Sunday, 27 October 2024 00:00

ቻርልስ ቡካውስኪ - የእብደት እርካታ

Written by  በኪሩቤል ሳሙኤል
Rate this item
(1 Vote)

ምድር አምጣ ያመጣቻቸው ደራሲዎች አብዛኞቹ ቀውሶች ናቸው፡፡ ዥው የሚልባቸው፡፡ ማህበረሰቡ የሚወዳቸው፣ የሚንቃቸውና መደበሪያው የሚያደርጋቸው፡፡ አብዛኞቹ ደራሲዎች ግን ማህበረሰቡን አይወዱትም ….አብዛኞቹ፡፡ አጠገባቸው ባይደርስ ደስታቸው ነው፡፡ ደቦነት ደራሲ ነፍስ ውስጥ ቦታ የለውም፡፡ ደራሲ ብቻውን መሆን ነው የሚፈልገው፡፡ ብቻውን፤ ከሀሳቦቹና ከእብደቶቹ ጋር፤ የፈለገውን አይነት ህይወት እየኖረ፡፡ እዛ ብቸኝነት ውስጥ የሚፈጠሩ ብዙ አይነት ውዥብርታዎች ሊኖሩ ይችላሉ…በጊዜ ሂደት ውስጥ መፍትሄ የሚያገኙ፡፡ ሆኖም አንዳንድ ደራሲዎች ደግሞ አሉ፡፡ ትንሽ ብቻ ሳይሆን ደርዙ የማይታወቅ አወጣጥን የሚወጡ፡፡ ከነዚህ አስደማሚ ደራሲዎች መካከል ስለ አንዱ ደራሲ ከናንተ ጋር ልወያይበት አሰብኩ…ስለ ቻርልስ ቡካውስኪ፡፡


ቡካውስኪ የከበበውን ማህበረሰብ ህግጋቶች በሙላ መጣስ የሚፈልግ ደራሲ ነው፡፡ የአመፃ ልጅ ነው፡፡ ለአንዳንዶችም የነፃነት ከፍታን ሊፈበርክ የመጣ እንግዳ ነፍስ ነው፡፡ እኔ እና ሌሎች ከሚናገሩት በላይ እሱ ራሱ፣ ስለ ራሱ የሚናገረውን ብንመለከት እንዲህ ይለናል…
“ልክ ማንኛውም ሰው ሊነግራችሁ እንደሚችለው እኔ ጥሩ ሰው አይደለሁም፡፡ በቃላት ለመግለፅ ይከብደኛል፡፡ ከሌላው በላቀ ዱርዬውን፣ አሸባሪውንና አረመኔውን ነው አብልጬ የማከብረው፡፡ ሱፉን ለብሶና ፂሙን ተላጭቶ ወደ ስራው የሚሄደውን ልጅ ሳየው አይመቸኝም፡፡ ቀዥቃዣ ወንዶች ይመቹኛል… ከእነተሰበረ ጥርሳቸው፣ ከእነተሰበረ ጭንቅላታቸው እና ከተሰባበሩት መንገዶቻቸው ጋር----ሁሉ ነገራቸው ይመቸኛል፡፡ ትኩረቴን ይስቡታል፡፡ ሁሌም ቢሆን በአስደናቂ ገጠመኞችና ፍንዳታዎች የተከበቡ ናቸው፡፡ እብድ ሴት ትመቸኛለች፤ በላያቸው ላይ ስቶኪንጋቸው የሰፋቸው፤ ማስካራቸው በፊታቸው ላይ ተድጦ የጨቀየባቸው ሰካራም ዱርዬ ሴቶች ውስጤ ናቸው፡፡ ከቄሶች ይልቅ ለዘማዊ ትኩረቴን እሰጣለሁ፡፡ ከእብድ ጋር መዝናናት እችላለሁ፤ ምክንያቱም እኔ ራሱ እብድ ነኝና፡፡ መርሆች፣ ስነ ምግባር፣ ሀይማኖትና ህግጋቶች አይመቹኝም፡፡ በማህበረሰብ መሰራት ፍፁም ፍላጎቴ አይደለም፡፡”
ይህን የሚለው ቡካውስኪ፤ በምንም አይነት ህግጋቶች ሳይያዝ፣ በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች እየተዘዋወረ ህይወቱን ጨርሶታል፡፡ ”እኔ ለአለም የማስተላልፈው ምንም አይነት መልዕክት የለኝም፡፡ ምናልባት ለመሪነት የሚሆን ንቃት ላይኖረኝ ይችላል፤ ሆኖም ማንንም ላለመከተል የሚሆን ብልጠት ግን በውስጤ አለ፡፡” ይለናል፤ ከማህበራዊ ጭንቅላት ራሱን ገሸሽ ሊያደርግ ሲሞክር ፡፡


