በአንዲት ትንሽ የገጠር ከተማ ውስጥ በሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ ላይ ተሰማርቶ የሚኖር አንድ ሰው ነበር፡፡ በአካባቢው ብዙ ነጋዴዎች ስላልነበሩ ለአያሌ ዓመታት በታዋቂነት ሠርቷል፡፡ ቀስ በቀስ ከተማዋ እያደገችና ነጋዴዎች እየተበራከቱ ሲመጡ ሕዝቡ የተለያዩ አማራጮችን መጠቀም ጀመረ፡፡ አንጋፋው ነጋዴም ከጊዜ ወደ ጊዜ ገበያው እየቀዘቀዘ፤ ደንበኞች እየቀነሱ፤ ገቢው እያሽቆለቆለ ከሥራ ውጭ በመሆኑ ቤተሰቡን ለማስተዳደር አቃተው፡፡
የቤተሰቡን እለታዊ የምግብ ፍላጎት ለሟሟላትም በአቅራቢያው ወደሚገኙ ከተሞች እየተንቀሳቀሰ ጊዜያዊ ሥራዎችን በመሥራት፣ ያገኛትን ለቤተሰቦቹ ያቃምስ ነበር፡፡ማልዶ ከቤቱ በመውጣት ቀኑን ሙሉ ሲንከራተት ውሎ ሲመሽ ወደ ቤቱ ይገባል፡፡ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ መምራት የተለመደ ተግባሩም ሆነ፡፡
ይሁን እንጂ ተስፋ ባለመቁረጥ በየጊዜው ወደተለያዩ አካባቢዎች በመጓዝ ያገኘውን ሥራ እየሠራ አካባቢውን ያጠና ነበር፡፡ በፍለጋው መሃል አንድ ቀን በርካታ የሰዎች ፍሰትና ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ወደሚታይባት ትንሽ ከተማ ደረሰ፡፡ በዚያም ለተወሰኑ ቀናት ተመላልሶ ከሠራ በኋላ፣ በዚያች ከተማ የምግብ ቤቶች እጥረት መኖሩን አስተዋለ፡፡ አነስተኛ ምግብ ቤት ቢከፍት እንደሚያዋጣውም አሰበ፡፡ ወዲያው የመሥሪያ ቦታ ተከራይቶ ሥራ ጀመረ፡፡
እንደ ጀመረም ጥሩ ምግብ ይሠራ ስለነበር በርካታ ደንበኞችን አፈራ፡፡ ደንበኞቹ ከመብዛታቸው የተነሳ አንዳንድ ጊዜ ረጅም ሰዓት ጠብቀው ይመገቡ ነበር፡፡ ገበያው በጣም አደገ፡፡ ትርፋማም ሆነ፡፡ ሁለተኛ ቅርንጫፍም ከፈተ፡፡ ታዋቂ ሆነ፡፡ የበለጠ ትርፍ ማግኘትም ተመኘ፡፡ ከዚያም ቀስ በቀስ ለገበያ ነው በሚል ሰበብ ምግቡን የሚያበራክት፣ ገቢውን በእጥፍ የሚጨምር፣ ለጤና የማይስማማ ግብአት መጠቀም ጀመረ፡፡ ዱቄቱ፣ ሽሮ በርበሬው፤ ዘይቱና የእንስሳት ተዋጽኦው ሁሉ የተቀላቀለ፤ ቀኑ ያለፈበት፤ ለጤና የማይስማማና በእርካሽ የሚገዛ ነበር፡፡ ሠራተኞቹ እያደረገ እያለው ትክክል እንዳልሆነ ቢነግሩትም፣ “ለገበያ የሚቀርብ ምግብ እንዲህ ካልተቀላቀለ አያዋጣም” በማለት ቀጠለበት፡፡ ደንበኞችም የሚቀርበው ምግብ ምቾት እየነሳቸውና ጤናቸው እየታወከ በመምጣቱ ቅሬታ ማቅረብ ጀመሩ፡፡ ገበያውም ቀነሰ፡፡ በዚህም ሳያበቃ ሰዎች ምግቡን ከተገቡ በኋላ በከፍተኛ የጤና መታወክ እራሳቸውን እየሳቱ ሆስፒታል መግባታቸው ተሰማ፡፡ የሚመለከተው አካል ቤቱን አሸገ፡፡ ነጋዴውም በቁጥጥር ሥር ዋለ፡፡ ለካስ ነጋዴው ቀድሞም ለኪሳራ የተዳረገው በዚሁ ምክንያት ነበር፤ ካለፈው ስህተቱ መማር ባለመቻሉም ለከፋ ችግር ተዳረገ፡፡
ጥራቱን ጠብቆ የተዘጋጀ ምርት ለገበያ ማቅረብ የተገልጋዩ፤ የአቅራቢውና የሃገር የጋራ ጥቅም ሲሆን ፤ በአንጻሩ ጥራቱን ያልጠበቀ ምርት ማቅረብ የሁሉም የጋራ ጉዳት ቢሆንም የኋላ ኋላ የአቅራቢው ጉዳት ያመዝናል፡፡
ጥራቱን የጠበቀ ምርት ማለት ምን ማለት ነው?
