Monday, 28 October 2024 00:00

ከተመኙ አይቀር “ቢሊዮነር” ለመሆን መመኘት ነው፡፡ አይደለም እንዴ?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

ጣፋጩን ፍሬ ለመቅመስና ለመግመጥ መመኘት፣ ክፋት የለውም። እንዲያውም ተገቢ ነው። ጠቃሚና አስደሳች ነገር ለማግኘት መመኘት፣ የጤናማ ሕይወት ገጽታ ነው። አለዚያማ ሕይወት ትርጉም ያጣል። ወይ ሌሎችን የማገልገል ዕዳ የተጫነብን ባሮች እንሆናለን። ወይ “ከንቱ ድካም ይወድልናል”… “ውጤት ለሌለው ልፋት ተፈጥረናል” እንደማለት ይሆናል።
ከምር እናስበው ከተባለማ፣ መልካም ነገር አለመመኘት፣ የሕይወትን ጣዕም ከማበላሸት አልፎ ሕይወትን ያሳጣል ብለን መናገርም እንችላለን። ያለ መልካም ነገር፣ ሕይወት አይሰነብትም።
እንዲህ ሲባል ግን፣ መልካም በመመኘት ብቻ ሕይወታችንን እናሳምራለን ማለት አይደለም። ጣፋጭ ፍሬ ለመብላት ከተመኘን፣… በአንዳች ተአምር ዓለም ሁሉ ታዛዥ ባሪያችን፣ ምኞታችንን ለማሟላት የሚተጋ የግል አገልጋያችን ይሆንልናል ማለት አይደለም። ምኞት ብቻውን አይበቃም። ከንቱ ምኞት ብንለው ነው የሚሻለው። እንዲያውም፣ “ከምር እንፈልገዋለን ወይ? ከምር እንመኘዋለን ወይ?” ሊያስብለንም ይችላል።


ከምር ከፈለግነው፣ ከምር ከተመኘነው… እንዲሁ በራሱ ጊዜ ይመጣል ብለን እጃችንን አጣጥፈን እንጠብቃለን እንዴ? ይነስም ይብዛ፣ የተወሰነ ያህል ደፋ ቀና ለማለት መሞከራችን ይቀራል? ካልሞከርን፣ ትንሽ ካልጣርን፣ ምኞታችን የውሸት አይመስልብንም? ኢሎን ሞስክ ይህን እየነገረን ሊሆን ይችላል።
ውጤትና ስኬቴን ብቻ እንጂ መከራዬን አላያችሁም ሊለን የፈለገ ይመስላል። እውነትም ስኬት በየዓመቱ ይወራለታል። ዘንድሮም የአለማችን ቁጥር 1 ቢሊየነር ነው ተብሎ በዜና ይሰራጫል። ሀብት ንብረቱን ያፈሰሰባቸው የቴክኖሎጂ ፋብሪካዎች፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፉና አስደናቂ “ፈር ቀዳጅ” ስኬቶችን ቢያስመዘግቡም፣ ከእያንዳንዱ ግሥጋሤና እመርታ ጋር ተጨማሪ ኢንቨስትመንትን የሚፈልጉ ናቸውና በተደጋጋሚ የኪሳራ አፋፍ ላይ አድርሰውታል።
ሀብቱ ሁሉ እየተራቆተ ከጓደኞቹ ባገኘው ብድር ለመንቀሳቀስ የተገደደበት ጊዜ ነበር።
የኤሌክትሪክ መኪና አምራች ኩባንያው “ቴስላ” በ2018 ከነባሮቹ መኪና አምራቾች ጋር ስሙ ለመጠራት የበቃበት ጊዜ ነው። ነገር ግን ደግሞ፣ በኪሳራ ለመፍረስ የጥቂት ሳምንታት ዕድሜ ብቻ ነበር የቀረው።
በሳምንት 2 ሺ የኤሌክትሪክ መኪኖችን ማምረት የቻለ ሌላ ኩባንያ በወቅቱ አልነበረም። ነገር ግን በዚያው ዓመት ውስጥ፣ ከዕጥፍ በላይ ካላመረተ፣ በየሳምንቱ 5 ሺ መኪኖችን ለገበያ ማቅረብ ካልጀመረ፣ ኩባንያው በኪሳራ እንደሚፈርስ፣ ኢሎን ሞስክ ባዶ ኪሱን እንደሚቀር ይታወቅ ነበር። የሂሳብ መዝገቡ ላይ በግልጽ ይታያል። እና ምን ተሻለ?
በሳምንት 5 ሺ መኪኖችን ማምረት እንደሚቻል ታይቶታል። ሌሎቹ ግን አልታያቸውም። አንዳንዶቹ የመኪናውን ዲዛይን ለነባር ኩባንያዎች መሸጥ ይሻላል ብለዋል። ሌሎቹ ለኤሌክትሪክ መኪና የሚያገለግል የባትሪ ፋብሪካ ላይ ማተኮር ነው የሚያዋጣን ብለው ወስነዋል። የኩባንያው ባለድርሻ ናቸው። የፋብሪካውን ሥራ የሚመሩ ባለሙያዎችም፣ ሌላ መፍትሔ አልታያቸውም። ሊያሳምናቸው ቢሞክርም በቀላሉ የሚሳካለት አልሆነም።


