“የቦሌ መንገድ” የሚለው ስያሜ ከአድናቆትና ከበጎ ስሜት ጋር የተያያዘ ነው። ለመኪኖችና ለእግረኞች፣ ለሥራና ለኑሮ፣ ለግብይትና ለመዝናናት ከሚመረጡ መንገዶች መካከል አንዱ ነው የሚል ስሜት ያስተላልፋል። የትኛው የቦሌ መንገድ? ነባሩ ወይስ አዲሱ?
ነባሩ “የቦሌ መንገድ” ከጥቂት ወራት በፊት በአዲስ ገጽታ ተሠርቶና አካባቢውም ተሻሽሎ አምሮበታል።
አሁን ደግሞ ሌላ አስደናቂ “የቦሌ መንገድ” መጥቶለታል፤ ወይም ተጨምሮለታል። የቦሌ - መገናኛ መንገድ።
በእርግጥ በርካታ የአዲስ አበባ መንገዶችና አካባቢዎች በኮሪደር ልማት እየተስፋፉና እያማረባቸው ነው። የቦሌ - መገናኛ መንገድ ግን ይለያል። በስፋትም በውበትም።
“የመዲናችን ትልቁ ሰፊ ጎዳና” የሚል ማዕርግ ተሰጥቶታል። የኢትዮጵያ መግቢያ በር ልንለውም እንችላለን። በልዩ ውበት ተሠርቷል።
የቦሌ መገናኛ መስመር… ርዝመቱ 4.3 ኪሎ ሜትር ነው።
አስፋልቱ ብቻ 68 ሜትር ስፋት አለው።
ሥራው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
በተንጣለለው መንገድ ላይ በግራና በቀኝ 10 መኪኖች ሽር… ይሉበት ጀምረዋል። ታክሲዎችና አውቶቡሶች፣ የቤትና የንግድ መኪኖች ሳይጨናነቁ፣ ለሰዓታት ሳይጉላሉ፣ ለአደጋ ሳይጋለጡ ይመላለሱበታል።
እግረኞችም ተመችቷቸዋል።
ከግራና ከቀኝ በአምስት በአምስት ሜትር ስፋት የእግረኞች መንገድ ከጫፍ እስከ ጫፍ ተሠርቶለታል። ለዚያውም በኮንክሪት ነው የተሠራው። ሲያዩት ያምራል፤ ሲራመዱበት ይመቻል። ወዲህ ወዲህ ሳይል ለብዙ ዓመታት እንደሚያገለግልም በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ የስራና ክህሎት ቢሮ ኀላፊ ጥራቱ በየነ ይገልጻሉ።
ከእግረኛ መንገድ አጠገብ፣ በሦስት በሦስት ሜትር ስፋት የብስክሌት መስመር አለው።
ይህም ብቻ አይደለም። መንገዱ ከጫፍ እስከ ጫፍ አረንጓዴ መንፈስ ተላብሷል። ዛፎች ተተክለዋል። ሣር የለበሱና በሥርዓት የተዘጋጁት ውብ መስመሮችም፣ መኪኖችንና እግረኞችን በክብር ለማጀብ የተሰናዱ አረንጓዴ ምንጣፎች ይመስላል።
ግራና ቀኝ ፍስስ በሚሉት መኪኖች መሀል ያለው ቦታ ሣር ለብሷል። ከዳርና ከዳር ሣር አለ። የጥበብ ጥለቶች ይመስላሉ። ከእግረኞችና ከብስክሌት መንገዶች ወዲያም በሣርና በዛፎች ያጌጡ አረንጓዴ አጃቢዎች አሉ።
መብራቶቹም ልዩ ናቸው - “ስማርት ላይት” ይሏቸዋል። በቴክኖሎጂ የበለጸጉ ናቸው። ምን የሌላቸው ነገር አለ? የጎደለ ነገር የለም። የማታ ድምቀታቸውና ውበታቸውም ጭምር።
ከመንገዱ መሀል እንዲሁም ከግራና ቀኝ የተተከሉት አዳዲስ መብራቶች… መሬት ላይ “የተተከሉ” አይመስሉም። የብርሃን ዐምድ ላይ የተንሣፈፉ የብርሃን ክንፎች ይመስላሉ። ወጪ ወራጁን ለመጠበቅና ለማስተናገድ የተዘረጉ ብርሃናማ ክንፎች ናቸው ብንላቸው አይበዛባቸውም።
አቶ ጥራቱም፣ በቦሌ መገናኛ መስመር የተዘረጋው የመንገድ መብራት፣ ከተማችንንና አገራችንን ከፍ የሚያደርግ ነው ይላሉ። የዘመኑን ቴክኖሎጂ የሚያሟላ መሆኑ አንድ ነገር ነው። ግን ደግሞ ወደ ፊትም ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር እንዲራመድ ተደርጎ እንደተሠራ አቶ ጥራቱ ተናግረዋል።
ለነገሩ ዝርዝሩን ሁሉ የማያውቅ ተመልካችም መመስከር ይችላል። ከዳር እስከ ዳር መንገዱንና አካባቢውን አድምቀዋል። ለእይታ ይማርካሉ። ግን መብራት ብቻ አይደሉም።