በቂ ጊዜ፤ ጉልበትና ግብዓት የፈሰሰበት፤
ውበቱ፤ ጤንነቱ የተጠበቀና ለረጅም ጊዜ አገልግሎት የሚሰጥ ቁስ ወይም ከባእድ ነገር ጋር ያልተቀላቀለ፤ያልተበረዘ ያልተከለሰ፤ ይዘቱና መጠኑ ተጠብቆ የተሰራ፤ ለጤና ምቹ የሆነ የምግብ ምርት ማለት ነው፡፡ በተቃራኒው ጥራቱን ያልጠበቀ ምርት ማለት፣በአነስተኛ ግብአት፤ ወጪና ጉልበት፤ ሳይጨነቁና ሳይለፉ በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ትርፍ ማግኘትና በአቋራጭ መክበር የሚፈልጉ ጥቂት ሰዎች፣ “ለገበያ ነው” በሚል ቋንቋ ሸፍነው የሚያቀርቡት የተጭበረበረ፣ የጥራት ደረጃውን ጠብቆ ያልተሰራ ወይም ያልተዘጋጀ፤ የመጠቀሚያ ጊዜ ገደቡ ያለፈበት፤ የተበላሸ፣ ዋጋው የወረደ፤ ጤናንና ምቾትን ከሚነሱ ግብዓቶች ጋር የተቀላቀለ ቁስ ወይም የምግብ ምርት ማለት ነው፡፡
ለገበያ ነው የሚለው ቋንቋ ምንን ይገልጸል?
ለገበያ ነው ! እንደ ሰዎች አስተሳሰብና እይታ ሁለት አይነት ትርጉም ወይም አጠቃቀም ሊኖረው ይችላል፡፡ የመጀመሪያው ለገበያ የሚቀርብን ምርት በጎ ገጽታ ለማሳየት የሚጠቅም ሲሆን፤ ለገበያ የሚቀርብ ምርት በተመረጡ ግብዐቶች ፤የጥራት ደረጃውን ጠብቆ በጥንቃቄ የሚሰራ ፤ተመራጭ ፤የተገልጋዩን ማህበረሰብ ፍላጎት የሚያረካ፤ ሁለንተናዌ ጤንነትን የሚጠብቅ ደንበኝነትን የሚያጠናክር፤ ተአማኒነትን የሚያተርፍ፣ ገበያን የሚያሳድግ፤ የግልን የማህበረሰብንና የሃገርን ኢኮኖሚ የሚያሳድግ ምርት መሆኑን ያመለክታል፡፡ በሌላ መልኩ ዛሬ ዛሬ እየተለመደ የመጣው ትርጉም ለገበያ የሚቀርብ ምርት በትንሽ ወጭና ጉልበት ብዙ ምርትና ትርፍ የሚገኝበት፤ ጎጂና ጤናን የሚያውክ ግብአት የሚቀላቀልበት፤ ጥራቱን ያልጠበቀ ፤ ለጊዜው ከፍተኛ ትርፍ የሚያስገኝ ምርት ማለት ነው፡፡
ጥራቱን ያልጠበቀ ምርት፡- አርቆ ባለማሰብ በሚፈጠር ከፍተኛ የጥቅም ፍላጎት ትርፋማ የሚያደርግ ቢመስልም፣ በየትኛውም መንገድ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ ማህበረሰቡ፤ አምራቹና ሃገር ጥራታቸውን ባልጠበቁ ምርቶች በሚከሰቱ ችግሮች ያልተጠበቁ ጉዳቶችን ለማስተናገድ ይገደዳሉ፡፡ ከነዚህም ጉዳቶች ውስጥ ጥቂቶቹን እንመልከት፡፡
