Saturday, 26 October 2024 19:39

ኤስ ኦ ኤስ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች ፈተና እንደሆኑበት አስታወቀ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ኤስ ኦ ኤስ የሕጻናት መንደሮች በኢትዮጵያ፤ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች ስራዎቹን በአግባቡ እንዳያከናውን አስታውቋል።
የተቋም ምክትል ብሔራዊ ዳይሬክተር አቶ ኤቢሳ ጃለታ በተለይ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፣ በአስቸጋሪና ድጋፍ በሚያስፈልጋቸው ቦታዎች ላይ ድጋፍ ማድረግ የኤስ ኦ ኤስ መለያ መሆኑን ጠቁመው በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች ለስራቸው ተግዳሮት እንደሆኑባቸው አመልክተዋ። አያይዘውም፣ ተቋማቸው ከሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በአጋርነት የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው፣ “በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ አደጋ የመጀመሪያ ተጋላጭ የሚሆኑት ሕጻናት ናቸው” ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ግጭት በሚስተዋልበት የአማራ ክልል የሕይወት አድንና የማገገሚያ ስራዎች እየተሰራ መሆኑን ያብራሩት አቶ ኤቢሳ፣ ለአብነት ያህል በሰሜን ወሎና ሰሜን ሸዋ ዞኖች እንዲሁም በሌሎች የአማራ ክልል አካባቢዎች እነዚሁ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል። ይሁንና እነዚህ ስራዎች በሚሰሩበት ጊዜ በርካታ ተግዳሮቶች እንደሚገጥማቸው ተናግረዋል።
ከተግዳሮቶቹ መካከል በዋናነት የአደጋ ጊዜ ስራዎች ሲሰሩ፣ የመንገድ መዘጋትና የዕንቅስቃሴ መገደብ ተጠቃሽ ሲሆኑ፣ ይህም በተለይ በአማራ ክልል ካለው ግጭት ጋር እንደሚያያዝ አቶ ኤቢሳ ተናግረዋል። “ሆኖም ይህንን ገደብ በጥንቃቄ በማለፍ ስራዎቻችንን ለመስራት እየሞከርን ነው” ሲሉ ጠቅሰዋል።
የሕዝቡ ፍላጎት መብዛትና ከዚህም ጋር የኤስ ኦ ኤስ የሃብት ውስንነት ሌላኛው ተግዳሮት መሆኑን አቶ ኤቢሳ አልሸሸጉም። ከጦርነት ጋር በተያያዘ የደህንነት ስጋት መኖሩን አንስተው፣ “ስራችንን ስንሰራ ከፍተኛ ጥንቃቄ እናደርጋለን።” ብለዋል።
ለዚህም ተቋማቸው በጥናት ላይ የተመረኮዘ የጥንቃቄ አካሄድ እንደሚከተል ነው አቶ ኤቢሳ የገለጹት። “እንደ አገር አሁን ያለንበት ሁኔታ ማንንም አይጠቅምም። ሕጻናትን በተለየ መልኩ ይጎዳል።” ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ሁሉም ወገኖች ዓለምአቀፍ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሕጎችን እንዲያከበሩ ጠይቀዋል።
ባለፈው ማክሰኞ ጥቅምት 12 ቀን 2017 ዓ.ም. ድርጅቱ በኢትዮጵያ ስራ የጀመረበትን 50ኛ ዓመት ክብረ በዓል የማጠናቀቂያ መርሃ ግብር በሸራተን አዲስ ሆቴል ሲያከብር፣ የድርጅቱ አመራሮች፤ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የመገናኛ ብዙሃን ባለሞያዎች ተገኝተዋል።
የኤስ ኦ ኤስ የሕጻናት መንደሮች በኢትዮጵያ በ50 ዓመታት የበጎ ተጽዕኖ ጉዞው፤ 8 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሰዎችን መድረስ እንደቻለ “Global Exceptional Excellence Consultancy” የተባለው ድርጅት ያደረገው ጥናት ያመለክታል።

Read 582 times