፨ ጉብታ ላይ ከተንሰራፋው የምኒልክ ቤተ-መንግሥት ግርጌ ከተኮለኮሉት ጎስቋላ ሠፈሮች አንዷ የኾነችው ባሻ ወልዴ ችሎት፣ ደራሲውን ዓለማየሁ ገላጋይን አፈራች፤ አራት ኪሎ። አራት ኪሎ ለዓለማየሁ አድባሩ ናት። ልጅነቱ፣ እድገቱ፣ ስሪቱ፣ ሀሳቡ፣ ትዝታው፣. . . ናት። ፈረንሳዊው የታሪክ ምሁር F.p Guizot እንደሚለው፤‹‹Man With All His Thoughts And Feelings Is The Product Of Environment.›› በርግጥም ዓለማየሁ እንደዚህ ነው። ‹‹የሰው ልጅ ከሚያድግበት አካባቢ ወግና ልማድ የተለየ፤ ከየት አባቱ የራሱ የኾነ ባህል ይፈጥራል? ከየትም።›› (አጥቢያ፣107) የሚለው የሰው ልጅ ሥሪቱ የተወለደበት አካባቢ መኾኑን እያስገነዘበ ነው። ሰው፤ ታለ የትውልድ መንደሩ ምንም ነው። ተቀምጦም ኾነ ተኝቶ የሚያልመው አራት ኪሎን ነው። ጽሑፎቹን ያነበበ ይህን ይረዳል። በመጽሐፎቹ በአንድም ኾነ በተዘዋዋሪ አራት ኪሎ ትነሳለች። የአራት ኪሎ ሠዎች ይጠራሉ። በ ‹አጥቢያ› ሙልጌታ የተባለው ገጸ-ባሕሪ፣ ‹አዲስ ዘመን› ጋዜጣ ላይ እንደጻፈው፦ ‹‹እንደሚታወቀው አራት ኪሎዎች ከአራት ኪሎ የአኗኗር ይትበሃል ተነቅለን ሌላ ቦታ ብንተከል የሚፀድቅ ባሕርይ የለንም ብለን እናምናለን። እንደውም ዕጣ - ፈንታችን ጠውልጎ መጥፋት እንደኾነ ተቀብለነዋል።››(26) ይላል። [ለኔ ‹አጥቢያ› ደብዳቤዎቹ ላይ ያለው ሙልጌታ፣ ዓለማየሁ ነው።] ለዛም ነው በአካል ጥቂት ርቋት በሀሳቡና በጽሑፎቹ ያልተለያት። ለዛም ነው ‹‹መንደሬ በውስጤ የደረጀ መሠረት በመጣሏ እርሷ በተናጋች መጠን ሰብዕናዬ ይሰነጣጠቃል።›› (አጥቢያ፣46) የሚለው። ‹‹የመኖሪያ አካባቢውን ከንጥቂያ ለመከላከል የማይዋጋ እንስሳ ኾነ ነፍሳት የለም።›› (አጥቢያ፣61) እያለ በራሱ መንገድ በጽሑፎቹ የመጣው።
፨ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርቱን እዚያው አራት ኪሎ ዳግማዊ ምኒልክ፤ እዚያው አራት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ‹ስኩል ኦፍ ጆርናሊዝም› ጋዜጠኝነት ተምሮ ተመረቀ። ወደ ሥራም የገባው እዚያው አራት ኪሎ ‹ፋና አሳታሚ› ነው። ሠላሳ ዓመት ኾኖት ለጋዜጠኝነት ሥራ ድሬደዋ ሲሄድ ነው - ከአዲስ አበባም ኾነ ከአራት ኪሎ የተለየው። ከአራት ኪሎ ትንሽ ከፍና ዝቅ ብሎ፣ ካዛንቺስና ፒያሳ እያለ ሳይለያት ነው