Monday, 11 November 2024 00:00

ከዚህ ህዝብ ጋር እንዴት መኖር ይቻላል?

Written by  ኪሩቤል ሳሙኤል
Rate this item
(2 votes)

      የራሳችሁ ጭንቅላት ነገር ፈልጓችሁ አያውቅም? ተሸክማችሁት ሳለ ድንገት ራሳችሁን ሲጠላችሁ ታውቋችሁ ያውቃል? የመጨረሻ አሰልቺ ፍጥረት እንደሆናችሁ ነግሯችሁ ምንም እንዳልተፈጠረ በፀጥታ ከእነ እድፋችሁ ጥሏችሁ ሄዶ የሚያውቅበት ቀን የለም? ማንም ሳይነካችሁ የታመማችሁበት…ማንም ሳይሰማችሁ የጮኸችሁበት…የቃላት ዶፍ መሀከል ሆናችሁ ማዳመጥ ያቃታችሁ…እነዚህ ቀናት እናንተ ጋር ደርሰው ያውቃሉ? በትንኝ ነፍሳችሁ የዝሆኑን ድርሻ እንወጣ ያላችሁበት ዘመናችሁ…? ትዝ ይላችኋል?
ከዚያ የተሸከማችሁትን ስሜት ሰው ላይ ስታዩት፣ ሁላችንም ተመሳሳይ እንደሆንን ስታውቁ፣ ካወቃችሁም በኋላ ጭንብላችሁን ማንም እንዳያይባችሁ ለመደበቅ ስትሞክሩ… መሳያችሁን (የራሳችሁን ቢጤ) የሆኑትን በቅጥያ ስም ሰበብ ከራሳችሁ ስታሸሹ ትዝ ይላችኋል?
እንትና “እብድ” ነው…እንትና “አበደች” ስትሉ?…ቃል መርጣችሁ እውነታችሁን ስታንገላቱት? ራሳችሁን ማከም አቅቷችሁ እብደታችሁን ሰው እብደት ውስጥ ስላችሁ በቃላት ሰበባችሁን ልትገሉ ስትሉ? ይህ ሁላ ሲሆን ምን ያህል የሚያስፈራ ሰው ወደ መሆን እየገሰገሳችሁ እንደሆነ ትረዱታላችሁ?
እውነት ነው… ይገባኛል ህይወት ከሞት በላይ አስፈሪ ነው፡፡ እየተነፈሱ መቆየት ብዛት ያለው ጣቃ ቅፅበቶችን እየበታተኑ ቦታ ለማስያዝ የሚጋልብ የሀሳብና የተፈጥሮ የጋራ ጦርነት ነው፡፡ ጉዞው ሀብትም ላይ ሆናችሁ፣ ሰላምም ሆናችሁ፣…ሳቃችሁ ከናፍሮቻችሁ ላይ የሚሰነብትላችሁ እድለኛም ሆናችሁ ቢሆንም ህይወት ከእነውስብስብነቷ ከባድ ናት፡፡ ሁሌ አዲስ መስላ በመደጋገም ስልት ዘመናችን ላይ ጥልቀቱ የግላችን የሆነውን መሰልቸትን ታቀብለናለች፡፡ ቀላል መንገድ የለም፡፡ ለኛም …ለመሰሎቻችንም፡፡
የምለውን የሚያጠናክርልኝን ሀሳብ አልበርት ካሙ “The Fall” በሚለው መፅሐፉ ውስጥ እንዲህ አድርጎ ይገልፀዋል….
“The true horror of existence is not the fear of Death, but the fear of life. It is the fear of waking up each day to face the same struggle, the same disappointment, the same pain. It is the fear that nothing will ever change, that you are trapped in the cycle of suffering that you cannot escape. And in that fear, there is a desperation, a longing for something, anything, to break the monotony, to bring meaning to the endless repetition of day.”
