Saturday, 09 November 2024 13:03

ለ እናቶች ሞት መንስኤ የሆኑ 4 ችግሮች.....

Written by  ሃይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

           እ.ኤአ የ2020 የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው ከእርግዝና እና ከወሊድ ጋር በተያያዘ በ1 ቀን የ8መቶ ሴቶች ህይወት ያልፋል። የእናቶች ሞት በ2 ደቂቃ ውስጥ ይከሰታል። ከዚህ የእናቶች ሞት መካከል 95 በመቶ በዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ውስጥ ይከሰታል። በኢትዮጵያ ከእርግዝና እና ወሊድ ጋር በተያያዘ ችግር በ1 ዓመት ውስጥ 14ሺ ሴቶች (በቀን 38 እናቶች ማለት ነው) ህይወታቸውን ያጣሉ። እናቶቹ ህይወታቸውን የሚያጡት አስቀድሞ መከላከል በሚቻልባቸው መንስኤ(ችግሮች) ነው። 
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ጥቅምት 12 2017 ዓ.ም የእናቶች ሞት መንስኤ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር። የውይይት መድረኩ ለእናቶች ሞት መንስኤ የሆኑ ጉዳዮች ላይ ጥናታዊ ፅሁፍ የቀረበበት ሲሆን ፅሁፉ ለፖሊሲ እና መመሪያ ግብአት የሚሆን ነው ተብሏል። የቀረበው ጥናታዊ ፅሁፍ ከእርግዝና ጋር ተያይዞ ስለሚመጣ የደም ግፊት፣ በወሊድ ወቅት ስለሚያጋጥም የደም መፍሰስ፣ ስለየማህፀን ጫፍ ካንሰር እና ስለመንገድ ደህንነት ነው።
በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የጤና ስርአት ምርምር (Ethiopian health institute health system research) ዳይሮክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር አደራጀው መኮንን እንደተናገሩት የህብረተስብ ጤና ኢንስቲትዩት የጤና ስርአት ምርምር ዳይሮክቶሬት በስሩ 4 ክፍሎች አሉት። በውይይት መድረኩ የቀረበው የእውቀት ሽግግር እና ትግበራ ክፍል ነው። በዚህ ክፍል የቀረቡት ጥናቶች የእናቶችን ሞት እና ጉዳቶች (maternal mortality and morbidity) ለመቀነስ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ ናቸው። እንደ ዶ/ር አደራጀው መኮንን ንግግር ጥናቱ የእናቶች እና ህፃናትን ህይወት ለመታደግ ወሳኝ የሆኑ አማራጮችን ይዟል።


የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንዳስቀመጠው በዓለም አቀፍ ደረጃ በ1 ዓመት ውስጥ 14 ሚሊዮን እናቶች በወሊድ ወቅት ከፍተኛ የሆነ የደም መፍሰስ ያጋጥማቸዋል። ከዚህ መካከልም ወደ 70 ሺ የሚሆኑት ህይወፊታቸውን ያጣሉ።
ከወሊድ በኋላ ስለ ሚያጋጥም የደም መፍሰስ ጥናት ያደረጉት እና በመድረኩ ለውይይት ያቀረቡት ተመራማሪ ፊርማዬ ቦጋለ ናቸው። ይህ ጥናት ለፖሊሲ መረጃ፣ ማሻሻያ እና ማርቀቂያነት የሚውል ነው። እንደ ተመራማሪዋ ንግግር ጥናቱ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ እና ለመከላከል የተሻለ ለውጥ (መፍትሄ) ሊያመጡ የሚችሉ ጉዳዮችን ይዟል። በጥናቱ ለፖሊሲ ለውጥ (መሻሻል) ሊያመጡ የሚችሉ ሁለት መፍትሄዎች መኖራቸውን ተመራማሪ ፊርማዬ ቦጋለ ተናግረዋል። የመጀመሪያው የጤና ስርአት መቆጣጠሪያ (monitoring and evaluation) ላይ ተጨማሪ ነገሮች ለማካተት የሚውል ነው። ይህም የእናቶችን ሞት በተመለከተ የህክምና ተቋማት እና የህክምና ባለሙያዎች እየሰሩ ስለሚገኙት ስራ ለማወቅ እና ለመገምገም ይረዳል። ሁለተኛው ደግሞ የዓለም የጤና ድርጅት መመሪያ ላይ መሰረት በማድረግ ከወሊድ በኋላ የሚያጋጥም የደም መፍሰስ መመሪያ (Guideline) ላይ ማሻሻያ ማድረግ ነው። ይህም ማሻሻያ የሚደረገው እናቶች ለቅድመ ወሊድ የህክምና ክትትል የህክምና ታቋም ሲሄዱ አገልግሎት የሚያገኙበት መንገድ (ሁኔታ) ላይ ይሆናል። የዓለም የጤና ድርጅት ለችግሩ አጋላጭ ናቸው ብሎ ካስቀመጣቸው ጉዳዮች መካከል አንዲት እናት ያላት የልጆች ብዛት (እርግዝና) እና የተረገዘው ልጅ የክብደት መጠን ተመራማሪዋ በምሳሌነት ጠቅሰዋል።