ጥራት ያላቸው ስክሪኖች ይዘዋል። ካሜራ ተገጥሞላቸዋል።
“ዋይፋይ” የኢንተርኔት አገልግሎት ለማቅረብ ይጠቅማሉ። ባትሪ ቻርጅ ለማድረግ ያገለግላሉ። ለተሽከርካሪዎችም ለእግረኞም አስፈላጊ መልዕክት ለማስተላለፍ ሲያስፈልግም ችግር የለም። “ስፒከር” አላቸው። ሁሉም በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተሳሰሩ ናቸው።
መንገደኞችና አሽከርካሪዎች የአካባቢውን የትራፊክ እንቅስቃሴ በኢንተርኔት ለማየትና ለመከታተል የሚችሉበት ቴክኖሎጂም ተሟልቶላቸዋል።
ኢትዮቴሌኮም የአገራችን ግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋም እንደሆነ አቶ ጥራቱ ጠቅሰው፣ የመብራትና የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ሥራዎችን በኀላፊነት ወስዶ በብቃት እንዳከናወነ ገልጸዋል። እናም፣ “የመንገድ መብራት” ብለን ብንጠራቸውም፣ ዓለማቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የዘመናችን ቴክኖሎጂዎችን ያሟሉ ነው። የመጪው ዘመን ቴክኖሎጂስ?
መቼም፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራ በየጊዜው እየተሻሻለና እየጨመረ ይሄዳል እንጂ፣ አሁን ባለበት አይቆምም። ለዚህም ታስቦበታል ይላሉ - አቶ ጥራቱ። አሁን የተተከሉት መብራቶች፣ ወደ ፊት የሚመጡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በቀላሉ እያካተቱና ደረጃቸውን እያሳደጉ እንዲቀጥሉ ተደርጎ ነው የተሠሩት። የኤሌክትሪክ ገመድ መቁረጥና መቀጠል አይኖርም። ከማዶና ከማዶ ሽቦ መተብተብ አይኖርም። እንደገና መቆፈርና ማፍረስ አይኖርም። ወደ ፊት ቴክኖሎጂዎችን ታሳቢ ያደረገ ዲዛይን ተዘጋጅቶ ነው የመሠረተ ልማት ግንባታ የተካሄደው።
የቀድሞው የቀለበት መንገድና አዲሱ የቦሌ መንገድ
ከሀያ አምስት ዓመት በፊት “የቀለበት መንገድ” ሥራ ሲጀመር፣ በአገልግሎቱና በጥራት ደረጃው ከሌሎች የከተማዋ መንገዶች የተሻለ ይሆናል ተብሎ ነበር። በእርግጥም ደህና አገልግሏል።
የቀለበት መንገዱ ከችግሮች ባያመልጥም፣ ጉድለቶቹ ቀስ በቀስ እየገዘፉ ቢመጡም፣ ለጊዜው ጠቃሚ አገልግሎቶች ነበሩት ይላሉ በምክትል ከንቲባ ማዕርግ የስራና ክህሎት ቢሮ ኀላፊ ጥራቱ በየነ። ነገር ግን፣ ከከተማዋ ዕድገት ጋር ሊጣጣም አልቻለም።
“ቀለበት” ተብሎ ነው የተሠየመው። ግን እንደ ስሙ አልሆነም። በከተማዋ ዳርቻ ዙሪያዋን የሚቅፍ መንገድ ይመስላል - ስያሜው። ግን አይደለም። ገና ከመነሻው በከተማዋ ዳርቻ ላይ አልተሠራም። በከተማ ውስጥም ነው መንገዱ የተገነባው። ዛሬ ደግሞ የከተማ መሀል ሆኗል ማለት ይቻላል።
ሌላው ይቅርና፣ ያኔ ብዙ ነዋሪ ያልነበራቸው አካባቢዎችም ዛሬ ብዙ ሕዝብ ይኖርባቸዋል። ሰፋፊ የሥራና የንግድ ማዕከላት ሆነዋል። በመገናኛ ቦሌ መንገድ፣ ከ25 ዓመት በፊት “ገርጂ” አካባቢ ብዙ ነዋሪ አልነበረም ቢባል እንኳ፣ ዛሬ ግን የከተማ መሀል ሆኗል።
መቼም የመንገድ አገልግሎት፣ ከቦታ ቦታ በፍጥነት ለመድረስ ነው። እናም፣ “ጊዜን ይቆጥባል” ወይም ደግሞ “የተራራቁ አካባቢዎችን ያቀራርባል” ብለን ልንገልጸው እንችላለን። የቀለበት መንገዱስ?
