Saturday, 09 November 2024 13:41

የሥራ ትውውቅ

Written by  ደራሲ፡- ዳንኤል ኦሮዝኮ ተርጓሚ፡- ኢዮብ ካሣ
Rate this item
(2 votes)

አዲሱ ሰራተኛ ወደተቀጠረበት መሥሪያ ቤት ሲያመራ ሁለት ልብ ነበረ፡፡ በአንድ በኩል ከብዙ ተወዳዳሪዎች ውስጥ እሱ በመመረጡ እየተደሰተ፣ በሌላ በኩል የሙከራ ጊዜውን በስኬት ይወጣው እንደሆነ እያሰላሰለ ደረሰ - አዲሱ መ/ቤት፡፡ የዛሬ የመጀመሪያ ተግባሩ የሚሆነው የቢሮ ጉብኝትና ትውውቅ  ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የተመደበለት ሠራተኛ አለ፡፡
”እነዚያ ቢሮዎቻችን  ሲሆኑ፤ እነዚህ  የምንሰራባቸው ክፍሎች ናቸው፡፡ የኔ ክፍል እዚያ  ጋ  ነው፡፡ የአንተ ደግሞ ይሄኛው ነው፡፡ ይኼ ያንተ  ስልክ  ነው፡፡ ስልኩን ማንሳት አይጠበቅብህም፡፡  በቮይስ ሜይል ራሱ መልስ ይሰጣል፡፡ የቮይስ ሜይሉ ማኑዋል እነሆ፡፡ የግል የስልክ ጥሪ ማድረግ አይፈቀድም፡፡ ድንገተኛ የስልክ ጥሪ ማድረግ ግን ይቻላል፡፡ ታዲያ በመጀመሪያ ለአለቃህ ማሳወቅ አለብህ፡፡ አለቃህ ከሌለ እዚህ ጋ የሚቀመጠውን ፊሊፕ ስፒርስን ታስፈቅዳለህ፡፡ እሱ እዚያ ማዶ ለተቀመጠው ለክላሪሳ ኒክስ ያስፈቅዳል፡፡ ሳታስፈቅድ ድንገተኛ ጥሪ ካደረግህ ግን ከሥራ ልትባረር ትችላለህ፡፡
“ሥራህን ምንጊዜም በ8 ሰዓት  ውስጥ ማጠናቀቅ አለብህ፡፡ አልገባኝም ነው ያልከኝ? ጥሩ፤ ላብራራልህ፡፡  ለምሳሌ 12 ሰዓት የሚፈጅ  ሥራ ተከምሮብሃል እንበል፣ ያንን ሥራ እንደምንም ጨምቀህ በ8 ሰዓት ውስጥ ፉት ማለት አለብህ፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ የአንድ ሰዓት ሥራ ብቻ ነው ያለብህ እንበል፡፡ ይኼን ሥራ ለ8 ሰዓት አከፋፍለህ ስትሰራ መዋል ነው፡፡ ጥያቄ መጠየቅህ ይበረታታል፡፡ ጥያቄ ለመጠየቅ  ፈጽሞ ወደ ኋላ አትበል፡፡ ነፃ ሁን፡፡ ጥያቄዎችህ ካለቅጥ ከበዙ ግን ከሥራ የመባረር እጣ ሊገጥምህ ይችላል፡፡
“ያች እንግዳ ተቀባያችን ናት፡፡ ጊዜያዊ ቅጥር ነች፡፡ እንግዳ ተቀባዮች እዚህ ቤት አይበረክቱም፡፡ ቶሎ ቶሎ ይለቅቃሉ፡፡ እነሱን በትህትና እና በእንክብካቤ ልንይዛቸው ይገባል፡፡ ስማቸውን ማወቅና አልፎ አልፎ ምሳ መጋበዝም ይኖርብናል፡፡ ነገር ግን ብዙም አትቅረባቸው፣ ምክንያቱም ሲለቁ የሚቸገሩት እነሱው ናቸው፡፡ መልቀቃቸው ደግሞ አይሬ ነው- ስለእሱ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ፡፡
