አሁን አይደል ትዝ የሚለኝ፣ ለካ የባለፈው ማስታወሻዬ ላይ ስሜን አልነገርኳችሁም፡፡ ቦርሳንዴዝ ይባላል ስሜ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የተንሰራፋው የማንነት ንጭንጭ ሰልችቶኛል፡፡ የትኛው ጠቅላይ ሚኒስትራችን ነበሩ ለቅሶ እየተናነቃቸው፣“ጦርነት በቅቶናል መሮናል ሰልችቶናል” ያሉት? እንደዚያ ብለው ግን እሳቸውም በጦርነት ውስጥ ነው የኖሩት፡፡ ጦርነትን የሚያስቀር መሪ የምናገኝበት ቀን ግን አይናፍቃችሁም? ወደ ስሜ ጉዳይ ስመለስ ሆን ብዬ ነው፣ ስሜን ከየትኛውም ኢትዮጵያ ውስጥ ካለ ብሔርና ሃይማኖት ጋር እንዳይገጥም ቦርሳንዴዝ ያልኩት፡፡ የሚገጥም ነገር ካገኛችሁ አጋጣሚ ስለሆነ እለፉት፡፡
ስሜን የባለፈው ማስታወሻዬ ላይ ተናግሬ ቢሆን ኖሮ፣ ዛሬ ከላይ የማስቀምጠው ርዕሴ ጥልቅ ብስጭት የሚል ነበር፡፡ ርዕሱ በስሜ ቢወሰድም ግድየለም የብስጭቴን ጥልቀት አይቀንሰውም፡፡ በሜትር የምንለካው ባይሆንም ብስጭት በልቦናችን ውስጥ እንደሚሰራው ጉድጓድ ጥልቀቱ ይለያያል፡፡ 2009 ዓ.ም. ላይ ይመስለኛል፣ ሀገራችን በህዝባዊ አመፅ በምትናጥበት ጊዜ፣ የወቅቱ ገዢ ፓርቲ ኢህአዴግ ጥልቅ ተሃድሶ አድርጌያለሁ ብሎ በቴሌቪዥን ብቅ አለ፡፡ ተሃድሶ የተባለው ነገር ሲታይ ታዲያ ከበፊቱ ያልተሻለና አንዳንዱ እንዲያውም ከበፊቱ የባሰ ሆኖ ተገኘ፡፡ ይሄን ያስተዋለው አንድ የስራ ባልደረባዬ፤ ይሄማ ምን ጥልቅ ተሃድሶ ሆነ ጥልቅ ብስጭት እንጂ ብሎ ተረተ፡፡ ጎበዝ፤ ስሜታችንን ዋጥ ካላደረግነው የሚያናድደው ነገር መብዛቱ፡፡ ለምሳሌ ኢንተርኔቱ እንዲሁ እየማሰነ የምትፈልጉትን ነገር አልከፍት ሲል አያናድዳችሁም? ትግስት አታጡም? ኢንተርኔቱ ሲሄድልህ ደግሞ መብራት ይጠፋል፡፡ የቢሮ ዴስክቶፕ ላይ ባንድ ጣትህ ፊደሎችን እያነጣጠርህ የምትመታ አባሮ ገዳይ ፀሀፊ ከሆንክ፣ ሴቭ ማድረግ ትረሳና መብራት ሲጠፋ የሰራኸው ሁሉ አብሮ ይደመሰሳል፡፡ የሰራህ ሲመስልህ እንደገና ወደ ነበርህበት ስትመለስ ቀኑ ይመሻል፡፡ ብስጭትህን ተናግረህ የምታበርድበት ለችግሩ ሃላፊነት የሚወስድ ሰው አጠገብህ አታገኝም (ያው የፈረደበትን ጠረጴዛ በቡጢ ትነርተዋለህ)፡፡ የምትገናኘው ከችግሩ ጋር እንጂ ከችግሩ ፈጣሪ ጋር አይደለም፡፡ ብስጭትህን ትውጣለህ፤ ብስጭትህ ሽበትና ማዲያት ሆኖ በገፅህ ላይ ብቅ ይላል፡፡
አሁን ብናረጅ በእድሜያችን ነው? ህልማችንን ሳናሳካ ብንሞት በእኛ ብቻ ስንፈት አይደለም፣ በእነዚህ ሁሉ እንቅፋቶች ተደናቅፈን ነው፡፡ ይሄንንም መጪው ትውልድ እባካችሁ ተረዱልን፡፡ ይህቺ ሀገር መራኛለች፤ በቅታኛለች፤ ሰልችታኛለች፤ ሃሃሃ--፡፡ ግን ሌላ የምሄድበት ሀገር የለኝም፡፡ እንግዲህ ምን አደርጋለሁ በአየሯና በመልክአምድሯ እየተፅናናሁ መኖር ነው እንጂ፡፡