በብረት የታጠረው የቀለበት መንገድ፣ ከተማ መሀል ውስጥ ተዘርግቶ ከተማውን ከማዶና ከማዶ ከፍሏል። ጎረቤት ሰፈሮችን ለያያቷል። ቅርብ ለቅርብ የሆኑትን አካባቢዎች አራርቋል። ከመንገዱ ማዶ ለመሻገር፣ አንድ ኪሎ ሜትር ሁለት ኪሎ ሜትር መጓዝ የግድ ሆኗል። ጊዜ የሚቆጥብ ሳይሆን ጊዜ የሚፈጅ ከሆነ… ችግር አለው።
በቂና አመቺ የእግረኞች መሸጋገሪያ እንዳልነበረው አቶ ጥራቱ ገልጸው፤ ተሽከርካሪዎችም ወደሚፈልጉት አቅጣጫ ለመሄድ የማቋረጫና የማዞሪያ አማራጭ በቅርበት የሚያገኙበት ዕድል አልነበራቸው ብለዋል።
ለነገሩ፣ የብረት አጥሩ እንዲሁ ሲታይም ለእይታ አያምርም። ነገር ግን ዋናው ችግር እሱ አይደለም። አመቺ መሸጋገሪያ ባለመኖሩ፣ አጥር ዘለው መንገድ ለመሻገር የሚሞክሩ እግረኞች ላይ ብዙ አደጋ ደርሷል።
ይህም ብቻ አይደለም።
የአዲስ አበባ የመኪኖችና የእግረኞች ቁጥር በእጅጉ እንደጨመረ የገለጹት አቶ ጥራቱ፣ የቦሌ መገናኛ መስመር ላይ የነበረው የቀለበት መንገድ ይህን በብቃት ማስተናገድ አልቻለም ብለዋል።
የመገናኛ መስመር ከጥዋት እስከ ምሽት የትራፊክ እንቅስቃሴ የሚበዛበት መስመር ነው። መንገዱ ይጨናነቃል። መንቀሳቀሻ ይጠፋል። መኪናና እግረኛ ሲጋፋ ይውላል ማለት ይቻላል።
በፍጥነት ለመተላለፍ መንቀሳቀሻ ያጡ መኪኖች ተደረድረው ስንዝር ስንዝር ሲንፏቀቁ፣ የሥራ ሰዓት ይባክናል፤ የጉዳይ ቀጠሮ ይስተጓጎላል። አምስት ደቂቃ የማይፈጅ መንገድ፣ የአንድ ሰዓት እንግልት ይሆናል። ነዳጅ ይቃጠላል። የተሳፋሪዎችና የአሽከርካሪዎች መንፈስ ላይ የሚያሳድረው ጭንቀትም የዚያኑ ያህል ነው። ኑሮም መንፈስም ይረበሻል።
ይህን ሁሉ የሚፈታ ነው - በኮሪደር ልማት የተሠራው አዲሱ የቦሌ መንገድ።
ይህም ብቻ አይደለም።
ትልልቅ ተቋማት በመገናኛ ቦሌ መስመር ላይ ቢኖሩም፣ አካባቢው ለተጨማሪ አገልግሎት የሚያመች ቅርጽ አልያዘም ነበር። በሰፋፊ ግቢ ትልልቅ የመንግሥትና የቢዝነስ ተቋማት የሚገኙበት መስመር እንደሆነ የተናገሩት አቶ ጥራቱ፣ ሞኢንኮ፣ አምቼ፣ ኒያላ ማተርስና አንበሳ አውቶብስን በምሳሌነት ጠቅሰዋል።
ነገር ግን፣ የመገናኛ ቦሌ መስመር ለሥራና ለግብይት ከፍተኛ አገልግሎት ሊሰጥ የሚችል መስመር ቢሆንም አገልግሎቱን ለማዘመንና ለማሻሻል ተመቻችቶ አልተሠራም። መገናኛ አደባባይ አቅራቢያ የሚገኝ አካባቢ በተለይ ትንሽ ከመሸ በኋላ፣ ጭር ማለት አልነበረበትም።
አሁን ግን ለተለያዩ የአገልግሎት ተቋማት ተመቻችቷል። የካፊቴሪያና ንግድ መደብሮች፣ የመዝናኛ ቦታዎችና የመጸዳጃ ስፍራዎች ተሠርተዋል።
ይህም ብቻ አይደለም።
የአገራችንና የከተማችንን በጎ ገጽታ የሚመሰክር!
