Saturday, 26 October 2024 20:37

ፈጣጣው

Written by  ኢዮብ ካሣ
Rate this item
(3 votes)

(የጋዜጣው ዜና እንደ አጭር ልብወለድ)

 ይህ አስገራሚ ታሪክ የተፈጸመው በቤኪንግሃም ቤተመንግስት እንግሊዝ ሃገር ውስጥ ነው፡፡ ሐምሌ 1982 ማለዳ ላይ ነበር፡፡ ህይወት የተለመደ ዑደቷን ቀጥላለች፡፡ ንግሥት ኤልሳቤጥን ድንገት አንድ የማታወቀው ሰው ከእንቅልፏ ቀሰቀሳት፡፡ ሰውየው ባዶ እግሩን ነው፡፡ ጂንስ ሱሪና ያደፈ ሸሚዝ ለብሷል፡፡ የተሰበረ የሲጋራ መተርኮሻ በእጁ ይዞ፣ የንግሥቲቱ አልጋ ጫፍ ላይ ተቀምጧል፡፡ የንግሥቲቱ አልጋ ልብስ ላይ ደም ተንጠባጥቧል፡፡

ሰውየው አስፈሪ ለሆኑ አስር ደቂቃዎች ያህል ንግሥቲቱን አነጋግሯታል፡፡ ደግነቱ አንዳችም የማስፈራራት እንቅስቃሴ አልሞከረም፡፡ ንግሥቲቱ ከድንገተኛ ውጥረቷ እፎይ ያለችው፣ የግል አገልጋይዋ ወደ መኝታ ክፍሏ በገባች ጊዜ ነበር፡፡ አገልጋይዋ ወደ ንግሥቲቱ ክፍል እንዴት ተሽሎክሉኮ እንደገባ ያልታወቀውን እንግዳ ሰውዬ ስትመለከት፤ “ወላዲተ-ቅድስት፤ ይህን የመሰለ ሰይጣን፣ እዚህ ምን ይሰራል?” ስትል ጠየቀች፡፡
እውነቷን ነው፡፡ የተከበረችው የእንግሊዝ ንግሥት መኝታ ክፍል ውስጥ ይሄ ሰውዬ ምን ይሰራል? ወደ መኝታ ክፍሏስ እንዴት ገባ? ጥበቃዎቹስ የት ነበሩ? ለመሆኑ ልዑል ፊሊፒስ የት ነው ያለው? የዚህ ልብ አንጠልጣይና አጓጊ ሙሉ ታሪክ አደባባይ የወጣው ከአያሌ ሳምንታት በኋላ ነበር፡፡


ንግስቲቱ መኝታ ክፍል ውስጥ ድንገት የተገኘው እንግዳ፣ ሚካኤል ፋጋን ይባላል፡፡ ዕድሜው 33 ነው፡፡ በምዕራብ ለንደን ነዋሪ ሲሆን፤ በጌጣጌጥ ሥራዎች ላይ የተሰማራ ነው፡፡ ፋጋን ፍ/ቤት የተጠራው ንግሥቲቱ መኝታ ክፍል ውስጥ በመግባቱ አይደለም፡፡ ቀደም ሲል በፈጸመው ሌላ ወንጀል ነው፡፡
ሚካኤል ፋጋን ቀደም ብሎም ቤተመንግስት ውስጥ ገብቶ ነበር ቢባል ማን ያምናል፡፡ ግን እውነት ነው፡፡ ሰኔ 7 ምሽት ላይ ቤተ መንግስቱ ውስጥ ገብቶ እንደነበር ራሱ መስክሯል፡፡ ፋጋን የተከሰሰው ግን ከቤተመንግስቱ ግማሽ ጠርሙስ ቪኖ በመስረቁ ነው፡፡ የዛሬው “የለመደች ጦጣ” መሆኑ ነው፡፡
ሚካኤል ፋጋን በብረቶች ላይ ዘሎ ከወጣ በኋላ፣ በፍሳሽ ቱቦዎቹ ላይ ተንጠላጥሎ፣ በአልጋ አንጣፊዋ መኝታ ክፍል መስኮት በኩል ድንገት ብቅ አለ፡፡ ሰራተኛዋ ከጸሎት ቤት ወደ ክፍሏ መመለሷ ነበር፡፡ ከዚህ ሰውዬ ከሲታ ፊት ጋር ድንገት ተፋጠጠች፡፡ ባንድ ጊዜ በድን ሆና ቀረች፡፡ የምታደርገው ጠፋት፡፡ ከአፍታዎች ቆይታ በኋላ እየሮጠች ሄዳ፣ የገጠማትን አስደንጋጭ ጉዳይ፣ ለቤተመንግስቱ የሥራ ባልደረቦቿ ነገረቻቸው፡፡ ማንም ያመናት ግን አልነበረም፡፡ ጭራሽ “ጻእረ ሞት” ነው ያየሽው ብለው አፌዙባት፡፡