የኖረው - 40 ዓመት ሞልቶት ጠቅልሎ ወጥቶ ካዛንቺስ እስኪገባ ድረስ። ለዚያም ነው በተቀመጠበት ሰፈሩ ያልፈረሰ እየመሰለው ውል የሚልበት። የ‹አጥቢያ›ው ሙልጌታ ለእርጥባን እንደሚላት ‹‹በትውልድ መንደር መለከፍ፣ አራት ኪሎ ውል ይልሻል። ስትነጠይ አንዳች የቀረብሽ ነገር ያለ ይመስልሻል። አብሮ አደጎችሽ በፌሽታ ላይ ኾነው ሲሳሳቁ፣ ወጉ ሲደምቅ ይታይሻል። ስትመጪ ያ - የተለመደ አዚም ነው። የማያቋርጥ አዚም። ግን ከዚህ ስትነጠይ አካባቢሽ በፌሽታ ሁካታ ውስጥ ኾና አንዳች የማይደገም ነገር ሲያመልጥሽ ይታይሻል።›› (39) ይላል። ይህም ራሱ በአንድ መጽሐፉ ውይይት ላይ እንደተናገረው ነው። ካዛንቺስ ኾኖ ሠፈሩ ያልፈረሰ ኾኖ ሲሰማው፣ ጓደኞቹ ውል ሲሉበት ተነስቶ ወደ አራት ኪሎ ሲጓዝ፤ የፈራረሰውን የልጅነቱን መንደር አይቶ አዝኖ ሲመለስ. . . የዓለማየሁ አጥቢያ። ‹‹መንደሬ ለኔ መኖሪያዬ ብቻ አይደለችም። የቤቴ መገኛ፣ ጣሪያና ግድግዳ ያቆምኩባት ብቻም አይደለችም።›› (አጥቢያ፣ 45)
፨ ቤት ፈረሳን፣ ሠፈር እደሳን፣ ሀገር ልማትን አይቃወምም፣ ዓለማየሁ። እሱን ሁልጊዜም የሚያብከነክነው ቤትም ኾነ ሠፈር ሲታደስ ስለሚጎዱት ሠዎች ነው። የሱ ምሬት ሰው ነው። ‹ልማትን አልጠላም፤ ግን ልማቱ ሰውን ያማከለ ይሁን› ነው የሚለው። እንዴት ነው የሚኾነው? ብሎ ለጠየቀም፣ የ‹አጥቢያ›ው ሙልጌታ ‹አዲስ ዘመን› ላይ እንደጻፈው፤ ‹‹አራት ኪሎን እና አራት ኪሎዎችን ከማፍረስ እለፉን አልልም። ከዚህስ “እንጃ!” ማለትን እመርጣለሁ።››(28) ይላል። አሁንም ‹እንዴት እንጃ?› ከተባለ እንዲህ ይለናል፤ ‹‹እኛ አራት ኪሎን የተጣባን ነዋሪዎች፣የአኗኗር ይትበሃላችን በአካባቢው ተጽዕኖ ሥር ወድቋልና በመኖሪያ ለውጥ ከሚፀድቀው “ተክል” ይልቅ የሚጠፋው ያመዝናል።››(27) እንዲህም ይላል፦ ‹‹ለመኾኑ ወደ ልማት እየተጓዝን ነው ወይንስ ወደ ውድቀት? ሰውን ያላማከለ ሥልጣኔ መዳረሻው ምንድን ነው? ኑሮ ላይ ያልታየ እድገት መለኪያው ምን ሊኾን ነው? አለ ያልነው አድሮ እየሻሸረ? የጨበጥነው ሕይወት ላይ ዋስትና ካጣን የራዕያችን መቆናጠጫ የት ላይ ነው?....ኤጭ!›› (ኢህአዴግን እከስሳለሁ፣ 57-58) በነባር መንደሮች ውስጥ የሚኖሩ ማኅበረሰቦች ከውልደታቸው ጀምሮ ሕይወትን የሚያውቋት በብሎኬቶች ሳይኾን በሠዎች ተከበው ነው። ኢኮኖሚያቸውን የመሠረቱትም ከነኚው ከሚያገኟቸው ሠዎች ላይ ነው።
