አንድ አባ ዳካ የሚባሉ በሠፈር ባገሩ በጨዋታና በነገር አዋቂነታቸው የታወቁ አዛውንት በየጊዜው በየዕድሩ፣ በየሰንበቴውና በየድግሱ ሁሉ እየተገኙ በሚያጋጥማቸው ነገር ላይ ይተርባሉ፣ ወግ ያወጋሉ፣ ቀልድ ይቀልዳሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ሰው አባባላቸውን እየጠቀሰ፤ “አባ ዳካ እንዲህ አሉ” እያለ ይተርታል፡፡ አለቃ ገብረ- ሃና እንዲህ አሉ፡፡ ካሳ ደበሉ እንዲህ አሉ፤ እንደሚባለው መሆኑ ነው፡፡
አባ ዳካ፣ አንድ ቀን ከአንድ ሹም ጋር ተጣልተው በብዙ ጅራፍ ተገርፈው ሲመጡ ወዳጃቸው የሆነ ሰው ያገኛቸውና “ምን አርገው ነው እንዲህ የተገረፉት አባ ዳካ?” ሲል ጠየቃቸው፡፡
አባ ዳካ፣ “ያየሁትን ተናግሬ” ይላሉ፡፡
“ምን አይተው፣ ምን ተናገሩ?” ብሎ ይጠይቃቸዋል፡፡
“ትላንትና ወንዝ ወርጄ ውሃ ቀጂዎቹ እወንዙ ዳር ሆነው በብዛት ውሃ ይቀዳሉ፡፡ ይሄኔ አንድ ሹም ከሚስቱ ጋር ይመጣል፡፡ ከዚያም ሚስቱ ከሌሎቹ ውሃ-ቀጂዎች እኩል መቅዳቷ የውርደት ይመስለውና፣ በሰላም ውሃ እየቀዱ ያሉትን ሴቶች፣ “አንቺ መጀመሪያ፣ ቀጥሎ አንቺ፣ ቀጥሎ አንተ” ማለት ጀመረ፡፡
ይሄኔ እኔ በሆዴ “ወንዙ ላገር የሚበቃ ነው፡፡ ሁሉም እንደየአቅሙ መቅዳት ይችላል፡፡ አሁን ተራ ግቡ፣ በዚህ ውጡ፣ በዚህ ውረዱ፣ ማለትን ምን አመጣው? አልኩና ባካባቢዬ ላሉት ሰዎች የሀገሬ ሰው “ሹመት የለመደ፣ ወንዝ ወርዶ፣ እርስዎ ይቆዩ፣ እርስዎ ይቅዱ” ይላል አልኩኝ፡፡
ሰው ሲስቅ ሹሙ ተናደው አርባ ጅራፍ ፈረዱብኝ፡፡
ሌላ ቀን ደግሞ አባ ዳካ ብዙ ያገር ሰው የተጠራበት ሰንበቴ፣ ድግስ ሄደው ኖሯል፡፡ እዚያ የሚመገቡትን ተመግበው ሲያበቁ የሚጠጣው ጠላ ቀረበ፡፡ በመጀመሪያ ዙር የተሰጣቸው ጠላ ጉሽ ነበር፡፡
እንደምንም ብለው “እንትፍ፣ እንትፍ” እያሉ ጠጡ፡፡
ሁለተኛው ዙር መጣ፡፡ አጋፋሪው ቀዳላቸው፡፡ አሁንም ጉሽ ነው፡፡
ሦስተኛውን ደገሙ፡፡ አሁንም ጎሸባቸው፡፡ ያም ሆኖ አባ ዳካ ሞቅ እያላቸው ሄዱ፡፡
በአራተኛው፣ አጋፋሪው ሲመጣ አባ ዳካ ቀና አሉና፣
“ሰማህ ወይ አጋፋሪ?”
“አቤት አባ ዳካ፣ ምን ፈለጉ?”