ፋጋን ወዲህ ወዲያ እያለ፣በቤተመንግሥቱ ውስጥ ያሉትን ስእሎች ሲመለከት ቆየና፣ ወደ ክፍሎቹ ውስጥ መግባት ጀመረ፡፡ ጥቂት ክፍሎችን እንዳለፈ በአንዱ በር ላይ “ልዕልት”፣ በሌላኛው ደግሞ “ማርክ ፊሊፕ” የሚል ጽሁፍ አነበበ፡፡ እንቅልፍ ላይ ይሆናሉ በሚል ሊረብሻቸው አልፈለገም፡፡ ቀጥሎ “ልዑል ፊሊፕ” ተብሎ የተጻፈበት በር አገኘ፡፡ ከዚያም የልዑል ቻርልስ የግል ክፍል ውስጥ ሰተት ብሎ ገባ፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ ለግማሽ ሰዓት ያህል ቆየ፡፡ ቢፈልጉ ይያዙኝ ብሎ ነው፡፡ ማንም ግን ዝር አላለም፡፡
በክፍሉ ውስጥ አዲስ ለተወለደው ለልዑል ቻርልስና ለልዕልት ዲያና ልጅ በርካታ ስጦታዎች ተቀምጠዋል፡፡ ከህጻኑ ልጅ ቆዳ ቦት ጫማ አጠገብ አንድ የወይን ጠጅ ጠርሙስ አለ፡፡ ፋጋን ሆዬ፤ ያንን የቪኖ ጠርሙስ ከፈተና ሁለት ብርጭቆ ተጎነጨለት፡፡ “እፎይ ጠምቶኝ ነበረ፡፡ ለንግስቲቱ ትልቅ ስራ ስሰራ ነው የዋልኩት” አለ፤ፋጋን ለራሱ፡፡ ወቸ ጉድ! በዚህ ሁሉ ሰዓት ውስጥ እኮ አንድ ሰው መጥቶ እንዲይዘው ፈልጎ ነበር፡፡
“እናታቸውን! ማንም የለም” አለ፤ ተናዶ፡፡


ፋጋን ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ቤተመንግስቱ የገባው፣ በአምባሳደሮች መግቢያ በር በኩል ባለው ብረት ላይ ተንጠላጥሎ ነው፡፡ ከጠዋቱ 12፡45 ላይ የግቢው ፖሊሶች አንድ እንግዳ የሆነ ሰው ወደ ቤተመንግሥቱ እንደገባ ምልክት ያገኙ ቢሆንም፣ የፖሊስ ቁጥጥር ክፍሉ፣ ነገሩን ችላ ብሎ አለፈው፡፡
ምድር ቤት ውስጥ ባለ አንድ ያልተቆለፈ መስኮት በኩል ዘሎ፣ ወደ አንድ የቴምብር ክፍል ውስጥ ገባ፡፡ በርካታ ቁጥር ያላቸው የንጉሳውያኑ ቴምብሮች ይታያሉ፡፡ ሲገባ ድንገተኛ የጥሪ ደውል ተሰምቶ ነበር፡፡ ማንም ከቁብ አልቆጠረውም እንጂ፡፡ አጅሬ በዚያው መስኮት ተመልሶ ወጣና በቋሚው አሸንዳ ላይ ተንጠላጥሎ ሽቅብ ወጣ፡፡ ጫማና ካልሲውን አወለቀና ሰራተኛዋ ባልዘጋችው ሌላ መስኮት በኩል በመዝለል ወደ ውስጥ ገባ፡፡ ለሩብ ሰዓት ያህል በቤተ-መንግስቱ ኮሪደር ላይ ቢንጎራደድም አንድም የጠየቀው ሰው አልነበረም፡፡
ሚካኤል ፋጋን በቤኪንግሃም ቤተመንግስት ዙሪያ የተተከሉትን ልዩ ልዩ የማስጠንቀቂያ መሳሪያዎች አልፎ በግድግዳ ላይ የተሰቀሉትን ስዕሎች እየተከተለ፣ ከጋለሪው ጋር ወደ ተያያዘው የንግስቲቷ የግል ክፍል ደረሰ፡፡