ሕይወታቸው፣ እሳቤያቸው፣ ህልማቸው ከነዚሁ ሠዎች ጋር የተቆራኘ ነው። ከዚህ ለቀው ወጥተው ወደሌላ ቦታ ቢሄዱ ሕይወታቸው ቀጣይነቱ ዝቅተኛ ይኾናል። ይህ በዕውን ታይቷል። ከሠፈራቸው ተነቅለው በተለያየ ቦታ መኖር በጀመሩ ወር ሳይሞላቸው በርካቶች ሞተዋል። ‹‹የትኛውም ጥሩ አካባቢ፣ የትኛውም የተሻለ ሁኔታ ለኛ ሕይወት ፀር ነው።››(27) ማለቱም ለዚህ ነው። ‹‹ሰው ሁሉ ለአገሩ የሚሞተው መንደሩን እያለመ ነው። የነባር መንደር መፈራረስ የሚሞቱለት አገር ማጣት ነው፣ የሚያመልኩት አምላክ መነጠቅ ነው።›› (46) ብሎ የሚመረረው ያየውን ስላየ ነው። አራት ኪሎ እርሱ ስለኖረባት፣ ጓዳ ጓድጓዳዋን በደንብ ስላየላት ተደጋጋሚ ‹አራት ኪሎ› ተባለ እንጂ ተምሳሌትነቷ፣ ለሁሉም ነባር መንደር ነው። በልማት ሥም ከነበሩበት ወጥተው የሄዱ ሰዎች ጎዳና ተዳዳሪ፣ ብዙ ሳይቆዩ ሟች፣ አዕምሯቸውን የሳቱ፣ ሴተኛ አዳሪ ኾነዋል። ‹‹ይህ እንጂ ሌላ ሠፈር የለንም!›› በማለት የፈረሰው ሠፈራቸው ላይ ውሎና አዳራቸውን አድርገው የኖሩ በርካቶች ናቸው። ‹‹መንደርተኞቹ ሲያድሙ እና ሲተባበሩ እንደ አንድ ሰው ኾነው ነው።›› (አጥቢያ፣82) እናም ከዚህ ተለይተው ሲወጡ ተጎጂዎች ይኾናሉ። ከ‹ተደጋግፎ ኑሮ› ተፈናቅለው ኮንደሚኒየም የተሰጣቸው ማኅበረሰቦች እየሞቱ ነው። እነሱ እዚያ ‘ያረጀ’ መንደር ውስጥ ሲኖሩ ያስፈልጋቸው የነበረው ምግብ እንጂ የብሎኬት ድርድር አልነበረም። ‹ኢህአዴግን እከስሳለሁ› ገጽ 115 ላይ ከቤታቸው ተፈናቅለው ኮንደሚኒየም ተሰጥቷቸው የሞቱትን ይነግረናል፤ ‹‹በዚህ አንድ ዓመት ብቻ አንድ መቶ ባተሌዎች በግፍ አልቀዋል።››
፨ ‹‹የመንደራችን ነዋሪዎች ይህቺን መንደር ሙጥኝ የሚሉበት ከቁጥር ባሻገር እንደ ነፍስ ያለ ምክንያት አላቸው። እንዴት እንደሚገለጽ አላውቅም።...›› (44) የሚለው እርሱም ሠፈሩን እየተዘተ ሲቆዝም ነው። ያሳደጉት፣ እናቶቹ፣ አባቶቹ፣ ጓደኞቹ፣ ጎረቤቶቹ እንደ ድኀ አጥር በከተማዋ በተለያዩ ቦታዎች መተከላቸውን አይቶ ነው - ሥርዓቱን መክሠሡ። ስለ ቀጣይ ሁኔታቸው፣ ስለ ሌሎች መንደሮች በማሠብ ነው የሚብሰለሰለው። ስለ ሠዎች፣ ስለ ድሆች መጨነቁ ነው፤ ‹የድኀ ሀገሩ የት ነው? ተቆርቋሪውስ ማነው?› ብሎ መጠየቁ። ‹ልማት ሰውን በማፍረስ አይደለም› የሚለው። ማርክስ እንኳ እንደሚለው፤ ‹‹የሰው ልጅ ውድ ሀብትና ታላቅ ፀጋ እራሱ ሰው ነው።›› ቁሳዊነት ያመጣብን አጥፊ ነቀርሳ፣ ሰውን ንቀን ከሃይማኖት እሴት ጋር እንድንቃቃር እያደረገን ነው። ‹‹ስለ ሰዎች ዋይታ የግሬደሮች ጩኸት ምላሽ ይቀርባል፣ ስለ ቤተሰብ መፍረስ የመንገዶች መገንባት እንደ ምክንያት ይሰጣል፣ ስለ ሰው ልጅ ሆድ ባዶ መኾን የምድር በህንፃ መጥገብ እንደ ማካካሻ ይሆናል..›› እያለ በ‹ኢህአዴግን እከስሳለሁ›(167) ይመረራል።
