Monday, 21 October 2024 00:00

ይህ አምድ “የነቢይ መኮንን አምድ” ተብሎ ተሰይሟል

Written by  ሙሉጌታ ቢያዝን
Rate this item
(3 votes)

“ልጅህ በጎ ናት?”



ኮማንድ ፖስቱ በተነሣ ማግስት፡፡ ቀትር  ላይ፡፡
ከመንገዱ ማዶ በዜብራው ትይዩ የልጁን መምጣት በጉጉት የሚጠብቅ አባት መኪናው ውስጥ በጸጥታ ተቀምጧል፡፡ ጸጥታው ግን አልዘለቀም፡፡ ወዲያው ‘ጓ’ የሚል ድምጽ ከማዶ ተሰማ፡፡ ከተቀመጠበት እመር ብሎ ከመኪናው ወጥቶ ድምፁን ወደሰማበት ተጣደፈ፡፡ ሰዎች ገለል አሉለት፡፡ ከመቅጽበት በድኑ ላይ ‘ልጄ’ ብሎ ዘፍ አለ፡፡ ብቸኛ ሴት ልጁ በዚያ ተዘርራ ወድቃ ነበር፡፡ መንገዱ ከመቅጽበት በሰዎች ተሞላ፡፡ ኮሪደር የሚያለሙ የቀን ሠራተኞች ከነአካፋና ዶማቸው ተገኝተዋል፡፡ ከአስፋልቱ ማዶ ግራና ቀኝ ያሉት የሆቴል አስተናጋጆች ከነሽርጣቸው ተገኝተዋል፡፡ ከት/ቤት የተለቀቁት ብላቴና ተማሪዎች ከነ ነተበ ዩኒፎርማቸው ተገኝተዋል፡፡ ብቻ እንደ ጾም ወጥ በያይነቱ ሰው በስፍራው ተኮልኩሏል፡፡
እኩሉ ከንፈሩን ይመጣል፡፡ ጥቂቶች ሰውነታቸውን ክደው ትዕይንቱን በካሜራ ለመቅረጽ ይተጋሉ፡፡ እኩሉ አጋጣሚውን በመጠቀም ኪስ ለመዳበስ ይገላመጣል፡፡ የሁሉም ፍላጎት ግን  የተጋደመውን በድን ለማየት ነበር፡፡ ፈንጠር ብሎ የሚንቆራጠጥ አንድ ሰው በባዶው ሰማይ ላይ አፍጥጧል፡፡
ኮማንድ ፖስት መነሣቱን ተከትሎ አንቀላፍታ የነበረችው ከተማ ታስራ እንደከረመች እምቦሳ እጅና አግሯን እያፍታታች ነበር፡፡ ተማሪ ቤቶች፣ ቢሮዎች በራቸውን ከፍተው ተፍ ተፍ ማለት ጀምረው ነበር፡፡ ከተማዋ ሸረሪቷን በጣጥሳ ሥራዋን ‘ሀ’ ብላ መጀመሯ ቢያስደስትም፣ የአንዲት ብላቴናን ንጹህ ደም በመገበር መኾኑ ግን እጅግ ያሳዝናል፡፡
አባት በደም የተበከለ የልጁን ጭንቅላት ወደ ደረቱ አስጠግቶ ትንፋሽዋን አረጋገጠ፡፡ ትንፋሽ የለም፡፡ እምባ የለም፡፡ መጮህ የለም፡፡ እራሱም በድን ኾነ፡፡ ቀና ብሎ ከማዶ ይንቆራጠጥ ወደነበረው ሰው ዐይኑን ላከ፡፡ ባዶው ሰማይ ላይ ዐይኑን አፍጥጦ ደንዝዞ የቆመው ሰው፣ ይይዘው ይጨብጠውን አጥቶ ወዲያ ወዲህ ይላል፡፡  ያ ሰው ሹፌሩ ነበር፡፡  አባት ዐይኑ ሹፌሩ ላይ ተሰክቶ ቀረ፡፡ ዐየው፡፡ ተያዩ፡፡ ዐይኑን መንቀል አቃተው፡፡ ይተዋወቃሉ፡፡ በደንብ ይተዋወቃሉ፡፡ ሁለቱም ደንዝዘዋል፡፡ ሁለቱም ውሉ የጠፋ ሀሳብ ማፍተለተል ላይ ነበሩ፡፡