ይህን ሀሳብ በስሱ ለመበተን ልሞክር፡፡
አንዳንዴ “ምንድን ነው ነገሩ?” የሚያስብልበት ወቅት ሊመጣ ይችላል….እውነትም የመፈጠር ስቃይ ውስጥ ያለው ሞትን በመፍራት የሚመጣ ሰቀቀን ሳይሆን ህይወትን እንዴት እንደምንገፋው በማሰብ ላይ ያለ መምታታት ውስጥ ያለ መደንገጥ ይመስላል፡፡ ካሙ እንደሚለው፤ ትልቁ ፍርሀት ያለው በየቀኑ ከእንቅልፍ እየነቁ ወደ ተመሳሳዩ ስቃይ፣ መከራ፣ ንዴትና ህመም ጋር እየሄዱ መላተም የምርም ያስፈራል፡፡ በምንም አይነት ንቃት ውስጥ ሆነህ ከእንቅልፍህ አለም ተላቀህ ስትመጣ የሚጠብቅህ እነዛው ቅጠሎች፣ እነዛው አከራዮችህ፣ ራሱ ትላንት ሲያጥንህ የከረመው አቧራ፣ እነዛው ሴቶች…ከዛ የማይጠግብ እና ስንት የምድርን መከራ ያሳየህ ሆድህ እና ከዛ ቢጠቀጠቅ ቢጠቀጠቅ ምንም ሳይገባው የሚሰናበትህ ጭንቅላትህ ጋር ሆነህ ነው የምትነቃው፡፡
በየቀኑ፡፡
እስክትሞት ድረስ፡፡
የሚሸሽህ ሸሽቶህ…ብቻህን እስክትቀር ድረስ፡፡
ብዙ ቦታ የሚመስል አንድ የህላዌ ምዕራፍ ላይ ስትሽከረከር ትከርማታለህ፡፡
ያኔ ድክም ሊልህ ይችላል፡፡ በእውቀትና በጥበብ ጭንቅላትህን አሰልጥነኸው ካልመጣህ ቅጥ ያጣ እብደት ውስጥ ሊከትህ ይችላል፡፡ እርግጥ ነው የገዛ እውቀታቸውና ጥበባቸው አስክሮ የጣላቸው በተለምዶ እብዶች እያልን የምንጠራቸው የኛ ቢጤዎች በብዛት በአካባቢያችን ማየታችሁ አይቀርም፡፡ እኔ እነሱን አላልኩም፡፡ እኔ ልል ያሰብኩት “No great mind has ever existed without the touch of Madness.” ብሎ አርስቶትል የገለፃቸውን ነው፡፡
ይህንንም ፅሁፍ እንድፅፍ መነቃቃት የፈጠረብኝ አንድ አስናቀ ተገኝ የተባለ ጎበዝና አወዛጋቢ ሰዓሊ ጋር ተቀምጬ በምወያይበት ወቅት ላይ ነው፡፡


በአንድ ወቅት IOM (International Organization for Migration) የተባለው ተቋም አንድ ፕሮጀክት ነድፎ ነበር፡፡ ይህም ፕሮጀክት የሚያተኩረው ስነ ጥበብን በመጠቀም የአዕምሮ ህሙማን በሽተኞችን ማከም ላይ ነው፡፡ ይህ ተቋም አለምን በዚህ መልካም እቅዱ እየዞረ ሲያድን ከርሞ እኛ ሀገር በመምጣት በስዕል ሙያ ላይ ብቃት ያላቸውን እንደነ አስናቀ ተገኝ፣ ዳዊት ሙሉነህ፣ ዳዊት አድነው፣ ተስፋሁን ክብሩ፣ ቴዎድሮስ በቀለና ሌሎችንም ሰዓሊዎችን ተጠቅሞ በአማኑኤል የአዕምሮ ህሙማን ሆስፒታል ውስጥ ልዩ የስዕል ዝግጅት አድርጎ ነበር፡፡  
በዚህ ብሩክ የሆነ ዝግጅት ላይ ስፋት ባለው ግድግዳ ላይ የተዋበ ስራ ያቀረበው ወዳጄ አስናቀ ተገኝ፣ አንድ አይኑን የሚደማው ብሩሹ ላይ አድርጎ በሌላው አይኑ ባለበት የመመገቢያ አዳራሽ ውስጥ የሚከናወኑትን ነገሮች ሲያጠና ከርሞ ነበር ለካ፡፡ የዛን ቀንም አንድም ሳይሰስት ያየውን በአስደናቂ አተራረክ ተረከልኝ፡፡ ከተለያየን በኋላ ጭንቅላቴ እረፍት አጣ፡፡ እጅግ የሚያሳዝኑም በዛው ልክ ደግሞ እጅግ የሚያስቁ ገጠመኞቹን ሰምቻለሁ…ሆኖም እኔ ከታሪኮቹ ጀርባ ተሰንቅሮ ያለውን…ትውልዴን በአዕምሮ በሽታ የሚያሰቃየው ነገር ላይ ትንሽ ለመመሰጥ ሞከርኩ…ጥቂት አነበብኩ…ይሄ ገባኝ….
