Monday, 21 October 2024 00:00

የዘመኔ መልኮች

Written by  አብርሀም ገነት
Rate this item
(3 votes)

ወግ በሉት ከፈለጋችሁ፡፡ ገጠመኝ በሉት ካሻችሁ፡፡ በልቦለድነት ያዙት ከመሰላችሁ፡፡ ሁሉም ውስጥ ግን አንድ መልክ አለ፣ የህይወት መልክ፡፡ የእኔና የናንተ፣ በዙሪያችን ያለው መልክአ-ማህበራችን መልኮች፡፡ የህይወት ብቻ ሳይሆን የዘመናችንም መልኮች፡፡ ደጋግሜ እከሰታለሁ፡፡ ወደ ፊትም ወደ ኋላም እሄዳለሁ፡፡ ወደ ፊትና ወደ ኋላ ሄዶ መኖር ባይቻልም፣ ወደ ፊትና ወደ ኋላ እየተመላለሱ የህይወትና የዘመን መልኮችን መተረክ ይቻላል፡፡ 

 
ደንበኛ ያልሆንኩበት፣ ገብቼ የማላውቅበት በመንገዴ ያጋጠመኝ አንድ ካፌ ገብቼ ውጭ በረንዳ ላይ ተቀመጥኩ፡፡ በረንዳው ላይ አራት ወይ አምስት ተስተናጋጆች እዚህና እዚያ ተቀምጠዋል፣ በቡድንና በነጠላ፡፡ መጀመሪያ ሀሳቤ ጭማቂ ለመጠጣት ነበር፡፡ ሆዴን ሳዳምጠው ግን የእውነት ርቦኛል፣ በጭማቂ የማረካው አልመሰለኝም፡፡ በዚህ አመት ማንጎ ተክል ላይ በተከሰተው በሽታ የተነሳ እኔ የምፈልገው የማንጎ ጭማቂ ከሌላ ጭማቂ ጋር ተቀላቅሎ ካልሆነ ራሱን ችሎ አይቀርብም፡፡ በዚህና በረሀቤ ምክንያት የጭማቂ ሀሳቤን ወደ ፆም ፍርፍር ቀየርኩት፡፡ ስለመሸ አንድያዬን ራቴንም ልገላገለው ብዬ ነው፡፡ እንደሌላው ጊዜ ስልኬን አውጥቼ ኢንተርኔት መክፈት አላሰኘኝም፡፡ ቅሬታ ላይ ነኝ፡፡ ብቻዬን ውዬ፣ ብቻዬን አምሽቼ፣ ብቻዬን ላድር በመሆኑ ቅሬታ ላይ ነኝ፡፡ ቀን ያላዘጋጁት ማታ ከየት ይመጣል ሃሃ….፡፡ ሀቁን አውቃለሁ፣ የመተግበር አቅሙ የለኝም፡፡ ሀሳቤን የምተገብርበት እቅድ ወኔና ትጋት በሌሎች ትናንሽ ሀሳቦችና ተግባሮች ውስጥ ይጠፋል፡፡ ህይወቴ ጠዋት ተስፋ፣ ማታ ቅሬታ ነው፡፡ የወጣትነቴ መልክ ቀን ባለ ህብረቀለም ብሩህ ምናብ፣ ማታ ግራጫ ድብርት ነው፡፡  
ፍርፍሩ በሚያምር ቅርፅ ተጠቅሎ በሰፊ የኒኬል ትሪ ላይ ሆኖ ቀረበልኝ፡፡ መታጠቢያው ያለበትን ጠይቄ እጄን ለመታጠብ ተነሳሁ፡፡ ፍርፍሩን ያመጣችልኝ ወጣት ልጅ ታጥቤ እስክመለስ ባካባቢው ከነበሩ ተስተናጋጆች ጋር እያወራች ምግቤ አጠገብ ቆማ ጠበቀቺኝ፡፡ ተመልሼ መጥቼ ስቀመጥ ፈገግ ብላ አየቺኝና ሄደች፡፡ አንገቴን ሰበር አድርጌላት አልፌ ተቀመጥኩ፡፡ ተግባብተናል፡፡ ስጠብቅልህ ነበር መጣህ? ማለቷ ነው፣ እኔም አመሰግናለሁ ቅን አሳቢዬ ማለቴ ነው፡፡ ፍርፍሩ ግሩም ነው፡፡ ስለራበኝም ይሆናል፡፡ ወይም፣ ርቦኛል ፍርፍሩም ይጣፍጣል፡፡ የትሪው ትልቅነትና ቆርቆሮነት ብቻ ይደብራል፡፡ ፍርፍሩ በትንሽዬ ነጭ ሳህን ሆኖ ቢቀርብልኝ እመኝ ነበር፡፡