አቶ ጥራቱ እንደሚሉት፣ የቦሌ መገናኛ መስመር፣ ከመላው ዓለም የሚመጡ እንግዶችን የምንቀበልበትና የምናስተናግድበት የኢትዮጵያ መግቢያ በር ነው ማለት ይቻላል። በመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት ውስጥ የተካተተውና አሁን የተጠናቀቀው የመገናኛ ቦሌ መስመር፣ ዘንድሮው በሁለተኛ ዙር የኮሪደር ልማት ወደ ጫካ ፕሮጀክት ከሚዘልቀው መስመር ጋር የሚገናኝ ነው።
አዲስ አበባ… የኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን የአፍሪካ መዲናም ናት። የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከልም ናት። ከዚህም በተጨማሪ፣ አገራችንና ከተማችን፣ ለኢንቨስትመንት፣ ለንግድና ለቱሪዝም በዓለም ዙሪያ ተመራጭ የመሆን ትልቅ ዐቅም አላቸው።
የቦሌ መገናኛ መስመር፣ ለዚህ ሁሉ የሚመጥን የጥራት ደረጃና ውበት ሊኖረው ይገባል። የአገራችንና የከተማችንን በጎ ገጽታ የሚያሳይና የሚመሰክር መሆን አለበት።
የከተማችን አኗኗር የሚያሻሽል፣ ኢኮኖሚን የሚያሳድግ፣ ለመኪኖችና ለእግረኞች እንቅስቀሴ የሚያመች፣ የከተማችንና የአገራችንን ገጽታ ከፍ የሚያደርግ መሆን እንዳለበት ታስቦበት ዲዛይን እንደተዘጋጀ ገልጸዋል - አቶ ጥራቱ። ግንባታውም በጥራትና በፍጥነት እንደተሠራ ተናግረዋል።
አንድ የቀረ ሥራ አለ።
ለእግረኞችና ለመኪኖች ጭንቅንቅ ትልቅ እፎይታ!
በምድር ሥር ለእግረኞች ከሚዘጋጁት ሁለት መተላለፊያዎች መካከል አንዱ ተገንብቶ ተጠናቅቋል። ሁለተኛው ግን በዚህ ሳምንት ነው የተጀመረው። ለምን?
ሁለት የምድር ሥር መተላለፊያዎችን በአንድ ጊዜ ለመሥራት መንገዱ ሁለት ቦታ ላይ ከተዘጋ፣ ከጫፍ ጫፍ መንገዱን እንደመዝጋት ነበር የሚሆነው። በነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ እንግልት ያስከትል ነበር። ለዚህም ነው፤ በየተራ ግን በፍጥነት ለመገንባት የተመረጠው።
ሰሞኑን የተጀመረው የምድር ሥር መተላለፊያ፣ 53 ሜትር ርዝመት አለው። ሰፊ ነው። በውስጡ በርካታ ሱቆችና አገልግሎት መስጫ ስፍራዎች ይኖሩታል። ቢሆንም ግን በ45 ቀን ግንባታው እንደሚጠናቀቅና ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን አቶ ጥራቱ ቃል ገብተዋል።
ለዚህም በቂ ዝግጅት ተከናውኗል። የግንባታ ማሽኖችና የግንባታ ቁሳቁሶች አዘጋጅተናል። በየቀኑ በ3 ፈረቃ፣ 24 ሰዓት እንሠራለን። በታቀደው ጊዜ ወይም ከዚያ በፊት እናጠናቅቃለን ብለዋል - አቶ ጥራቱ። በመገናኛ አካባቢ ለሚታየው የእግረኞችና የመኪኖች ጭንቅንቅ ትልቅ እፎይታ እንደሚሆንም ተናግረዋል።