Saturday, 19 October 2024 12:31

ወገን አለኝ!

Written by  ዮናስ ታምሩ ገብሬ
Rate this item
(0 votes)

‹‹ውበትሽን አይቶ፣ የማያደንቅ ሰው፤
በርግጥ ያስታውቃል፣ ችሎታ እንዳነሰው፤››
(‹‹የጠላሽ ይጠላ››፣ ጥላሁን ገሠሠ፤ ዜማ፡- ጥላሁን ገሠሠ፤ ግጥም፡- ሻለቃ አፈወርቅ ዮሐንስ)።
….1933 ዓ.ም. አንድ ሥጦታ በምድራችን ከቸች አለ - ጥላሁን ገሠሠ በወሊሶ ተወለደ፤ በአዲስ አበባ ከተማ፣ ጠመንጃ  ያዥ አካባቢ በሚኖሩ ቤተሰቦቹ ዘንድ መራራና ጣዕሙን ሲያጣጥም ከርሟል፤ አዲስ አበባን ለቅቆ ወደ ድሬዳዋ እስከመሰደድም ያበቃው ነገር እንደነበር ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ሙዚቃ የወርቃማውን ዘመን ኮርቻ እንዲፈናጠጥ ጥላሁን ገሠሠ ትልቅ አበክሮ ነበረው፤ ለሞያው ታማኝ፣ ድምጻዊ፣ የዜማ ደራሲ እና ተግባቢ ሙዚቀኛ ነበር፤ አፉን ዘግቶ ድምጽ እያወጣ በማንጎራጎር የሚስተካከለው የለም - ለዚህም የሻለቃ አፈወርቅ ዮሐንስ ድርሰት የሆነው ‹‹አይከዳሽም ልቤ›› ላይ የትራንሲዝሽኑን ክፍል አፉን ዘግቶ የሚያዜምበትን መመልከት ተገቢ ነው…
…‹‹አምሳሉ›› በተሰኘ የአራራይ ለዛን በተላበሰ ዘፈኑ የኢትዮጵያን ውበት ተርኳል፤ ‹‹የጠላሽ ይጠላ›› መልዕክቱም ለአገር እንደሆነ ዕሙን ነው… ረጅም ትንፋሽ አውጥቶ ካንጎራጎራቸው ዘፈኖች መካከል ‹‹ሐሜታ መሆኑ››፣ ‹‹ናፍቆቷ ነው››፣ ‹‹አካም ናጉማ››፣ ‹‹ስትሄድ ስከተላት››፣ ‹‹ኧረ ምን ይሻለኛል›› እና ሌሎችም ተጠቃሾች ናቸው።
ሰብዐዊ መብትን፣ ኃላፊነትን፣ ሰብዕናን እና መልካም ነገርን አስመልክቶ ‹‹አይ ዘመን አይ ጊዜ››፣ ‹‹አንዳንድ ነገሮች››፣ ‹‹ሐሜታ መሆኑ››፣ ‹‹ሰው ከሰው ይለያል››፣ ‹‹አለፍኩ ሁሉን ችዬ›› እና ‹‹ፍቅር ከእኛ እንዳይለየን›› የሚሉ ዘፈኖችን ተጫውቷል።
ውበትን አስመልክቶ ‹‹ቅመም››፣ ‹‹የዘንባባ ማር››፣ ‹‹አካል ዓይንሽን›› እና ሌሎች ተወዳጅ ዘፈኖችን እንካችሁ ብሎናል፤ ሲናፍቅ አንጀት ያረግፋል፤ ‹‹ከረምኳታ››፣ ‹‹አለኝታዬ››፣ ‹‹ናፍቆቷ ነው›› እና ‹‹አካም ናጉማ›› ተወዳጅ የናፍቆት ዘፈኖች ናቸው።
ጥላሁን እና ውክልና፡-
ጥላሁን ገሠሠ ውክልና ያላቸውን እና ተምሳሌታዊ ዘይቤ የተላበሱ ዘፈኖችን ሰጥቶናል፤ ለምሳሌ ያህል አገርን በውበት ከወከለባቸው ዘፈኖች መካከል ‹‹አምሳሉ›› ተጠቃሽ ነው፤ ውበት የሚነሳው፣ ወይም ያ ሁሉ ውብ ውበት፣ መዋብን የተቀዳጀው ከአንቺ ከአገሬ ነው የሚልበት ዘፈን ሲሆን፣ ወርቁ፣ ደኑ፣ መዓዛው ሁሉ ውበትን የቀዱት ከእሷ እንደሆነ ይናገራል…