ደራሲው ሰዎችን አይወድም፡፡ ይህ ምናልባት በልጅነቱ በከባድ ጭካኔ ያሳደገው አባቱ ያመጣበት ፍልስፍና እንደሆነ ይገመታል፡፡ ”አባቴ ህመምን ያለ ምክንያት መታመም የሚል ትምህርት አስተምሮኝ ነው የሄደው” የሚለው ቡካውስኪ፤ ሰዎች ተሰብስበው ሲያይ ምርር ነው የሚለው፡… በተለያዩ ታዋቂ ቃለምልልሶቹ ውስጥ ከላይ የገለፅኩትን ሀሳብ ለማጠናከር ይሞክራል…
”ሰዎች በጣም ብዙ ነገር ያደርጋሉ፣ በጣም ብዙ ነገር ያቅዳሉ፡፡ እሱን ትነት ግን ቀኑን ሙሉ ተኝነት የተሸከምነውን ቀን መርሳት ነው የሚገባን፡፡…ለኔ አንድ ሰው ልክ ወደ ቤቴ ሲገባ መጀመሪያ ማሰብ የምጀምረው ነገር፣ ሰውየውን እንዴት አድርጌ ከቤቴ ውስጥ እንደማስወጣው መቀመር ነው፡፡ …ብቻዬን መሆን በጣም ነው የምወደው፤ ውስጡ ምንም አይነት የብቸኝነት መንፈስ የለውም...የምርም ደግሞ ብቸኝነቴን ነው ሁሌ የምናፍቀው፡፡ እጅግ ውብ ነው፡፡ በምድር ላይ ምርጡ ነገር ከሌሎች ሰዎች ርቆ መኖር ነው፡፡ ውስጡ ታላቅ ክብር አለው፡፡ ….በቃ እንግዲህ ምን ልበልህ ሰዎች ሳያቸው ደስ አይሉኝም፡፡ የምወደው ራሴን ብቻ ነው፡፡ …ውስጡ ምንም ህመምም ሆነ ትግል የለውም፤ እጅግ የተዋበና በጣም ቀላል ነገር ነው፡፡ …የሚገርምህ አንድ ሰው በመንገድ ላይ እየሄድኩ ባለሁበት ወቅት ከህዝብ መሀል መጥቶ በትከሻው ቢነካኝ የሆነ ነገር ያደርገኛል፡፡ …የሰው ዘሮች ደስ የሚሉ ፍጥረቶች አይደሉም… እኔም አይመቹኝም፡፡ አለምን ማዳን አልፈልግም፡፡ እንደውም ይህን ካልኩ አይቀር ራሴንም ማዳን አልፈልግም፡፡”


እንግዲህ የዚህ ታላቅ ደራሲ ነፍስ ውስጥ ገብታችሁ ብታደምጡ ፍፁም የሆነ ጥላቻና ፍፀም የሆነ የራስ ፍቅር አብረው ተቃቅፈው ሲወዛወዙ ማየት ትችላላችሁ፡፡ ሆኖም ከዚህ ሁሉ የጥላቻ ትርምስ ውስጥ ግን ቡካውስኪ ለመላው የሰው ዘር ሊበጁ የሚችሉ ፍልስፍናዎችንም ጥሎልን አልፏል፡፡ በ73 ዓመቱ ህይወቱ እስክታልፍ ድረስ ከፃፋቸው ብዛት ያላቸው ስራዎቹ መካከል፡- Post office, Factotum, Women, Ham on rye, Hollywood እና Pulp ተጠቃሽ ናቸው፡፡
እነዚህን መጻሕፍት ያነበበ ሰው የተለያዩ አይነቶች ፍልስፍናዎችን በጭንቅላቱ ውስጥ ማፍላቱ አይቀርም፡፡ እኔ በራሴ ጥናት የደረስኩበትንና ሌሎችም አጥኚዎች የተፈላሰፉበትን ፍልስፍናዎቹን በተቻለኝ ውስን አቅም ዋነኞቹን ለመተንተን ልሞክር፡፡
መጣርህን አቁም
በቡካውስኪ ፍልስፍና ውስጥ ግዘፍ ነስቶ የምናገኘው አንደኛውና የመጀመሪያው ሀሳብ፤ ጥረት የሚባል ነገር መጣርህን አቁም የሚል ነው፡፡ እኛ ያደግነው እንደዚህ አድርጉ፣ እንደዚህ አታድርጉ እየተባልን ነው፡፡ ይህም ያሰብነውን ለማሳካት አቅማችንን በሙላ አሟጠን እንድንጠቀምና እንድንታገል ያደርገናል፡፡ ይህ የኛ ህይወት ብቻ አይደለም፤ የሰው ልጅ ህይወት ነው፡፡ ይህ የአስተሳሰብ ስልት በየሀይማኖቱ ጥራዝ ውስጥም ሳይቀር የምናገኘው ነው፡፡
ሆኖም ይህ ደራሲ ይህን ሁሉ የህይወት መርህ ጣጥለን መጣራችንን እናቁም ነው የሚለን፡፡ በዚህ ምድር ላይ አንድም ነገር በተለይም ሥነፅሁፍን ጨምሮ በጥረት የመጣ ነገር የለም የሚለን ቡካውስኪ፤ መጀመሪያ ለሚሰማው ሰው ከምድር ስርዓት የራቀና ስንፍናን የሚያለምድ የሀሳብ ውጤት እንደሆነ አስቦ ሊሸሸው ይችላል፡፡
ሆኖም እንደ እሱ አመለካከት፤ህይወት የምትወረውርልን ተፈጥሯዊ መክሊት ወይም ስጦታ መቼና እንዴት እኛ ዘንድ ሊደርስ እንደሚችል ስለማናውቀው፣ በጥረት የምንቀይረው ምንም አይነት የተፈጥሮ ስርዓት እንደሌለ ነው የሚነግረን፡፡ ይህም ምንም ጥርጥር በሌለው ሁኔታ በውስጡ ፍለጋ እንዳለበት ግልፅ ነው፡፡ ይህንንም ሲያስረዳ፤ ”የምትወዱትን ነገር ፈልጋችሁ አግኙት፤ ከዚያም እንዲገላችሁ እድል ስጡት” ይላል፡፡