የመጀመሪያው የገባኝ ነገር አብዛኛው እብድ እያልን የምንጠራው ሰው ያሳበደው የግል አስተሳሰቡ ሳይሆን የማህበረሰብ ተቀባይነት ማጣትና ሀሳቡን የሚተነፍስበት፣ ጭንቀቱን የሚያቀልበት ማህበረሰብ አጠገቡ ስለሌለው ነው፡፡
መሰማት እንፈልጋለን …ሁላችንም፡፡ ቀኑን ሙሉ የሚሰማንና የሚያደንቀን ካገኘን እድሜ ልካችንን የምናወራ ይመስለኛል፡፡ የማንችለው በአብዛኛው መስማት ነው፡፡ ችግር ህይወታችን ውስጥ መሰንበት ሲጀምር…ከሰው የሚቀላቅለን ሀሳብ ከጭንቅላታችን ውስጥ ተናጥቦ ሲሸሸን…በራሳችን የምንተማመንበት እምነታችንን መሸጥ ሲዳዳን …..አዎ ያኔ መስማት እንጀምራለን፡፡ እያመመንም ቢሆን፣ እያቅለሸለሸንም ቢሆን እንሰማለን፡፡ ለማድነቅ ጉቦ እንፈልጋለን፣ ለመሳቅ ክፍያ ማግኘት ግድ ነው፣ እውነታችንን ለመስጠት ሙስና መቀበላችን የግድ እየሆነብን ነው፡፡
ይህ ሁሉ የማንነት እንግልት ውስጥ ከገባን በኋላ ራሳችንና መከራችን በወለደው ማንነታችን ውስጥ ሆነን…ከዛ የተመረዘ የህይወት ክስተት ጋር ተዳርተን የፈጠርነው ማህበረሰብ ላይ ጣታችንን መቀሰር ያምረናል፡፡ አሁን የደረስንበት መከራ ላይ ለመድረስ ማህበረሰቡ ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ እንደሆነ አድርገን በማይገቡ ድምፆች እንጮሀለን፡፡
መስኮቱን ራሴው ከፍቼው ሳለ እንዴት አድርጌ ንፋሱ ቤቴ ውስጥ ገብቶ እቃዎቼን በጠበጠብኝ ማለት እችላለሁ? ሀላፊነቱን መውሰድ አለብን፡፡ ለማበድ የምንደርገውን ጉዞ ሁላችንም ከመከሰቱ በፊት እናውቀዋለን፡፡ ገና ከርቀት ሲመጣብን ጨለማው ይታየናል፡፡
እንደዛ እንደሚሆን እያወቅን በአጉል አዋቂ ነኝ ባይ ሰበብ፣ በአጉል እኔ ብዙ ስላነበብኩ ከማህበረሰቡ ወጣ ያልኩ ነኝ የሚል ምክንያት፣ በአጉል ውስጤ ፈጣሪ ካልሆነ በቀር ማንም ሊረዳኝ አይችልም በሚል የግል ፍቅር እብደትና ብዙ የሰበቦች ድር ውስጥ ሆነን ከሰብዕ ዘር ራሳችንን ከሰወርን በኋላ ማንም አላየንም እንላለን፡፡ ፈላስፋው ኮንፊሸስ እንደሚለው፤ “ህይወት ስትጀምር ገና በጣም ቀላል ናት፤ እኛ ግን እክሎቻችንን እያደንን ሰብስበን ውስብስብ እናደርጋታለን፡፡”
