Saturday, 02 November 2024 12:37

የማህጸን ጫፍ ካንሰር

Written by  ሃይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

“በህይወት ዘመን ውስጥ ከ7 እና ከ7 በላይ ወንዶች ጋር የግብረ ስጋ ግንኙነት መፈጸም ለማህጸን ጫፍ ካንሰር ያጋልጣል”
የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም የመራቢያ አካላት ካንሰር ሰብ ስፔሻሊስት ዶ/ር መሰረት ኦላና
በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥር ወር የማህፀን ጫፍ ካንሰር ግንዛቤ መስጫ ወር ሲሆን በዓለም የጤና ድርጅት መረጃ መሰረት እ.ኤ.አ የ2024 የማህፀን ጫፍ ካንሰር ግንዛቤ መስጫ ወር መሪ ቃል ስለ ካንሰሩ ማወቅ (መማር)፣ መከላከል እና ምርመራ ማድረግ የሚል ነው።
የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም የመራቢያ አካላት ካንሰር ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር መሰረት ኦላና እንደተናገሩት የማህፀን ጫፍ ካንሰር ከማህፀን ጫፍ (cervix) ተነስቶ የሚሰራጭ የካንሰር (እጢ) አይነት ነው። ከ1 እስከ 2 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች በዚህ ካንሰር የመጠቃት እድል አላቸው።
ለማህፀን ጫፍ ካንሰር የሚያጋልጡ ሁኔታዎች (ምክንያቶች) እና ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች
በኤችፒሺ (ሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ] መጠቃት; የማህፀን ጫፍ ካንሰርን በማስከተል በቀዳሚነት ተቀምጣል። ከ97በመቶ በላይ የማህፀን ጫፍ ካንሰር ከዚህ ቫይረስ ኢንፌክሽን ጋር ግንኙነት አለው። ይህም ቫይረስ በዋናነት የሚከሰተው በግብረ ስጋ ግንኙነት ነው። አንዲት ሴት በህይወቷ ውስጥ ከ7 እና ከ7 በላይ ወንዶች ጋር የግብረ ስጋ ግንኙነት ከፈፀመች በኤችፒቪ ቫይረስ የመያዝ እድል አላት። በተመሳሳይ የትዳር አጋሯ ከሌላ ሴት ጋር ወሲብ የሚፈፅም ከሆነ በቫይረሱ የመያዝ እድል ይኖራታል። ከዚህ በተጨማሪ በንክኪ(ከእናት ወደ ልጅ፤ ወንድ እና ሴት በሚኖራቸው ንክኪ) ቫይረሱ ሊተላለፍ ይችላል። ነገር ግን በዋናነት ቫይረሱ የሚተላለፈው በግብረ ስጋ ግንኙነት ነው።
የእድሜ መግፋት
ብዙ ልጅ መውለድ
የማህፀን ጫፍ ካንሰር ምርመራ አለማድረግ
የኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ ተጠቂ መሆን

የማህፀን ጫፍ ካንሰር ምልክቶች
የወርአበባ መዛባት
የወርአበባ ማየት ያቆመች ሴት ላይ ደም መኖር
ከግብረ ስጋ ግንኙነት በኋላ መድማት
ሽታ ያለው ፈሳሽ መኖር
ማህፀን አከባቢ ህመም መኖር
እግር አከባቢ እብጠት መኖር
በሽንት ወቅት ህመም መኖር
እነዚህ ምልክቶች ሲያጋጥሙ የህክምና ተቋም በመሄድ የችግሩን ምንነት ማወቅ [ማረጋገጥ] ያስፈልጋል።
በዓለም የጤና ድርጅት መረጃ መሰረት እ.ኤ.አ በ2020 6መቶ 4ሺ ሴቶች የማህፀን ጫፍ ካንሰር ምርመራ አድርገዋል። 3መቶ 42ሺ ሴቶች በካንሰሩ ምክንያት ህይወታቸው አልፏል። ከእነዚህ ውስጥ ወደ 90በመቶ የሚሆኑት ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሀገራት ውስጥ የሚገኙ ናቸው። እንደ ዶ/ር መሰረት ኦላና ንግግር በማደግ ላይ በሚገኙ ሀገራት የኤች ፒ ቪ ቫይረስ ክትባት በብዛት አለመዳረስ እና የቅድመ ካንሰር ምርመራ ተደራሽ አለመሆን የቫይረሱ ስርጭት እንዲጨምር አድርጓል።