የኩባንያው መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ቢሆንም፣ የአክሲዮን ኩባንያ ስለሆነ፣ ሌሎች ባለአክሲዮኖችንና ባለሙያዎችን ሳያሳምን ዕቅዱን ማሳካት አይችልም።
ቢጨንቀው፣ ለጊዜው ደሞዝ አትክፈሉኝ። በግማሽ ዓመት ውስጥ የኩባንያውን ምርት በዕጥፍ ካሳደግኩና በሳምንት 5 ሺ መኪኖችን ወደ ማምረት ካላደረስኩ፣ የኩባንያው የአክሲዮን ዋጋም በዕጥፍ ካላሳደግኩ፣ ምንም ክፍያ አልቀበልም። ዕቅዴ ከተሳካ ግን፣ ተጨማሪ የአክሲዮን ድርሻ ትሰጡኛላችሁ አለ።
የአክሲዮናቸውን ዋጋ በዕጥፍ የሚያሳድግላቸው ከሆነ፣ ምን ቸገራቸው? መቼም ዕቅዱ እንደሚሳካ አስተማማኝ ዘዴ ቢታየው ነው። እንደሚሳካለት እርግጠኛ ባይሆን ኖሮ፣ “ካልተሳካ ምንም አትክፈሉኝ” ይል ነበር? ባለአክሲዮኖች በዚህ ሐሳብ ተማምነው ነው እሺ ብለው የተስማሙለት።


ታዋቂ የአሜሪካ የሚዲያ ተቋማት ላይ የተሰራጩ ዘገባዎች ግን የኢሎን ሞስክ ዕቅድ ላይ የሚሳለቁ ናቸው። ዕቅዱ የማይቻልም አስቂኝም እንደሆነ ባለሙያዎች ይመሰክራሉ የሚል ዘገባ በኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ታትሟል።
ዕቅዱ ካልተሳካለት ባዶ ኪሱን ይቀራል። በጊዜ የመኪና ዲዛይኑን መሸጥ፣ የባትሪ ፋብሪካ ላይ ማተኮር ይችላል። ቢሊዮነር ሆኖ መቀጠል ይችላል። ነገር ግን፣ ሕልሙ ግን የኤሌክትሪክ መኪኖችን በገፍ የሚያመርት ኩባንያ መፍጠር እንጂ፣ ዲዛይን መሸጥ ወይም ባትሪ እያመረተ መቸርቸር አይደለም። ዲዛይኑም የባትሪ ፋብሪካውም የመጨረሻ ግብ አይደሉም - በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምርጥ የኤሌክትሪክ መኪኖችን ለማምረት የሚያገለግሉ ግብአቶች ናቸው እንጂ።


