Saturday, 19 October 2024 12:14

በተደጋጋሚ የሚከሰት የፅንስ መቋረጥ

Written by  ሃይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

“ተወልጄ ያደኩት በገጠር ውስጥ ነው። ከግብረ ስጋ ግንኙነት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ማውራት አይደለም ሌላ ሰው ሲያወራ መስማት እንደ ነውር ይቆጠራል። ትዳር የመሰረትኩበት በ14 ዓመቴ ነበር። እና ትዳር ውስጥ እስክገባ ድረስ ልጅ እንዴት እንደሚረገዝ እንኳን አላውቅም ነበር። ካገባው በኋላ ደግሞ ማርገዜን ያወኩት የወርአበባዬ ሲቀር ግራ ስለገባኝ ለአንዷ ጓደኛዬ አማክሬያት ነው። እንዴት እያፈርኩ እና እየተጨናነኩ እንደነገርኳት ሳስብ እስካሁን ድረስ ያስገርመኛል። ማርገዜን ካወኩ ወይም ከጠረጠርኩ ከ2 ወራት በኃላ ፅንሱ ወረደ። ለካ ጓደኛዬ የእኔን ማርገዝ ለቤተሰቦቼ እና ለሚቀርቡን ሰዎች በሙሉ አውርታ ነበር። እና ሁሉም የእኔን ሆድ መግፋት ይጠባበቃሉ። በኃላ ስሰማ የመጀመሪያዋ ስለሆነ ብዙም ላያስታውቅ ይችላል እየተባለ እስከ 7 ወር ሁሉም ሆድ ሆዴን ሲተባበቅ ነበር። በመጨረሻ እናቴ ከወሊድ በኃላ ስለሚኖረኝ ሁኔታ አወራችኝ። የተፈጠረውን ነገር እንደምንም ነገርኳት። በጣም አዘነች። በዘራችን እንደዚህ አይነት ነገር ኖሮ እንደማያውቅ ነገረቺኝ። “በተቻለ መጠን ለሌሎች ሰዎች እንዳታወሪ ሰይጣን ይሰማል” አለቺኝ እና ለ2 ሳምንት ፀበል ተጠመኩ። ከዛ ብዙም ሳይቆይ ሌላ እርግዝና ተፈጠረ በዚህ ወቅት ጤና ጣቢያ ሄጄ ማርገዜን አረጋገጥኩ። ግን አሁንም ፅንሱ አልቆየም ወረደ። ማርገዜን ለባሌም ነግሬው ስለነበር 2 ጊዜ መሆኑ ሁለታችንንም አስደነገጠን። መፍትሄ ካላት ብዬ ለእናቴ ነገርኳት። ግን ከመፍትሄ ይልቅ “ይሄ እርግማን ነው፤ ባልሽም እንዳይፈታሽ ሰውም እንዳያገልሽ ለማንም ውንዳትናገሪ” ብላ እያለቀሰች ጥላኝ ሄደች። ባለቤቴ የቤ/ክ እና የአስኳላ ትምህርት የተማረ ስለሆነ ይመስለኛል መውለድ አልቻለችም ወይም እርግማን ነው ብሎ አልተወኝም። ከዛ ለ3ኛ ጊዜ ተደገመ። በዚህ ወቅት የሰው ዐይን እና ወሬ መቋቋም በጣም ከበደን። ባለቤቴ ስራ አስቀይሮ ወደ ሌላ አከባቢ ሄድን። እኔም ልጅ ስለነበርኩ “መጀመሪያ ትምህርት ተማሪ እና ልጅ ቀስ ብሎ ይደርሳል” ስላለኝ እስከ 12ኛ ክፍል ተማርኩ። ህክምና አደረኩ እና ልጅም ዲግሪዬንም አንድ ላይ አገኘው።”
ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገች የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከ15 እስከ 20 በመቶ የሚሆኑት እርግዝናዎች የፅንስ መቋረጥ (መጨናገፍ) ያጋጥማቸዋል። የአሜሪካ የጽንስና የማህፀን ሐኪሞች ኮሌጅ መረጃ እንዳስቀመጠው እርግዝና በተደጋጋሚ መቋረጥ (መጨናገፍ) 1በመቶ በሚሆኑ የመውለጃ እድሜ ላይ በሚገኙ ሴቶች ላይ እንደሚከሰት ይገመታል።
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም የመሀንነት እና የስነ ሆርሞን ህክምና ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር አቤል ተሾመ “2 እና ከ2 በላይ የእርግዝና መቋረጥ ሲኖር ተደጋግሞ የሚከሰት ውርጃ (Recurrent pregnancy loss) ይባላል” በማለት ተናግረዋል። እንደ የህክምና ባለሙያው ንግግር ይህ የፅንስ መቋረጥ በተከታታይ እርግዝና ወይም በመሀል ልጅ ከተወለደ በኋላ ሊከሰት ይችላል። ነገር ግን በብዛት በተከታታይ እርግዝና ላይ የሚያጋጥም ነው። በመሀል ልጅ ከተወለደ በድጋሚ ፅንስ የመቋረጥ እድል ይቀንሳል።  አንዲት ነፍሰ ጡር ሴት የፅንስ መቋረጥ (ውርጃ) አጋጥሟታል ማለት የሚቻለው እስከ 28 ሳምንት ባለው ጊዜ ውስጥ ነው። “ኢትዮጵያ የምትከተለው የውርጃ እድሜ የዓለም የጤና ድርጅት ባስቀመጠው መመሪያ ነው። እስከ 28 ሳምንት ባለው ጊዜ እርግዝና ከተቋረጠ ውርጃ ይባላል። ከ28 ሳምንት በኋላ ከሆነ እንደወለደች ነው የሚቆጠረው” ብለዋል ዶ/ር አቤል ተሾመ።