ጥላሁን እና አበባ…
ጥላሁን ገሠሠ ሙዚቃን ሀ-ለማለት በ1943 ዓ.ም. አካባቢ ሀገር ፍቅር ቲያትርን ተቀላቅሎ ለመጀመሪያ ጊዜ ‹‹ጥላ ከለላዬ›› የተሰኘች ዘፈን አንቆረቆረ፤ በማስከተል ‹‹ጽጌረዳ›› የምትል ድንቅ ዘፈን ተደርሶ ተሰጠው፤ በዚህ ዘፈን በአበባ የመሰለው ውበት አለ፤ መዓዛን ከአበባ ይዋስና ጉብሉን ያወድሳል…
…‹‹የከረን ሎሚ›› (ጥላሁን አብዝቶ ከሚወድዳቸው ዘፈኖች መካከል ተጠቃሽ ነው) በሚል ዘፈን ደግሞ በሎሚ ሽታ፣ በሽቱ እና በተስረቅራቂ መዓዛ የሚያሞካሽበትን ሂደት መመልከት ይቻላል…
ጥላሁን እና ሰብዕና…
‹‹የምድራችን ስፋት፣ ለእኛ መች አነሰን፤
የአመል ጠባብነት፣ ነው የሚያናክሰን፤››
                (‹‹አይ ዘመን አይ ጊዜ››)
የሰው ልጆችን መልካም ሰብዕና የሚንዱ ግድፈቶችን አብዝቶ ይኮንናል፤ የሰዎች እሳቦት ላይ ይሠራል፤ ግመል ምን ተጭነኸል - ሽመል፤ ምን ያወዛውዝሃል - አመል ነውና አመላችን ከሰው ተራ አውጥቶናል፤ ወደነበረበት እንዲመለስ ይተጋል - ጥላሁን፤
ጥላሁን እና የዜማ ድርሰት…
ጥላሁን ከድምጻዊነት ባለፈ የዜማ ደራሲ ነው፤ ለአብነት ያህል ‹‹የጠላሽ ይጠላ››፣ ‹‹ምግብማ ሞልቷል››፣ ‹‹በቁም ካፈቀርሽኝ››፣ ‹‹ስቆ መኖር››፣ ‹‹እቱ ስምሽ ማነው››፣ ‹‹ጎመን በጤና››፣ ‹‹ምን ጥልቅ አድርጎኝ››፣ ‹‹ፍቅር ምን ዓይነት ነው››፣ ‹‹ያውልሽ አበባው››፣ ‹‹ቀረች ሳትረዳኝ›› እና ‹‹ያቺን ልጅ አትንኩ›› ለተሰኙ ዘፈኖች ዜማ ደርሷል።
ጥላሁን እና ኢትዮጲክስ…
ኢትዮጲክስ የኢትዮጵያ ሙዚቃ በቅንብር፣ በመሳሪያ አጠቃቀም እና በአዚያዚያም ከፍ ብሎ የታየበት ጎራ እና አልበም ነው፤ 17ኛውን የኢትዮጲክስ አልበም ጥላሁን ገሠሠ ብቻውን ነግሶበታል፤ በቅንብር ረገድ ሙላቱ አስታጥቄ ተሳትፏል፤ ‹‹ኩሉን››፣ ‹‹ላንቺ ብዬ››፣ ‹‹አይከዳሽም ልቤ››፣ ‹‹በየት ነው መንገዱ››፣ ‹‹ትዝ አለኝ የጥንቱ›› እና ሌሎች ተወዳጅ ዘፈኖች በዚህ አልበም ከፍ ብለው ተደምጠዋል፤ እየተደመጡም ይገኛሉ፤
በዚህ ለዛ ከተቀናበሩ ዘፈኖች መካከል ለ‹‹የከረን ሎሚ›› ልዩ ትኩረት እና ፍቅር አለኝ…
…‹‹አለሁ አለሁ ብለሽ፣ እንደክረምት ጀንበር፤
ድንገት ስትለይኝ፣ ምን ብዬ ልናገር?!
