ከዓመታት በፊት አዲስ አበባ አንድ የፌደራል መ/ቤት ውስጥ እሰራ ነበር፡፡ ከእለታት ባንዱ ቀን እንደተለመደው፣ ተኮላና ሳሙኤል ከተባሉ ባልደረቦቼ ጋር ምሳ በመ/ቤታችን ግቢ ውስጥ ባለ ካፌ ከበላን በኋላ ወጣ ብለን ቡና ለመጠጣት እያወራን፣ እየተቀላለድን አምባሳደር አካባቢ ወደሚገኝ ቤት እንጓዛለን፡፡ ከፒያሳ ወደ ለገሀር የሚወስደውን መንገድ ስናቋርጥ ታዲያ አንዲት መኪና ድንገት ደርሳ ክፉኛ አስደነገጠችኝ፡፡ የመጀመሪያውን መንገድ ተሻግረን ወደ ሁለተኛው መንታ መንገድ እየገባን ነበር፣ እኔ መኪናዋን ቀድሜ አላየኋትም፣ እና ድንገት አጠገቤ ደርሳ ሳገኛት ለማምለጥ ስንደፋደፍ አንዳች አይነት ዳንስ አስደነሰችኝ፡፡
ተኮላ፤ “እንዴ! የበላይ ዘር ሆነህ እንደዚህ ትፈራለህ?” አለኝ፤ባሳየሁት ሁኔታ እየሳቀ፡፡ ሳሙኤልም፤ “የበላይን ዘር አስደነሰቺህ እኮ! ታይቶ የማይታወቅ ዳንስ… ጋሞኛ ነው ምንድነው” እያለ አሾፈብኝ፡፡ ከድንጋጤዬ ተመልሼ ትንፋሼ መለስ ካለልኝ በኋላ የሆንኩትን ሳስበው በርግጥም የሰራሁት እንቅስቃሴ እንኳን ተመልካቹን እኔንም አሳቀኝ፡፡ መኪናዋ የታክሲ ቅርፅ ያላት ሆና ከታክሲ ያነሰች ናት፡፡ ከማነሷና ከመቅለሏ የተነሳ ስትሄድ የመንገዱ ጉርብጥብጥ ብድግ ብድግ ስለሚያደርጋት የምትፈነገል ትመስላለች፡፡ የመኪናዋን ስም አላስታውስም፣ ከመጠኗና ከአካሄዷ አንፃር ኩብኩባ የሚል ስም ሰጥቼያታለሁ፡፡ ትንሽዬ መኪና ናት፣ ቢሆንም እኔን ገጭታ ለመጣል አታንስም፡፡
“የበላይ ዘር አይፈራም ያለው ማነው?” አልኳቸው ጓደኞቼን፡፡ ወትሮም መበሻሸቅ የሚቀናን ጓደኛሞች፤ በእኔ ኪሳራ በተግባር የተሰራ ትያትራዊ መዝናኛ ስላገኘን እየተተራረብን፣ እየሳቅን ጥሩ የቡና ጊዜ አሳለፍን፡፡ ያን ሰሞን ለምሳ በወጣን ቁጥር ጓደኞቼ ስለሚያነሱት ነገሩ መዝናኛ ሆኖን ሰነበተ፡፡ በተለይ ሳሙኤል ተንከሲስ ለመተረብ ሰበብ ነው የሚፈልግ፡፡ ከወራት በኋላ ሌላ ባልደረባችንን ጨምረን እንዲሁ ቡና ለመጠጣት ከቢሮ ወጥተን ስንጓዝ፣ ያቺ ኩብኩባ መኪና አጋጠመቺን፡፡ ሳሚ ምን አለ፤ “ይቺን መኪና እንዳትንቃት፤ ቦርሳንዴዝን ያርበደበደች ናት”፡፡
