Saturday, 02 November 2024 12:33

የመክሳቷ ብዛት፤ የቸኮለ ይቀብራታል

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ቤሣ ቤስቲን የሌለውና የሚልሰው የሚቀምሰው ያጣ አንድ ልብስ-ሰፊ፣ ጫካ ለጫካ ሲዞር አንድ አይሁዳዊ ነጋዴ ያገኛል፡፡ በልቡ “መቼም ይሄ አይሁድ መዓት ብር ሳይኖረው አይቀርም፡፡ ስለዚህ እሺ ቢል በደግነት፣ እምቢ ቢል በጉልበት፣ ያለ የሌለውን ገንዘብ ሊሰጠኝ ይገባል” ብሎ አሰበ፡፡
ወደ አይሁዱም ዘንድ ሲደርስ፣
“ያለ የሌለህን ገንዘብ አምጣ፡፡ አለበለዚያ አሳርህን ታያለህ፡፡ ከዚያም አሻፈረኝ እላለሁ ካልክ ህይወትህን ትከፍላለህ” አለው፡፡
አይሁዱም፤
“ወዳጄ፣ እኔም እንዳንተው ገንዘብ የቸገረኝ ሰው ነኝ፡፡ ኪሴ ውስጥ ያለችኝ ሁለት ብር ብቻ ናት፡፡ ያም ሆኖ ካንተ ችግር የእኔ ይብሳል የምትል ከሆነ፤ ግዴለም አንድ አንድ ብር እንካፈል” አለው፣ በትሁት አንደበት፡፡
ልብስ - ሰፊው ግን አይሁዱ የሚለውን አላመነም፡፡
“ደሞ አይሁድ መቼ ነው ገንዘብ አጥቶ የሚያውቀው? አንተ ቀጣፊ እኔን ለማጭበርበር ፈልገህ ነው?” ብሎ፤ በያዘው በትር ይመታዋል፡፡ አይሁዱ ይወድቃል፡፡ የወደቀው አንድ ድንጋይ ላይ ኖሮ ጭንቅላቱን ከፉኛ ይጎዳዋል፡፡ ብዙ ደምም ይፈስሰዋል፡፡ ህይወቱ ጣር ላይ ትሆናለች፡፡ ነብሱ ከመውጣቷ በፊት፤
“ብሩህዋ ፀሀይ ጉዱን ወደ ብርሃን ታወጣዋለች!” አለ፡፡
ከዚያም ህይወቱ አለፈች፡፡
ገዳዩ የአይሁዱን ኪስ እየፈተሸ ገንዘብ መፈለጉን ቀጠለ፡፡ ያገኘው ግን ያቺኑ አይሁዱ ያላትን ሁለት ብር ብቻ ነበር፡፡ እሷኑ ወስዶ ሲያበቃ፣ ሬሳውን ጎትቶ ወደ ጫካው ሰዋራ ስፍራ ጥሎ መንገዱን ቀጠለ፡፡
ከጫካው ርቆ ሲሄድ ውሎ ወደ አንድ ከተማ ደረሰ፡፡ እዚያም ዋለ አደረና እድል ቀንቶት አንድ ኩባንያ ውስጥ ተቀጠረ፡፡ ከዓመት ዓመት እድገት እያገኘም ሄደ፡፡ ሰንብቶም የኩባንያው ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነ - ግን እጅግ ክፉ ሥራ አስኪያጅ፡፡ ተንኮለኛ ሥራ አስኪያጅ፡፡ ሰው ሁሉ የሚጠላው ሥራ አስኪያጅ፤ ሆነ፡፡ ቀን እየገፋ በሄደ ቁጥርም ባለፈው ግፍና በደሉ ተፀፅቶ ደህና ይሆናል ሲባል፤ ጭራሽ ክፋቱ ባሰበት፡፡ ሰውነቱ ግን ከቀን ቀን እየከሳና እየመነመነ ሄደ፡፡ በዚህም የተነሳ ሰው “የመክሳቷ ብዛት፤ የቸኮለ ይቀብራታል፤ እያለ ይሳለቅበት ጀመር፡፡
የኩባንያው ባለቤት አንዲት ቆንጆ ልጅ ነበረችው፡፡ ይህቺ ልጅ ይህንን ሥራ አስኪያጅ ታፈቅረዋች፡፡ እሱም ያፈቅራታል፡፡ ይጋቡና ሁለት ቆንጆ ቆንጆ ልጆች ይወልዳሉ፡፡
ከዚያ በኋላ የኩባንያው ባለቤትና ሚስትየው ሲሞቱ፤ ልብስ ሰፊውና ወጣቷ ባለቤቱ ኩባንያውን ይወርሳሉ፡፡