ፍርፍሬን እያጋመስኩ ሳለ አንዲት ሱሪ ለባሽ ወጣት ወደ ካፌው ገባችና ወደ አስፋልቱ ለመመልከት የሚያመቸውን ግድግዳ ይዛ ራቅ ብላ ከፊት ለፊቴ ተቀመጠች፡፡ የአገባቧ ፍጥነት ከሆነ ነገር ለማምለጥ የምትጣደፍ ወይንም አምልጣ የመጣች ይመስላል፡፡ ተቀምጣም ትቁነጠነጣለች፡፡ ….አንዲት ማስቲካ አዟሪ ህፃን ወደ ካፌው ገብታ ፊቷን ለሁላችንም አስመትታ ሳትሸጥ ተመልሳ ወጣች፡፡ ህፃኗ እኔን ተሳልማ ደግሞ ወደ ሌሎቹ ስትሄድ ሀዘን ወረረኝ፡፡ የያዘችው ሎሚ ቢሆን ኖሮ እገዛት ነበር፡፡ ይሄ ልቤን በየቀኑ በሀዘን የሚያደማው የዕለት ተዕለት የከተማዬ ገጠመኝ ነው፡፡
መብላቴን ላቆም ጥቂት ሲቀረኝ ያቺን ከሆነ አደጋ አምልጣ የመጣች የምትመስለዋን፣ የምትቁነጠነጠዋን ልጅ መልኳን አጥርቼ አየኋት፡፡ የምታምር መስሎኝ ነበር፣ እናም አለመረጋጋቷን ሰበብ አድርጌ ላናግራት አስቤ ነበር፡፡ የማውቃትም መስሎኝ ነበር፡፡ ፊቷ በብጉር ይሁን በነገር ጠልሽቷል፡፡ ያዘዘቺው ነገር የለም፡፡ ልጅቷ ስለደረሰባት ነገር የራሴን ግምት እየሰጠሁ ሳስብ ሌላ ከፍ ያለች አዟሪ ህፃን ወደ ካፌው ስትገባ አየሁ (የቅድሟ ባለማስቲካ  ህፃን ከኋላዋ ተከትላታለች)፡፡ ስትገባ ካገኘቻቸው ተስተናጋጆች ጀምራ እንዲገዟት እየጠየቀች እኔ ጋ ደረሰች፡፡ እንድገዛት ለመለመን ፊቴ ቀርባ ዝቅ ስትልልኝ፣ በቁናዋ የያዘቺው ሎሚ መሆኑን አየሁ፡፡ ያው እንደሌሎች ሰዎች አይገዛኝም ብላ ከፊቴ ዘወር ስትል “ነይ ነይ፣ ሎሚ አይደል የያዝሺው” አልኋት፡፡ እጄን ወደ ቁናው ሰድጄ ያለ ምርጫ ያገኘሁትን አንድ ፍሬ አነሳሁ፡፡ ቅጠል የመሰለ ያልበሰለ ሎሚ፡፡ አንድ ብሯን ሰጠኋት፡፡ ዞረው ከመሄዳቸው በፊት “ጋሼ ይሄን እንብላው?” አለቺኝ ትልቋ ህፃን፡፡