በተደጋጋሚ የሚያጋጥም የፅንስ መቋረጥ (Recurrent pregnancy loss) የሚያጋጥምበት ወቅት
ከ28 ሳምንት በፊት ባለው የእርግዝና ወቅት የሚያጋጥም; በዘረመል ችግር፣ ስኳር፣ በሆርሞን መዛባት እና በማህፀን ኢንፌክሽን ሊከሰት ይችላል።
ከ28 ሳምንት በኋላ የሚከሰት; አር ኤች ፋክተር(RH factor) ወይም በተለምዶ ሾተላይ ተብሎ በሚጠራው እና በማህፀን ችግር ምክንያትነት የፅንስ መቋረጥ ሊያጋጥም ይችላል።

መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በሥነ ተዋልዶ ሕክምና ውስጥ የተደረጉት ምርምሮች እና የተገኙ ውጤቶች እርግዝና ለተደጋጋሚ እንዲቋረጥ መንስኤ የሆኑ ምክንያቶች እንዲታወቁ እገዛ አድርገዋል። ከዚህ ቀደም አንዲት ነፍሰ ጡር ሴት በተከታታይ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ እርግዝናዎችን በምን ምክንያት እንዳጣች (እርግዝናው እንደተቋረጠ) ላታውቅ ትችላለች። በአሁኑ ወቅት ግን 60 በመቶ ለሚሆኑት የፅንስ ጨነናገፍ ሁኔታዎች አስፈላጊውን ምርመራ ማድረግ እና ትክክለኛውን ምንስኤ ማወቅ ይቻላል።