አባት ‘…ያንን ገንዘብ ባልቀበል ኖሮ፣’ ሹፌርም ‘…ያንን ገንዘብ ባልከፍል ኖሮ፣ …ኖሮ፣ኖሮ ኖሮ፣ …’ እያሉ እያሰቡ ይሆን? ዐይታወቅም፡፡
የት ተዋወቁ?
ከዚህ ክፉ ክስተት በፊት የተነጋገሩት ባጭሩ የሚከተለውን ይመስል ነበር፡፡
የሟች አባት፤ “…ብዙ መሰናክል ጥለሃል፣ ኮምፒውተሩንም አላለፍክም፣ ይኹንና መንጃ ፈቃዱን ማግኘት ከፈለግህ ያልኩህን ገንዘብ መክፈል አለብህ …”
ሹፌር፤ “…ይሄን ያህል ገንዘብ መክፈል አልችልም፡፡ ምክንያቱም ታማሚ ልጅ አለችኝ…ወላጅ ከኾንክ አትጨክንብኝ፡፡ እባክህ ልለምንህ…”
***
አምቡላንሷ ዋይ ዋይ በማለት የሐዘን ጉንፋን እየሳለች ስፍራውን ቀወጠችው፡፡ የትራፊክ ፖሊሶች ደረሱ … ሹፌሩን ያዙ፣ አባትን ከበድኑ ላይ አነሡ፡፡ “ሥራ የላችሁም፤ ዞር በሉ!” ሲሉ የተሰበሰበውን ወፈ ሰማይ መንጋ ይበትኑ ገቡ፡፡
‘ፀሓዩ ንጉሥ’ ባለበት አፉ፣ ‘ሌባ’ ለማለት የማይሸክከው፤ ‘ቆራጡ መሪ’ ባለበት አፉ፣ ‘ፈርጣጭ’ ለማለት አፉን የማይዘው፤ ‘ባለራእዩ መሪ’ ባለበት አፉ፣ ‘ዘረኛ’ ለማለት ይሉኝታ የማይነካካው፣  ዘመን ዘንበል ባለበት ሰው ጭካኔው ለከት የሚያጣው ፣ በወደቀ ግንድ ምሳር ለመሰንዘር ክንዱ የማይዝለው መንጋ፣ ‘ደግሞ አያለቅስም …ጥቂት እንኳ ርኅራኄ አያሳይም’ እያሉ ደንዝዞ የቆመውን ሹፌር መንጃ ፈቃድ አውጥቶ ከቦዘኔነት ሲፋታ ‘እሰይ ሰው ኾነ’ ባለበት አፉ ይረግመው፣ አስቦ ኾን ብሎ እንደገጨ ‘ነፍሰ ገዳይ’ እያለ  ይሰድበው፣ያሸማቅቀው ያዘ፡፡ ‘እኔ አባቱን ብኾን እዚሁ ላይ ነበር የምደፋው፣ የምን ሕግ? ሲጀመር ፍትሕ ሲኖር አይደል?…’ ሲል ግራ ተጋብቶ ለቆመው የሟች አባት ዱላ ያቀብል ጀመር፡፡
ፖሊሶቹ የሟችን አባት ሲመለከቱ ባንድም በሌላም አለቃቸው ሳይኾን አይቀርምና ሹፌሩን በማንገላታት ማሽቃበጥ ጀመሩ፡፡ ሹፌሩ  ዐይኑን የሚያሳርፍበት ቢያጣ ወደ ሰማይ አንጋጠጠ፡፡