“እሺ ከጠቀማችሁ”
ትንሿን ህፃን “ነይ” አለቻትና ትሪውን መሬት ላይ ይዘውት ተቀመጡ፡፡ ሲሻሙ ላያቸው አልፈለግሁም፡፡ ምኑን አየዋለሁ ምግቡን ጨርሼዋለሁ፣ ትሪው ላይ የቀረው አንድ ጎረምሳ በአንድ ሰደዳ ሊሰበስበው የሚችል ጠንካራ ጉርሻ ነው፡፡ የመጨረሻዎቹን ጉርሻዎች ስውጥ ከቁንጣኔ ጋር እየታገልሁ ነበር፡፡ ራሴን ጠላሁት፡፡ እነዚህ ብላቴናዎች ማዕዴን መጋራት እንደሚፈልጉ ባውቅ ኖሮ ግማሹን እተወው ነበር፡፡ አዲስ ምግብ ላዝዝላቸው አሰብኩ ግን አላደረግሁትም፡፡ ከሁለቱ አዟሪ ህፃናት በፊት መጥታ የነበረቺዋን ህፃንም አስታወስኩና ለቅሶ ተናነቀኝ፡፡ ሽንሽን ሽብሽቦ የለበሰች፣ ቆሻሻ ፎጣ የደረበች፣ ፀጉሯን ዋግኛ ሹርባ የተሰራች ህፃን፡፡ ከፊቴ ቆማ ቆማ ሄደች፣ ህፃን ልጅ ልመና አላስተምርም ብዬ ገፋኋት፡፡ የእኔ ክልከላ በልጅነቷ የወደቀባትን የልመና እጣ ከልቦናዋ ለማክሰም አስተዋፅኦ ይኖረው ይሆን? ከንፍገቴና ከአርቆ አሳቢነቴ የትኛው ያመዝናል? ….ልጆቹ በሰከንዶች ውስጥ ሰሀኑን አፅድተው “እናመሰግናለን” ብለውኝ ተነሱ፡፡ ሊሄዱ ሲሉ ትንሿን ህፃን ጠራኋት፡፡ ጥቂት የባናና ማስቲካ እሽጎች ያሉበትን ክርታስ አቅፋ ቀረበቺኝ፡፡
“ስንት ነው ማስቲካ?”
“አንዱ ሁለት ብር”
ኪሴ ውስጥ ዝርዝር ብር እንደሌለኝ ትዝ አለኝ፡፡ የጠራኋት እንዲሁ መሸኘት ስላላስቻለኝ ነበር፡፡ ….ልትሄድ አንድ ሁለቴ ስትራመድ እንደገና ጠራኋት፡፡ በጣም ተጠግታኝ ከፊቴ ቆመች፡፡ አወይ መልክ! አወይ ቁንጅና! ከቀይ መልኳ ከከንፈሯ ከአይኗ… ከሁለመናዋ ወለላ የሚንጠባጠብ ትመስላለች፡፡ ችግር ያልጋረደው የልጅነት ውበት፡፡ ቁንጅናዋና ማስቲካ አዟሪነቷ አልገጥምልህ አለኝ፡፡ ቆንጆዎች የሚከፋቸው የሚቸግራቸው የማይመስለን ብዙ ነን እኮ፡፡
“ከማን ጋር ነው ምትኖሪ?” አልኋት
“ከእናቴ ጋር”  
“ትማሪያለሽ?”
“አልማርም”
“አሁን በመስከረም ት/ቤት ግቢ እሺ”
የማስተምራት አልመስልም? ባዶ ምክር ምን ያደርጋል፡፡
“እሺ” አለቺኝ ድምጿን አሳንሳ፡፡ ሳታውቀው አንገቷን ሰብራ በአሮጌ ኪቶ ጫማዋ የስሚንቶውን ወለል ልትቆፍር ትታገላለች፡፡ ድፍን አስር ብር ከኪሴ አውጥቼ፣ አጣጥፌ በፕላስቲክ ጠረጴዛዬ ስር ከልዬ ያዝኩና አልኳት፡
“ት/ቤት ግቢ እሺ…. እንቺ ደብተር ግዢበት”
በጠረጴዛው ስር እጇን ሰዳ ዝቅ ብላ ተቀበለቺኝ፡፡ የእጇ ማማር፣ የጣቶቿ ልስላሴ፡፡ ከልብ በሆነ ቅላፄ “አመሰግናለሁ” ብላኝ መንገዷን ቀጠለች፡፡ ብሩ ስንት እንደሆነ አላየቺውም፣ ለማየትም አይመችም፣ እኔም ስንቀባበል ሌላ ሰው እንዲያይ አልፈለግሁም፡፡ ደግሞም ምሽቱ ደንገዝገዝ ብሎ ስለነበር በበረንዳው ደካማ መብራት ይሄን ትዕይንት አጥርቶ ለማየት አይመችም፡፡ ልጅቷን ሸኝቼያት ቀና ስል ሰዎች ትኩረታቸው እኛ ጋ እንደነበር አየሁ፡፡ ጉዳዬን ስለጨረስሁ ልጅቷን ተከትዬ ከካፌው ወጣሁ፡፡ ሁለቱም አዟሪ ህፃናት ካፌውን ታኮ ከሚያልፈው የእግረኛ መንገድ ላይ ቆመዋል፡፡ አልፌያቸው ስሄድ ለራሴ እንዲህ እያልሁ ነበር፡ ባሳድጋትስ? እናቷን አግኝቼ ብተዋወቃትስ? ግን ከሌሎች ልጆች በምን ተለየችና ነው እንዲህ ልቤን የነካችኝ?