ሌሎች ባያምኑትም እንደሚቻል አውቋል። ሌሎች ቢስቁም ማሳካት እንደሚችል ታይቶታል።
ይቻላል፤ እችላለለሁ ብሎ ካሰበ ደግሞ፣ ዓለም ሁሉ ቢቃወመው እንኳ ይሁንላችሁ ብሎ መቀመጥ አይሆንለትም። የሕይወት ፍልስፍናው እንዲህ ነው። እንዲያውም ከዚህም ያልፋል።
ዕቅዳችን እንዳናሳካ የሚከለክል የተፈጥሮ ሕግ አለ ወይ? ብለን መጠየቅ እንዳለብን ይገልጻል። የተሻለ ነገር እንዳንሠራ የሚከለክል የፊዚክስ ሕግ ከሌለ፣ የተሻለ ነገር ከመሥራት ወደኋላ ማለት የለብንም ይላል።
ፍልስፍና አበዛሳ! ብለን ልንቀልድበት እንችላለን። እሱ ግን ከምሩ ነው። ከምሩም ስለሆነ፣ ዕቅዱ እስኪሳካ ድረስ፣ ውሎና አዳሩ ፋብሪካው ውስጥ አደረገ። ፋብሪካው አዲስ ነው። ነገር ግን፣ የማምረት ዐቅሙን በዕጥፍ ለማሳደግ፣ ሥራውን የሚያጓትቱ ነገሮችን ለማስወገድ፣ ሥራውን የሚያፋጥኑ ዘዴዎችን ለመፍጠር አላመነታም። እንደ አዲስ ሸነሸነው።
ማንም ባያምነውም፣ ለበርካታ ወራት፣ ከፋብሪካው ሳይለይ፣ ብዙ ሌሊቶች ከጠረጴዛው ስር ለጥቂት ሰዓታት ብቻ እየተኛ ሲዋከብ ከረመ። በርካታ ሙያተኞችና ሠራተኞች፣ በዕቅዱ አልተስማሙም። አሳማኝ አልሆነላቸውም። የዐቅማቸውን እስከተጉ ድረስ ግን ችግር የለውም።
አንዳንዶቹ ግን እንቅፋት ለመሆንና ለመለገም ሞክረዋል። እነዚህን ሊታገሣቸው አልፈቀደም። ሳያመነታ ማባረር ነበረበት። ባያባርራቸውና ዕቅዱ ቢሰናከል፣ ኩባንያው ይከስራል፤ ብዙ ሠራተኞች ይበተናሉ።


ቀሽሞችንና ልግመኞችን መታገሥ፣ ባለሙያዎችንና ታታሪዎችን መበደል ነው ብሎ ያምናል። ልግመኞች እንዳይጠሉት የሚጨነቅ የሥራ መሪ፣ የትጉህ ሠራተኞችን እንጀራ ይዘጋል ባይ ነው።
ለማንኛውም፣ ከወራት የቀን ተሌት ጥረት በኋላ፣ ስድስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ዕቅዱን ለማሳካት ችሏል። በየሳምንቱ 5 ሺ መኪኖችን ማምረት ጀምሯል። በዓመት ግማሽ ሚሊዮን መኪኖች ማለት ነው። ከዚሁ አልቆመም።
ተጨማሪ ግዙፍ ፋብሪካ በቴክሳስ ከፍቷል። በአንድ በኩል የኩባንያው ምርት እንደገና ወደ ስድስት ዕጥፍ ጨምሯል - በሳምንት ከ30 ሺ በላይ መኪኖች፣ በዓመት ከ1.5 ሚሊዮን በላይ መኪኖች ማለት ነው። በዚያው ልክ ለብዙ ባለሙያዎች ተጨማሪ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል። ልግመኛ ሰዎችን ያላባረረ፣ ለብዙ ሰዎች የሥራ ዕድል መክፈት አይችልም ብሎ የሚናገረው አለምክንያት አይደለም ለካ!
ዕቅዱ ስለተሳካ፣ ተጨማሪ አክስዮን እንዲያገኝ ከ80 በመቶ የኩባንያው ባለአክሲዮኖች ተስማምተው ወስነዋል። የተወሰኑት ባለአክሲዮኖች ግን ሐሳባቸውን ስለቀየሩ፣ ለፍርድ ቤት አቤቱታ አቅረበዋል። እናም እስከዛሬ እልባት ስላላገኘ፣ ኢሎን ሞስክ ክፍያውን አላገኘም። ክፍያው ከ40 ቢሊዮን ዶላር በላይ ነው። አሁን እንዲህ በቁጥር ሲገለጽ፣ አፍ ያስከፍታል። ያኔ ግን መሳቂያ ነበር። ዕቅዱ ስለማይሳካ ቀልጦ ይቀራል እያሉ ቀልደውበታል።
ይልቅስ አስደናቂው ነገር ሌላ ነው።