ፊትሽ ሲፈነጥቅ፣ የደስታ ጮራ፤
ይዘልቅ መስሎኝ ነበር፣ ፍቅርሽ ከእኔ ጋራ፤
ፍቅሬ ውዴ፣ የኔ -
አንቺ የበርበር ሽቶ፤
አንቺ የከረን ሎሚ፤
በይ ደህና ክረሚ፤…..››
             (‹‹የከረን ሎሚ››)
በማለት አስቆጭቶናል፤ በዕምነት የሰፈርነው በክህደት ሲበተን የተከዝን ዕለት፣ ይህቺን ልብ መዝማዥ ዘፈን እየሰማን ቀልብና አደባችንን ጣጥለን ነጉደናል!
ጥላሁን…
‹‹ጥሩ መቼ ጠፋ፣ ከቅመም ድንብላል፤
ከሴት አንቺን አየሁ፣ ዓይንሽ ያባብላል፤››
             (‹‹ቅመም›› - ደራሲ፡- ንዋይ ደበበ)
…በማለት ለተወደደች እንስት መኀልዬ የሆነ ዘፈን ሰጥቶናል፤ ጥላሁን ትመሰገን ዘንድ ምክንያት አትጣ!
‹‹የባሕል፣ ቅርስ - ቋንቋ ሰገነት፤
ኢትዮጵያ ሀገሬ - ገነት፤
እናት ሀገር - ኢትዮጵያ፤…››
     (‹‹ኢትዮጵያ›› - ዜማ፡- አበበ መለሰ፤ ግጥም፡- ዓለምፀሐይ ወዳጆ)
በማለት፣ የሰንደቅዓላማ መዝሙር በመሰለ ዘፈኑ የአገር ፍቅርን አትሞብን አልፏል፤
‹‹በመድረክ - ለምስጋና እጅ ነሳሁ፤
በአገሬ በወንዜ፣ በወገኔ እየተመካሁ፤
ፍቅር ነው ሕይወቴ፣ ሕዝብ ነው ንብረቴ፤
ቋንቋዬ ሙዚቃ፣ ሀገሬ ነው ቤቴ፤…››
(‹‹ወገን አለኝ›› - ግጥምና ዜማ፡- ንዋይ ደበበ፤ ተጨማሪ ግጥም - ዓለምፀሐይ ወዳጆ)  
በማለት ከጎኑ የነበረውን፣ የሚያከብረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ አክብሮ ተሰናብቷል!
ጥላሁን ገሠሠ፣ በመስቀል ተወለደ በፋሲካ አረፈ፤ በዓመት በዓሎች የታጀበ ነው ጥላሁን፤  እንዳንረሳው፣ ከልባችን እንዳይፋቅ ሆኗል! ሙዚቃችንን እንደሞላት፣ ጥላ እንደሆነላት ይኖራል፤ ክብረት ይስጥልኝ!!
‹‹ትንፋሼ ተቀርጾ፣ ይቀመጥ ማልቀሻ፤
ይህ ነው የሞትኩ እለት፣ የእኔ ማስታወሻ፤››
(‹‹የእኔ ማስታወሻ›› - ደራሲ፡- ሲራክ ታደሠ)
ሲል ቃል አስገብቶናልና፣ ትንፋሹን በካሴትና በልባችን ቀርጸን እንሰማዋለን - ተባረክ እያልን! እንዲህ፣ እንዲህ እያለ በ2001 ዓ.ም. የረፍቱ ዜና ተሰምቷል፤ ነፍስ ይማር!  
* * *
ከአዘጋጁ
ዮናስ ታምሩ ገብሬ በእንግልዚኛ ቋንቋ ማስተማር /ELT/ የፒ.ኤች.ዲ. ተማሪ ሲሆን፣ በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የእንግልዚኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ መምህር ነው፤ ሁለት ሥነ-ጽሑፋዊ መጻሕፍትን በግል፣ አንድ ደግሞ በጋራ ለማሳተም በቅቷል፤ ከዚህ በተጨማሪ የአንደኛና የስምንተኛ ክፍል የእንግልዚኛ ቋንቋ አጋዥ መጻሕፍትን አዘጋጅቷል፡፡ እነዚህን መጻሕፍት የምትፈልጉ በ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. በኩል ማግኘት ትችላላችሁ።


Read 319 times