Saturday, 26 October 2024 19:31

“ቡና መጠጣት ለፅንስ መቋረጥ ሊያጋልጥ ይችላል”

Written by  ሃይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

ከዚህ ቀደም በእርግዝና ወቅት በተደጋጋሚ ስለሚያጋጥም የፅንስ መቋረጥ ምንነት፣ መንስኤ እና ምልክት ለንባብ ማቅረባችን ይታወሳል። በዛሬ እትም በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም የመሀንነት እና የስነ ሆርሞን ህክምና ሰብ ስፔሻሊስት ከሆኑት ዶ/ር አቤል ተሾመ ጋር ያደረግነውን ቃለመጠይቅ ቀጣይ ክፍል ለንባብ አቅርበናል። የህክምና ባለሙያ የሰጡንን ማብራሪያ ከማስነበባችን አስቀድሞ የአንድ ሰው ታሪክ እናካፍላችሁ።
“ብሩክ እባላለው። ያደኩት እና የምኖረው ቤተሰቦች ተሰብስበው መንደር መሰረቱ ከሚያስብል አይነት አከባቢ ውስጥ ነው። በአከባቢያችን የእናቴ እና የአባቴ ቤተሰቦች ናቸው ያሉት። ጣራ እና ግድግዳ ተለያየ እንጂ አንድ ቤት ውስጥ ነው የምንኖረው ማለት እችላለው። ከሁላችን ጋር ለመቀላቀል ፍቃዳኛ ያልሆነ ግን አንድ ቤተሰብ ነበር። የአባቴ ወንድም አጎቴ እና ሚስቱ። ልጅ እያለው አጎቴ እና ሚስቱን አልወዳቸውም ነበር። የትኛውም ልጅ ፊቱን ያጠቆረበትን ሰው እንደማይቀርበው ሁሉ ማለት ነው። ነገር ግን ለምን ከሰዎች ጋር ለመቀላቀል እንደማይፈልጉ የገባኝ ካደኩ በኋላ ነበር። ልጅ አልወለዱም። ይህ ደግሞ ይበልጥ ብቸኛ እንዲሆኑ እና እንዲገለሉ አድርጓቸዋል። ይበልጥ ደግሞ የጎዳቸው የአጎቴ ሚስት ማርገዝ ችላ ለመውለድ አለመታደሏ ነበር። ከ4 ጊዜ በላይ እያረገዘች ወርዶባታል። ለካ ልጆችን ሲያሸሻት የነበረ ጥላቻ ሳይሆን ብሶት ነው። የአከባቢው ሰውም “ እነርሱ ሰው አይቀርቡም” በማለት ይበልጥ አራቃቸው። ጆሮ ሰጥቶ ችግራቸውን ለማዳመጥ የደፈረ አልነበረም። እንደውም በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ እነሱን በማግለል ችግራቸውን አብሶባቸዋል። “ትንሽ አይምሮዋን ያማታል” እየተባለም ትታማ ነበር። አሁን ላይ ይሄን ካወኩ በኋላ ያሳዝኑኛል። ምናልባት በዚህ ዘመን ቢሆን ታክመው መውለድ ይችሉ ነበር እያልኩም አስባለው። ብቻ አንዳንድ ጊዜ ሰዎችን ከሩቁ በመፈረጅ እና ባለመረዳት ብቻ ቁስላቸውን እናባብሳለን። አሁን ላይ አጎቴ እና ሚስቱ ችግራቸው ተፈቶ ልጅ ማግኘት ባይችሉም በተመሳሳይ ችግር ላይ ያሉ ሰዎች እንዳይጎዱ እና ህክምና እንዲያገኙ ከማድረግ በተጨማሪ የስነልቦና ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የእኔ ታሪክ ትምህርት ይሆናል ብዬ አስባለው።”
ብሩክ ከአዲስ አበባ
በተደጋጋሚ የእርግዝና መቋረጥ ሲያጋጥም የተፀነሰውን ልጅ ከማጣት ጋር ተያይዞ የተለያየ የስነልቦና ችግር ሊያጋጥም ይችላል። ከስነልቦና ችግሮቹም መካከል ጭንቀት፣ ድብርት፣ ንዴት እና የጥፋተኝነት ስሜት ተጠቃሽ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ። በተመሳሳይ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም የመሀንነት እና የስነ ሆርሞን ህክምና ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር አቤል ተሾመ የስነልቦና ችግር እንደሚያጋጥም ተናግረዋል። እንደ የህክምና ባለሙያው ንግግር በተደጋጋሚ ፅንስ የመቋረጥ ችግር ያጋጠማቸው ሴቶች ከአካላዊ ጉዳት ይልቅ ስነልቦናዊ ችግር ያጋጥማቸዋል። እንዲሁም የስነልቦና ችግሩ በሁለቱም (በጥንዶች) ላይ ሊከሰት ይችላል። “እርግዝና እየፈለጉ ማጣት ድባቴ ውስጥ ሊከት ይችላል” ብለዋል ዶ/ር አቤል ተሾመ።