አባ ዳካ ጮክ ብለው ቀጠሉ፣
“ቁና- እህል ጠላ ጨረስን፣
እባካችሁ ማጥለያ ስጡን” አሉ፡፡
ተጋባዡ ሁሉ በሆዱ ይህንኑ ያስብ ኖሮ ሳቅ በሳቅ ሆነ፡፡
***
ፈረንጆች “ማንኛውም ነገር ሊቀለድበት የማይችልበት ደረጃ ሲደርስ፣ ተስፋ እየራቀ ሄደ ማለት ነው” ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ምናልባት በተቃራኒው፣ ተስፋ የማይደረስበት ርቀት ላይ ቢሆን እንኳ ህዝቡ እንደልብ መቀለዱን፣ እንደልብ መጫወቱን፣ እንዳሻው መተረቡን አይተውም ማለት ይቀላል፡፡ እንደነሩሲያ፣ እንደነሩማኒያ፣ መራር ቀልድ ለመቀለድ የሚችል ሕዝብ ነው፡፡ ቻይናውያን እንደሚሉት “እሳተ-ገሞራ ላይ ሆኖም በራሱ ላይ አነጣጥሮ የሚቀልድ እውነተኛ ኮሜዲያን” ነው፡፡ አባ- ዳካ አንዱ ምሳሌ ናቸው፡፡ አንዳንዴ እንደ አባ ዳካ ያሉ ሰዎች ባይኖሩን ምን ይውጠን ነበር? ያሠኛል፡፡ መራር ቀልድ የሚቀልዱ ሰዎች ማግኘት መታደል ነው፡፡
የሀገራችን የፖለቲካ መንገድ ሁሌም ረዥም ነወ፡፡ ደረጃው ይለያይ እንጂ ወጣ ገባም፣ መራራም ነው፡፡ የፖለቲካ መንገደኞቹ ደግሞ በብዛት ረዥም መንገድ ተጓዥ ሆነው አይገኙም፡፡ ወይ የንድፈ-ሀሳብ ስንቅ ይጎድላቸዋል፡፡ ወይ የልምድ መዳበርና መሰናዶ ያንሳል፡፡ ወይ በቀና አመለካከት የታነፁ አባላት ይጎድላቸዋል፡፡ ወይ በትግሉ ጥልቀትና ጠመዝማዛ ርቀት ላይ ያለው አስተውሎት ደብዛዛ ይሆናል፡፡ ወይ በሰርጎ-ገብ፣ ወይ በአድርባይ፣ ወይ ባለሁሉ-አለሁ ባይ፣ ወይ በዕውቀት የበታችነት ስሜት፣ አሊያም በአመለካከት የበላይነት ጫና፣ በየጊዜው ውጥረት ውስጥ ሲገቡ ይታያል፡፡ አጠቃላዩ የፖለቲካ አየር ሁሌ በተለመደና ተደጋጋሚ ውጥረት ውስጥ መግባቱ አስገራሚ ነው፡፡ እርግጥ የፖለቲካው ሀይል የስበት ማእከል በጋለ ሙቀት በተከበበ ቁጥር የተቃራኒ ሀይሎች ፍትጊያ ሰበቃ አይቀሬ ነው፡፡ በዚህ ሰበቃ ውስጥ እየተሸረፈ የሚወድቅ፣ እየተፈረካከሰ የሚበተን፣ እንደ ባቡር ፉርጎ የሚጎረድ፣ እንደ ባህር ጨው ሟሙቶ የሚቀር መኖሩ፣ ያለ፣ የነበረና የሚኖር ነው፡፡ ይህ ሀቅ ገዢ ተገዢ ሳይል በየፓርቲው ላይ ሁሉ ሲከሰት የሚታይ ነው፡፡ ዋናው ነገር ግን የዚህ ሁሉ መጨረሻ አገር ወዴት እያመራች ነው? ህዝቡስ ምን ፋይዳ እያገኘ ነው? የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ይህን ጥያቄ ለአፍታም አለመዝለል ያሻል፡፡