ከዚያ ሁሉ ወከባ ጎን ለጎን፣ ኢሎን ሞስክ በሮኬትና በመንኮራኩር ቴክኖሎጂ ላይ ሌላ የማይታመን ታሪክ እየሠራ ነበር። ለጊዜው፣ ዝርዝሩን ትተን በዐጭሩ ገልጸን ብናልፈው ይሻላል።
ስፔስኤክስ የተሰኘው የኢሎን ሞስክ ኩባንያ ዛሬ የዓለማችን ቁጥር 1 የሮኬትና የመንኮራኩር ኩባንያ ቢሆንም፣ የዛሬ ዐሥር ዓመት ግን ገና “ጀማሪ” ነበር ማለት ይቻላል።
የትም አይደርስም ነበር የሚሉት።
ያኔ፣ በዓለማችን ዙሪያ በዓመት 80 ሮኬቶች ወደ ጠፈር ይመጥቁ ነበር። ከእነዚህ ውስጥ ሦስቱ የስፔስኤክስ ሮኬቶች ናቸው። ዘንድሮስ?
ባለፉት በዘጠኝ ወራት ውስጥ 185 ሮኬቶች ወደ ጠፈር መጥቀዋል። ከእነዚህ ውስጥ 100ዎቹ የስፔስኤክስ ናቸው። ይህም ብቻ አይደለም።
በዓለም ዙሪያ ከሚሽከረከሩ 10ሺ ገደማ ሳተላይቶች መካከል 7 ሺዎቹ የስፔስሊንክ ኩባንያ ሳተላይቶች ናቸው። ስፔስሊንክ በኢሎን ሞስክ የተቋቋመ ኩባንያ ነው። በሳተላይት አማካኝነት በዓለማቀፍ ዙሪያ የኢንተርኔት አገልግሎት የሚሰጥ ኩባንያ።
ይሄ ሁሉ አስደናቂ ስኬት የተገኘው፣ በምኞት ብቻ አይደለም።
ሰሞኑን በታተመው የፎርብስ መጽሔት ላይ ኢሎን ሞስክ የዓለማችን ቁጥር 1 ቢሊዮነር ተብሎ የተጽፎለታል። የ244 ቢሊዮን ዶላር ጌታ ነው ተብሏል። ይሄም በምኞት ብቻ የተገኘ አይደለም።


