የኻን ዩኑስ የዘካ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት፣ ዶ/ር ጀሚል አቡ ቢላል እንዳስተላለፉት
እኔ ግዞትን ወደ ጊዜያዊ እናት አገር፣ ሕልሙንም ወደ ዳርቻ የለሽ ትግል መለወጥ የቻለ ስደተኛ ልጅ የሕያ (ሲንዋር) ነኝ። እኒህን ቃላት ስደረድር የሕይወቴን ቅፅበቶች በመላ እያስታወስኩ ነው። ያደግሁባቸውን ጠባብ ጎዳናዎች፣ ያሳለፍኩትን ረጅም የወህኒ ኑሮ፣ በፍልስጤም ምድር የፈሰሰችዋን እያንዳንዷን ደም አስታውሳለሁ።
ፍልስጤም አንዲት ቅዳጅ ትውስታ፣ በፖለቲከኞች ጠረጴዛ ላይ የተረሳች ቁራጭ ካርታ በሆነችበት ዘመን፣ በኻን ዩኑስ የስደተኞች መጠለያ በ1962 ተወለድኩ። ሕይወቴ የተፈተለው በእሳትና አመድ መካከል ነበር። በወረራ ሥር መኖር ዘላለማዊ ወህኒ መሆኑን ገና በልጅ ዕድሜዬ ተረዳሁ። በፍልስጤም ምድር ተርታ የሚባል ሕይወት እንደሌለ በአፍላነቴ ተገነዘብኩ። በዚህች ምድር እኖራለሁ ያለ ሰው፣ ዝናሩ የማይነጥፍ መሣሪያ በልቦናው ይታጠቅ፤ ለረጅሙ የነፃነት ጉዞ መንፈሱን ያዘጋጅ ዘንድ ግድ ይለዋል።
ኑዛዜዬ ከዚህ ይጀምራል…! ወረራውን በመቃወም የመጀመሪያዋን ድንጋይ ከወረወረው ታዳጊ ግዙፍ እውነታን ተረድተናል። የምንወረውራት እያንዳንዷ ድንጋይ፣ ቁስላችንን አይቶ ዝም ላለው ዓለም የምናሰማት ቃላችን ናት። የሰው ማንነት የሚለካው በዕድሜው ሳይሆን፣ ለእናት አገሩ በከፈለው መስዋዕትነት መሆኑን የጋዛ ጎዳናዎች አስተምረውኛል። የእኔም ሕይወት ያለፈው በዚሁ መልክ ነበር… ተደጋጋሚ ወህኒ፣ በርካታ ውጊያ፣ የበዛ ሕመምና እስከገደፉ በተስፋ የተሞላ ሙቅ ሕይወት…
በ1988 ነበር የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶብኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ወህኒ ቤት የገባሁት። ፍርሃትን ከነጭራሹ አላውቀውም። በጨለማ የእስር ቤት ክፍሎች ሆኜም በግድግዳው ገጽ ላይ ወደ ሰፊው አድማስ የሚከፈት መስኮት፣ በብረት ፍርግርጎቹ መካከልም የነፃነቱን ጉዞ የሚያበራ ፋኖስ ይታየኝ ነበር። በእስር ቤት ሶብር መልካም ባህሪ ብቻ አለመሆኑን፣ ይልቁንም ባህርን ጠብታ በጠብታ የመጭለፍ ያህል እንደ ብረት ጠንካራ መሣሪያ መሆኑን ተረዳሁ።
ኑዛዜዬን እንካችሁ…! ወህኒ ቤትን አትፍሩ። ወህኒ ቤት የነፃነት ጉዟችን አንድ ግብዓት ነው። ነፃነት ከተሰረቀ መብት ይልቅ ከህመም ተፀንሶ በትዕግስት የሚቀረጽ ሐሳብ መሆኑን የተማርኩበት መድረሳ ነው።
