂ ሰዎች”፣ እ.ኤ.አ በ2022 ዓ.ም፣ በድምሩ 412 ሚ.ዶላር ገቢ ማግኘታቸውን የፎርብስ ሪፖርት ይጠቁማል፡፡
የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ የነበረው ማይክል ጃክሰን፣ በ2023 ዓ.ም ከየትኛውም “ሟች ታዋቂ ሰው” የላቀ ከፍተኛ ገቢ አግኝቷል - 115 ሚሊዮን ዶላር፡፡ ጃክሰን እ.ኤ.አ በ2009 ዓ.ም በሎስአንጀለስ፣ ካሊፎርኒያ በ50 ዓመት ዕድሜው ነው የሞተው፡፡
ኤልቪስ ፕሬስሊ ሁለተኛው ከፍተኛ ተከፋይ ነው - ከሞተ በኋላ፡፡ ኤልቪስ እ.ኤ.አ በ1977 ዓ.ም በ42 ዓመቱ በድንገተኛ የልብ ህመም ነው የሞተው፡፡ በ2022 ዓ.ም ታዲያ 100 ሚሊዮን ዶላር አግኝቷል፡፡
በሦስተኛ ደረጃ የተቀመጠው የቀድሞው የኪቦርድ ተጫዋች ሬይ ማንዛሬክ ሲሆን፤ እ.ኤ.አ በ2013 ዓ.ም በ74 ዓመቱ በካንሰር በሽታ ነው የሞተው፡፡ ይሁን እንጂ ይሄ ሙዚቀኛ በ2022 ዓ.ም 45 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቱን የፎርብስ መረጃ ይጠቁማል፡፡
በዚህ ዝርዝር ውስጥ የምትካተተው ሌላዋ ባለ ትልቅ ስም ደግሞ ድምጻዊቷ ዊትኒ ሂዩስተን ናት፡፡ ሂዩስተን እ.ኤ.አ በ2012 ዓ.ም፣ በ48 ዓመቷ፣ በሆቴል መታጠቢያ ገንዳ ውስጥ በድንገት ሰጥማ ነው የሞተችው፡፡ እርሷም በ2022 ዓ.ም 30 ሚሊዮን ዶላር አግኝታለች ተብሏል፡፡
እኔ የምለው እኒህ የአሜሪካ ዝነኛ አቀንቃኞችና ሙዚቀኞች፣ እስከ ወዲያኛው አሸልበው ይሄን ሁሉ ሚሊዮን ዶላሮች ካገኙ፣ በህይወት ቢኖሩ ስንት ሊያገኙ ነበር?
ለነገሩ በህይወት እያሉ የለፉበትና የደከሙበት ነው ከሞት በኋላም ጭምር የሚከፍላቸው፡፡ በአብዛኛው የገቢዎቻቸው ምንጭ የሙዚቃ አልበሞቻቸው ሽያጭ፣ በደህና ጊዜ የገዟቸው መኖሪያ ቤቶችና የመሬት ይዞታዎች እንደሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