የኤሌክትሪክ መኪና ኩባንያው ስኬታማ እንዲሆን፣ ፋብሪካ ውስጥ እየዋለ እያደረ ብዙ መከራ አይቷል ይባላል። የሮኬትና የመንኮራኩር ኩባንያው ስኬታማ የዓለም መሪ እንዲሆን ደግሞ፣ ብዙ ዕጥፍ መከራዎችን እየተጋፈጠ ማሸነፍ ነበረበት። ዛሬም ጭምር ሥራው አላባራም።
ስኬታማ ለመሆን መመኘት፣ በዚያው ልክ ሸክሙ ከባድ ነው።
እንደ ምኞታችን ትልቅነት ነው፣ የመከራው ክብደት።
ያን ሁሉ ሸክም ለመጋፈጥና ለማሸነፍ የሚፈልግ ሰው ስንት ቢሆን ነው? ብዙ ሰዎች እንደኔ ለመሆን የሚፈልጉ አይመስለኝም ብሎ መናገሩም ለዚህ ነው ይላሉ - የስነ ልቦና ተመራማሪው ጆርዳን ፓተርሰን።
ምኞትና ሸክም ግን መነጠጣል የለባቸውም። ጥረትና ውጤት፣ ወይምሥራና ፍሬ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። እንደ መጓዝና እንደ መድረስ ናቸው። አንዱ ያለሌላኛው አይኖርም። ቢኖርም ትርጉም አይሰጥም።
መድረሻው የማይታወቅ ጉዞ፣ “ለፍሬ ያላለው” ከንቱ ልፋት ነው።
ያለ ጉዞ መድረስም ስንዝር የማይራመድ “ለፍሬ የማይደርስ ምኞት” ነው።
ጥረትና ውጤት እንዳይነጣጠሉ “Value and Virtue” ብለው ያጣምሯቸዋል - በፍልስፍና። እነዚህን አለያይቶ መነጠል ቀላል ስህተት አይደለም።


ሶቫሊዝም ባርነትን የአካባቢ ጥበቃ። ዋና ዋና የአስተሳሰብ ስህተቶች መካከል አንዱ፣ ጥረትን ከውጤት ጋር የማፋታት፣ የግል ዓላማን ከግል ኀላፊነት የመነጠል ስህተት ነው ይባላል - በአየን ራንድ ፍልስፍና።
ሥራውንና ፍሬውን የሚነጥሉ ስህተቶች በየዘመኑ መልካቸውን እየለዋወጡ የሚመጡ ቢሆኑም፣ ሁሌም ወደ ክፉትና ወደ ጥፋት ያመራሉ። የሰዎችን ንብረት ለመውረስ የሚያሰፈስፍ የኮሙኒዝም ወይም የሶሻሊዝም ፖለቲካ አንድ ምሳሌ ነው። ሰዎች፣ የሥራ ፍሬያቸውን መጠቀም፣ መገበያየት ወይም በልግሥና መስጠት አይችሉም ይላል -ኮሙኒስቱ። “ዜጎች ይስሩ፣ እኔ ምርታቸውን አከፋፍላለሁ” ባይ ነው።
የሚሠሩ እጆች እና የሚሰጡ እጆች ተለያዩ ማለት ነው።
ከጥንታዊው የባርነት ሥርዓት ብዙ ልዩነት የለውም። የገዢው ዓላማ እንዲሳካና ምኞቱ እንዲሟላ፣ ባርያው ላይ የኀላፊነት ሸክም ይጫንበታል፤ በሰንሰለት ታስሮ በግዴታ ይሠራል።
ባርያ ያለክፍያ ይለፋል፤ ገዢው ፍሬውን ያፍሳል።
ዛሬ በዘመናችን ደግሞ፣ ነባሩ የሶሻሊዝም ፓለቲካ ላይ የአካባቢ ጥበቃ ፈሊጦች ተጨምረውበታል። “የሰው እጅ ያልነካው ተፈጥሮ” ከሁሉም የላቀ ውጤት እንደሆነ ይናገራሉ።፣ እጃችንን አጣጥፈን እንድንኖር ይፈልጋሉ። ወፍ ዘራሽ ውጤት ምን የሚሉት ውጤት ነው? እንዲሁ በባዶ መኖርስ እንዴት ይቻላል?
እጅ ከታጠፈ እጅ ያጥራል። እጅ ሥራ ከፈታ፣ ከእጅ ወደ አፍ ቁራሽ ጉርሻ ይጠፋል።


