የአፍሪካ መሪዎች ብሩህ ተስፋ
ዶናልድ ትራምፕ ከዋይት ሃውስ ከለቀቁ ከአራት ዓመት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ በመመረጥ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ይህን ታሪካዊ ድል ተከትሎም በርካታ የአፍሪካ መሪዎች ከትራምፕ ጋር በቅርበት ለመስራትና ከአሜሪካ ጋር ያላቸውን ትስስር የበለጠ ለማጠናከር ተስፋና ጉጉት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ የትራምፕ ዳግም መመረጥ አፍሪካን አሜሪካን ወደተሻለ ቅርርብና ትብብር ሊመራ እንደሚችልም ተገምቷል፡፡
ለተመራጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት በማስተላለፍ ከቀዳሚዎቹ የአፍሪካ መሪዎች የአገራችን ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ “በምርጫ ድልዎትና ወደ ስልጣን በመመለስዎ እንኳን ደስ አለዎት ማለት እፈልጋለሁ” ሲሉ በኤክስ ገፃቸው መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ፤ “በእርስዎ የሥልጣን ዘመን የሁለቱን አገራት ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር በጋራ የምንሰራበትን ጊዜ እጠብቃለሁ” ብለዋል፡፡
የዚምባቡዌው ፕሬዚዳንት ኢመርሰን ምናንጋግዋ በበኩላቸው፤ አገራቸው ከአዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ጋር በትብብር ለመሥራት ያላትን ፈቃደኝነት ገልፀዋል፡፡ “ዚምባቡዌ የተሻለች፤ የበለጠ የበለፀገችና ሰላማዊ ዓለም ለመገንባት ከእርስዎና ከአሜሪካ ህዝብ ጋር ለመስራት ዝግጁ ናት” ብለዋል፤ ፕሬዚዳንቱ በመልእክታቸው፡፡
የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ቦላ ቲኑቡ፣ ለተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባስተላለፉት የእንኳን ደስ ያለዎት መልእክት፤ “በአንድ ላይ የኢኮኖሚ ትብብርን ማሳደግ፤ ሰላምን ማጎልበትና ዓለማቀፍ ተግዳሮቶችን መፍታት እንችላለን፡፡” ብለዋል፡፡
የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ለተመራጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባስተላለፉት የእንኳን ዳግም ተመረጡ መልዕክት፤ በቀጣዮቹ ዓመታት ለአገሮቻችን የጋራ ጥቅም ከእርስዎ ጋር ለመሥራት በጉጉት እጠብቃለሁ ብለዋል፡፡
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ በበኩላቸው፤ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን “የጋራ ተጠቃሚነት አጋርነት” ለመቀጠል በጉጉት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡
በቅርቡ በፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ግብዣ በአሜሪካ ጉብኝት ያደረጉት የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ ለዶናልድ ትራምፕ ባስተላለፉት የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት፣ “ባለ ራዕይ፣ ደፋርና ፈጠራ የታከለበት አመራር ያላቸው” ሲሉ አድንቀዋቸዋል፡፡
ከመሪዎች ባሻገር አፍሪካውያንም የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤትን አስመልክቶ በማህበራዊ ሚዲያ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ አብዛኞቹች ውጤቱ ለአሜሪካ ትልቅ ድል መሆኑን ጠቁመው፤ ዶናልድ ትራምፕ በዓለም ላይ እየተካሄዱ ያሉ ጦርነቶችን እንደሚያስቆሙ ተስፋቸውን ገልፀዋል፡፡ በአንፃሩ ሌሎች ደግሞ ትራምፕ ድሉን የተቀዳጁት የተሻለ ተቀናቃኝ ስላልገጠማቸው ነው ብለዋል፡፡ ለትራምፕ አሸናፊነት የአሜሪካውያንን ለሴት ፕሬዚዳንት ዝግጁ አለመሆንን በምክንያነት የጠቀሱም አልጠፉም፡፡
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ምን አሉ?