“የወንዶች የመፀዳጃ ክፍል እዚያ ጋ ነው፣ የሴቶቹ እዚህ ነው፡፡ በዚያ ክፍል የተቀመጠው  ጆን ላፎንቴን፣ አልፎ አልፎ የሴቶቹን ክፍል ይጠቁማል፡፡ ሁልጊዜ ታዲያ ተሳስቼ ነው ይላል፡፡ ተሳስቶ እንዳልሆነ ብናውቅም ዝም ብለን እናልፈዋለን፡፡ ወደተከለከለው የሴቶች ክፍል የሚገባው ከደብዛዛው ልሙጥ የህይወት መስመር ቅንጣት ታህልም ቢሆን ለመገላገል ሲል ነው፡፡
”ከአንተ በስተግራ ያለው ክፍል የተቀመጠው ሩሴል ናሽ፣ በስተቀኝ ባለው ክፍል ከተቀመጠችው አማን ፒርስ ጋር በፍቅር ከንፏል፡፡ ከሥራ በኋላ በአንድ አውቶቡስ ተሳፍረው ይሄዳሉ፡፡ ለሩሴል ናሽ፣ ይህ ጉዞ የቀኑ ትልቁ ተግባሩ ነው፡፡ የህይወቱ ትልቅ ተግባር ነው ማለትም ይቻላል፡፡ ለአማንዳ ፒርስ ግን ረዥምና አድካሚው ጉዞ በእሱ ወሬ ትንሽ ከመቃለሉ ውጪ ሌላ ፋይዳ የለውም፡፡ ሩሴል ናሽ 40 ኪ.ግ ክብደት ጨምሯል፡፡ በወር በወር ክብደቱ በፍጥነት እያሻቀበ ነው፡፡ ሁልጊዜ  አማንዳ ፒርስ ወደተቀመጠችበት እያጮለቀ የድንች ጥብሱን ያሻምዳል፡፡ ማታ ደግሞ ቲቪው ላይ አፍጥጦ ቀዝቃዛ ፒዛውንና አይስክሬሙን ይጎሰጉሳል፡፡
“በስተቀኝህ ባለው ክፍል ውስጥ ያለችው አማንዳ ፒርስ፣ ጃሚ የተባለ የስድስት ዓመት ልጅ አላት - የአዕምሮ  ችግር አለበት፡፡ ክፍሏ፣ ከላይ እስከ ታች በልጇ ስዕሎች ተሸፍኗል፡፡ በየሁለት ሳምንቱ አርብ አርብ ስዕሎቹን ቦታ ትቀያይራቸዋለች፡፡  ስለ ስዕሎቹ አስተያየት መስጠት እንዳለብህ ታዲያ አትዘንጋ! አማንዳ ጠበቃ ባል አላት፡፡ እሷ ፈቃደኛ ባትሆንም ባሏ በተለያዩ የወሲብ ድርጊቶች ክፉኛ ያሰቃያታል፡፡ ጠዋት ሥራ ስትመጣ ደካክማና ቆሳስላ ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ነገር እንኳ ማወቅ ያለብህ አይመስለኝም፡፡ አደራ ለማንም እንዳታወራ! ካወራህ ግን ሥራህን ልታጣ ትችላለህ፡፡
“ክሩሴል ናሽ ጋር በየቀኑ በአውቶብስ የምትሄደው አማንዳ ፒርስ፣ አልበርት ቦሽ ከተባለ ሰው ጋር ፍቅር ይዟታል - ቢሮው እዚያ ጋ ነው፡፡ አልበርት ቦሽ ግን  አማንዳ ፒርስ ጭርሱን ትዝ አትለውም ፡፡ እሱ እዚያ የተቀመጠችውን ኤሊ ታፐርን ሲወዳት ለጉድ ነው፡፡ ኤሊ ታፐር ግን አልበርት ቦሽን ልታየው እንኳ አትፈቅድም፡፡ እሷ ደግሞ  ኩርቲስ ላንስን ነፍሷ እስኪወጣ  ታፈቅረዋለች፡፡ ክፋቱ ደግሞ ኩርቲስ፣ ኤሊ ታፐርን ሲጠላ ልክ የለውም፡፡ አየህ! ዓለም እንዴት አስቂኝ እንደሆነች!