ከተራ ሸፍጥና ከስርቆት ጀምሮ እስከ ዝርፊያና ባርነት፣ ቀማኛ የፖለቲካ ሥርዓትና የንጥቂያ ሕጎች ጭምር፣ የክፋታቸው መጠን ቢለያይም፣ የስህተታቸው ቅኝት ተመሳሳይ ነው። የእገሌ እጆች ይሠራሉ፤ የእከሌ እጆች ይጎርሣሉ።
አንተ ያለ ዕዳህ ለብልጣብልጥ ሰዎች ተሸካሚ፣ አንቺም ያለፈቃድሽ ለጉልበተኞች አገልጋይ እንድትሆኑላቸው…
በተቃራኒው አንተና አንቺ እሳት መሞቅ ሲያምራችሁ ሌሎች ሰዎች የምድጃ ማገዶ እንዲሆኑላችሁ መጠበቅ እንደማለት ነው።
እውነትም ቀላል ስህተት አይደለም።
መሥራትና መኖር ሁለት የተለያዩ አማራጮች አይደሉም። መንታ ገጽታዎች ናቸው። አንድ ላይ አጣምረን ልናዋሕዳቸው ይገባል። ጥረትና ውጤትም ለየብቻ ከተነጣጠሉ ሕይወትን የሚያረክሱ፣ አብረው ሲኖሩና በጋራ ሲያድጉ ደግሞ ሕይወትን የሚባርኩ ጥንዶች ናቸው። አዳም… “ጥረህ ግረህ ትበላለህ” ተብሎ የተነገረው ለከንቱ አይደለም። ሔዋንም “በምጥ ትወልጂያለሽ” የተባለችው አለምክንያት አይደለም።.
በሌላ አነጋገር፣ “ሠርተህ ትኖራለህ” የሚለው ሐሳብ እንደ እርግማን መቆጠር የለበትም።
የግል ዓላማና የግል ኀላፊነት በጥምረት ነው ወደ ትክክለኛ ተግባር ወደ መልካም ኑሮ መሸጋገር የሚችሉት።
የአዳምና የሔዋን ትረካ፣ አድካሚ የኑሮ ጥረትንና ፍሬያማ የኑሮ ጣዕምን አንድ ላይ በጥንድ ያስተሳስራቸዋል።
“ውድ ነገር” በባዶ አይገኝም።


ዕውቀትና የሙያ ክህሎት፣ ሀብትና ንብረት ወፍ ዘራሽ አይደሉም።
በቀጥታና በተዘዋዋሪ ዋጋ ተከፍሎባቸው የሚመጡ ናቸው።
ምኞታችሁ እንዲሟላ በቅድሚያ ማሟላት የሚኖርባችሁ ነገር ይኖራል።
የወደዳችሁትን ለማግኘት ከፈለጋችሁ፣ ከእናንተ የሚፈለግባችሁ ነገር ይኖራል።
ሕይወት ውድ ነው። የዚያኑ ያህል ብዙ ዋጋ ይጠይቃል። የዋጋው ዐይነት ብዙ ነው። ለእውነት መታመንና ዕውቀት መጨበጥን ይጠይቃል። ዓላማንና ትጋትን፣ የሥነ ምግባርና የፍትሕ መርሖችን ይጠይቃል። ብቃትንና የግል ኀላፊነትን፣ ሕግና ሥርዓትን ይፈልጋል።
ተወዳጅና ተፈላጊ የሕይወት በረከት፣ ሁሌም ከጎኑ ውድ ክፍያ ይኖረዋል።
አዳምና ሔዋን ላይም ይህን እናያለን። የሕይወት ጥንድ ገጽታዎችን አጣምረው በጥንቃቄ እንዲገነዘቡ፣ በስንፍና እንዳይዘናጉ፣ ኮስተር ያለ ምክር ተሰጥቷቸዋል። አንተ ጥረህ ግረህ ትበላለህ! አንቺ በምጥ ትወልጂያለሽ! ተብለዋል። ቢሆንም ግን እርግማን አይደለም። በእርግጥ ለአዳምና ለሔዋን ብቻ የመጣ ምክር አይደለም። ለሁላችንም ነው።
የኢሎን ሞስክ ሕይወትም እንደዚያው፣ ይህን እውነት ያሳየናል የስኬቱና የውጤቱ ያህል ነው ጥረት ግረቱ።

Read 553 times