የጓደኞቼ ተረብ የቀልድ ቢመስልም ነገሩን ስንመረምረው ጥልቅ የሆነ ትርክታዊ መነሻ አለው፡፡ እንዴት የበላይ ዘር በመሆኔ በሁሉ ነገር እንድደፍር እጠበቃለሁ? ዘር የደም ግንኙነትን የሚያመለክት ነውና በመጀመሪያ እስከማውቀው ድረስ የበላይ ዘመድ አይደለሁም፡፡ ምናልባት በላይ እና እኔ በምንጅላትና በምንጅላት እንገናኝ ይሆናል፣ ርቆ ከተሄደ የሰው ዘር በሙሉ ዘመድ ነው፡፡ በላይና እኔ የምንጋራው ነገር ቢኖር በአባይ ወንዝ እጥፋት በተካለለ፣ በአንድ የወል ስም በሚጠራ አካባቢ ማደጋችን ነው፡፡ በላይን ከወንድሞቹና ከጓዶቹ ጋር እንዲጀግን ያደረገው ከዚያ በፊት በዚያ አካባቢ የተፈጠረ ጀግና ነው? አይመስለኝም፡፡ የበላይና የዘመን ጓዶቹ ስኬት በግልና በቡድን ጥረት የተገኘ ነው፡፡ በተጨማሪም አንድን ሰው በጦር ሜዳም ይሁን በሌላ ዘርፍ ዝነኛ የሚያደርገው ስራው ብቻ ሳይሆን የስሙ ደጋግሞ መነሳት ነው፡፡ ስሙ በደንብ የሚነሳው ደግሞ ብዙ ጊዜ አጨራረሱ አሳዛኝ ሲሆን ነው፡፡ በላይ ባይሰቀል ኖሮ ጣሊያን ላይ በሰራው ጀግንነት ብቻ እንዲህ ዝነኛ ይሆን ነበር?
የሆነው ሆኖ በላይ ዘለቀ ራሱን ፈጠረ እንጂ ጎጃም በላይን አልፈጠረም ባይ ነኝ፡፡ ጎጃም በላይን አልፈጠረም ስል ግን በላይ ከተወለደበትና ካደገበት አካባቢ የወረሰው የጉብዝና ልማድ የለም ለማለት አይደለም፡፡ ከዚያ የበለጠ ግን በላይ አባቱ በሰው ልጅ ሲገደልበት በልጅነት አእምሮው ተቀርፆ የቀረው ምስል ለጉብዝናው ዋነኛ ጉልበት ሳይሆነው አልቀረም፡፡ አንድ ሰው እንዲጀግን አስተዳደጉ፣ ግላዊና ቤተሰባዊ ገጠመኙ፣ የማህበረሰቡ ልማድ፣ እንዲሁም ከዚህ ባሻገር የሆኑ ውጫዊ ክስተቶች ሁሉ አስተዋፅኦ አላቸው፡፡ ዘር ግን እንዴት ሊሆን ይችላል? ጀግንነት እንደ በሽታ በዘር ይተላለፋል? ያውም እስከምንጅላት ቆጥሮ? በአንድ ሰፊ ግዛት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን የወል ባህርይ የሚያላብሱ ሰዎች ሁለት ነገሮችን ረስተዋል፡፡ አንደኛ፡ ታሪካዊ ክስተቶች በግለሰቦች ማንነት ላይ የሚፈጥሩትን ተፅእኖ ረስተዋል፡፡ ጦርነት ጀግናን ይፈጥራል፡፡ የሚጋፈጠው ነገር ካላጋጠመው አንድ ሰው በባዶ ሜዳ ጀግና ሊሆን አይችልም፡፡ የአባቱን ደም ለመበቀል በረሃ በወረደበት ጣሊያን ኢትዮጵያን ባይወር በላይን አሁን እንደምናውቀው እናውቀው ነበር? በላይ የሚባል ሰው ከነመፈጠሩስ እናውቅ ነበር? ሁለተኛ፡ ሁላችንም የሁለት ነገሮች ድምር ውጤት ነን– የተፈጥሮና የባህል፡፡ በእንግሊዝኛው nature vs nurture ይባላል፡፡ የትኛው