“የአኒካ ብሉም ክፍል ይሄኛው ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ከቤሪ ሃከር ጋር የሩብ ዓመት ሪፖርት ሊገመግሙ ተቀምጠው  ሳለ የግራ እጇ መዳፍ መድማት ይጀምራል፡፡ የቢሮ መግቢያ በሩ ላይ ወድቃ ነበር፡፡ እጇን ጎንበስ ብላ ተመለከተችና የቤሪ ሃከር ሚስት መቼና  በምን እንደምትሞት ነገረችው - ጠነቆለች ማለት ይቀላል፡፡ እኛ  በሳቅ ፈረስን - ያኔ አኒካ አዲስ ሰራተኛ ነበረቻ፡፡ እውነትም ያለችው አልቀረም የቤሪ ሃከር  ሚስት ሞተች፡፡ አንተም መቼና እንዴት እንደምትሞት ማወቅ  ካልፈለግህ በቀር አኒካ ብሉም የደረሰችበት እንዳትደርስ፡፡
“ኮሊን ሄቪ የሚቀመጠው እዚያ ማዶ ነው፡፡ አንድ ጊዜ እንዲህ እንዳንተ አዲስ ሠራተኛ በነበረ ሰሞን ስለ አኒካ ብሉም አስቀድመን አስጠንቅቀነው ነበር፡፡ ባለፈው የገና  በዓል ብቸኛ መሆኗ አሳዝኖት ነው መሰለኝ መጠጥ ጋበዛት፡፡ ከዚያ በፊት እኮ እሱ ራሱ መጠጥ ቀምሶ አያውቅም፤ ፈርዶበት ከእርሷ ስር አይጠፋም፡፡ እኛም  ምንም ልናደርግለት አልቻልንም፡፡ አንተ ታዲያ ከኮሊን ሄቪ  መራቅ አለብህ፤ ለሱ ምንም አይነት  ሥራ እንዳትሰጠው፡፡ ልስራ ብሎ ከጠየቀህ እንኳ በቅድሚያ እኔን ማማከር እንዳለብህ  ንገረው፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ከጠየቀህ ገና እንዳላገኘኸኝ ነግረህ  ሸኘው፡፡
“ይኼ የእሳት አደጋ መውጪያ ነው፡፡ በዚህ ፎቅ ላይ ብዙ መውጪያዎች አሉ፡፡ ሁሉም ተመሳሳይ ምልክት አላቸው፡፡ እሳት ቢነሳ እንዴት ከፎቅ እንደምንወጣና  መውጪያው በር የቱ እንደሆነ በየሦስት ወሩ ፈተና ይሰጠናል፡፡ ይሄ የሚሆነው ለቅድመ-ጥንቃቄ  እንጂ አደጋው ይከሰታል ተብሎ አይደለም፡፡ አደጋው ፈጽሞ አይከሰትም፡፡
“ለጠቅላላ ዕውቀትህ አጠቃላይ  የጤና ህክምና እንዳለን እንድታውቅ እፈልጋለሁ፡፡ ማንኛውም በአደጋ ምክንያት የተከሰተ ህመም የህክምና ወጪ ሙሉ በሙሉ በድርጅቱ ይሸፈናል፡፡ እዚያ ጋ  የሚቀመጠው  ላሪ የስድስት ሴት ልጆች አባት ነው፡፡ ከሴት ልጆቹ አንዷ ወይ ሁሉም  አደጋ ደርሶባቸው  ቢታመሙ ድምቡሎ ሳያወጣ በድርጅቱ ወጪ ይታከሙለታል፡፡ የጤናን ነገር በተመለከተ ምንም የሚያስጨንቀው ነገር የለም፡፡ የዕረፍት ፈቃዳችንም የተንበሻበሸ ነው፡፡ የህመም ፈቃድ ፖሊሲም አለን፡፡ ድንገት ለሚከሰት የአካል ጉድለት ኢንሹራንስ ገብተናል፡፡ ዳጎስ ያለ የጡረታ ገንዘብም እንሰጣለን፡፡
”ይሄ ወጥቤታችን ነው፡፡ ይሄኛው ደግሞ ቡና መጠጫችን ሲሆን ለቡና፣ ለሲጋራና ለስኳር በሳምንት ሁለት ሁለት ዶላር  እናዋጣለን፡፡ ይሄ የማይክሮዌቭ ምድጃችን ነው፡፡ በምድጃው ውስጥ ምግብ ማሞቅ  ይፈቀድልሃል፡፡ ማብሰል  ግን አይቻልም፡፡
