“የንጋት ኮከብ ለኢትዮጵያ” የተሰኘው አዲስ ፓርቲ በዋቢሸበሌ ሆቴል ሊሰጠው የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ በፀጥታ ሃይሎች መከልከሉን ተከትሎ የፓርቲው አደራጆች በሰጡት አስተያየት “ይሄ ከመንግስት የምንጠብቀው ተግባር ነው” ብለዋል። የፓርቲው አደራጅ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ሃብታሙ ኪታባ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ ባለፈው ረቡዕ ጥቅምት 13 ቀን 2017 ዓ.ም. ከጠዋቱ 4:30 ላይ ፓርቲያቸው በዋቢሸበሌ ሆቴል ሊሰጥ የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በጸጥታ ሃይሎች መከልከሉን አረጋግጠዋል። “ይህም ተግባር የምንጠብቀው ስለነበር ብዙም አልገረመንም።” ብለዋል።
ጋዜጣዊ መግለጫን የመከልከልና ሌሎች የመብት ጥሰቶች “ወደፊትም ሊኖር እንደሚችል ፖለቲከኛው ተናግረዋል።
“በአሁኑ ወቅት ያለው መንግስት የሃይማኖት ተቋማትን ጨምሮ ሁሉንም ነገር መቆጣጠር የሚፈልግ መንግስት ነው ያለው” የሚሉት አቶ ሀብታሙ “በተለመደው መንገዳቸው ቢቀጥሉ አይገርምም” ሲሉ ትችታቸውን ሰንዝረዋል።
በየጊዜው በመንግስት ላይ ለምናቀርበው ትችትና ወቀሳ እውነትነት ተጨባጭ ማሳያ ነው ያሉት አቶ ሀብታሙ በዚህም ባለፈው ረቡዕ ያለምክንያት የተከለከለው የፓርቲያችን ጋዜጣዊ መግለጫ “መንግስት ስራችንን እያቀለለልን ነው” ብለዋል። “በዚህ ዘመን መግለጫ ለመስጠት የግድ ሆቴል መከራየት አያስፈልግም፤ ቴክኖሎጂው ብዙ አማራጭ ስለሚሰጥ ያን ያህል ለእኛ አይቸግረንም።” ሲሉ በሰላማዊ ትግላቸው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
የፓርቲው የቅድመ ምስረታ መግለጫ እንደተመለከተው፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለግል ሃብታቸው ዋስትና ያጡባት፣ ኢንቨስተሮች የሚሸሹባት፣ መንግስታዊ ሽብር በመስፋፋቱ ሰላም የሌለባት፣ ብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ ተስፋ ቆርጦ ጥቂቶች ለጊዜው የሚፈነጩባትና ዘመነ መሳፍንትን ለመመለስ በቋፍ ላይ እንደምትገኝ ተጠቅሷል። አዲሱ ፓርቲ ባስተላለፈው ጥሪ፤ “ብልፅግና ፓርቲ የችግር ምንጭ እንጂ መፍትሔ ሊሆን የሚችል ስብስብ ባለመሆኑ፣ በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምን ሁሉ ጥቃቅን ልዩነቶች በማራቅ በጋራ በመቆም ሊታገለው ይገባል” ብሏል።
ፓርቲው አክሎም፤ “ዕውነተኛ” የሲቪል ማሕበራት፣ የማሕበረሰብ አንቂዎች፣ የመገናኛ ብዙሃንና የፖለቲካ ፓርቲዎች “በመተባበርና በመከባበር” ለጋራ ሕልውናና ለትውልዱ ቀጣይነት በጋራ እንዲቆሙ ፓርቲው ጥሪ አስተላልፏል፡፡ አገሪቱ ከተጋረጠባት ብሔራዊ አደጋ እንድትወጣ ዜጎች በአጠቃላይ ከንጋት ኮከብ ለኢትዮጵያ ፓርቲ ጎን እንዲቆሙና በጋራ እንዲሰሩ የትግል ጥሪ ማቅረቡን በመግለጫው ተገልጿል፡፡
Published in
ዜና