‹‹ጠብታ ውሃ መርከብ ታሰጥማለች››፣ ‹‹የኪሎ ሜትሮች መዳረሻ በአንድ እርምጃ ይጀመራል››፣ ‹‹ቁጭ ብለው የሰቀሉት ለማውረድ ይቸግራል›› እና መሰል አባባሎች፤ በየዕለት ሕይወታችን የሚገጥሙን አስደሳችም ሆኑ አስደንጋጭ ተግባሮች፤ የትናንሽ ጅማሬዎች ድምር ውጤት ስለመሆናቸው ያመለክታሉ፡፡ ሉላዊነትን እውን ካደረገው የቴክኖሎጂው በፍጥነት መቀያየር ጋር በተያያዘ፤ በአንድ መድረክ ያስተዋልኩት ሰሞነኛ ገጠመኜ ለዚህ ጽሑፍ ሰበብ ሆኖኛል፡፡
የአዲስ አበባ ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ‹‹ሒስን ባህላችን እናድርግ›› በሚል መሪ ቃል በተከታታይ እያዘጋጃቸው ካሉት መርሐ ግብሮች 23ኛውን መድረክ፤ ሐሙስ መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም፤ በብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ (ወመዘክር) የመሰብሰቢያ አዳራሽ አሰናድቶ ነበር፡፡ ለዕለቱ የተመረጠው ርዕስ ‹‹በዓላትን አስመልክተው የሚሰሩ ዘፈኖች ለማህበራዊ ትስስር ያላቸው ፋይዳ›› የሚል ሲሆን፤ ለውይይት መነሻ የሚሆነውን የዳሰሳ ጥናት እንዲያቀርቡ የተጋበዙት ተባባሪ ፕሮፌሰር የሻው ተሰማ ነበሩ፡፡
በባለፉት ዓመታት መድረኮች በስዕል፣ በሙዚቃ፣ በፊልም፣ በስነ ጽሑፍ፣ በቴአትር፣ በአደባባይ ሐውልቶች፣ በፎቶ ግራፍ ጥበብ፣ በአፍ መፍቻ ቋንቋ ስለተዘጋጁ መጻሕፍት… እና መሰል ርዕሰ ጉዳዮችን ማዕከል በማድረግ፤ በተለያዩ የኪነ ጥበብና ስነ ጥበብ ስራዎች ላይ ጥናቶች ቀርበው ውይይት እንደተደረገባቸው በተጠቆመበት መድረክ፤ የዕለቱም ዝግጅት የዚያ ቀጣይ ሆኖ ለ2017 ዓ.ም ከተያዙ መርሐ ግብሮች ቀዳሚው መሆኑ ተገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ በሒስ ዙሪያ የጀመረውን ዝግጅት እያሳደገ መጥቶ የማስቀጠል ዕቅድ እንዳለው መገለጹ፤ መድረኮቹ ለሙያውና ባለሙያዎቹ መጎልበት የሚያስገኙት ጠቀሜታ ከፍ ያለ ከመሆኑ አንጻር የሚያስደስት ብቻ ሳይሆን አስመስጋኝም ነው፡፡ እንዲህም ሆኖ በርዕሰ ጉዳዮቹ ዙሪያ ጥናት አዘጋጅተው እንዲያቀርቡ የሚጋበዙ ባለሙያዎች፣ የደከሙበትን ለታዳሚያን በምልዐት እንዳያስተላልፉ እንቅፋት የሚሆንባቸው ሳንካዎች እንዳይፈጠሩ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡
ለዕለቱ መርሐ ግብር የዳሰሳ ጥናት እንዲያቀርቡ የተጋበዙት ተባባሪ ፕሮፌሰር የሻው ተሰማ፤ ከተለያዩ ስፍራዎች፣ በዓላትን አስመልክቶ ስለተዘፈኑ ‹‹ሕዝባዊ ዘፈኖች›› በቴፕ ካሴት ያሰባሰቧቸው ማሳያዎችን ለማቅረብ ቢፈልጉም፤ የመድረኩ አዘጋጆች ካሴት ማጫወቻ ቴፕ ሊያገኙላቸው እንዳልቻሉ አመልክተዋል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ በዕለቱ መድረክ፤ ታዳሚያን ፊት ለፊት ያዩት ሌላ ቅር የሚያሰኝ ክፍተትም ነበር፡፡ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሻው ተሰማ ጥናታቸውን በላፕቶፕ ይዘው በመምጣት፣ መረጃዎቹን ከቃል ገለጻም በዘለለ በፕሮጀክተር (LCD) በመታገዝ የማሳየት እቅድ ነበራቸው፡፡