በተደጋጋሚ ለሚያጋጥም የፅንስ መቋረጥ የሚሰጥ ህክምና
የማህፅን ኢንፌክሽን ህክምና
የማህፀን እጢ ህክምና
በተፈጥሮ ለሚመጣ የማህፀን መከፈል የሚሰጥ ህክምና
የዘረመል ችግርን በአይ ቪ ኤፍ ህክምና እርግዝና እንዲፈጠር በማድረግ ችግሩን ማስተካከል
የስኳር በሽታ ህክምና
ለደም መርጋት የሚሰጥ ህክምና (ደም ማቅጠኛ መድሃኒት)
ዶ/ር አቤል ተሾመ እንደተናገሩት በተደጋጋሚ ለሚፈጠር የፅንስ መቋረጥ የሚሰጥ ህክምና ከምክንያቱ (መንስኤ) ጋር የተያያዘ ነው። አንዲት ሴት በተደጋጋሚ የፅንስ መቋረጥ (መውረድ) ሲያጋጥማት የችግሩ መንስኤ እንዲለይ ይደረጋል። በቀጣይ እርግዝና ከመፈጠሩ አስቀድሞ ለችግሩ መንስኤ ህክምና በመስጠት በድጋሚ የፅንስ መቋረጥ እንዳያጋጥማት ማድረግ ይቻላል። ነገር ግን ህክምናው የሚሰጠው እርግዝና ከመፈጠሩ አስቀድሞ ነው። ማለትም እርግዝና ከተፈጠረ በኋላ የፅንስ መቋረት እንዳይፈጠር ለማድረግ (መንስኤውን ለይቶ ህክምና ማድረግ) አዳጋች ይሆናል። ምክንያቱም ከላይ ከተጠቀሱት መንስኤዎች መካከል እርግዝና ከመፈጠሩ አስቀድሞ ህክምና ካልተደረገ ፅንሱ ጤናማ በሆነ ሁኔታ እንዲይቆይ የማያደርጉ ችግሮች አሉ። እንዲሁም የህክምና ባለሙያው እንደተናገሩት ከዚህ ቀደም ተደጋጋሚ ውርጅ ያላጋጠማት ሴት ወይም አንድ ፅንስ (ነፍሰ ጡር ሴት) ሊቋረጥ ይችላል ተብሎ መገመት የሚቻልበት ምልክት (ሁኔታ) የለም። ችግሩ በቀጣይ ሊያጋጥም ይችላል ተብሎ የሚገመተው ወይም ተደጋጋሚ ፅንስ ማቋረጥ ችግር መኖሩን ታውቆ ህክምና መስጠት የሚቻለው ከዚህ ቀደም ፅንስ መቋረጥ ያጋጠማቸው ሴቶች ላይ ነው።
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም የመሀንነት እና የስነ ሆርሞን ህክምና ሰብ ስፔሻሊስት ለሆኑት ዶ/ር አቤል ተሾመ “የሚሰጠው ህክምና ውጤታማነት ምን ይመስላል” የሚል ጥያቄ አቅርበንላቸዋል። “በተፈጥሮ ማህፀን ላይ እንደ ግድግዳ የሚከፍል ነገር ካለ ቅፍፍ ተደርጎ ከተነሳ ማህፀን ጤነኛ ይሆናል። ችግር አይኖርም። እጢ ከሆነም እጢው ሲወጣ የመስተካከል እድሉ ከፍተኛ ነው። የዘረመል ችግር ግን አስቸጋሪ ነው” በማለት ምላሽ ሰተዋል።
በተደጋጋሚ ለሚያጋጥም የፅንስ መቋረጥ እንደ መንስኤ የተቀመጠው የዘረመል ችግር የሚፈጠረው ፅንስ ከእናት 23 እና ከአባት 23 በድምሩ 46 ዘረመል ሊወስድ ሲገባ ከእናት ወይም ከአባት ከ23 ያነሰ ወይም የበለጠ ሲይዝ ነው። ዶ/ር አቤል ተሾመ እንደተናገሩት በአይ ቪ ኤፍ ህክምና ይህ የዘርመል ችግር መስተካከል ይችላል። የአይ ቪ ኤፍ ህክምና ማለት የሴት እንቁላል እና የወንድ ዘር ከማህፀን ውጪ (Laboratory) በህክምና ፅንስ እንዲፈጥር ከተደረገ በኋላ ወደ ማህፀን ተመልሶ እንዲቀመጥበት የሚደረግበት ነው። እንደ ህክምና ባለሙያው ንግግር ከዚህ ቀደም አይ ቪ ኤፍ የተባለው ቴክኖሎጂ ባልነበረበት ወቅት ቤተሰብ ላይ የዘረመል ችግር ካለ ጥንዶች ልጅ መውለድ አይችሉም ነበር። ከዘረመል ችግር በተጨማሪ የአር ኤች ፋክተር (ኢንኮምፓተብሊቲ) በተለምዶ ሾተላይ ተብሎ የሚጠራው ችግር ለህክምና አስቸጋሪ መሆኑን የህክምና ባለሙያው ተናግረዋል። ነገር ግን አስቸጋሪ የሚባሉትን ችግሮች ጨምሮ ለአብዛኛው ችግር መፍትሄ መኖሩን ነው ባለሙያው አክለው የተናገሩት።

