፨ ከዓለማየሁ ገላጋይ ‹ውልብታ› ስድስት ዓመት በኋላ በሀይሉ ገብረእግዚአብሔር (ሁምናሳ ገርቢቸ ረቢ) የማምሻ ውልብታዎችን ይዞልን መጣ። በ220 ገጽ ወደ 260 የሚጠጉ ወጎችን ሳቅን ለውሶ አቀረበልን። ‹‹ማምሻ ግሮሰሪ›› በሚል የተከፈተው የፌስቡክ ገጽ ላይ ያቀርባቸው የነበሩ ጽሑፎችን ‹ለሌላው ኅብረተሰብም ይደርስ ዘንድ ተመርጠውና ብርቱ ማስተካከያ ተደርጎባቸው› በአንድ ተጠረዙ። ዓለማየሁ ገላጋይ እንደሚለው፤ ዘመን የሚፈጥራቸው ቀልዶችና ምጸቶችን ሰብስበን ማስተላለፍ ወደፊት ዘመኑንና ህዝቡን እንድንረዳ ያስችላል። የማምሻ ወጎች በኃይሉ እንደ ታገል ሰይፉ ‹ዝንቡላ እና ካሮት›፣ እንደ ዓለማየሁ ገላጋይ ‹ወሪሳ› ሳቅን ለውሶ ሀዘንና ምሬታችንን ያቀረበልን፤ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ኂስ ነው። Birth of Tragedy ላይ ኒቼ እንደሚለው፤ ‹‹ሐዘንና መከራን የቀልድ መነሻ ማድረግ ያስፈልጋል፤ ካልኾነ ማበድ ይከተላልና።››... ሩሲያዊው ደራሲ አንቷን ቼኾቭም፤ ‹‹እንድቀልድና እንዳሽሟጥጥ ያደረገኝ የሐዘን መናኸሪያ መኾኔ ነው።›› ይላል። ሁምናሳም ሀዘንና ምሬቶቻችንን በመጠጥ ቤት አስተናጋጅነቱ ከተለያዩ ሠዎች የታዘበውን ያቀርብልናል። እንደዚህ ዓይነት ‹ወጎችን› መርምረን አይተን ዘመናችንን እንገነዘባለን። ‹ኢህአዴግን እከስሳለሁ› ላይ ዓለማየሁ ገላጋይ ‹‹ጥርስን ከመገሽለጥ ባለፈ የቀልዱን መሪር ዕውነታ ፈልፍሎ የሚያወጣና የቅሬታ ምርቱን የሚፈትን ህዝብ ማስፈለጉ የግድ ነው።›› (95) ይለናል።
፨ ሁምናሳ፤ የሰካራም፣ አስከሬን፣ አመንዝራ የሚሉ ስያሜዎች ከየት እንደመጡም ይነግረናል። ምን ስለ እኛ የማይነግረን ነገር አለ? ጥርስ የማያስከድኑ ወጎቹ ኅብረተሰባችንን፣ መንግሥታችን፣ ፖለቲካችንን፣ አስተሳሰባችንን ይወቅሳሉ (መብራትና ውኃ ኃይሎችም አይቀሩ)። ከሳቅን በኋላ ነው ሕመሙን የምንረዳው፤ ደግመን የምናነበውም። ሕመሙ ሲሰማን ስህተቶቹ እንዲሻሻሉ እንጥራለን። ‹‹በቀልድ ክንብንብ ውስጥ ያለው ማኅበረሰባዊ ሽሙጥ ስህተቶችን ለማረም እንደ ዓይነተኛ ጉዳይ ቦታ ያገኛል።›› (ኢህአዴግን እከስሳለሁ፣ 93)...
‹‹ መኖርም መሞትም የከበደብሽ፤
የነንጠቅ አገር ጦቢያ እንዴት ነሽ!?››(40)...፣ ‹‹እዚኽ አገር ፈጣሪ ሊጠብቅ ያልቻለው ወንድሙን ከወንድሙ ጥቃት ነው።››... እያለን ቆም ብለን እንድናስብ ያስታውሰናል።
፨ ከሁምናሳ ውልብታዎች ሀገራችንንና ፖለቲካችንን በምጸት የገለጸበትን ሦስት አራት እንጥቀስ፦
ቢራ በሳጥን የሚገዛ ደንበኛችንን፣ ጠርሙሱን በአግባቡ እንዲመልስ ሙሉ ስሙን ወረቀት ላይ እየመዘገብኹ ነው፤
‹‹ስም ማን ልበል?››
‹‹ፍርድ ያውቃል!››
‹‹ፍርድ ያውቃል ማን?››
‹‹ፍርድ ያውቃል መንግሥቱ››
‹‹ምን?››
‹‹ፍርድ ያውቃል መንግሥቱ››
‹‹እሺ! ... ዜግነት!››
‹‹ኢትዮጵያዊ!››
በ ለ ው! ... ይኼን የካድሬ ስም ደኅና አድርገኽ ተሸክምኸዋልና! (17) ፤
‹‹ለመንግሥቱ ፍጻሜ የለውም!›› በማለት ጮኽ ብዬ ስጸልይ ጥግ ተቀምጦ ድራፍት የሚጠጣው ዐዲስ ምልምል ካድሬ፣ ምራቁን በጉምዥት ገርገጭ አድርጎ ፈገግ ብሎ ያየኛል፤ ‹‹ልክ ብለኻል!›› ዐይነት።
‹‹ይቅርታ ወንድሜ፤ እኔ ‘ለመንግሥቱ ፍጻሜ የለውም!’ ያልኹት ትናንትም ዛሬም፤ በቸርነቱ እያኖረኝ ያለውን፣ የላይኛውን ነው። ... ትልቁን! ... እጅግ በጣም ትልቁን! ... ሰማያዊውን! ... ያንተን መንግሥት አይደለም! ... ሆ!›› (18)፤
ሞቅ ብሏታል። ግራ ክንዷን እየቆነጠጠች፣ “እሰይ ኤታባቱ!” ትላለች። አብራት ወደ ምትጠጣ ጓደኛዋ ጠጋ አልኹና፣ “ተዪ በያት እንጂ! ራሷን እየጎዳች እኮ ነው!” አልኋት።
“ተወው! ኤታባቱ! ይገባዋል!” አለች ጓደኛዋም።
“ማን ነው እሱ!”