ለዶናልድ ትራምፕ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት ያስተላለፉት ቭላድሚር ፑቲን፣ ተመራጩን ፕሬዚዳንት “ደፋር” ሲሉ አሞካሽተዋል። የሩሲያው ፕሬዚዳንት በሶቺ ከተማ በተካሄደ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ትራምፕ በዋይት ሃውስ በነበሩበት የመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው ከየአቅጣጫው ጫና በዝቶባቸው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ትራምፕ የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም እሠራለሁ ማለታቸው “ቢያንስ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል” ሲሉም ፑቲን በንግግራቸው አክለዋል። ባለፈው ሐምሌ በዶናልድ ትራምፕ ላይ የተፈጸመውን የግድያ ሙከራ በተመለከተም ሲናገሩ፤ “በእኔ አስተያየት በጣም ትክክለኛ በሆነ መንገድ አንድ ደፋር ሰው ማድረግ ያለበትን አድርጓል” ሲሉ ፑቲን ለትራምፕ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ለመወያየት ዝግጁ እንደሆኑ የተጠየቁት ፑቲን፤ “ዝግጁ ነን፣ ዝግጁ ነን” ሲሉ መልሰዋል።
ትራምፕ ከፑቲን ጋር ለመነጋገር መዘጋጀታቸውን ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ለኤንቢሲ ኒውስ በሰጡት ቃል፤ “የምንነጋገር ይመስለኛል” ብለዋል። ይህ በዚህ እንዳለ፣ በዩክሬንና በአውሮፓ የሚገኙ በርካቶች፣ ትራምፕ ወደ ኪዬቭ የሚላከውን የአሜሪካ ወታደራዊ እርዳታ ሊገቱ ወይም ሊያዘገዩ ይችላሉ የሚል ጭንቀት እንደገባቸው ተዘግቧል።
የትራምፕን ድል “በቮድካ” እንዳከበሩ የገለጹት የሃንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን በበኩላቸው፤ አሁን አሜሪካና አውሮፓ በንግድ መስመር ላይ ከባድ ንግግሮች ይገጥማቸዋል ብለዋል። የትራምፕ የቅርብ አጋር የሆኑት ኦርባን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫው፤ “ከአሜሪካ ጋር የሚኖረው የንግድ ጉዳይ ከመነሳቱም በላይ ቀላል አይሆንም” ብለዋል።
የአውሮፓ ሀገራት መሪዎች ምክክር
50 የሚደርሱ የአውሮፓ መሪዎች የዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆኖ መመረጥ በአህጉሩ ላይ የሚፈጥረውን ተጽዕኖ በተመለከተ መመክራቸው ተዘግቧል፡፡ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ በሃንጋሪ ቡዳፔስት በተደረገው ስብሰባ ላይ የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮልድሚር ዘለንስኪና የኔቶ ዋና ፀሀፊ ማርክ ሩትን ጨምሮ የአውሮፓ ሀገራትና ድርጅቶች መሪዎች ተገኝተዋል፡፡
መሪዎቹ በሩስያ ጉዳይ በፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የስልጣን ዘመን እንዳለው ጠንካራ የጋራ አቋም እንዲንጸባርቅ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡ የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ድርጅት ኔቶ ዋና ጸሀፊ ማርክ ሩት በስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግር፤ “ሩሲያ ለሰሜን ኮሪያ የተለያዩ የሚሳኤልና የሳተላይት ቴክኖሎጂዎችን በመስጠት በምላሹ ከፒዮንግያንግ ወታደራዊ ድጋፍ እያገኘች ነው፤ ይህ ለአውሮፓ የኔቶ ክፍል ብቻ ሳይሆን ለአሜሪካ ደህንነትም ከፍተኛ ስጋት ነው” ብለዋል፡፡
ትራምፕ በመጀመርያው የፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው የኔቶ አባል ሀገራት ለድርጅቱ የመከላከያ ወጪ የሚጠበቅባቸውን ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት 2 በመቶ እና ከዛ በላይ እንዲያወጡ እንዲሁም ከአሜሪካ ወታደራዊ እገዛ ጥገኝነት እንዲላቀቁ በጥብቅ ይገፋፉ ነበር፡፡ ይህንኑ ሀሳብ የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቻርልስ ሚሼል በስብሰባው ላይ ያነሱ ሲሆን፤ አህጉሩ በአሜሪካ ወታደራዊ ድጋፍና የኔቶ መዋጮ ላይ ጥገኛ ከመሆን መላቀቅ አለበት ብለዋል፡፡
ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ከአውሮፓ ጋር ከሚኖረው የንግድ ጦርነት አንስቶ ከኔቶ ለመውጣትና ዩክሬን ከሩሲያ ጋር በምታደርገው ጦርነት መሰረታዊ የሆነ የድጋፍ ለውጥ እንደሚያደርጉ ዝተዋል፡፡ ይህም በመላው አውሮፓ በሚገኙ ሀገራት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያስከትል እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡
በ2018 የትራምፕ አስተዳደር የውጭ ምርቶች በአሜሪካ አጋሮች ቢመረቱም ለአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት አስጊ ናቸው በሚል በአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት በሚመረቱ የብረትና አሉሚኒየም ምርቶች ላይ የታሪፍ ጭማሪ አድርጎ እንደነበር ይታወሳል፡፡
በሌላ በኩል፤ የአውሮፓ ሀገራት ትራምፕ የዩክሬን ጦርነትን ለማስቆም በሚያደርጉት ጥረት ለሩስያ ሊያደሉ እንደሚችሉ ስጋት አላቸው፡፡ የአውሮፓ አገራት መሪዎች የተሰባሰቡበትን ጉባኤ ያዘጋጀችው ሀገር ሀንጋሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን፣ ምርጫው ከተጠናቀቀ በኋላ ከትራምፕ ጋር በስልክ እንደተነጋገሩና የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም ትልቅ እቅድ እንዳላቸው ከስብሰባው በፊት ተናግረዋል፡፡
የአሜሪካ ምርጫ ውጤት በዩክሬንና በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት፣ በስደት እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከቱ ጉዳዮች ለሚቀጥሉት አመታት በአውሮፓ አጠቃላይ ግንኙነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ተጽዕኖ ሊፈጥር እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