አንድ ቀን ያ ልብስ ሰፊ ቤቱ፤ መስኮቱ አጠገብ ተቀምጦ፣ ባለቤቱ ያመጣችለትን ቡና ሊጠጣ ስኒውን ወደ አፉ ሲያቀርብ፤ በመስኮቱ የምትገባዋ ፀሀይ ቡናው ላይ ስታንፀባርቅ፣ ግድግዳው ላይ የክብ ቀለበቶች ምስል ሰራች፡፡ ልብስ - ሰፊውም “አይ ፀሐይ! ሚስጥሬን ወደ ብርሃን ልታወጪ እየሞከርሽ ነው፡፡ ግን አትችይም” አለ፡፡
አጠገቡ ሆና ይህን ስትሰማ የነበረችው ባለቤቱ በጣም ደንግጣ፤
“የሰማያቱ ያለህ! ብቻህን ታወራ ጀመረ? ምን ለማለት ፈልገህ ነው? ፀሀይ የምታወጣው ሚስጥርስ ምንድነው?” ስትል ትጠይቀዋለች፡፡


ልብስ -ሰፊውም፤ “ይሄንን ልነግርሽ አልችልም” ይላታል፡፡
እሷም፤ “እውነት ከልብህ የምታፈቅረኝ ከሆነ ንገረኝ፡፡ የምትነግረኝን ሚስጥር ከአፌ አንዲት ቃል ላላወጣ ቃል እገባልሃለሁ” አለችው፡፡ ከዚያም ካልነገርከኝ ብላ አላስወጣ አላስገባ አለችው፡፡ እረፍት ነሳችው፡፡
በመጨረሻም፣ ለማንም እንደማትነግር ቃል ከገባችለት በኋላ፤ ከዓመታት በፊት አይሁዱን እንዴት እንደገደለውና ከመሞቱ በፊትም፣ “ብሩህዋ ፀሀይ ጉዱን ወደ ብርሃን ታወጣዋለች” እንዳለው ነገራት፡፡ ቀጥሎም “ታዲያ በአሁንዋ ቅጽበት ፀሀይ በመንፀባረቋ ግድግዳው ላይ ቀለበት ስትሰራ አይቼ፣ ፀሐይን ’አትልፊ ጉዱን አታወጪውም‘ ስል ሰምተሽ አንቺ ጠየቅሺኝ” አላት፡፡ “ግን ነግሬሻለሁ፣ ለማንም እንዳትናገሪ!” ሲል ደጋግሞ አስጠነቀቃት፡፡ እሷም ደጋግማ ቃል ገባች፡፡
ልብስ ሰፊው ወደ ስራው ሲሄድ ሚስቱ የምትወዳት ጓደኛዋ ጋር ሄዳ ሲጨዋወቱ፤ በጣም ስለምታምናት፤ ታሪኩን ነገረቻት፡፡ ከዚህ ወዲያ ሦስት ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ድፍን አገር አወቀው፡፡ ከአፍ ከወጣ አፋፍ እንዲሉ፡፡
ልብስ ሰፊው ተከሶ ፍርድ ቤት ቀረበ፡፡ ለዓመታት ሲመላለስ ቆይቶም በመጨረሻ ሞት ተፈረደበት፡፡ ያም ሆነ ይህ፤ ብሩህዋ ፀሀይ ግን ጉዱን ወደ ብርሃን አወጣችው፡፡
*   *   *
ማናቸውም ክፉ ተግባር፣ ማናቸውም ጉድ የማታ ማታ ወደ ብርሃን ይወጣል፡፡ ብሩህዋ ፀሀይ ከማጋለጥ ወደ ኋላ አትልም፡፡ “ደባ ራሱን ስለት ድጉሱን” ይሏልና፣ በሌላው ላይ የጎነጎኑት ተንኮል፣ የሸረቡት ሴራ፣ ጊዜ አመቸኝ ብሎ የዋሉት ግፍ፤ ጊዜው ይጠርም፣ ይርዘምም ሰሪውን እንደ ጥቁር ጥላ ተከትሎ መምጣቱና በአደባባይም መታየቱ፤ አይቀሬ ነው፡፡
በርካታና ህብረ - ቀለም ያላቸውን ማህበረሰብ ባቀፈችው ሀገራችን እየተካሄደ ባለው የዲሞክራሲን መሰረት የመጣል ረዥም ጉዞ ውስጥ፣ ለለውጥ ስንዱ የሚያደርጉን ነባራዊና ህሊናዊ ሁኔታዎች ተመቻችተው ሳለ፤ ለውጡ የተሸራረፈ አሊያም ኢ-ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ያደረጉ አያሌ ክስተቶችን አይተናል፡፡