የሲጋራ መተርኮሻ በተመለከተ ጊዜ ድንገት ራሱን የማጥፋት ወይም ህይወቱን የመተርኮስ ሃሳብ ብልጭ አለበት፡፡ መተርኮሻውን ሰበረና፣ 1፡15 ሲሆን ስባሪውን እንደያዘ፣ ወደ ንግስቲቱ መኝታ ክፍል አመራ፡፡ ንግስቲቱ ፊት የእጁን ደም ሥር በመተርኮሻው ሊቆርጥ አስቦ ነበር፡፡ እንዲያውም ወደ መኝታ ክፍሉ ሲገባ የቀኝ አውራ ጣቱ እየደማ ነበር፡፡
አገልጋይዋ የደረሰችው እንግዲህ ይሄኔ ነበር፡፡ ሁለቱ ሴቶች እንዴት እንደሚያስወጡት መላው ጠፋቸው፡፡ ገልጋይዋ እንደምንም አድርጋ ከክፍሉ ካስወጣችው በኋላ፣ ንግስቲቱ ሲጋራ እንድትሰጠው አዘዘቻት፡፡ አገልጋይዋ እንደታዘዘችው አደረገች - ወደ አንደኛው ጓዳ ይዛው ሄደች፡፡ በዚህ ጊዜ የቤተ መንግሥቱ እንግዳ ተቀባይ ከሄደበት ሥፍራ ተመልሶ መጣ፡፡ ምን እንደምታደርግ ግራ ገብቷት የነበረችው ንግሥት፣ ወዲያውኑ ሁኔታውን ለእንግዳ ተቀባዩ ነገረችው፡፡ እንግዳ ተቀባዩም ለፋጋን ተጨማሪ ሲጋራና ውስኪ ጋበዘው፡፡ እንደ መደለያ መሆኑ ነው፡፡ ፋጋን ውስኪውን ከደጋገመ በኋላ ዳግም ወደ ንግሥቲቱ ክፍል ለመግባት ያዙኝ ልቀቁኝ አለ፡፡ እንግዳ ተቀባዩ ግን በጄ አላለውም፡፡ የንግስቲቱ አገልጋይ ወዲያው ወደ ፖሊሶች ጋ ሄዳ ጉዳዩን አሳወቀች፡፡ ከመቅጽበት ተረኛው ፖሊስ ከተፍ አለ፡፡
የአገሬው የወሬ እናት የሆኑት የለንደን ጋዜጦች፤ የቤኪንግሃም ቤተመንግስት ዐቢይ ርዕሰ ዜናቸው ሆነ፡፡ ከሁሉም ጋዜጦች ወሬውን ከህዝብ ጆሮ ለማድረስ ዘ ዴይሊ ኤክስፕረስን የቀደመ ማንም የለም፡፡ ------ “በ30 ዓመት የንግስና ዘመኗ ከባዱና አሳፋሪው የደህንነት ጥበቃ መላላት” በሚል ርዕስ ዝርዝር ዘገባ አውጥቷል፡፡ ዘ ሰን የተሰኘው ጋዜጣ ደግሞ፤ “በሞል ጎዳና ስትጓዝ ውሃ ከጠማህ፣ ለምን ወደ ቤኪንግሃም ቤተ መንግስት ጎራ ብለህ፣ አንድ ሁለት ብርጭቆ የወይን ጠጅ አትጎነጭም” ሲል አፊዟል፡፡