የማህፀን ጫፍ ካንሰር ደረጃዎች
ቅድመ ካንሰር
ደረጃ አንድ; ካንሰሩ የሚገኘው የማህፀን ጫፍ ላይ ብቻ ነው። ወደ ሌላ የሰውነት ክፍል አልተሰራጨም። በዚህ ደረጃ ላይ የሚገኝ ካንሰር ሙሉ በሙሉ የመዳን እድል አለው። እንዲሁም በዚህ ደረጃ ላይ የሚገኙ ታካሚዎች ለረዥም ዓመታት የመኖር እድል አላቸው።
ደረጃ ሁለት; ካንሰሩ ከማህፀን ጫፍ ወደ ሌላ የሰውነት ክፍል የተሰራጨ ቢሆንም ስርጭቱ የማህፀን ጫፍ አካባቢ በሚገኙ ክፍሎች ላይ ብቻ ነው።
ደረጃ ሦስት; ካንሰሩ ከማህፀን ክፍሎች በተጨማሪ የሽንት ፊኛ፣ ፊንጢጣ እና የአንጀት ክፍል ላይ ተሰራጭቷል ማለት ነው። እንዲሁም ወደ አጥንት የተሰራጨ ሊሆን ይችላል።
ደረጃ አራት; የማህፀን ጫፍ ላይ የተፈጠረው ካንሰር ወደ ጉበት፣ ሳንባ እና ወደ ተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ተሰራጭቶ የሚገኝበት ደረጃ ነው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በማህፀን ጫፍ ካንሰር ከተጠቁ ሴቶች መካከል በተለይም ደረጃው ከፍ ሳይል ምርመራ እና ህክምና ያደረጉ ታካሚዎች 90 በመቶ ከበሽታው የማገገም፣ 5 ዓመት እና ከ5 ዓመት በላይ በህይወት የመቆየት እድል እንዳላቸው መረጃዎች ያሳያሉ። እንደ ዶ/ር መሰረት ኦላና ንግግር የማህፀን ጫፍ ካንሰር ተጠቂዎች በመጀመሪያ ደረጃ (በሽታው ሳይሰራጭ) ህክምና ካገኙ ከ5 ዓመት በላይ በሽታው በድጋሚ ሳይመለስ [ሳያገረሽ] የመቆየት እድላቸው ከ80 በመቶ በላይ ነው።

የማህፀን ጫፍ ካንሰር ህክምና; የህክምና ባለሙያው እንደተናገሩት ህክምናው የሚሰጠው የበሽታውን ደረጃ፣ የታካሚን ልጅ የመውለድ እድል እና እድሜን ታሳቢ በማድረግ ነው።
የቀዶ ጥገና ህክምና; ካንሰሩ ደረጃ 1 ላይ የሚገኝ እና ታካሚዋ ልጅ መውለድ የምትችል (የምትፈልግ) ከሆነ እጢው ብቻ እንዲወጣ ይደረጋል። እንዲሁም ደረጃው ከፍ ያለ ወይም ልጅ የመውለድ ሁኔታ ለሌላቸው ታካሚዎች ደግሞ በቀዶጥገና ማህፀን ሙሉበሙሉ እንዲወጣ ይደረጋል።
የጨረር ህክምና
የኬሞቴራፒ ህክምና

መከላከያ መንገዶች;
የኤችፒቪ (ሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ) ክትባት መውሰድ; እድሜያቸው 14 ዓመት የሆነ ታዳጊ ሴቶች ክትባቱን መውሰድ ይችላሉ።
ቅድመ ካንሰር ምርመራ ማድረግ; ሴቶች እድሜያቸው 21 ዓመት ከሆነ በኋላ በየ3 ዓመት ምርመራ ቢያደርጉ ይመከራል።
ከብዙ ወንዶች ጋር የግብረ ስጋ ግንኙነት አለመፈፀም
በሽታው ከተፈጠረ ደግሞ ሳይዘገዩ ህክምና እና ክትትል ማድረግ
የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም የመራቢያ አካላት ካንሰር ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር መሰረት ኦላና እድሜያቸው 14 ዓመት የሆናቸው ሴቶች ክትባት እንዲወስዱ እና ከ21 ዓመት በላይ የሆኑ ሁሉም ሴቶች የቅድመ ካንሰር ምርመራ እንዲያደርጉ በማለት ጥሪ አስተላልፈዋል።

Read 422 times