“ለምሳ የአንድ ሰዓት ጊዜ አለን፣ ከሰዓት 15 ደቂቃ እፍት ተሰጥቶናል፡፡ ሁልጊዜ ዕረፍትህን ሳታዛባ  መውሰድ አለብህ፡፡  ተሳስተህ ከዘለልከው ምንጊዜም አታገኘውም፡፡ የፈሰሰ ውሃ ማለት ነው፡፡ የ15 ደቂቃዋ ዕረፍት በጥቅማጥቅምች የምትታሰብ ናት፡፡  የዕረፍት ፖሊሲውን ካዛባህ እረፍት የሚባል ነገር እንዳይኖርህ የማድረግ ስልጣን ተሰጥቶናል፡፡ ይሄ ፍሪጃችን ነው፤ ምሳህን እዚህ ውስጥ ማስቀመጥ ትችላለህ፡፡ እዚያ ክፍል የሚቀመጠው ቤሪ ሃከር፣ የሰው ምሳ ከፍሪጅ ውስጥ በመስረቅ ይታወቃል፡፡ ይሄ ተራ ሌብነት ሃዘኑን ለመወጪያ የሚፈጽመው ሳይሆን አይቀርም፡፡ ባለፈው የአዲስ ዓመት ዋዜማ ከሚስቱ  ጋር ሲሳሳም አንጓሏ ውስጥ አንድ የደም ስር ፈነዳና ታመመች፡፡ ያን ጊዜ ሚስቱ  የሁለት ወር ነፍሰ-ጡር ነበረች፡፡ ለ6 ወር በኮማ ውስጥ ቆይታ ሞተች፡፡ ይሄ ለቤሪ ሃክር አሳዛኝ አጋጣሚ ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሃከር የድሮው ሃከር  አልሆነም፡፡ ሚስት ቆንጆ ነበረች፡፡ የእሷም የህክምና ወጪ ሙሉ በሙሉ የተሸፈነው በድርጅቱ ነው፡፡  ሃከር አንዲት ሳንቲም አላወጣም፡፡ ግን የሙት ሚስቱ መንፈስ ቤሪ ሃከርን እየተከታተለው ተቸግሯል፡፡ እሱን ብቻ ሳይሆን እኛን  ሁላችንንም አልተወችንም፤ ሚስቱ ቢሯችን ውስጥ አትጠፋም፡፡ ኮምፒውተራችን ስክሪን ላይ ድንገት ብቅ ትላለች፡፡ በዴስኮቻችን በኩል ታልፋለች፡፡  ፎቶ ኮፒ ማሽናችንም ላይ  ትታያለች፡፡  የእንግዳ መቀበያ መዝገቡ ላይ “ቤሪ ሃከርን ለማየት መጥቼ ነበር” የሚል ማስታወሻ ጽፋ ትሄዳለች፡፡ ለማንኛውም ምሳ ይዘህ የምትመጣ ከሆነ ትንሽ ነገር ለቤሪ  ጨምረህ አምጣ፡፡ የሚገርምህ ደግሞ እዚህ ቢሮ  ውስጥ አራት ቤሪዎች  አሉ፡፡


“ይኼ የማቲው ፓይኔ ቢሮ ነው፡፡ ሥራ አስኪያጅ ነው፡፡ ታዲያ ሁልጊዜ በሩ እንደተቆለፈ ነው፡፡ ፈጽሞ አይተነው አናውቀም፡፡ አንተም ፈጽሞ  አታየውም፡፡ ግን እዚህ ነው ያለው፡፡ እዚህ ስለመኖሩ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ፡፡ እሱ በሁላችን ዙሪያ አለ፡፡
”ይኼኛው ደግሞ የጥበቃው ክፍል ነው፡፡ እጥበቃ ክፍል ምንም የምትሰራው ነገር ስለሌለ ማወቅ አያስፈልግህም፡፡ የንብረት ማውጪያ  ካቢኔቱ ይኸውልህ፡፡ የምትፈልገው እቃ ካለ መጀመሪያ  ኩርቲስ ሌንስ ጋ ትሄዳለህ፡፡ እሱ የንብረት ማውጭያ መዝገብ ላይ ይመዘግብህና የንብረት  መቀበያ ፈቃድ ይሰጥሃል፡፡ ሃምራዊውን ደረሰኝ ለኤሊ ታፐር ትሰጣለህ፡፡ ከዚያም የግምጃ ቤቱን ቁልፍ ይሰጥሃል፡፡ ግምጃ ቤቱ የሚገኘው ከሥራ አስኪያጁ ቢሮ አጠገብ ስለሆነ ድምፅ ማሰማት የለብህም፡፡ በጸጥታ የምትፈልገውን ሰብስበህ መውጣት ነው፡፡
