Saturday, 02 November 2024 12:34

“የኢትዮጵያን የማንሰራራት ዘመን የምንጀምርበት ዓመት ነው”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“የጀመርናቸውን የሪፎርም ስራዎችን አጠናቀን  የኢትዮጵያን የማንሰራራት ዘመን የምንጀምርበት ዓመት ነው” ሲሉ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናግረዋል። በዘንድሮ ዓመት 300 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ይመረታል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጹት ጠ/ሚኒስትሩ፤ በቀጣናው ከፍተኛ የስንዴ አምራች ኢትዮጵያ መሆኗን  ጠቁመዋል፡፡
ባለፈው ሐሙስ ጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከኢኮኖሚ ሪፎርሙ ወዲህ ባሉት ሦስት ወራት “ተገኝተዋል” ያሏቸውን  አንኳር ድሎችን ጠቃቅሰዋል፡፡ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በ6 ነጥብ 4 በመቶ ማደጉን የተናገሩት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ፤ በዘንድሮ በጀት ዓመት የግብርና ዘርፉ 6 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት ያመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም አብራርተዋል።
በዚህ ዓመት 72 ያህል የሚሆኑና ከፋብሪካ በላይ የሚቆጠሩ ፕሮጀክቶች ማምረት እንደሚጀምሩ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “ከኢንዱስትሪው ዘርፍ 12 ነጥብ 8 በመቶ ዕድገት ይጠበቃል” ብለዋል፡፡ በተጨማሪም፣ ከኮንስትራክሽን 12 ነጥብ 3 በመቶ፣ ከአገልግሎት ዘርፉ ደግሞ 7 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት እንደሚጠበቅ ጠቅሰዋል።


ኢትዮጵያ በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሪ ፖሊሲን ተግባራዊ ካደረገች በኋላ ባሉት ሦስት ወራት የብሔራዊ ባንክ መጠባበቂያ ገንዘብ የ161 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን የገለጹት ጠ/ሚኒስትሩ፤ የግል ባንኮች መጠባበቂያም በ29 በመቶ ማደጉን ጠቁመዋል፡፡
በውጭ አገር ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገር ቤት የሚላክ የገንዘብ መጠን (ሬሚታንስ) ደግሞ 24 በመቶ ዕድገት አምጥቷል ነው ያሉት - ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ፡፡
የኢትዮጵያ ባንኮች ከሪፎርሙ በኋላ ባሉት ሦስት ወራት  652 ሚሊዮን ዶላር በመግዛት፣ ወደ 1 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ መሸጣቸውን ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አረጋግጠዋል። ሀገሪቱ ባፀደቀችው የአራት አመት የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር፣ 27 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ወደ ሀገሪቱ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።
አገሪቱ ባለፉት ሦስት ወራት ከኤክስፖርት 1.5 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቷን የገለጹት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ፤ በተመሳሳይ ጊዜ ከታክስ የተሰበሰበው ገቢ 170 ቢሊዮን ብር መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት ከፌደራል መንግሥትና ከክልሎች ባጠቃላይ 1.5 ትሪሊዮን ብር የታክስ ገቢ ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ ኢትዮጵያ ግብር ከማይሰበስቡ አገራት አንዷ መሆኗን  ጠ/ሚኒስትሩ በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡
“ላለፉት ስድስት ዓመታት የማፍታታት ስራ ስንሰራ ቆይተናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ “ከዚህ ዓመት ጀምሮ ሪፎርሞቻችንን ጨርሰን የኢትዮጵያን የማንሰራራት ዓመት የምንጀምር ይሆናል” ብለዋል፡፡


Read 388 times