፨ አውሮጳውያኖች ‹አሳቢዎቼ› በሚሏቸው ግለሰቦች የሃይማኖትን መልክ ሽረው ሥልጣኔያቸውን በቁስ ላይ ብቻ መስርተው ይኖራሉ። ከሰው ልጅ ነፍስ ይልቅ የአንድ ብረት መዛግ የሚያሳስባቸው ናቸው። ይህን እሳቤያቸውን በዓለም ላይ ዘርተው ሁሉም ጋር እንዲበቅል ሻቱ፤ ተሳካላቸውም። የሥልጣኔን ምንነት ቁስ አደረጉት፤ በርሱም አሳመኑን። በሞራል ላይ የተመሠረተውን የበፊት ልከኛ ሥልጣኔዎችን ‘ኋላቀር ናቸው’ እንድንል አስቻሉን። ከአንደኛው ዓለም ጦርነት ወዲህ ዓለምን በቁስ አምላኪነት አጠመቁ። እንደኛ ያለ፤ መተዛዘን፣ ከራስ ሌላን ማስቀደም፣ የሁሉም ሃይማኖት መሪ ቃል የኾነውን ‹‹በራስህ ላይ እንዲደረግ የማትፈልገውን በሌላው ላይ አታድርግ›› የሚለውን ተግብረን በምንኖር ሃገር ላይ ይህን የአውርጳ ብክለት ማስረጽ የለብንም። ‹‹እንደ አንደኛው ዓለም ጦርነት ሰው በገፍ ሰውቶ ድል ለማስመዝገብ መፎከር የልማቱ መርህ ሊኾን አይገባውም።›› (ኢህአዴግን እከስሳለሁ፣ 168) የሚለው ለዚህ ነው። እዝነት ጠፍቷል! ሞራል የለም! ‹ቁስ! ቁስ! ቁስ!› የዓለማችን መሪ ቃል ኾኗል፤ ይህ ሀገራችንን ያጠፋብናል። በቁሳዊነት ዘመን ያልጨመረና ያልተወደደ ነገር የለም፤ ከሰው ነፍስ ውጪ። የሰው ነፍስ ጊዜ በሄደ ቁጥር የሚረክስ ነው። ለአንድ ብረት ብለህ ቤተሰብህን ትሸጣለህ።
፨ ‹‹መንደሩ ሰው፣ ሰዉ መንደር ኾኖ ተደበላልቋል። አንዱ ሲነካ ሌላው ይናጋል። አሮጌ ቤት ላይ የምንወጣው ሰው ለማፍረስ ነው። የምንመዘው የሕይወት ጎድን እንጂ የአሮጌ ቤት ግድግዳ አይደለም። የምንንደው ሥጋ እንጂ ጭቃ አይደለም። እዚህ ነባር መንደር ላይ ሳያገናዝቡ ድጅኖ ማንሣት ጥፋት እንጂ ልማት አይኾንም። ከዚያስ? ተብሎ የማይጠየቅበት፣ ፍጥነት ያለው የደኀ ቀብር ላይ እንጂ ሕይወት ላይ አይደለም።