Friday, 25 October 2024 12:09

የአዲስ ኪዳን ግሪከኛ - አማርኛ መዝገበ ቃላት ለሕትመት በቃ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በአቶ ብሉጽ ፍትዊ የተዘጋጀውና የብዙ ዓመታት ድካምና ጥረት ውጤት እንደሆነ የተነገረለት፣ የአዲስ ኪዳን ግሪክኛ - አማርኛ መዝገበ ቃላት ስራ ተጠናቅቆ ለሕትመት መበቃቱ ተገልጿል። መዝገበ ቃላቱ የግሪክ አቡጊዳ፣ ሙዳየ ቃላትና አጠቃላይ የግሪክ ቋንቋን ታሪካዊ ዳራ እንደሚያቀርብ ተነግሯል።

አቶ ብሉጽ የጤና እክል ከማረፋቸው በፊት ለዓመታት የደከሙበት የመዝገበ ቃላት ስራ የሕትመት ብርሃን ያይ ዘንድ ለገርጂ አማኑኤል ሕብረት ቤተ ክርስቲያን በአደራ እንደሰጡት የታወቀ ሲሆን፣ በዚህም መሰረት የቤተ ክርስቲያኗ አገልጋዮች ተቀብለው ተገቢውን የአርትዖትና የእርማት ሂደት በመከተል ለሕትመት ብርሃን ሊያበቁት ችለዋል። መዝገበ ቃላቱ ከ5 ሺሕ በላይ የአዲስ ኪዳን ግሪክ ቃላትን በቀጥታ ወደ አማርኛ እንደሚተረጉም፣ እንዲሁም ለእያንዳንዱ የቃል ፍቺም ተዛማጅ የአዲስ ኪዳን ክፍሎችን እንደሚያጣቅስ ለማወቅ ተችሏል።

መዝገበ ቃላቱ በኔዘርላንድ አገር በ1 ሺሕ 100 ኮፒ ብቻ እንደታተመ ተገልጿል። በ1 ሺሕ 88 ገጽ የተቀነበበው ይህ መዝገበ ቃላት በ14 ሺሕ ዩሮ ወጪ እንደታተመ ተመላክቷል።

የግሪክ አቡጊዳ፣ ሙዳየ ቃላትና አጠቃላይ የግሪክ ቋንቋን ታሪካዊ ዳራ እንደሚያቀርብ ሲጠቀስ፣ ይህም በኢትዮጵያ የመዝገበ ቃላት ሕትመት ታሪክ ውስጥ በዓይነቱ ልዩና የመጀመሪያ እንደሚያደርገው ነው የታወቀው። ሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም. ከ10:00 ጀምሮ በስካይላይት ሆቴል በሚካሄደው የምረቃ መርሃ ግብር የቤተ ዕምነት መሪዎች፣ የቤተ ክርስቲያን መጋቢዎች፣ የነገረ መለኮትና ልዩ ልዩ የከፍተኛ ትምሕርት ተቋማት አመራሮች እንዲሁም የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ተወካዮችን ጨምሮ ከ 1 ሺሕ 500 በላይ እንግዶች በተገኙበት ይከናወናል።

የምረቃ መርሃ ግብሩ በበርካታ የሚዲያ አካላት የሚዘገብ ሲሆን፣ በቀጥታ ሰርጭትም ለተመልካቾች እንደሚተላለፍ ለማወቅ ተችሏል።

Read 918 times