በተደጋጋሚ የሚያጋጥም የፅንስ መቋረጥ (Recurrent pregnancy loss) መንስኤ
የፅንስ የአፈጣጠር(የዘረመል) ችግር; ፅንስ ከእናት 23 ዘረመል (Chromosome) እና ከአባት 23 ዘረመል (Chromosome) መውሰድ አለበት። ነገር ግን ከእናት ወይም ከአባት የሚወስደው ዘረመል ካነሰ አሊያም ከበዛ ችግር ሊያስከትል ይችላል።
የሆርሞን መዛባት; እናት ላይ የሆርሞን መዛባት መኖር ለፅንስ መቋረጥ ሊያጋልጥ ይችላል። ለምሳሌ የእንቅርት ሆርሞን ማነስ
የስኳር ችግር
የማህፀን ኢንፌክሽን
የማህፀን አፈጣጠር ችግር
የማዮማ (ፋይብሮይድ) እጢ
አር ኤች ፋክተር(RH factor) ወይም አር ኤች ኢምኮፓተብሊቲ (RH incompatibility)        (በተለምዶ ሾተላይ ተብሎ የሚጠራው)
የአልኮል መጠጥ
ከልክ በላይ ቡና መጠጣት (በይበልጥ የእርግዝና የመጀመሪያ ወቅት)
ከፋብሪካ የሚወጡ የተለያዩ ኬሚካሎች
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም የመሀንነት እና የስነ ሆርሞን ህክምና ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር አቤል ተሾመ እንደተናገሩት ፅንስ ከመቋረጡ (ውርጃ) አስቀድሞ የሚታይ ምልክት የለም። አንዲት ሴት ለተደጋጋሚ ፅንስ መቋረጥ ተጋላጭ መሆኗን መመርመር የሚቻለው ውርጃ ካጋጠማት በኋላ በቀጣይ እርግዝና ከመፈጠሩ በፊት ወደ ህክምና ተቋም ከሄደች እና ባለሙያ ካማከረች በኋላ ነው። አንድ ጊዜ የሚፈጠር የፅንስ መቋረጥ አሳሳቢ ላይሆን ይችላል። ነገር ግን 2 ጊዜ ወይም ከዛ በላይ ካጋጠመ በቀጣይ እርግዝና ከመፈጠሩ አስቀድሞ ጥንዶች የህክምና ባለሙያዎችን ማማከር እንደሚገባቸው ዶ/ር አቤል ተሾመ ተናግረዋል።
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ብዙውን ጊዜ ሴቶች ስለ ፅንስ መጨንገፍ (መቋረጥ) ወይም በእርግዝና ወቅት ያጋጠማቸውን ድንገተኛ ችግሮች ለመናገር አይፈልጉም። እንዲሁም እንደ ማህበረሰብ የተፀነሰ ልጅ ከመቋረጥ (መጨንገፍ) ጋር ተያያዞ የተሳሳቱ ግንዛቤዎች ይስተዋላሉ። በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም የመሀንነት እና የስነ ሆርሞን ህክምና ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር አቤል ተሾመ በተደጋጋሚ የፅንስ መቋረጥ (መውረድ) ችግር ካጋጠማቸው እና ህክምና ካገኙ ሴቶች መካከል የሁለት ሰዎች ታሪክ አካፍለውናል።
የመጀመሪያዋ ባለታሪክ ዶ/ር አቤል ተሾመ ጋር ለህክምና የሄደችው 3 ፅንስ ከተቋረጠ (ከተጨናገፈ) በኋላ ነበር። የማህፀን ምርመራ በአልትራሳውንድ ተደረገላት። የስኳር መጠኗም ተለካ። ነገር ግን ምንም ችግር አልተገኘም። ይቺ ታካሚ ሶስቱንም እርግዝናዎች ያጣችው ከ10 ሳምንት የእርግዝና ወቅት በፊት ነው። “ጥርጣሬ የነበረኝ የደም መርጋት ይኖራል የሚል ነበር። እሱን ለማረጋገጥ በተደጋጋሚ ምርመራ መደረግ አለበት። ምርመራ የሚደረገው ደግሞ ናሙና ወደ ውጪ ሀገር ተልኮ ነው።” በማለት የሂደቱን አስቸጋሪነት ዶ/ር አቤል ተሾመ አብራርተዋል። ስለሆነም ይህን ምርመራ ውጪ ሀገር ለማድረግ ከሚወስደው ጊዜ እና ገንዘብ አንፃር ምርመራው ሳይደረግ ህክምናውን መሞከር የተሻለ አማራጭ ሆነ። ህክምና ተደረገላት እና ፅንሱ ከዚህ ቀደም ይቋረጥበት ከነበረውን 10ኛ ሳምንት አለፈ። በመጨረሻም ልጇን በቀዶጥገና መውለድ ቻለች። ሁለተኛዋ ዶ/ር አቤል ተሾመ ያካፈሉን ታሪክ ባለቤት በተመሳሳይ 3 እርግዝናዎች ላይ የፅንስ መቋረጥ አጋጥሟታል። ይቺ ታካሚ ማህፀን በተፈጥሮ ችግር ያለበት (ለ2 የተከፈለ) ነበር። “በማህፀን ኢንዶስኮፒ በካሜራ እያየሁ እንደ ግድግዳ ከፍሎ ያለውን ማህፀኗን አጥብቦ የነበረውን ነገር አላቀኩላት” በማለት ስለተሰጣት ህክምና ዶ/ር አቤል ተሾመ ተናግረዋል። እንደ ባለሙያው ንግግር ይህ ህክምና (ቀዶጥገና) ከተደረገ በኋላ ቢያንስ ለ2 ወራት እርግዝና መፈጠር የለበትም። ነገር ግን ታካሚዋ ልጅ ለማግኘት ካላት ጉጉት የተነሳ ቀዶ ጥገናው 2 ወር ሳይሆነው አረገዘች። እናም የተፀነሰው ልጅ ወረደ። ከዛም የተሰጣትን የህክምና ባለሙያ ምክር በማዳመጥ አስፈላጊውን የእረፍት ጊዜ ከወሰደች በኋላ ፀነሰች። በአሁኑ ወቅት ለወሊድ ተቃርባ (24 ሳምንት ላይ) ትገኛለች።
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም የመሀንነት እና የስነ ሆርሞን ህክምና ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር አቤል ተሾመ እንደተናገሩት በተደጋጋሚ ፅንስ ከመቋረጥ ጋር ተያይዞ ላለው ለአብዛኛው ችግር(መንስኤ) መፍትሄ አለ። ስለሆነም ከእርግማን እና መሰል የተሳሳቱ ግንዛቤዎች ጋር ከማገናኘት ይልቅ ወደ ህክምና ተቋም መሄድ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

Read 885 times