በ2011 ዓ.ም በ”ወፋኡል አሕራር” የእስረኛ ልውውጥ ስምምነት ስፈታ፣ ማንነቴ እጅጉን መቀየሩን ለማስተዋል በቃሁ። የወጣሁት እምነቴ ጠንክሮ ነበር። ትግላችንም ከትግልነት ባለፈ እስከ መጨረሻዋ የደም እንጥፍጣፌያችን ተሸክመነው የምንዘልቅ፣ የአላህ ውሳኔ (ቀደር) መሆኑን ተገንዝቤ ነበር።
ኑዛዜዬን እንካችሁ…! ነፍጣችሁን፣ ለድርድር የማይቀርብ ክብራችሁን፣ መሞት የማያውቅ ሕልማችሁን አጥብቃችሁ ያዙ። ጠላት ትግላችንን ማስቆም ይሻል። ወኔያችንን በማለቂያ የለሽ የድርድር ተስፋ ጠፍሮ ለማኮላሸት ይደክማል። እኔ ግን እላችኋለሁ… በመብታችሁ አትደራደሩ። ትግላችን በተሸከምነው ነፍጥ ብቻ የሚሰፈር አለመሆኑን አትርሱ። ትግላችን ፍልስጤምን መውደዳችን፣ በከበባና በድብደባ የማይፈታ ወኔያችን መሆኑን አስታውሱ።
ኑዛዜዬን እንካችሁ…! ለሸሂዶቻችን ደም ታማኝ ሁኑ። እሾሃማውን መንገድ ያሳየን ትውልድ፣ በደሙ መስዋዕትነት የነፃነትን መንገድ አስጀምሮናልና በፖለቲካ ጨዋታ፣ በዲፕሎማሲ ውስለታ ክብሩን ዝቅ ከማድረግ ተጠንቀቁ። የእኛ መኖር ዓላማ ቀደምቶቻችን የጀመሩትን ትግል ከዳር ማድረስ ነውና፣ የፈለገው ቢሆን ከመንገድ ማፈንገጥ አይገባም። ጋዛ ምንጊዜም የትግሉ ዋና ከተማ፣ የፍልስጤማዊ ወኔ መቀመጫ ልቦና ሆና ኖራለች። ወደፊትም ትኖራለች።
በ2017 የሐማስን የጋዛ ክንፍ አመራር ኃላፊነት ስወስድ፣ ለእኔ ጉዳዩ የአመራር መቀያየር ጉዳይ ብቻ አልነበረም። ይልቁንም ከወንጭፍ ጀምሮ ወደ ነፍጥ ያደገው ገናና ትግላችን ዕድሜ፣ የቀጣይነት ሠንሠለት ነበር። በእያንዳንዷ ቀናት የሕዝባችንን ዘወትራዊ ፍዳ፣ በዓይኔ በብረቱ ታዝቤያለሁ። የነፃነት ጉዟችን እያንዳንዷ እርምጃም ብዙ መስዋዕትነት የሚከፈልባት መሆኑን ተረድቻለሁ።
አንድ ነገር ግን እርግጠኛ ሆኜ እነግራችኋለሁ…! እጅ መስጠት የባሰ ዋጋ ያስከፍለናል። ግዴለም በጥንካሬያችን እንዝለቅ። ዛፍ በሥሮቹ አፈሩን አንቆ እንደሚረጋ ሁሉ የፍልስጤምን አፈር ሙጭጭ አድርገን እንያዝ። ለመኖር የወሰነን ሕዝብ የትኛውም ንፋስ ከመሬቱ ሊነቅለው ከቶ አይችልም።
የአቅሷ ማዕበል ዘመቻ መሪ መሆን ለእኔ ትልቅ ክብር ነበር። የአንድ ግሩፕ ወይም የአንድ ንቅናቄ መሪ ሳይሆን ነፃነትን የሚያልም ፍልስጤማዊ ሁሉ ድምጽ መሆን እንደቻልኩ ተሰምቶኛል። ትግል ኃላፊነት እንጂ ምርጫ እንዳልሆነ ሁሌም እረዳ ነበር። እናም ይህ ልዩ ዘመቻ በፍልስጤማውያን የትግል መዝገብ አዲስ ገጽ የሚገልጥ፣ የተለያዩ ታጋይ ቡድኖችን በጠላት ፊት በአንድነት የሚያሠልፍ ዘመቻ እንዲሆን ጥልቅ ፍላጎት ነበረኝ፤ ጠላታችን ሕፃን ከሽማግሌ፣ ድንጋይ ከዛፍ ሳይለይ ሁሉንም ያጠቃልና።