ከቶውንም የመሰረት ደንጊያ፣ ልስንና ማገር ሆነው ሊያገለግሉ የሚችሉትን እሴቶች፣ ማለትም የሰብዓዊ መብቶችን፣ ፍትህና ርትዕን፣ የዲሞክራሲያዊ መብት አላባውያንን ወዘተ ሁሉ በአግባቡ ውል ለማስያዝ እንዳይቻል፣ በየጊዜው እንቅፋት የሆኑ አያሌ ክስተቶችን አስተውለናል፡
በመንግስትነት ደረጃም ሆነ በፖለቲካ ፓርቲዎች ደረጃ፣ በውስጣዊ መሰነጣጠቅም ሆነ በውጫዊ ተጽእኖ፣ ለዚህ ምክንያት ከሆኑት መካከል ከሀገር በፊት ፓርቲንና ድርጅትን ፍጹም በሆነ መልኩ ማስቀደም፣ ስልጣንን ለማጋራት ቅንና ዲሞክራሲያዊ አሰራር አለመከተልና ከእኔ ወዲያ ላሳር ማለት፤ ሙስናዊ አካሄድ ማዘውተር፣ ላልተዘጋጁበት ድልም ሆነ ሽንፈት ብስለት ያለው ምላሽ አለመስጠትና እርስበርስ ሲጠላለፉ መኖር፣ አንኳር አንኳሮቹ ናቸው፡፡ ከሁሉም በላይ ግን በየአንዳንዷ እርምጃ ውስጥ ህዝቡን አለማሰብ ዋና እንከን ነው፡፡ የህንድ መሪ የነበሩት ማህተመ ጋንዲ በትግሉ ወቅት ያሉትን መጥቀስ እዚህ ጋ ፋይዳ ይኖረዋል፡- በወቅቱ ለጨቋኞቹ ገዢዎች ያሏቸው ይህንን ነበር፡-
“እንዳሻችሁ ልትቆራርጡንና ልትበጣጥሱን ትችላላችሁ፡፡ በመድፍ አፍ ላይ እያሰራችሁ ብትንትናችንን ልታወጡንም ትችላላችሁ፡፡ ምንም አድርጉ ምን ከእኛ (ከህዝቦች) ፈቃድ ውጪ ለምታደርጉት ማናቸውም ድርጊት ቅንጣት ድጋፍና እርዳታ አናደርግላችሁም፡፡ ያለ እኛ ድጋፍና እርዳታ ደግሞ አንድም እርምጃ ወደፊት እንደማትሄዱ ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡ እርግጥ ይሄንን ስናገር በስልጣን ሰክራችሁ ከት ብላችሁ ትስቁ ይሆናል፡፡”
የህዝቡን የልብ - ትርታ ከልብ ማድመጥና ለዲሞክራሲያዊነት ግልጽ - ተገዥነት ካሳየንና አልፎ ተርፎም “ካፈርኩ አይመልሰኝ” ሳንል ስህተትን ለማረምና ለመቻቻል ሆደ - ሰፊነቱን ካደለን ደረጃ በደረጃ ወደ ሰለጠነና ወደ በለፀገ ህብረተሰባዊ እርከን ለመሸጋገር እድሉ ይኖረናል፡፡ ራሳችንን ከድርጅታዊ ቅጽር ማውጣት ይኖርብናል፡፡ አለበለዚያ በሰፊ ግቢ ውስጥ እንዳለና ብዙ መጫወቻ እንደተገዛለት የሀብታም ልጅ፣ በወጉ እንኳ ሳንጠቀምባቸው መጫወቻዎቹ የጎረቤት ሲሳይ ይሆናሉ፡፡
የዘመኑ ጀግንነት ዲሞክራሲያዊነት እንጂ ማናቸውም የኃይል እርምጃ አይደለም፡፡ የሥልጣኔ ቆራጥነት በውይይትና በምክንያታዊ ሙግት መረታታት እንጂ እያደቡ መጠፋፋትና አንዱ ለአንዱ መቃብር መቆፈር አይደለም፡፡ ከየመንገዳችን ሁሉ በኋላ ዛሬም አገርና ህዝብ አለ፤ ብሎ ማሰብ ደግ ነው፡፡
የትላንት ታሪካችንን ለማደስ ዝግጁ አለመሆን ክፉ እርግማን ነው፡፡ ከስልጣን ውጣ - ውረድ፣ ከፓርቲ የውስጥ ለውስጥ ሽኩቻ ባሻገር የአገር አደራ መኖሩን አለመርሳት የታላላቅ ፖለቲካዊ መሪዎች ሁሉ እፁብ ዓላማ ነው፡፡ ያለፈ ስህተታችንን ለማረም ልቦናችን ውስጥ አንዲት የመፀፀቻ ጥግ ልትኖረን ይገባል፡፡

Read 1401 times