“ልጁ?”
“የቱ ልጅ?”
“ግራ ክንዷ ላይ ስሙን የተነቀሰችው ልጅ!”
በ ለ ው! ... ግዴላችኹም ይኼ የበቀል መንፈስ እንደ አገር እየጎዳን ነው ! (118) ፤
ደንቦች ከፖሊሶች ጋር መጥተው ግሮሰሪያችንን ዙሪያዋን ዐይተዋት በመኼዳቸው ብዙ ደንበኞቻችን፣ ‹‹ሊያፈርሱብን ይኾን?›› ብለው ሲጨነቁ ዐየኹ።
ውድ ደንበኞቻችን ግሮሰሪያችን አትፈርስም። ምክንያቱም ቤቱ ቅርስ አይደለማ፤ አገራዊ ፋይዳ ያለው አይደለማ።(44)
፨ ማኅበረሰባችን ጋ ሲመጣም
‹‹ሐበሻ መርዝ ነው!›› አለ ጮኽ ብሎ። ... ዝም አልኹት፤ ‹‹ሐበሻ መርዝ ነው!›› አለ በድጋሚ።
ጨምድዶ እንዲያስወጣው ለጥበቃው በጥቅሻ ነገርኹት፤ ‹‹አስወጣው! ገበያ እያበላሸ ነው።››
ሰውዬው ተንጠልጥሎ ሲወጣ እንዲኽ በማለት እየጮኸ ነበር፤ ‹‹እባካችኹ ልቀቁኝ፤ ልቀቁኝ! ... ቢራውን እኮ አይደለም ያልኹት!››
‹‹ታዲያ እንደሱ አትልም! ... በል ልቀቀው!››(41)
‹‹ኹሉም ሃይማኖቶች ሰላምን ይሰብካሉ፤ ፍቅርን ይሰብካሉ፤ እርስ በርስ ተከባብሮ መኖርን ይሰብካሉ፤ ....›› ሲል ሰማኹት አንዱን በቴሌቪዥን።
ተንኮለኛ! ‹‹እዚህ አገር ሃይማኖትም ሃይማኖተኛም የለም!›› ለማለት ፈልጎ እኮ ነው። (57)
፨ ‹እንደዚህ ኾነናል፣ እዚህ ደርሰናል›.. ሊለንም፤ በስካር አሳብቦ
‹‹ግራ ገባን እኮ! ... የግሮሰሪውን የቴሌቪዥን “ሪሞት” ይዘኽ የኼድኸው ሰውዬ፣ ሞባይልኽን ጥለኽ ኼደኻል።››(18)... ፤
ዛሬ የምር ሰክሬያለኹ። ፊት ለፊት እያየኹ፤ ‹‹እንዴት ወፍሬያለኹ፤ እንዴትስ አምሮብኛል! ጺሜን እንዲኽ በቄንጥ የተላጨኹት መቼ ነው?›› እያልኹ ራሴን ሳደንቅ፣ ፊት ለፊቴ የቆመ ሰውዬ፤ ‹‹ መንገድ ዘግተኽ ምን ታፈጥብኛለኽ!? አሳልፈኝ እንጂ!›› አላለኝም። ‹‹ኦ! ይቅርታ! ሌላ ሰው ነኽ እንዴ!››...(69).... ይለናል።
፨ አንብበን ስንጨርስ ‹ለካ እንደዚኽ ነን?› ብለን እንጠይቅና፤ ‹‹አማን አውለኝ ጌታዬ!›› ብለን እንማፀናለን።
፨ በመጨረሻ ሁምናሳን አመስግነን፤
ከተናግሮ አናጋሪ፤ ከሐሰት መስካሪ፤
ከሌሊት ወራሪ፤ ከቀን አባራሪ፤
ከብር አጭበርባሪ፤ ከሳይጠጣ ሰካሪ፤
ከጸብ አጫሪ፤ ከሳይመቱት እሪ፤
ከፖለቲካ አውሪ፤ ከነገር መሰሪ፤
ከልብ አውላቂ፤ ከዱቤ ጠያቂ፤...
ሰባ፣ ረባ፣ ወጣ፣ ገባ፣ ኼደ፣ ነጎደ፣ ከሳ፣ አገሳ፣..
(10)... ከሚሉት ጠብቀው እንላለን።
Saturday, 09 November 2024 13:31
የሁምናሳ ውልብታዎች
Written by ነቢል አዱኛ
Published in
ጥበብ