በሀገራችን ከ1960ዎቹ ጀምሮ በመንግሥት ውስጥም ሆነ ውጪ ብዙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመሥርተዋል፡፡ ዛሬም ብዙ የፖለቲካ ፓርዎች አሉ፡፡ የዱሮዎቹ በተለይ ተቃዋሚዎቹ፣ ጥቂትና በህቡዕ (በሚሥጥር) የተደራጁ ሲሆኑ፣ የአሁኖቹ በአደባባይ ሰው አውቋቸው፣ ፀሐይ ሞቋቸው የተቋቋሙና ብዙ መሆናቸው ነው፡፡ በሁለቱም ዘመን፣ በጋራ የምናየው ብርቱ ጉዳይ፣ አንዱ በሌላው ፓርቲ ወይም ቡድን ውስጥ በታኝ ሃይል ማስረጉ ነው፡፡ ያህያ ቆዳ ለብሰህ ጅብን ውጋ፣ አሊያም የበግ ለምድ ለብሰህ ተኩላ ነኝ በል፣ ነው ነገሩ፡፡ ሌላው ክስተት፣ ለብዙኃን ዲሞክራሲ ተገዢ አለመሆን፣ የመሰነጣጠቅ አደጋ፣ የግትር እምቢተኝነት ጠባይ፣ በፊት ለፊት እምቢ ሲል በጓሮ መሄድ፣ በማላተም እምቢ ሲል፤ በማጠቋቆም መጠቀም፣ በምክክር ሲያቅት በሸር፣ በረድፈኝነት ሲያቅት በአንጀኝነት፣ በድቁና ሲያቅት በሙስና፣ በማስፈራራት ሲያቅት በመቅጣት፣ በመሞዳሞድ ሲያቅት በማዋረድ፣… መጓዝ ነው፡፡
እነዚህ ሁሉ የፖለቲካ ፈሊጦችና አካሄዶች አገሪቱ ባለችበት እንድትረግጥ አሊያም የኋሊት እንድትንሻተት ማድረጋቸውን ልብ አለማት፣ ክፉ የጥፋት አባዜ ነው፡፡ ነገ ከነግወዲያ ለሀገርና ለህዝብ ምን ፈየድኩ? ሲባል በእኩይነታችን ማፈር፣ በውድቀታችን መፀፀት ይሆናል፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ በተለይም ጠንካራ ተቃዋሚ ድርጅቶች መኖር፣ ለዲሞክራሲያዊ ሁኔታዎች ማበብ ወደድንም ጠላንም እርሾ ነው፡፡ ያለእነዚህ ድርጅቶች የህዝቦችን ፍላጎት ማንፀባረቅና ማርካት ምኞት ብቻ ነውና፡፡ በእርግጥም አንዴ የትግል አምባ ከተወጣ ድካሙን፣ ሥቃዩን፣ ውጣ ውረዱን፣ አታካችነቱን፣ በተደጋጋሚ ሊያጋጥም የሚችለውን እልህ- አስጨራሽ ፈተና መቀበል አሌ የማይባል የጉዞው አካል ነው፡፡ ይህ ግን ገና ትግልን ሲጀምሩ መጤን ያለበት የትግሉ ሥጋና ደም ነው፡፡ ትግልን ረዥምና እሾሃማ የሚያደርገውም ይኸው ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብትን ማስከበር፣ ፍትሐዊ ሁኔታን መፍጠርና ሰላምን መጎናፀፍ የአንድ ጀምበር ተግባር አይደለም የሚባለውም ለዚሁ ነው፡፡ ዐይንን ከፍቶ ክፉና ደጉን መለየት፣ ነገሮች ሲጎሹ ሳይደናገጡ ማጥራት፣ ለዲሞክራሲያዊ ሂደት ሠናይነት እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ “ቁና-እህል ጠላ ጨረስን፤ እባካችሁ ማጥለያ ስጡን” የሚባለው ተረትም ይህንኑ የሚያፀኸይ ነው፡፡