በቤተ-መንግስቱ በተፈጠረው ድንገተኛና ያልተጠበቀ ሽብር፣ ብዙዎቹ የመንግሥት ባለስልጣናት ተደናገጡ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ታቸር፣ ቤኪንግሃም ቤተ መንግስት መጥታ ለደረሰው ሁሉ በመንግስት ስም ይቅርታ ጠየቀች፡፡ በአደጋ ጊዜ እንደሚሆነው ሁሉ አስቸኳይ የምክር ቤት ስብሰባ ተጠራ፡፡ የሀገር ውስጥ ጸጥታ ሃላፊው በደህንነት ጉዳይ ላይ ንግግር ለማድረግ ወደ መድረክ ሲወጣ፣ በሰዎች ገጽታ ላይ ንዴትና ብስጭት ይስተዋል ነበር፡፡ “በቅርብ አመታት ተጨማሪ የጥበቃና ደህንነት እርምጃዎችን በቤኪንግሃም ቤተመንግስት ማድረጋችን የሚታወቅ ቢሆንም፣ በቅርቡ የተከሰተው ሁኔታ፣ ገና ብዙ መሥራት እንደሚጠብቀን ይጠቁመናል፡፡ ከዚህ ብዙ እንማራለን፡፡” እያለ ሃላፊው ሲደሰኩር የም/ቤቱ አባላት በማሽሟጠጥና በማፌዝ አፋቸውን አጣመሙ፡፡ የሽርደዳ ሹክሹክታ ይሰማ ጀመር፡፡
ፋጋን የመጀመሪያ ክሱን ለመስማት ወደ ፍ/ቤት በሄደ ጊዜ፣ አዳራሹ በሰዎች ተጨናንቆ ነበር፡፡ እጁን ወደ ኋላ አድርጎ ወደ ተከሳሽ መቆሚያ ስፍራ አቀና፡፡ በየጊዜው ቀና እያለ ቤተሰቦቹን ይመለከትና ፈገግ ይላል፡፡ ፋጋን ሳቅ አለና፣ ለሚስቱ ለክርስቲንና ለእናቱ ለኢቭ እጁን አወዛወዘ፡፡ እራሱን በማዝናናት ላይ ያለ ሰው ይመስል ነበር፡፡ የንግስቲቱ ስም በተጠራ ጊዜ ግን ተናደደ፡፡ ደሙ ፈላ፡፡ የሚናገረው ጠፋው፡፡ “የንግስቲቱን ስም እዚህ እንዳታነሳ፤ ኋላ ነግሬሃለሁ” ብሎ ጠበቃው ላይ አፈጠጠበት፡፡ “የንግስቲቱ ስም እዚህ ከሚነሳ ጥፋተኛ መሆኔን ማመን ይቀለኛል” አለ፤ በቁጣ፡፡ በነዚህ ሁሉ አስደንጋጭና እንግዳ የሆኑ ጉዳዮች ውስጥ በእርግጥም አንድ ነገር ግልጽ እየሆነ መጣ፡፡ ሚካኤል ፋጋን ንግስቲቱን ከማክበርም አልፎ ያመልካታል፡፡