ኑዛዜዬ ግለሰባዊ አይደለም…! ይልቁንም ነፃነትን ለሚያልም እያንዳንዱ ፍልስጤማዊ ሁሉ፣ በትከሻዋ ሰማዕት ልጇን ለምትሸከም እናት ሁሉ፣ በዕኩያን ጥይት ልጁ ለተገደለችበት አባት ሁሉ የጋራ ስንቅ የሚሆን ውርስ ነው።
የመጨረሻ ኑዛዜዬን እንካችሁ…! ትግላችን መና እንደማይቀር አትርሱ። የምንከፍለውን ዋጋ ብቻ ሳይሆን፣ በወኔና በክቡር ሰብዕና ጌጠን የኖርነውን ሕይወት አስታውሱ። የጋዛ የከበባ ኑሮና የወህኒ ውጣ ውረድ፣ ትግሉ ትከሻ የሚያጎብጥ፣ ጉዞውም ሰውነት የሚያዝል መሆኑን አስተምሮኛል። ግና እጅ አልሰጥም ባይ ሕዝብ ብዙ ተዓምር ይሠራል።
ከምድራዊ ሕይወት ፍትህ አትጠብቁ። የዓለም ሕዝብ ሕመማችንን ዓይቶ እንዳላየ መሆን መምረጡን ስረዳ ኖሬያለሁ። እናንተም መረዳታችሁ አይቀርምና፣ ከሌሎች ፍትህ መጠበቁን ትታችሁ ራሳችሁ ፍትህ ሁኑ። የፍልስጤምን ሕልም በልቦናችሁ ያዙ። ከእያንዳንዱ ቁስለት ጥንካሬን፣ ከእያንዳንዷ ዘለላ እንባ ተስፋን መምዘዝ ተማሩ።
ይሃችሁ የእኔ ኑዛዜ ነው…! መሣሪያችሁን በፍጹም አትጣሉ። ወንጭፎቻችሁን አታስቀምጡ። ሸሂዶቻችሁን አትዘንጉ። ሕልማችሁን አትተዉ። እኛ በአፈራችን፣ በልቦናችን፣ በልጆቻችን የወደፊት ተስፋ ውስጥ እንደምንኖር አትዘንጉ።
ኑዛዜዬ ይህ ነው…! እስከ ሕይወቴ መጨረሻ የታመንኩለትን የፍልስጤም ውዴታ፣ በጫንቃዎቼ የተሸከምኩትን ታላቅ ሕልም ከዳር አድርሱ። እኔ ብወድቅ እናንተ አትውደቁ። ወደ መሬት ያልጣልኩትን ሠንደቅ ዓላማ ከፍ አድርጋችሁ አውለውልቡ። መስዋዕትነቴን እንደ ድልድይ ተጠቅማችሁ ለተተኪው ክንደ ብርቱ ትውልድ መደላድሉን ፍጠሩ። እናት አገር በተግባር የሚኖሩት ተጨባጭ እንጂ የሚተርኩት ተረክ አይደለምና፣ በሚሰዋው እያንዳንዱ ታጋይ፣ እልፍ ተተኪዎች እንደሚፈጠሩ ጥርጣሬ አይግባችሁ።
የእኔ ተራ ደርሶ ከተለየኋችሁ የነፃነቱ ማዕበል የመጀመሪያ ጠብታ እንደነበርኩ፣ ሕይወቴንም ጉዟችሁን ስትፈጽሙ በማየት ጉጉት የገፋሁ መሆኔን አትዘንጉ። በጠላታችሁ ጉሮሮ ውስጥ የተሰካችሁ እሾህ ሁኑ። ዓለም ለሐቃችን መታገላችንን እስኪረዳ፣ ለዕለታዊ ዜና የቁጥር ግብዓት ብቻ እንዳልሆንን እስኪገነዘብ ድረስ ትግላችሁን ቀጥሉ።
የሕያ ኢብራሂም ሲንዋር | ጋዛ