ይህ ፍልስፍና በጥረት ውስጥ የሚመጣውንና የህይወትን ፍልስፍና እንዳሻው የሚያመናሽረውን ውስብስብ የህላዌ ትርምስ፣ ትርጉም ያለውና ቅርፅ የተለጠፈበት ስርዓት እንዲይዝ የማድረግ አቅም አለው፡፡ በጥረታችን ውስጥ የሚመጡትን አላስፈላጊ የተስፋ መቁረጥና ራስን የመጥላት መራር የሀሳብ ዘንጎችንም አባሮ የሚያስወጣ ነው፡፡
ምድር ዝም ብላ እንዳላመጣችን፤ ፈጣሪያችን ዝም ብሎ በዝርው ወደ ምድር እንዳልበተነን የሚያስረዳንን ሀሳብ በውስጡ እናገኝበታለን፡፡ ለሁላችንም የተበጀ የመክሊት አይነት እንዳለና ያንንም መክሊት በመንቀዥቀዥ ሳይሆን፣ አጥልቆ በማሰላሰል የሚደረስበትና ከፍተኛውን እርካታ የምንቀዳጅበትን መንገድ የመስራት አቅም አለው፡፡ ለዛም ይመስለኛል በ35 ዓመቱ እርቃውና ሸሽታው የነበረችው የስነጥበብ ዛር ተመልሳ መጥታ ስትጎበኘውና በጥበባዊ አለም ውስጥ ስታሰክረው ይሄን ያለው…
”ድርሰት ከእብዶች መኖሪያ፣ ከግድያና ራስን ከማጥፋት አድናኛለች፡፡ አሁንም እፈልጋታለሁ፣ ነገም፣ እስከ መጨረሻው እስትንፋሴ ድረስ፡፡”
የነፍሱ ከፍታ ድረስ የረካ ሰው የሚያወጣው የተስፋ ጉልበት፣ እነዚህ ቃላት ድረስ ሊያስኬደው እንደሚችል አስረዳን፡፡ ለዛም ይመስለኛል፣ በመቃብር ድንጋዩ ላይ ”መጣር አቁም” ብሎ በቃላት የከተበው፡፡
በሌላም መልኩ፤ ቡካውስኪ የሚነግረን ነገር ሁሌም ቢሆን፣ እውነቱን ተናገሩ የሚል ነው፡፡ ይህንንም ያለበት ዋናው አላማ፤ ሁሉምን ሰዎች ማስደሰት አንችልም፡፡ ያለችን አንድ እውነት ናት፡፡ እኛ ነን ለራሳችን እውነት፡፡ እሷን መደበቅ አይጠበቅብንም፡፡ ምክንያቱን አጥርታችሁ ከተመለከታችሁት አንዳንድ ሰዎች የምታደርጉትን ነገር ይወዱላችኃል፣ ሌሎቹ ደግሞ ይጠሉታል፤ ሆኖም አብዛኞቹ ሰዎች ስለ እናንተ ጉዳይ ጉዳያቸው አይደለም፡፡ አሁን ሰምተዋችሁ በኃላ ይረሱዋችኃል፡፡ ማንም ምን ትሰሩ፣ ምን ታደርጉ ማወቅ የሚፈልግ ይመስላል እንጂ ትንሽ ቆይታችሁ ስታዩት፣ ከእነመፈጠራችሁም ረስቶዋችሁ እንደሆነ ትረዳላችሁ፡፡