በተደጋጋሚ ለሚያጋጥም የፅንስ መቋረጥ መከላከያ መንገዶች
የእንቅርት ሆርሞን ማነስ ካለ እርግዝና ከመፈጠሩ አስቀድሞ እንዲስተካከል ማድረግ
የስኳር ችግር እንዲስተካከል ማድረግ
የደም መርጋት ማስተካከል
አልኮል መጠጥ እርግዝና ከመፈጠሩ አስቀድሞ (ሲታሰብ) ማቆም
ትንባሆ እርግዝና ከመፈጠሩ አስቀድሞ (ሲታሰብ) ማቆም
የማህፀን ኢንፌክሽን፣ የማህፀን እጢ እና በተፈጥሮ የሚያጋጥም የማህፀን ችግር ህክምና ማድረግ
ቡና መጠጣት ማቆም (መቀነስ)
የህክምና ባለሙያው እንደተናገሩት እርግዝና ከመፈጠሩ አስቀድሞ ገና ሲታሰብ ከላይ የተጠቀሱትን ነገሮች ማስተካከል ወይም ህክምና ማድረግ ያስፈልጋል። “እርጉዝ ሆና ከመጣች ለመከላከል አስቸጋሪ ይሆናል” ብለዋል ዶ/ር አቤል ተሾመ። አክለውም “የአልኮል አይነት የለውም። ሰዎች አልኮል የሚመስላቸው በፋብሪካ የተመረተውን ብቻ ነው” በማለት በቤት ውስጥ የሚዘጋጅ ማንኛውም አይነት የአልኮል መጠጥ እርግዝና ሲታሰብ መቆም እንዳለበት ተናግረዋል። እንዲሁም “ቡና ሱስ ካለ 1 ሲኒ ቢጠጣ፤ ከ1 በላይ ግን አይመከርም” ብለዋል ዶ/ር አቤል ተሾመ።
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም የመሀንነት እና የስነ ሆርሞን ህክምና ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር አቤል ተሾመ የፅንስ መቋረጥን ከሌላ የተሳሳተ እሳቤ ጋር ማያያዝ እንደማያስፈልግ ተናግረዋል። ስለሆነም ችግር ሲያጋጥም ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ ህክምና ማድረግ ተገቢ ነው በማለት መልእክት አስተላልፈዋል።

Read 645 times