›› (ኢህአዴግን እከስሳለሁ፣ 23) መንደር ሲነካ ሰው ነው የሚደማው። እናትህ የምትኾነው የወለደችህ ብቻ አይደለችም፤ የመንደሩ ነዋሪ ጠቅላላ፣ መንደሩም ጭምር ነው፤ አባትህም እንደዚያው። ቤትህ፣ ሠፈርህ ፈርሶ የተለያየ ቦታ ስትኖር፣ እናት አባትህን ትተህ ነው፣ ከወንድም ከእህትህ ተለይተህ ብሎኬት ድርድር ቤት ታቅፈህ ነው። ይህን ሕብረትና ፍቅር ስታጣ ነው ሰውኛ ባሕሪህ ጠፍቶ አመፀኛ የምትኾነው። ‹‹ያለ ምንም ጥናት ሰው በመጠለያ ብቻ ብቻ ይኖር ይመስል የብሎኬት ድርድር ውስጥ ወሸቁት።›› (ኢህአዴግን እከስሳለሁ፣92) ማለቱም ከመጠለያ በላይ የኾነ ስሜት በሰዎች ልብ ውስጥ መኖሩን እየነገረ ነው።
፨ ‹አጥቢያ› ላይ ዓለማየሁ በእርጥባን በኩል ትላልቅ አጥር ቤቶችን ይተቻል። ‹‹ግቢያችን አጥሩ ረዥም ከመኾኑ የተነሳ ፀሐይ እንኳን እንደልቧ አትገባበትም።›› (21) እያለ. . . ‹‹ይሄ መንደር ምቾት አይሰጠኝም። ጭር ያለና በብዙ መኖሪያ ቤቶች ቅርጫ የገባ ነው። ጭር - ጭር...›› (22) እያለ. . . ያለ ሰው፣ የዓለ ቤት ለዓለማየሁ ምቾት አይሠጠውም። ለዓለማየሁ ብቻ ሳይኾን ነባር መንደር ተወልደው ያደጉ፣ የኖሩ በሙሉ። ከቤቱ በሩን ከፍቶ ሲወጣ የተደረደረ ፎቅ፣ የሚያንጸባርቅ መኪና ሳይኾን ሰው ነው የሚፈልገው። ‹‹ደህና አደርክ፣ ደህና እደር›› ብቻ የሚለውን ሳይኾን፤ የልቡን የሚያዋየው፣ ያስከፋውን ያስደሰተውን የሚነግረው ሰው ነው የሚፈልገው። ያደገው፣ የኖረው እንደዚህ ነው። ከዚህ ሌላ ይህን ኅብር የሚያስተው ሲመጣ ዓለማየሁ ይከፋል። ሃዘን፣ ምሬቱን በጽሑፎቹ ይገልጣል። ‹‹ባንቺ ጉዳይ እየገባ በመፈትፈት የሚያበሳጭሽ ጎረቤትሽ ሁሉ ለካ ፍሰሃ ነው። ወደፊት ሕመም አይደለም፣ አለመታየት ነው የሚገድለን። ሁሉም ሀብት ለመሰብሰብ ይንጦዘጦዛል። ታዲያ ማን - ማንን ልብ ይላል? ሀሜተኛ አታሳጣኝ፣ አሽሟጣጭ አትንሳኝ፣ የዕለት አሽሙረኞችን ስጠን ማለት ደግ ነው።›› (35) እያለ ‹አጥቢያ› ላይ ሙልጌታን የሚያስወራው የምሩን ነው።
፨ ሀገር ማለት ሕዝብ፤ ሕዝብ ማለት ሐገር ነው። ሰው ከሌለ ‘ሀገር’ ባዶ መሬት ነው። የፎቅ ድርድር ሳይኾን ያልተራበ ሕዝብ ሳቅ ሀገርን ያስቀጥላል።
‹‹አሮጌ ከተማ ሥር የምትሰደው በደሳሳ ጎጆዎቿ አይደለም። በነዋሪዎቿ ሕይወት ነው። አቧራ የቃሙ የእግር መንገዶቿ ለነዋሪዎቿ የደም ሥሮች ናቸው። የጉልት ካቦቿ መተንፈሻ ሳንባ፣ መሸታ ቤቶቿ የልብ ምቶቿ ናቸው። እነዚህን ድንገት ተነስቶ በዶሮ ስልት መጫር ኃላፊነትን ከግምት የከተተ ተግባር አይደለም። የግዴለሽነትና የምን ታመጣላችሁ መታበይ እንጂ። በእርግጥም ደግሞ ምንም አላመጣንም፣ ምንም አናመጣምም።