አንዳንዴ ህይወታችንን አንድ ጥጋት ስር ተቀምጠን ስናሰላስለው፣ ሁሉም ነገር በአንድ ጊዜ የሚታየን ይመስለንና ቅዠቱንም ሆነ የቀን ህልሙን ህይወት እንደሆነ አድርገን እንተረጉመዋለን፡፡ እሱም የመጨረሻው ህይወታችን እንደሆነ ድምዳሜ ውስጥ እንገባለን፡፡ ባደረግናቸውና በተናገርናቸው ነገሮች መጨነቅ ሲገባን፣ እኛን የሚረብሸን የገዛ ተስፋችንና ሀሳቦቻችን ናቸው፡፡ እንዴትና በምን አይነት ምክንያት ያንን ጨለማ ሀሳብ እንዳሰብነው ሳንመረምረው የመጣውን ድንገቴ ሀሳብ በሙላ የግላችን እንደሆነ አድርገን እንመለከታለን፡፡ ከዛም በላይ የሚያስቀው የምናምንበትን ነገር ስናደርግ እንከርምና መጨረሻ ላይ ያስደሰቱንን ነገሮች በሙሉ ሀጥያት ናቸው በማለት ንስሀችንን ስናዥጎደጉድ እንገኛለን፡፡


ከማህበረሰቡ ጋር የገዛ ሀሳቡን ማጣጣም ያቃተው ሰው፣ በዚያ  ሰዓት ላይ የሚሰማውን ሰው ፍለጋ ማሰስ ውስጥ ይገባል፡፡ ህዝቡን በጣም በራቅነው ቁጥር በጣም የጠላነው ይመስለናል፡፡ ሆኖም እስከዛች ቀን ድረስ ስንጠላው የነበረው እነሱ ውስጥ ያየነውን የራሳችንን መልክ መሆኑን ለመረዳት ጊዜ ይወስድብናል፡፡ የምሬን ነው የምላችሁ፣ የራሳችንን ማንነት የማናይበት ነገር ረብሾን አያውቅም፡፡ ለዛም ነው የምናስበው፣ ሀሳብ ራሳችንን ለመለወጥ ሳይሆን እንዴት አድርገን ራሳችንን መፍጠር እንደምንችል ለማወቅ የሚደረግ መንገታገት መስሎ ነው የሚሰማኝ፡፡
ራቢንድራናት ታጎሬ እንዲህ ይላል፤ “We read the world wrong and say that it deceives us.”
የምርም የከበበን ማህበረሰብ የምናወራው የማይገባው ከሆነ ዝም እንበል፡፡ እንጠብቅ፡፡ ለሁሉም ጊዜ አለው የሚለውን አመለካከት ለጊዜውም ቢሆን ወደ አላማችን የሚያሻግረን መንኮራኩራችን እንደሆነ ሀሳባችንን ፈትለን እንድረስበት፡፡ አለበለዚያ አይቀርልህም… ይህ ህዝብ ያሳብድሀል፡፡ ፈልጎትም ላይሆን ይችላል፡፡  አቀውሶ ይሸሽሀል፡፡ ሸሽቶ ያማሀል፡፡ አምቶ ሞትህን ይመኝልሀል፡፡ ምን እንደገደለህ ሳታውቅ በህይወት እያለህ በቁምህ ነፍስህ መሞቷን እዛው ታረዳሀለች፡፡
በቁም መሞት ውስጥ ያለውን እኔነትህን ማንም በማይረዳው እውቀትህ ውስጥ ሆነህ አለምን ትራገምበታለህ …እንዲህ እያልክ…
I am so tired of waiting,
Aren’t you,
For the world to become good
And beautiful and kind?