ተመራማሪዋ አክለውም በኢትዮጵያ ያለው ከወሊድ በኋላ የሚያጋጥም የደም መፍሰስ መመሪያ ውስጥ የተካተቱ ጉዳዮች በቂ አለመሆናቸውን በጥናት መረጋገጡን ገልፀው የዓለም ጤና ድርጅት ላይ ከተቀመጡት አጋላጭ ሁኔታዎች መካከል አስፈላጊ የሆኑት መካተት እንደሚገባቸው ተናግረዋል። እናም በሁለቱ መመሪያዎች ላይ ማሻሻያ መደረጉ ከወሊድ በኋላ የሚያግልጥም የደም መፍሰስ በ1 ዓመት ውስጥ የሚቀጥፈውን የ8ሺ 3 መቶ 21 እናቶች ህይወት ወደ 5 ሺ ለመቀነስ ያስችላል ብለዋል የህክምና ባለሙያዋ። 
ለእናቶች ሞት መንስኤ በመሆን በወሊድ ወቅት ከሚያጋጥም የደም መፍሰስ ቀጥሎ  በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥም የደም ግፊት በ2ኛ ደረጃ ተቀምጧል። በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥም የደም ግፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለእናቶች ሞት ምክንያት ከሆኑ 5 በሽታዎች መካከል ይመደባል። በዓለም ላይ በዚህ በሽታ ምክንያት በ1 ዓመት ውስጥ 63ሺ የሚሆኑ እናቶች ህይወታቸውን ያጣሉ። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ድንገተኛ የጽንስ እና ጨቅላ ህጻናት ድጋፍ ሰጪ [Ethiopian National Emergency Obstetric and Newborn Care] መረጃ እንደሚያሳየው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ 10 በመቶ ለሚሆኑ እናቶች ሞት ምክንያት በመሆን የተቀመጠው በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥም የደም ግፊት ነው። በሀገሪቱ ከ1መቶ ሺ ወላድ እናቶች መካከል 412 እናቶች ህይወታቸው ያልፋል። ከዚህም ውስጥ 19በመቶ የሚይዘው በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የደም ግፊት ነው።


ተመራማሪ ተስፋዬ ዳኜ ለእናቶች ሞት መንስኤ ተብለው ከቀረቡ ጥናቶች መካከል በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥም የደም ግፊት ላይ ነው ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡት። ተመራማሪው እንደተናገሩት በብዛት ጥናቶች ሲጠኑ በሚመች መልኩ (አንድ ላይ) ሳይሆን ለየብቻ (በተበጣጠሰ መልኩ) ነው። ይህም ጥናቶችን ለፖሊሲ ለመጠቀም አመቺ እንዳይሆን አድርጎታል። ስለሆነም ለፖሊሲ እና መመሪያ አውጪዎች አመቺ በሆነ መንገድ ኢንስቲትዩቱ እየሰራ ይገኛል። እነዚህ ጥናቶች የእናቶች ጤና ላይ እየሰራ ለሚገኝ፣ ለሚሻሻል እና አዲስ ለሚወጣ ፖሊሲ ግብአት ይሆናል ብለዋል ተመራማሪው።
እንደ ተመራማሪው ንግግር በኢትዮጵያ በእርግዝና ወቅት በሚከሰት ደምግፊት ምክንያት ከመቶ ሺ እናቶች ውስጥ 267 እናቶች ህይወታቸውን ያጣሉ። “በዓለም መንግስታት የተቀመጠው በ2030 በ1 ዓመት ውስጥ ቢበዛ የ70 እናቶች ህይወት ብቻ ቢያልፍ የሚል ነው” ብለዋል ተመራማሪ ተስፋዬ ዳኜ። ስለሆነም በኢትዮጵያ በ1ዓመት ውስጥ ከ200 በላይ እናቶች ህይወት ማለፍ ከተቀመጠው የዓለም መንግስታት እቅድ ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ልዩነት ያለው መሆኑን አክለው ተናግረዋል። እንዲሁም ከእርግዝና ጋር ተያይዞ የሚያጋጥም የደም ግፊት እና ከወሊድ በኋላ የሚፈጠር ከፍተኛ የሆነ የደም መፍሰስ ችግር ላይ ከተሰራ የእናቶችን ሞት መቀነስ እንደሚቻል ተመራማሪ ተስፋዬ ዳኜ ተናግረዋል።
በውይይት መድረኩ ከተካተቱት ጥናታዊ ፅሁፎች ውስጥ ሌላኛው ለእናቶች ሞት የሚዳርገው የማህፀን ጫፍ ካንሰር ነው። በዓለም የጤና ድርጅት መረጃ መሰረት እኤአ በ2020 604ሺ ሴቶች የማህፀን ጫፍ ካንሰር ምርመራ አድርገዋል። 3መቶ 42ሺ ሴቶች በካንሰሩ ምክንያት ህይወታቸው አልፏል። ከእነዚህ ውስጥ ወደ 90 በመቶ የሚሆኑት ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሀገራት ውስጥ የሚገኙ ናቸው። የማህፀን ጫፍ ካንሰር ምርመራን አስመልክቶ በተጠቃሚዎች ዘንድ ፍቃደኝነት አለመኖሩን ዶ/ር አደራጀው መኮንን ተናግረዋል። ይህም የሆነው በህክምና ፍራቻ፣ ማፈር እና በባህል ጫና ምክንያት ነው ብለዋል። ስለሆነም ለማህፀን ጫፍ ካንሰር መነሻ በመሆን በቀዳሚነት የሚቀመጠው የኤች ፒ ቪ (ሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ) ናሙና ሴቷ እራሷ ብትወስድ ይመረጣል። ምርመራውን እራሷ ማድረጓ ነፃነት እንዲሰማት ያደርጋል። እንዲሁም ለተጨማሪ ምርመራ ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ የካንሰሩ መኖር አለመኖር ማረጋገጥ ትችላለች። 