የመንጋውን ክፉ ምክርና የጋለ ስሜት የተረዱት ፖሊሶች፣  የሟችን አባት  በዐይነ ቁራኛ ይጠባበቁ ያዙ፡፡  ዘሎ ሹፌሩ ላይ እንዳይከመርበት በመስጋት ይመስላል ከብበው አየር ከለከሉት፡፡
ወዲያው ከመንጋው መሃል ‘ይሄ ነፍሰ ገዳይ’ የሚል የታፈነ ድምፅ ተሰማ፡፡ አባት ድምፁን ወደሰማበት ፊቱን አዙሮ ከት ብሎ ሳቀ፡፡ ‘ሳቅ የደስታ ምንጭ ነው’ ያለው ሰው ተሳስቷል፡፡ ሳቁ በቶሎ ሊያባራ አልቻለም፡፡ ወዲያው መላ ፊቱን ፈገግታ ወረሰው፡፡ ‘ሰላም ከፈገግታ ይጀምራል’ ያለችው እማሆይ ተሬዛ ልክ ሳትኾን አትቀርም፡፡ ፈገግታው ግን ወዲያው ክስም አለ፡፡  እጁን ለመያዝ ባይደፍሩም የከበቡትን ፖሊሶች ገነጣጥሎ አሽከርካሪው ፊት ቆመና ድምፁን ወደሰማበት ፊቱን አዙሮ፤ ‘ገዳይዋማ እኔ ነኝ!’ ሲል ጮኸ፡፡  ‘በለው በለው…’  የሚል የመንጋው ድምጽ ሲበረታ፣ ፖሊሶች ፈራ ተባ እያሉ የሟችን አባት እጁን ጠፍንገው ያዙት፡፡ እጁም እግሩም እንደብረት ጠንክሮ ሹፌሩ ፊት የቆመው የሟች አባት ግን እጁን ወደ ሹፌሩ እየጠቆመ፤ ‘እሱ ገዳይ አይደለም፡፡ ገዳይ እኔ ነኝ’ ሲል ያንኑ ቃል እየተናገረ ሳቅ አቋረጠው፡፡ የማያባራ ሳቅ፣ ተግ እያለ የሚቀጥል ሳቅ፣ አስፈሪ ሳቅ፣…
መፈረጅ የማይሰለቸው መንጋ፣ ‘ሰውየው ለቀቀ’ ለማለት የቀደመው አልነበረም፡፡ ስፍራው በሰዎች ጉርምርምታ ተዋጠ፡፡
አባት ሹፌሩን ‘አንድ ጥያቄ ብቻ ልጠይቅህ?’ ብሎ ቀረብ አለው፡፡ ያ ሁሉ የመንጋ ድምፅ እረጭ አለ፡፡ ይሄን ብሎ ሁለት ቃላት ተነፈሰ፡፡ ጥያቄውን የሰማው ሹፌር እንባውን መቆጣጠር አልቻለም፡፡ አፉ ተንቀጠቀጠ፡፡  ከመንጋው መሃል ጆሯቸውን ያቆሙት ሰዎችና ፖሊሶች ጥያቄውን ሲሰሙ እርስ በርስ ተያዩ፡፡  
ፕሌቶ ‘የሰው እውነተኛ ጠባይ የሚገለጠው ሥልጣን በጁ ሲኾን ነው’ ማለቱ ተሳስቷል - ሐዘኑ ሥልጣኑን በልጧልና፡፡ ከዛ ይልቅ የቧልት ንጉሡ ቻርሊ ቻፕሊን ‘የሰው እውነተኛ ጠባይ የሚገለጠው ሲሰክር ነው’ ማለቱ ለዚህ ሰው ስሜት ቅርብ ሳይኾን አይቀርም፡፡ ልቡ በሐዘን ሰክሯልና፡፡ መንጋው ‘ምን አለ? ምን አለ? ምን ብሎ ነው የጠየቀው?’ እያለ ጥያቄውን ለመስማት ይጋፋ ጀመር፡፡ የሰማው ላልሰማው ያሰማ ጀመር፡፡  
አባት ሹፌሩን የጠየቀው ጥያቄ ይህ ነበር፡- “ልጅህ በጎ ናት?”

Read 1173 times