ማንነታችንን የበለጠ ይወስናል የሚለው ሁሌም አከራካሪ ነው፡፡ ለእኔ ባህል ያመዝናል፡፡ ምክንያቱም በተፈጥሮ ይዘነው የምንወለደው ማንነት ቀጥተኛና ውስን ነው፡፡ ባህላዊ ተፅአኖ ግን በህይወታችን ሙሉ በገፍ ያጋጥመናል፡፡ ስንኖር ከቤተሰብ ሁኔታ ጀምሮ እስከ ታላላቅ ሀገራዊና አለማቀፋዊ ክስተቶች የሚደርሱ ነገሮችን እናስተናግዳለን፡፡ እነዚህ ነገሮች ከተፈጥሮ በበለጠ ማንነታችንን ጠፈጥፈው የመስራት አቅም አላቸው፡፡
እኛ ሀገር ዘር የሚባል ቃል አስተውሎታችንን ሸፍኖት ይገኛል፡፡ ባህላዊ ዘፈናችን ዘርን ካልጠራ አይሆንለትም፡፡ የባህል ዘፈናችን ጎንደሬን ሁሉ እንደ ቴዎድሮስ ቆራጥ አድርጎ ይደነግጋል፡፡ አይሆንም እንጂ ጉብዝና በዘር ይወረሳል ቢባል እንኳን ጠቅላላ ጎንደር የቴዎድሮስ፣ ምድረ ጎጃምም የበላይ ደም ሊኖረው አይችልም፡፡ አካሄዱ የቴዎድሮስንና የበላይን ጀግንነት ለድፍን ጎንደሬና ጎጃሜ አትረፍርፎ በማልበስ ማህበረሰቡን ማኩራት ነው፡፡ በጠባቡ ካየነው ጠቃሚ ነው፡፡ ጎጃሜ በላይን እያነሳ ይፎክራል፤ የእነ በላይን ተጋድሎ እያነሳ ጉብዝናውን ያጠናክራል፤ ምድረ ጎጃም በበላይ የተነሳ በአንድነት ተሳስሯል፡፡ የግለሰብን ስኬት ወደ ቡድን ስኬት አጠቃሎ መኩራት የዘመኑ ኢትዮጵያውን መገለጫ ሆኗል፡፡ በላይና ጎጃምን በግል ገጠመኜ የተነሳ አነሳሁ እንጂ፣ ይህ የግለሰብን ስኬት ወደ ማህበረስብ ስኬት አጠቃሎ መታበይ ብሄርተኝነት በተንሰራፋበት በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል በግልፅ የሚታይ ነገር ነው፡፡ አርቲስቶቻችን የጥቂት ግለሰቦችን ዝና እያነሱ በማወደስ ይሸቅላሉ፡፡ በላይ ባይጀግን ጎጃምኛ ዘፈኖች አሁን ላይ ምን መልክ ይኖራቸው ነበር? በዘመኔ ኢትዮጵያ ውስጥ የማየው ነገር ታሪክ መስራትን ሳይሆን ታሪክ መቀራመትን ነው፡፡ በላይ ቢጀግን በጥረቱ፣ እኔ ብፈራ በሰውነቴ፡፡
መፍራት ግን እኮ ተፈጥሯዊ ነው ጎበዝ፣ መሸሽም ደመነፍሳዊ፡፡ ያቺ ኩብኩባ መኪና እየሸመጠጠች አጠገቤ ደርሳ ሳገኛት ከሞት ማምለጤ እንጂ የበላይ ወገንነቴ እንዴት ትዝ ሊለኝ ይችላል? ምንስ ያህል የበላይ ጀግንነት ቢሰርፅብኝ እንዴት በዚያ ቅፅበት ልፎክር እችላለሁ? ሰው ነበርና በላይ ራሱ የማይቋቋመው አደጋ ሲመጣበት ዘወር እያለ አሳልፎታል፡፡ ታዲያ ምናለበት ብተውኝ ፈርቼ ብኖርበት ሃሃሃ……