4ኛው በዉይይት መድረኩ ላይ የቀረበው ለእናቶች ሞት መንስኤ የሆነው ጉዳይ የመንገድ ደህንነት ነው። የዓለም ባንክ መረጃ እንደሚያሳየው መሰረታዊ ለህክምና የሚያስፈልግ ግብአት እና አገልግሎት በማጣት የእናቶች ህይወት ያልፋል። በወቅቱ ለእናቶች እና ህፃናት አስፈላጊው ህክምና(ድንገተኛ የህክምና አገልግሎት) ቢሰጣቸው ወደ 75 በመቶ የእናቶች እና የህፃናትን ህይወት መታደግ ይቻላል ተብሎ ይገመታል። ዶ/ር አደራጀው መኮንን እንደተናገሩት በኢትዮጵያ የመኪና አደጋ ሲያጋጥም እንኳን ተጎጂዎች የህክምና ተቋም ከመድረሳቸው አስቀድሞ መስጠት ስለሚገባው እርዳታ ለሁሉም ሰው የሚሰጥ ስልጠና የለም። ነገር ግን ይህ ስልጠና ለብዙሀኑ ቢሰጥ “ቢያንስ በአዲስ አበባ በ1 ዓመት ውስጥ ከ1 መቶ በላይ ሰዎችን ማዳን እንችላለን” ብለዋል ዶ/ር አደራጀው መኮንን። አክለውም በተለይ በገጠር የሀገሪቱ ክፍል እናቶች በመንገድ እና መጓጓዣ ችግር ህይወታቸው ማለፉን ገልፀው ጥናቱ ይሄን ችግር ለማቃለል እንደሚያግዝ ተናግረዋል። በተመሳሳይ ተመራማሪ ተስፋዬ ዳኜ የመንገድ ደህንነት ለእናቶች ጤና የሚያበረክተው አስተዋፅኦ በሚፈለገው ልክ ጥናት እንዳልተደረገበት ገልፀው የሚመለከታቸው ባለሙያዎች ሊሰሩበት እንደሚገባ ተናግረዋል። 
በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የጤና ስርአት ምርምር ዳይሮክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር አደራጀው መኮንን እንደተናገሩት በ4 ርእሰ ጉዳይ ላይ የቀረቡት ጥናታዊ ፅሁፎች በተለያየ (4 ) ፖሊሲ ወይም መመሪያ ላይ ተግባራዊ ሊደረግ ይችላል። እንዲሁም ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮች በተመሳሳይ መመሪያ ወይም ፖሊሲ ላይ ሊካተቱ ይችላል።  ማህበረሰቡ እና ባለድርሻ አካላት ለእናቶች ሞት መቀነስ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱ ዶ/ር አደራጀው መኮንን መልእክት አስተላልፈዋል።

Read 346 times