ስለዚህ ባለቻችሁ ትንሽዬ እድሜ የእውነት ኖራችሁ፣ የእውነት እንድትሞቱ ነው ቦካውስኪ የሚመክረው፡፡ ተፈጥሮ የራሱዋ እውነትና ውሸቶችን ይዛ ነው የምትጓዘው፤ እንደዛም ሆኖ የትኞቹ ምን እንደሆኑ ሊነግሩን የሚችሉት አመታቶች ብቻ እንደሆኑ ይህ ሰው ይነግረናል፡፡ ስለዚህ በራስ እውነት ውስጥ መቆየት ለአንድ ደራሲ፣ የተሸከመውን የደም ስር ያህል ጠቃሚው ነው፡፡ አለበለዚያ የሚመጣውን የማንነት ቀውስ ለመቆጣጠር ቀደም ብሎ መዘጋጀቱ አስፈላጊ ነው፡፡
”ድርሰት የሚፅፉ ሰዎች ህይወትን እየፃፉ አይደለም፣ እነዛም ህይወትን የፃፉት ደግሞ ከድርሰት አለም ይገለላሉ” ይላል ደራሲው፡፡ ምንም እንኳን የዚህ ሰው ፍልስፍና ሰፊ ቢሆንም፣ ሦስተኛውንና የዛሬውን የመጨረሻ ፍልስፍና ተርኬ ላብቃ፡፡
ብቸኝነታችሁን አጣጥሙት
ጆን ፖል ሳርተር፤ “Hell is other people.” እንደሚለው የቡካውኪም አመለካከት ከዚያ የሚዘል አይመስልም፡፡ ”ብቸኝነትህ ካስጨነቀህ አጠገብህ ያለውን መፅሐፍ አንሳና ማንበብ ጀምር” የሚለን ደራሲው፤ በብቸኝነት ውስጥ ያለውን ልዕልና ተናግሮ የሚጨርስ አይመስልም፡፡ ሰዎች የመዓት ውስብስብ ሀሳብ ጥርቅሞች እንደሆኑና በአንድ ግለሰብ ህይወት ውስጥ ራስንና ማንነትን ከማሳጠት ያልዘለለ መከራ ይዘውብን እንደሚመጡ ያሳስበናል፡፡
በዚህም ምክንያት በብቸኝነታችን ውስጥ እያለን፣ ማንም በራሱ ካልሆነ በሌላ ሊረዳው የማይችለውን ጥልቅ ሚስጥር፣ ወደ ውስጣችን ተሰደን መልስ እንድናቀብለው ነው፤ የዚህ ሰው ጥበባዊ ሀሳብ የሚመክረን፡፡ ፡
ይህን አካሄዱ በየመፃህፍቱ ውስጥ የራሱን ገጸ ባህሪዎች በተደጋጋሚ እንድናገኛቸው አድርጎናል፡፡ በዘርፉ ላይም ጥናት የሚያደርጉ ባለሙያዎች፣ የቡካውስኪ ድርሰቶች ለግለ-ታሪክ የአፃፃፍ ዘዬ የቀረበ ነው የሚሉ ወገኖች እንዳሉ ይገልጻሉ፡፡
ይህ ሰው ብዙ ነው፡፡
ከዚህ በኋላም ስለዚህ ሰው በቀጣይ መጥቼ ብዙ እንድላችሁ የሚያሻኝም ብዙ ምክንያቶች አሉኝ፡፡ ሆኖም ያለኝ የሃሳብ ነፃነት እዚህ ጋ የሚያበቃ ስለሆነብኝ፣ የመጨረሻዋን ስጦታዬን አስረክቤ ለሌሎች ፍልስፍናዎች ጭንቅላቴን ላፀዳዳ፡፡


The genius of the crowd

There is enough treachery, hatred, violence, absurdity in the average human being to supply any given army on any given day. And the best at murder are those who preach against it and the best at hate are those who preach love. and the best at war finally are those who preach peace. those who preach God need God. Those who preach peace do not have peace. Those who preach peace do not have love. Be aware the preachers…be aware the knowers. They are afraid what they do not know. Be aware for those who quick to praise, for they need praise in return. Be aware those who seek constant crowds for they are nothing alone.
Be aware the average man and average women, be aware their love …there love is average, seeks average. but there is genius in their hatred…there is enough genius In their hatred to kill you. To kill anybody.
Not wanting solitude, not understanding solitude, they will attempt to destroy anything that differs from their own. Not being able to create art, they will not understand art. They will consider their failure as creators only as a failure of the world.
Not being able to love fully, they will believe your love incomplete. And then they will hate you. And their hatred will be perfect. Like shining diamond, like a knife, like a mountain, like a tiger… like Hemlock…their finest art.

Read 210 times