Let us take a a knife
And cut the world in two-
And see what worms are eating
At the rind.  
“You can ignore the reality, but you cannot ignore the consequences of ignoring that reality.”  
ለማንኛውም አብደን ስለምናሳብደው…ስለኛ አይነቱ እብዶች ይህን ካልኩኝ አሁን ደግሞ መሀይምነቱና ጥልቅ የሆነ የተፈጥሮም ሆነ ማህበራዊ ህይወት ቀመር ያልገባው ህዝብ እንዴት አድርጎ አንድ ግለሰብ ላይ የማሳበጃ ቀንበሩን እንደሚጭንበት በጥቂቱ ልዳስስ፡፡
Helene Cixous በተናገረችው ንግግር ይህ ሀሳብ እንጀምረው፤ “people do not see you, they invent you and accuse you.” በቀጥታ ትርጉሙ፤ ሰዎች ማንነትህን አያዩትም፤ ራሳቸው ፈጥረውህ ራሳቸው ይከሱሀል የሚል ሀሳብ እናገኝበታለን፡፡
አሁን አብረነው ያለነው ህዝብ (ደግሞ ሁሉንም አላልኩም) በመጀመሪያ ትምህርት ቤት እያለ፣ በቅዱስ ስፍራዎች እያለ፣ በማህበራዊ ህይወት እያለ በህግ ጠፍንጎ… ያሳደገን እየመሰለው ወደ ፍርሀታችንና ድክመታችን ድረስ ሲስበን ይከርማል፡፡ በዛ እውቀታችን ተመርተን እንደምንም ብለን አዲስ ሀሳብ ለማምጣት ስንሞክር ሲያመው እናያለን፡፡ ባህላችን መልካም ሆኖ ሳለ (አንዳንዱ ሰይጣናዊ ባህሪም ቢላበስም ቅሉ) ከአለም የእውቀት እድገት ጋር አብረን መራመድን አንፈልግም፡፡ ከዚህ ሀገር ውጭ ያለው የሰው ፍጥረት በሙላ ሌላ ፈጣሪ የፈጠረው ነው የሚመስለን፡፡ በዝና ብቻ የምናድግ ይመስለናል፡፡ ተመሳሳይ ታሪክ በየቀኑ ለልጆቻችንና ለልጅ ልጆቻችን እየጋትን፣ አዲስና የተለየ ትውልድ እንዲመጣ   እንፀልያለን፡፡
እንደ ማህበረሰብ የምናሳብድ ፍጥረቶች ነን፡፡ አንድ ሰው ከኛ ጋር ለመቀላቀል ቢፈልግ በግዴታ እኛን መስሎ መኖር እንዳለበት ነው የመጀመሪያ ህግ አድርገን የምንሰጠው፡፡ ሆኖም እንኳ እኛን መስሎ፣ አብሮን የምንተነፍሰውን ቢተነፍስ እንኳ እኛ ከዛን ቀን ጀምሮ እንደረሳነው አያውቅም፡፡ ያም ሰው እድሜውን ግራ እንደተጋባ ኖሮ ይሞታታል፡፡ ጋሽ ቦካውስኪ አንድ ጊዜ እንዲህ ብለው ነበር፤ “...አንዳንዶች መላው አዕምሮዋቸውን ስተው ሙሉ ነፍስ ብቻ ይሆናሉ…ጤነኞች ይባላሉ፣ አንዳንዶች መላው ነፍሳቸውን አጥተውት አዕምሮ ብቻ ይሆናሉ…አዋቂዎች ይባላሉ፡፡ ሆኖም አንዳንዶች ሁለቱንም ያጡና በማህበረሰቡ ውስጥ ተቀባይነትን ያገኛሉ፡፡”
አንደኛዬን በግልፅ ልናገረውና ሀሳቤን ልፈፅም፡፡