›› (ኢህአዴግን እከስሳለሁ፣ 20) መንደር እና ነዋሪ፤ ነዋሪ እና መንደር በአካልም በስሜትም የተጣበቁ ናቸው። አውሮጳን አምጥተን ኢትዮጵያ ከተከልን ኢትዮጵያ የታለች? ባህል እሴታችንን በገዛ ፈቃዳችን ለቅቀን አውሮጳዊ እየኾንን ነው። ኢትዮጵያ የደኀውም የሃብታሙም ነች። ራሷን የቻለች፣ የራሷን ‹ሥልጣኔ› መፍጠር የምትችል ነች። አውሮጳን አምጥተን ሳይኾን ዜጎቿን በማነቃቃት ነው ታላቅ የምንኾነው። በጦርነት ቅኝ ባንገዛሞ በአስተሳሰብ ግን በፈቃዳችን ሄደን እጅ ሰጥተናል። ያላትን ባህል በተሻለና ‹ኢትዮጵያዊ› በኾነ መንገድ ማዘመን እንጂ የሌላው ተገዢ መኾን መሸነፍ ነው። ‹‹ግብፅ “አሮጌዋን ካይሮ” እንዳለ ትታ “አዲሷን ካይሮ” ጥቂት ፎቀቅ ብላ ገንብታለች። ምክንያቱ ደግሞ የአሮጌዋን ከተማ አቧራማ መንገድ ደም ሥራቸው፣ ጉልቶቿን ሳንባቸው፣ ሺሻ ቤቶቿን ልባቸው. . . ያደረጉ ነዋሪዎች መኖራቸው በመታወቁ ነው። ናይጄሪያም እንደዛው አሮጌዋን ሌጎስ ለነዋሪዎቿ ትታ አቡጃን አቋቁማለች።›› (ኢህአዴግን እከስሳለሁ፣ 21)
፨ ሀገራዊ እና ሃይማኖታዊ እሴቶቻችን ቀስ በቀስ እየተሸረሸሩና እየተሻሩ ማቴሪያሊስት (ቁሳዊ) የኾነ ትውልድ እያፈራን ነው። የሀገር ‹ጀግኖቻችንን› ንቆ አንድ ፈረንጅ አምላኪ ማኅበረሰብ ላይ ደረስን። ምሳሌ ደራሲዎቻችን ጀግኖቻችን ናቸው። በሌላው ዓለም ደራሲ ሀገርን የሚለውጥ አብዮት ያስነሳል፤ አክባሪና አንባቢ ማኅበረሰብ ስላሉ። እኛ ሀገር ግን የተናቀና የወረደ ኑሮ የሚኖር አድርገናል። የሚገባቸውን ክብር አንሰጣቸውም። ዓለማየሁን ማንሳት እንችላለን። በ1806 በፈረንጆቹ ናፖሊዮን አውሮጳን እያጠፋና እያወደመ፤ ጀርመን ብሮንስዊክ ሲደርስ ‹‹አታጥፏት›› አለ። ለምን ሲባል ‹‹ከተማዋ ባለውለታችን ናት። ፈላስፋውና የሒሳብ ሊቁ ፍሬድሪክ ጉስ እዚህ ነበር የተማረው፤ ስለዚህ አትፈርስም።›› አለ። በሌሎች ሀገሮች ላይ ያሉ ታላላቅ ደራሲያን ቤት እንደነበር ተቀምጦ አሁን ለጉብኝት ክፍት ኾኗል። ኒቼን፣ ዶስትዬቭስኪን መጥቀስ እንችላለን። የኛ ደራሲ ዓለማየሁ ገላጋይ ግን ድርሰት ማሳተሙን ‹ሀ› ሲል የጀመረው የተወለደበትን ቤትና ሠፈር ለቅቆ አዲስ ቦታ ላይ ነው። አዲሱ ቤቱ፤ ለወጣቱ፣ ለትልቁ፣ ለደራሲው፣ ለጋዜጠኛው፣ ለአንጋፋው፣ ለጀማሪው በእኩል እንደ አብረሃም ቤት ክፍት ነበረች፡፡ በእንግሊዝ ሼክስፒር ይቀመጥበት የነበረው ወንበር አሁንም እንዳለ በዕውቀቱ ሥዩም አስነብቦናል፡፡ .............