ለዋናው ጥያቄው ፍ/ቤት በቀረበ ሰዓትም እንኳ “ፈጣጣነቱ” አለቀቀውም ነበር፡፡ እንደ ተዋናይ ቅንድቡን ወዲያና ወዲህ እየነቀነቀ፣ ቲያትራዊ በሆነ እንቅስቃሴና ፈገግታ፣ ሪፖርተሮችን በአይኑ ይጠቅስ ነበር፡፡
እንደውም ይባስ ብሎ የዳኛውን አርቴፊሻል ጥርሶች አውጥቶ በድዱ ከገለፈጠ በኋላ ከእስረኞች ላይ ጥቂት ምግብ አንስቶ በላ፡፡ በፍ/ቤቱ መሃላ እንዲያደርግ ሲጠየቅም፤ “እኔ ሃይማኖት የለኝም፤ የእርስዎ አምላኪ ነኝ” ሲል መለሰ፡፡ ፋጋን በእግዚአብሔር መኖር የማያምኑ ሰዎች የሚሰጣቸውን መሃላ እንዲወስድ ተፈቀደለት፡፡ ከላይ ጀምሮ አነበበው፡፡
“እባክህ ስምህን በግልጽ አንብበው፡፡” አሉት ዳኛው፡፡
በካርዱ ጫፍ ላይ የሰፈረውን ትዕዛዝ፣ ጣራ ሰንጥቆ በሚወጣ ድምጽ በድጋሚ አነበበው፡፡ ዳኛው ሳይቀሩ ፈገግ አሉ፡፡
“ለምንድን ነው ወደ ቤተ-መንግስቱ የገባኸው?” የዳኛው የመጀመሪያ ጥያቄ ነበረ፡፡
“አንድ የሆነ ድምጽ…” ብሎ ፋጋን ሳይጨርሰው ቀጥ አለ፡፡
ዳኛው ዓይን ዐይኑን እያዩ ትንሽ ከጠበቁት በኋላ፤ “ጥያቄውን መልስ እንጅ” አሉት፡፡
ፋጋን ኤሌክትሪክ እንደያዘው ሰው ዝም፤ ጭጭ አለ፡፡ ዳኛው ቁጣ በተቀላቀለበት ድምጽ፤ “ለምንድን ነው ወደ ቤተመንግስት የገባኸው?” ብለው አምባረቁበት፡፡


“አንድ የሆነ ድምጽ---ግባ ብሎ ሹክ አለኝ” አላቸው፡፡ በፋጋን መልስ ዳኛው ተገረሙ፡፡ አዳራሹን ከሞላው ህዝብ ጉምጉምታ ተሰማ፡፡
“በቃ የገባህበት ምክንያት ይሄው ነው?” ዳኛው ጠየቁ፡፡
“አዎ ይኼው ነው፤ ደሞም ለንግሥቲቷ ብዬ ነው”
ዳኛው የበለጠ ተገረሙ - በአዳራሹ የተሰበሰበው ህዝብ ልቡ ተሰቅሏል፡፡ ቀጥሎ ምን ሊል ይሆን እያለ በጉጉት ይጠባበቃል፡፡
“እንዴት ነው ለንግሥቲቱ ብዬ ነው ስትል?” ዳኛው ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ጥያቄያቸውን ሰነዘሩ፡፡
“ደህንነቷ አስተማማኝ እንዳልነበረ አስብ ነበር” አለ ፋጋን፤ በራስ በመተማመን ስሜት፡፡
“እና ከአንተ ወደ ቤተመንግሥት መግባት ጋር ምን ያገናኘዋል?” ዳኛው ጠየቁ፡፡
“በቃ ግምቴ ትክክል እንደሆነ አረጋገጥኩ” አለ፤ ሚካኤል ፋጋን፡፡
“እንዴት?” ዳኛው በግርምት ተሞልተው ጠየቁት፡፡
“ዘልዬ ወደ ቤተ መንግስቱ ስገባ ማንም የጠየቀኝ የለም፡፡ ከአንዴም ሁለት ጊዜ፡፡ እሺ ንግስቲቷ ብትደፈርስ -- ሌላ አደጋ ቢደርስባትስ?” አለና በሃዘን ስሜት አቀረቀረ፡፡ ወዲያው ቀና ብሎ፤ “እኔ በበኩሌ ባለብኝ የዜግነት ሃላፊነት፣ የንግስቲቱ ደህንነት አስተማማኝ እንዳልሆነ አሳይቻለሁ” አለ የቆመበትን ጠረጴዛ በእጁ እየደበደበ፡፡
ምንጭ ፡-(ዘ ወርልድስ ዊርደስት ውስፔፐር ስቶሪስ)

Read 677 times