እኛ ኢትዮጵያዊያኖች የምናሳብድ ፍጥረቶች ነን፡፡ እንዴት እስካሁን አብረን እንደቆየን ይገባኛልም አይገባኝምም፡፡ የሚበልጠን አንፈልግም፡፡ የሚረዳንን ጅል አድርገን የምናይ፣ አንገቱን በአክብሮት የደፋልንን በንቀት ሰደፋችን ማንነቱ ድረስ ገብተን የምንቆራርጥ፣ አዲስ ሀሳብ ሲመጣ እውቀታችንን ለማግዘፍ ስንል ጊዜያዊ ንዝረት ውስጥ የምንገባና አዲሱን ሀሳብ ስናጠፋው ቁጭትን እያጣጣምን የምንቆጫት ባለ ቀዥቃዣ ሀሳብ ባለቤቶች ነን፡፡
እኛ የምንፅፍ ሰዎች…እኛ የቀለም ብሩሽ ላይ ነፍሳችንን የምናንሳፍፍ ፍጡሮች…እኛ የዲጂታል አለም እውቀት ሊቆች…እኛ የቀን ሰራተኞች…እኛ እብድ የምትሉን…እናንተን የምንመስለው እኛ …አሁንም ቢሆን ትግላችንን አናቆምም፡፡
ሀሳብ የሚዘምንበት ዘመን እስኪመጣ፣ የሚያደምጥ ነፍስ ያለው እስኪፈጠር ድረስ፣ የሚያደንቅ ትውልድ እስኪከበን፣ እስክንታይ ድረስ…ማሰብ ወንጀል ነው እስኪሉን ድረስ ወደ ፊት እንሄዳለን፡፡
ሆኖም አሁንም ቢሆን መናገር የምፈልገው ነገር፤ እስካሁን እብድ እያላችሁ የምትጠሩትን ሰው ቀረብ ብላችሁ አድምጡት፡፡ ባይገባችሁም አዳምጡት፡፡ ለራሳችሁ ስትሉ ሳይሆን ለሱ ስትሉ ቅረቡት፡፡ በአማኑኤል የአዕምሮ ሆስፒታል ውስጥ ኮቴያችሁን አስገብታችሁ ስራዎቻቸውን ተመልከቱላቸው፡፡ እጅግ ትደነቃላችሁ፡፡ አትሽሹ፡፡


ሁሉም ነገር አልቆ፣ እነዛ ምስኪን ሰዎች የምድርን ቅጥር በሞት ጠርምሰውት ወደ እረፍታቸው ሲያገድሙ ያኔ መስጠት የምትችሉት ነገር በጣም ቀላል እንደነበር ትረዳላችሁ፡፡ ትንሽ ፈገግታ፣ ትንሽ ፍቅር፣ ትንሽ አክብሮት፣ ትንሽ ሰላምታ…ትንሽ፡፡
አይኖቻቸው ላይ የተፃፈውና የተሳለው ስዕል “ውደደኝ አላልኩህም…መውደጃዬን መልስልኝ፡፡ ድጋሚ ልውደድ፡፡” እንደሚል ስትረዱት ትልቅ ያላችሁት ትንሹ ፈገግታችሁ ሰው ሲሰራ ትደርሱበታላችሁ፡፡ እብደት እኛ የምንሰጠውም የምንቀበለውም ነገር እንደሆነ አምናችሁ፣ ሁሉም ነገራችሁ ውስጥ ምክንያቶቻችሁን ለማሰስ ሞክሩ፡፡
አሁን ሁላችንም ከፍቶናል፡፡
ይመስለኛልም ያላበዱት የተወሰኑት ናቸው፡፡
ይህ ከሆነ ዘንዳ እብደቶቻችንም ውስጥ ሆነን ቢሆን ሰው የሚያስብለንን ምክንያት እናስስ፡፡
የዳንኤል ሴንትን የምወድለትን ንግግር ጋብዤ እኔም ጤንነቴን ላስስ፡፡
“I have both madness and reason eternally warring inside my head, because of this, at times, my reasoning is mad and my madness has reasons.”

Read 924 times