ላፕቶፑን ከፕሮጀክተሩ ጋር የሚያገናኝ ኬብል በመጥፋቱ ምክንያት ግን እቅዳቸው አልተሳካም፡፡ አዘጋጆቹ የተለያየ ኬብል እያመጡ ላፕቶፑንና (LCD)ን ለማናበብ ያደርጉት የነበረው ጥረት መድረኩን ከመረበሽ ውጭ ምንም አልፈየደም፡፡ ‹‹ጥሬ ሥጋ አቅርቦ ቢላ መንፈግ›› የሚባለው ይኽው ነው፡፡ ችግሩ ‹‹በዕውቀት ቤት›› መታየቱም አስገራሚ ነበር፡፡
ከተመሠረተ ስምንት አስርት ዓመታት ያስቆጠረው ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ (ወመዘክር)፣ የተለያዩ አገልግሎት መስጫ 16 የሚደርሱ የተለያዩ ክፍሎችን በውስጡ የያዘ ብቻ ሳይሆን፤ ከሀገሪቱ አንጋፋ ተቋማትም አንዱ ነው፡፡ ከ16ቱ መሐል ‹‹ቀረፀ ድምጽና ምስል›› ክፍል አንዱ ሲሆን፤ ይህን ክፍልና ስለሒስ ውይይት ይደረግበት የነበረው አዳራሽ የሚለያያቸው አንድ ግድግዳ ብቻ ነበር፡፡ የአዲስ አበባ ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮና ወመዘክር በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸው የመግባቢያ ሰነድ አይኖራቸውም ተብሎ አይታሰብም፡፡ የካሴት ማጫወቻ ቴፕና የላፕቶፕ ኬብል ከ‹‹ቀረፀ ድምጽና ምስል›› ክፍልም ጠፍቶ ይሆን፤ አስተባባሪዎቹ ለጠያቂው ምላሽ መስጠት የተቸገሩት ? የሚያስብል ነበር፡፡
በብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ በተሰናዳ መድረክ፤ እንዲህ ዓይነት ችግር ሲታይ ይህ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ ከሳምንታት በፊት፣ ነሐሴ 11 ቀን 2016 ዓ.ም፣ በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ስም በተሰየመው አዳራሽ (አማርኛ ክፍል)፤ የከበደች ተክለአብ ‹‹ሱታፌ›› ሁለተኛ የግጥም መጽሐፍ በተመረቀበት ዕለትም፤ የገጣሚዋን ላፕቶፕ ከLCD ጋር ማናበብ ብዙ ስላታገለ፤ ጥቂት የማይባሉ ደቂቃዎች ባክነው ነበር፡፡
‹‹አንዱን ጥሎ ሌላውን የማንጠልጠሉ›› ጉዳይ፤ ሕትመትና ስርጭታቸው እየተመናመነ ከመጣው ጋዜጣና መጽሔቶችም ጋር በተያያዘ ችግር መከሰቱም ይታያል፡፡ በዚህም ዘርፍ እየተፈጠረ ያለው ክፍተት፤ ሰነባብቶ ማስቆጨቱ አይቀርም፡፡ እንደቀልድ ጣል ጣል መደረጋቸው ሲታይም ‹‹በምን እንዲተኩ ታስቦ ይሆን ?›› የሚያስብል ከሆነ ከራርሟል፡፡
በወመዘክር ለጋዜጣና መጽሔት ማንበቢያነት ታስቦ የተመደበው ቦታ፤ ‹‹የመዛግብት ንባብ አዳራሽ››፣ ‹‹ቀረጸ ድምጽና ምስል›› ክፍል እና መሰብሰቢያ አዳራሹን የሚያገናኘው ኮሪደር ነው፡፡ በዚህ ኮሪደር ጋዜጣና መጽሔቶችን የሚያነቡ ተገልጋዮች፤ በአዳራሹ የተለያዩ መርሐ ግብሮች ሲሰናዳ (በተለይ በአቴንዳንስና በሻይ ቡና ሰዓት) ሁሌም እንደታወኩ ነው፡፡
ከ1990ዎቹ በፊት ብቻውን በተሠራ አንድ ብሎክ ላይ በተመደበለት ትልቅ ክፍል፣ ሰፊ አገልግሎት ይሰጥ የነበረው ጋዜጣና መጽሔት ክፍል፤ አዲሱ ሕንፃ (ባሕረ ጥበባት ቤተ መጻሕፍት የሚገኝበት) ከተሠራ በኋላ፤ መዝናኛ ክበቡን የሚጎራበት ክፍል ቢመደብለትም፤ ከካፌው በሚወጣ ድምፅ አንባቢያን ክፉኛ ይረበሹ ነበር፡፡ በኋላ ከዚያ ተነስቶ አሁን ወደሚገኝበት ኮሪደር ተዛወረ፡፡ ጋዜጣና መጽሔት በወመዘክር ብቻ ሳይሆን በብዙ ስፍራዎች ክብር አጥተው ‹‹በስደት ዘመን›› ላይ ነው የሚገኙት፡፡
የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት ተግባራዊ በሆነባቸው አካባቢዎች ከጠፉ ነገሮች መሐል፤ ጋዜጣና መጽሔት መሸጫ ስፍራዎችና በማንበቢያነት ይታወቁ የነበሩ ካፌዎች ይገኙበታል፡፡ ለነገሩ አሁን ላይ ጋዜጣና መጽሔቶች ብቻ ሳይሆኑ የመጻሕፍት ሕትመትና ስርጭት ዘርፍም ችግር ተጋርጦበታል፡፡ ባሳለፍነው 2016 ዓ.ም ጥቂት የማይባሉ የመጻሕፍት መሸጫ መደብሮች፤ በዳግም ልማቱ ምክንያት ፈርሰዋል፡፡
በዚህ ብቻ ሳይሆን፤ በተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 1341/2016 ላይ በተደነገገው መሠረት፤ የመጻሕፍት ሕትመትና ስርጭት ቫት ይመለከተዋል መባሉን ተከትሎ ቅሬታዎች በተለያየ መልኩ ሲቀርቡ ነበር፡፡ ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር፤ ነሐሴ 8 ቀን 2016 ዓ.ም፣ ዐባላቱን ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ አዳራሽ ጠርቶ፤ ቅሬታውን አሰምቷል፡፡
ከጋዜጣ፣ መጽሔት እና መጻሕፍት ሕትመትና ስርጭት ጋር በተያያዘ የሚታዩ ችግሮች የሚታረሙበትና የሚሻሻሉበትን አሠራር መዘርጋት ሲገባ፤ ‹‹ታስቦበት እንዲጠፉ እየተደረገ ነው›› ብለው የሚያምኑ ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ይህ እምነትና እሳቤ ‹‹እውነት›› ከሆነ፤ ጠፊውን በቀድሞ ደረጃ፣ ቅርጽና ይዘት የሚተካው ምንድነው ? የሚለውም ወሳኝ ጥያቄ ይሆናል፡፡
በጽሑፌ መጀመሪያ ባነሳሁት የሒስ መድረክ የታየው ክፍተት፤ ዕለታዊና ድንገተኛ ሳይሆን የትናንሽ ክፍተቶች ድምር ውጤት ነጸብራቅ ነበር፡፡ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሻው ተሰማ፤ የጠየቁት የካሴት ማጫወቻ ቴፕ መገኘት አለመቻሉ፤ ከአንድ ቢሮ፣ ከጥቂት ኃላፊዎች… ጋር ብቻ በተያያዘ የተፈጠረ ችግር አይደለም፡፡ ጉዳዩ ከብዙ ነገሮቻችን ጋር የሚያያዝ፣ ዞር ስንል ከምናጣው፣ የትላንት ማንነታችንን ከሚያሳጣን፣ ከባድ አደጋ ላይ ከመውደቃችን ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ነገ ትልቅ ዋጋ ሊያስከፍል የሚችለው ችግር አሁን ላይ ትናንሽ ምልክቶች እያሳየ ነው፡፡
ከኮምፒዩተር ጋር መተዋወቅ እንደጀመርን አብሮ መጥቶ የነበረው ፋይል መቀባበያ ‹‹ፊሎፒ ዲስክ›› የዛሬ ወጣቶች፣ ቅርፅና መጠኑን ቀርቶ ስሙን እንኳን ያውቁት ይሆን? ከዓመታት በፊት በፊሎፒ ዲስክ መረጃዎቻቸውን ያስቀመጡ ግለሰቦችና ተቋማት ግን ይኖራሉ፡፡ ዛሬ የት ይሆን ፊሎፒ ዲስኮችን የሚያነብ ፒሲ (ፐርሰናል ኮምፕዩተር) ማግኘት የሚቻለው? ፊሎፒን ከተኩት ፋይል ማቀባበያዎች አንዱ የሆነው ሲዲም ታሪክ እየሆነ ነው፡፡ ላፕቶፖች ከዕለት ከዕለት እየዘመኑ ስለመጡ፤ አብሯቸው የዘመነውን ኬብል ካላገኘን ልንገለገልባቸው አንችልም፡፡ ነሐሴ 11 ቀን 2016 ዓ.ም እና መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም በወመዘክር አዳራሾች የታየው እውነት ይኸው ነው፡፡