የባህር ዳር ጎዳናዎች ውብና ፅዱ ናቸው፡፡ በእነዚህ ጎዳናዎች፣ በእነዚህ ውብ የምሽት አውዶች ከአመት እስከ አመት ብቻዬን እመላለሳለሁ ብዬ አልገመትኩም ነበር፡፡ ብዙ ነገዎችን ተስፋ አድርጌ ዛሬ ሆነው ሲመጡ እስካሁን ሁሉም አልተለወጡም፡፡ እና አሁን የነገዬን ነገም መተንበይ እችላለሁ፡፡ ባዶ ምኞት ምን ይወልዳል? ምናልባት ቁጭት፡፡ ለመመኘት ለመመኘትማ ማን የማይመኝ አለ፡፡ አሁን አሁን ይሄን የብቻ ተጓዥነቴን፣ ይሄን የራስ ለራስ ወጌን እንደ ትክክለኛ ማንነቴ እየተቀበልኩት መጥቻለሁ፡፡ ማንነቴን በሀሜት፣ በተራ የአሉባልታ ወሬ… ከመበረዝ ያዳንኩት እየመሰለኝ፡፡ እንግዲህ ከብዙኃኑ ጋር ተቀላቅሎ ከመጥፋትና ከብቸኝነት አለም አንዱን መምረጥ ነው፡፡ ትንሽ ትንሽ ባቀላቅልስ ምን ይፈጠራል? ከራሴ ጋር የምወዳደር እውነተኛ ሰው ለመሆን የግድ ብቸኛ መሆን አለብኝ? ከብዙኃኑ ጎዳና ለመውጣት በየምሽቱ ብቻዬን መጓዝ አለብኝ? የማፍቀርም የመፈቀርም አቅም እንዳለኝ አምናለሁ፡፡ ታዲያ አንዲት ሄዋን ከጎኔ ብትሆን ይሄን ለአመታት ፈልጌም ሳልፈልግም የገነባሁትን ማንነቴን ታፈርስብኝ ይሆን? አምናለሁ የራሴ የምለው ማንነት እየገነባሁ እንደሆነ፡፡ ዝምታዬ ግን እየበዛ መጥቷል፣ በዚህም የምጎዳው ነገር ይኖራል፡፡
ወደ ቀኜ ታጥፌ ተከራይቼ ወደምኖርበት ቤት አቅጣጫ የሚወስደኝን ሰፊ የአስፋልት ጎዳና ስይዝ የምሽቷን ጨረቃ አስማታዊ ውበት አየሁ፡፡ ከምስራቅ አድማስ ብቅ ያለች ሙሉ ጨረቃ ናት፡፡ ግዝፈቷ ፀሐይን ተገዳድሯል፡፡ ወጋገኗና የምሽት ፀዳሏ የጠዋት ጀምበርን ያስንቃል፡፡ ሰማዩ ላይ ግዙፍ የብር እንከብል መስላ ብቻዋን ነግሳለች፡፡ እዚህ መብራት ያለበት ከተማ ላይ እንኳን እጅግ ውብ የምሽት አውድ ፈጥራለች፡፡ ….የእግረኛው መንገድ ላይ በየርቀቱ በቆሎ የሚጠብሱ ሴቶች ተቀምጠዋል፡፡ ከጠባሾቹ ገሚሱ ጨቅላ ያዘሉ ናቸው፡፡ አንዷን ገዝቼ ባስደስታት እወድ ነበር፤ ግን በቆሎ መብላት አላሰኘኝም፡፡


…..ቤቴ ልደርስ ጥቂት ሜትሮች ሲቀሩኝ አንዲት የጨርቅ ቀሚስ የለበሰች፣ ደልዳላ ቁመና ያላት ሴት ፊት ለፊቴ ትመጣ ነበር፡፡ ብቻችንን ነን፡፡ ዠርጋዳዋ የሆነ ስበት ነበራት፡፡ ስንተላለፍ ተያየን፡፡ የማንኛውም ተላላፊ መንገደኛ አይነት አተያይ አልነበረም፡፡ ሁለታችንም ውስጥ መሻት ነበር፡፡ በጨረቃዋ ድምቀት አይቻታለሁ፤ አይኖቿ በምኞት ሲቀላውጡ፣ ብሌኖቿ ሲሰይቱ፡፡ እሷም እኔ አይኖች ውስጥ ተመሳሳይ ስሜት አንብባለች፡፡ ግን ምንም ሳንነጋገር ተላለፍን፡፡ ዘመናችን የመተያየት፣ በአይንና በልብ የመፈላለግ፣ ግን ደግሞ ያለመነጋገር፣ የመተላለፍ፣ የመፀፃፀት ነው፡፡ ማነው ዘመናችንን እንዲህ ባለ አይነርግብ አድርጎ የሸመነብን? ስልጣኔ ነው ተብለን፣ ነፃነት ነው ተብለን፣ ከእናትና ከአባት ወግ ተገፍተን ወጥተን፣ እጣችን እንዲህ ጎዳና ላይ እየተያዩ መተላለፍ ሆኗል፡፡
ጳጉሜ 2009 ዓ.ም. ባህር ዳር  


Read 170 times