- የተገልጋዩን ማህበረሰብ ገንዘብ፤ጊዜና ጉልበት ያባክናል፤ አካላዊ፤ አእምሯና ስነልቦናዊ ጤናን ይጎዳል ፤ እርካታን ፤ምቾትን፤ ሰላምንና እምነትን ያሳጣል፡፡
- በቶሎ ስለሚበላሽ፤ ስለሚቀየርና ስለሚጣል የአካባቢ ብክለትን ያስከትላል፡፡
- አምራቹ ተአማኒነትን ያጣል፤ ተገልጋይ ይርቃል፤ ሥራው ይቀንሳል፤ ለኪሳራ ይዳረጋል፤ የሕግ ተጠያቂ ይሆናል፤ በመጨረሻም ሥራውን ያጣል፡፡
- የንግዱን ዘርፍ ስለሚያዳክም፣ በሃገር ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል፡፡
በአጠቃላይ የሰው ልጅ በምድር ላይ ሲኖር ብቻውን ሠርቶ፤ብቻውን በልጽጎ ይኖር ዘንድ አይቻለውም፡፡ የእለት ተእለት ፍጆታውን ለማሟላት የግድ ሌሎች ሰዎች ያስፈልጉታል፡፡ ገበሬው ያመረተውን ምርት በገንዘብ የሚገዛው ወይም ለኑሮው በሚያስፈልገው ግብአት የሚለውጠው ሌላ ሰው ይፈልጋል፡፡ ነጋዴው ነግዶ በሚያገኘው ገንዘብ ለኑሮው የሚያስፈልጉ ግብአቶችን የሚያሟላለት ሌላ ሰው ይፈልጋል፡፡ የግልና የመንግስት ሠራተኛው፤ ወዝ አደሩ፤ የእለት ጉርስ ለምኖ አዳሪው… ወዘተ ሁሉም ሰው ሌላው የሚፈልገውን ሰጥቶ ለራሱ የሚያስፈልገውን ለመቀበል በዙሪያው ሰው ይፈልጋል፡በአጠቃላይ አንዱ ከሌላው ውጭ ትክክለኛ ሕይወት መምራት እንደማይችል በማመን፤ ማንም ሰው ለራሱ ጥሩ ነገር እንደሚያስፈልገው ሁሉ ሌላውም ጥሩ ነገር እንደሚፈልግ በማመን፤ሌላውን ጥሎ፤ ለበሽታ ዳርጎ፤ እርካታና ሰላም አሳጥቶ፣ በሌሎች ጉዳትና ችግር ላይ ተረማምዶ ብቻ መበልጸግ የትም እንደማያደርስ መገንዘብ ጠቃሚ ነው፡፡
ሌሎች ምን ያስፈልጋቸዋል? ምንና እንዴት? በምን ያህል ጥራት ቢመረት ገንዘባቸው ጤናቸው፤ እርካታቸውና ምቾታቸው ሊጠበቅ ይችላል? ብሎ በማሰብ በመደጋገፍና አንዱ የሌላውን ምቾት በመጠበቅ፣ አብሮ ለማደግ ቁርጥ ሃሳብ ይዞ መነሳት ብልህነት ነው፡፡