ይህን ስጋትና ተስፋ ከቴክኖሎጂው መስፋፋትና ማደግ ጋር ከተቀበልናቸው የተለያዩ ጉዳዮች ጋር እያያያዝን ብንፈትሽ ‹‹ጉድ ሆነናል!!!›› የሚያስብሉ ብዙ ችግሮች የሚያጋጥሙን ይመስላል፡፡ የአንድ ወዳጄን የቅርብ ገጠመኝ በማሳያነት ላቅርብ፡፡ የፎቶግራፍ ባለሙያ ያልሆነው ወዳጄ፤ በትርፍ ጊዜውና ባመቸው አጋጣሚ ፎቶግራፍ የማንሳት የቆየ ልምድ አዳብሯል፡፡ ፎቶግራፍ ማንሳት የጀመረው፤ ተጠቅልለው በታሸጉ የ‹‹ኮዳክ››፣ ‹‹ኮኒካ››፣ ‹‹ፉጂ››… ፊልሞችን በሚቀበሉ ካሜራዎች ነበር፡፡ በዚህ መልኩ ያነሳቸው ብዙ ጥቅል (ኔጌቲቭ) ፊልሞች አሉት፡፡ በወቅቱ በእነዚህ ፊልሞች ያነሳውን ፎቶ አስጠቁሮና አሳጥቦ ለሕትመት ማድረሱ ጊዜ ወሳጅ ነበር፡፡
ዲጂታል ካሜራዎች ሲመጡ፤ ‹‹አሮጌ›› ካሜራውን ጥሎ ዘመናዊውን ዓለም ተቀላቀለ፡፡ ቴክኖሎጂው ብዙ ነገሮችን አቀለለት፡፡ ዲጅታል ማተሚያ ማሽኖችንም ስላገኘ በዕድሉ በመጠቀም ከተደሰቱት አንዱ ሆነ፡፡ በወቅቱ ከሚሞሪ ካርድ ብቻ ሳይሆን በጨለማ ክፍል ‹‹የታጠቡ›› ፊልሞችን ወደ ፎቶግራፍና ዲጂታል ምስል የሚለውጡ ማሽኖች ስለነበሩ፤ የቴክኖሎጂ ለውጥና ሽግግሩ ያጎደለበት ነገር አልነበረም፡፡
በቅርቡ፤ ቀድሞ እንደሚያውቀውና እንደለመደው ኔጌቲቭ ፊልሙን ወደ ዲጂታል ምስል ለማስቀየር ፈልጎ፣ ወደ ፎቶ ቤቶች ሲሄድ፤ አሁን ያን አገልግሎት የሚሰጥ ባለሙያና ማሽን እንደማያገኝ አረዱት፤ ‹‹ምናልባት ይኖራቸው እንደሆን… እዚያ እዚያ ሞክር›› ተባለ፡፡ ይህ ማሳያ ደግሞ በግለሰቦች ብቻ ሳይሆን በትላልቅ የመንግሥትና የግል ተቋማት፣ የምስል መረጃ የተከማቸባቸው ኔጌቲቭ ፊልሞች ዕጣ ፈንታ ምንድነው የሚሆነው? የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ ነው፡፡ ስንቱስ ነው ይህን አደጋ ቀድሞ በመረዳት ለመፍትሔ ዝግጅት ያደረገው ?
ዛሬ ‹‹ዲጂታል ኢትዮጵያ››ን እውን ለማድረግ ታስቦ በተለያየ መልኩ ብዙ እቅድና ሥራዎች ተግባራዊ እየሆኑ ነው፡፡ እንዲህም ሆኖ እንድንድርስበት የሚታሰበው ምኞትን እውን ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ‹‹አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ›› እንዳይሆን ሊታሰብበት፣ ሊመከርበት፣ ከሁሉም በላይ ተግባራዊ እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል፡፡ የቀድሞ አባቶች ‹‹ሳይቃጠል በቅጠል›› እንዳሉት፤ ለዲጂታሉ ዓለም ግልቢያ ልጓም ካልተበጀለት፤ ‹‹ጉድ ሆነናል!!!›› የሚያስብሉን ጉዳዮች መበራከታቸው አይቀርም፡፡
ከአዘጋጁ፡-
ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡-
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ማግኘት ይቻላል፡፡
Saturday, 19 October 2024 12:24
‹‹ዲጂታሏ ኢትዮጵያ›› ዞር ስትል ‹‹ጉድ ሆኛለሁ !!!›› እንዳትል
Written by ብርሃኑ ሰሙ
Published in
ህብረተሰብ