“እዚያ ማዶ የተቀመጠው ኬቪን  ሄዋርድ የለየለት ነፍሰገዳይ ነው፡፡ በመላው ከተማው ብዙ ሰዎች እየቆራረጠ የሚጥለው እሱ ነው፡፡ ይሄን እንኳ ማወቅ ያለብህ አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ትንፍሽ እንዳትል፡፡ አይዞህ አትፍራ! ጥቃት የሚሰነዝረው እኮ እንግዳ ሰዎች ላይ ብቻ ነው፡፡ የጥቃት ሰለባው   ወንድ ፈረንጅ መሆን አለበት፡፡ አዋቂ፣ ዕድሜው  ከ30  ያልዘለለ፣ ግድንግድ፣ ጥቁር ፀጉር፣  ጥቁር ዓይንና የመሳሰሉት ያለው፡፡ የሚገድለውን ሰው  ፀሃይ ከመጥለቋ በፊት በአደባባይ በዘፈቀደ ይመርጣል፡፡ ከዛ ሰውየውን ቤቱ እየተከተለው ይሄድና ከታገሉ በኋላ ይገድለዋል፡፡  ኬቪን፤ ይሄን ተግባር  ከመደበኛ ሥራው ጋር አይደባልቅም፡፡ በዚህ ቢሮ ፈጣኑ ታይፒስት እንደውም እሱ ነው፡፡


”ይሄ ፎቶ ኮፒ ማድረጊያ ክፍል ነው፡፡ እዚህ ሆነን ውጭውን በደንብ መቃኘት እንችላለን፤ ጥሩ ትእይንት አለው፡፡ በዚህ በኩል የደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ ነው፡፡ የምዕራብ አቅጣጫ እዚያ ታች ነው -  ወደ ውሃው፡፡ ሰሜን ከኋላችን ነው፡፡ ሰባተኛ ፎቅ ላይ  ስለሆንን ድንቅ የሆነ ትእይንት ተችረናል፡፡ ውብ አይደለም? ቢሮአችን እነዚያ የዛፍ ቅርንጫፎች በሚታዩበት መናፈሻ በኩል መሆኑ ድንቅ ነው፡፡ እዚህ ቆመህ የእነዚያን ሁለት ህንጻዎች ከፊል አካል ማየት ትችላለህ፡፡ በእነዚህ ሁለት ፎቆች  መካከል ባለው ክፍተት ፀሃይ ስትጠልቅ ማየትም ትችላለህ፡፡
“ይሄን ፎቅ እዚያ ማዶ ባለው ፎቅ  መስተዋት ውስጥ ተንፀባርቆ ታያለህ፡፡ አየኸው እዚያ ማዶ አንተ’ኮ ነህ፤ እጅህን ስታወጣው የምትታየው፡፡ ተመልከት እንደገና… አኒካ ብሉም ከወጥ ቤት ሆና እጇን ስታወዛውዝ፡፡
”በዚህ ትእይንት እየተዝናናህ ፎቶ ኮፒ ማድረግ ትችላለህ፡፡ የፎቶ ኮፒ ማሽኑ ካስቸገረህ ለሩሴል ናሽ ንገረው፡፡ ማንኛውም ጥያቄ ሲኖርህ ተቆጣጣሪህን ጠይቅ፡፡ ተቆጣጣሪህ ከሌለ ፊሊፕ ስፒርስ አለልህ፡፡ እዚያ ጋ ነው የሚቀመጠው፡፡ እሱ ከክላሪሳ ኒክስ ጋር ይመክርበታል፡፡ እሷ ደሞ እዚህ ጋ ነው የምትቀመጠው፡፡ ሁለቱም ከሌሉ እኔ አለሁኝ፤ ከመጠየቅ ወደ ኋላ አትበል፡፡ የኔ ክፍል እዚያ ጋ ነው -እዚያ፡፡  አሁን ሥራህን መጀመር ትችላለህ፡፡”
(ምንጭ፡- ከአዲስ አድማስ የካቲት 4 ቀን 1998 ዕትም ላይ የተወሰደ)

Read 279 times
More in this category: « ፈጣጣው