አንዳንድ ጊዜ በቀሽም ነገሮች መደራረብ የተነሳ ጥልቅ ብስጭት ውስጥ እገባና እኔ ራሴ ሌሎችን ያለ አበሳቸው የሚያበሳጭ ነገር ወደ ማድረግ ወይም ወደ መናገር ገብቼ ቁጭ እላለሁ፡፡ የብስጭታችን ምንጮች ብዙ ናቸው፡፡ ሥርአት ወለድ ብስጭት አለ (ኢህአዴግን የመሰሉ ድርጅቶችና የእነሱ አልጋ ወራሾች የሚጭኑብን ብስጭት)፣ ኑሮ ወለድ ብስጭት አለ፣ ግለሰብ ወለድ ብስጭት አለ….፡፡ ሁለቱ በአብዛኛው ከቁጥጥራችን ውጭ ናቸው፡፡ ግብዝ፣ ብልጥ ወይም ደደብ ሰዎች የሚያመጡብንን ብስጭት ማስወገድ የምንችል ቢሆንም በተጨባጭ ግን ቀላል አይደለም፡፡ እኔ ግለሰቦች ሲያበሳጩኝ ብስጭቴን የበለጠ ጥልቅ የሚያደርገው ያበሳጩኝን ሰዎች ልክ ልካቸውን መንገር ሳልችል ስቀር ነው፡፡ ትንታግ የሆኑ ቃላትን አዘጋጅቼ እሄድና ያበሳጨኝን ሰው ሳገኘው ግን ስሜቴ ብቻዬን ሆኜ እንደሚሰማኝ የሞቀ አይሆንልኝም፡፡ ለምሳሌ ቴሌቪዥን እያየን ከሆነ ቴሌቪዥኑ ውስጥ ካለው ትዕይንት አንፃር እኔ ብስጭቴን ብናገር ነገር ማቆርፈድ ወይ ኋላ ቀርነት ሆኖ ይታሰበኛል– ሰላማዊና ተዝናኖታዊ ሁኔታ መሀል ነገር አምጥቶ የመደንቀር አይነት፡፡
ግን ዝም ስትል ሰዎች የሰሩትን ጥፋት የማትረዳ ወይም የማታውቅ ይመስላቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ዝምታህ ለግብዝነታቸው አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡ እነሱም በቅጥፈት ላይ ቅጥፈት እየጨመሩ ይሄዳሉ፡፡ ትክክል እንደሆኑ አድርገው እያስመሰሉ ያለፉትን ሁሉ ነገር የተቀበልካቸው ይመስላቸዋል፡፡ ብልጦች የሚንሰራፉት በይሉኝተኞች ትዕግስት ብዛት ነው፡፡ በህብረተሰባችን ተናጋሪ ላልሆነ ሰው የሚሰጠው ምደባ ምስኪን ወይም የዋህ ነው፡፡ በየዋሆች ውስጥ በደግነት የተከለለ ሞኝነት አለ፡፡ ብልጦች ይሄን ያውቃሉ፣ እናም ይጠቀሙበታል፡፡ ብልጦች ስለ የዋህነትህ አብዝተው ሲነግሩህ፣ በልባቸው አይ ጅሉ እያሉህ ሊሆን ይችላል፡፡ የሆነ ጊዜ ስለ ማንነታቸው አፍረጥርጠህ ልትነግራቸው ልትወስን ትችላለህ፡፡ ብልጦች ግን የወኔ ማርከሻ አላቸው፡፡ ሌላ ርዕስ እያመጡ እየተለማመጡ እያሳሳቁ ወኔህን ያፈርሱታል፡፡ ይሉኝታ ይይዝህና ያሰብከውን ሳትናገር ትተወዋለህ፡፡ ግን ተናግረህ ስላልወጣልህ ቆይቶ ብልጦች በሆነ ነገር ሲሸነግሉህ አልያም መጠቀሚያ ሲያደርጉህ ስታይ ጥልቅ ብስጭት ውስጥ ትገባለህ……፡፡ የሆነው ሆኖ ብልጦች ራሳችሁን ብታርሙ ጥሩ ነው፣ የየዋሆች ጥልቅ ብስጭት ብሎ ብሎ ሲፈነዳና ወደ ጥልቅ ማዕበል ሲቀየር ያን ጊዜ አትተርፉም፡፡ ልክ ኢህአዴግ በጥልቅ የህዝብ ብስጭት እንደተጠረገው፡፡