Monday, 11 November 2024 00:00

ተዋት ትኑርበት!

Written by 
Rate this item
(3 votes)

(ስለ እጅጋየሁ ሽባባው ክብር የተጻፈ)

አብርሀም ገነት


ያን ሰሞን በልቦናዬ የሚመላለሱት የእጅጋየሁ ሽባባው ዘፈኖች ነበሩ፡፡ ሳልሰለች ዘፈናቸውን በተደጋጋሚ ከምሰማቸው አርቲስቶች አንዷ እጅጋየሁ ናት፡፡ ዛሬም፡፡ አርቲስት ብዬ በሙሉ ልብ ከምጠራቸው በዘመኔ ከማውቃቸው ኢትዮጵያውያን አንዷ ጂጂ ናት፡፡ ለእኔ አርቲስት የሚያስተጋባ ሳይሆን የሚፈጥር ነው፡፡
ቀኔን እንዳዋዋሌ ውዬ፣ ራቴን በልቼ ወደ መኝታዬ እሄዳለሁ፡፡ ከመተኛቴ በፊት ግን አንድ ሁነኛ ነገር ይቀረኛል፡፡ እሱም ልብሴን አወላልቄ አልጋዬ ውስጥ ገብቼ አንድ ሁለት የጂጂን ዘፈኖች አይኖቼን ከድኜ መስማት ነው፡፡ ያን ሰሞን፡፡ የጂጂን ለስላሳና አባባይ ዘፈኖች አይኖቼን ጨፍኜ ስስማ ነፍሴ ወደሆነ አለም ትንሳፈፋለች፡፡ ያለሁበትን እረሳለሁ፡፡ ለደቂቃዎች ከገላዬ ተነጥዬ ነፍስና ምናብ እሆናለሁ፡፡ ጠዋት ተነስቼ አልጋዬን እያነጣጠፍሁ ቀኔን ስጀምር የማፏጨው ከጂጂ ዘፈኖች አንዱን ነው፡፡ የጂጂ ግጥሞች ውብ ናቸው፣ ዜማዎቿ ረቂቅ፡፡ ድምጿ ነፍስን ይዳብሳል፡፡ ጂጂ ጥልቅ ናት፡፡ ብርድልብስና ጨለማ ተከናንቤ አይኖቼን ከድኜ ዘፈኖቿን ስሰማ ፍፁም ፍስሃ ውስጥ እገባለሁ፤ አንዳንዴ የዘፈኑን ምት ተከትዬ በተኛሁበት ገላዬን እየሰበቅሁ በለሆሳስ እደንሳለሁ፤ አንዳንዴ እንባ ከአይኔ ኮለል እያለ በፀጥታ ላለቅስም እችላለሁ፡፡ ነፍሴ በሁሉም ትረካለች፡፡ በዚህኛው እንደዚህ በዚያኛው እንደዚያ እሆናለሁ ብዬ ዘፈኖቹን የማልጠቅስላችሁ የቱን አንስቼ የቱን እተዋለሁ ብዬ ነው፡፡ የምናውቅ እናውቃለን፣ ዝም ብሎ ማጣጣም ነው፡፡ የጂጂ ዘፈኖች ለጆሮና ለነፍስ የተሰሩ ናቸው፡፡ የሙዚቃ ባለሙያው ሰርፀ ፍሬስብሀት አንድ ጊዜ፤ “ሙዚቃ በመሰረቱ የጆሮ ነው” ሲል ሰምቼዋለሁ፡፡ በደንብ እስማማለሁ፡፡
የሆነ ጊዜ ስለ ጂጂ ከሙዚቃው አለም መጥፋት ሰዎች በዩቲዩብና በማህበራዊ መገናኛዎች እየተቀባበሉ ሲያወሩ ሰማሁና ስለ እሷ የበለጠ ለማወቅ ፈለግሁ፡፡ በሬዲዮና በምስል ያደረገቻቸውን ጥቂት ቃለ መጠይቆች ሰማሁ፡፡ በደንብ የሰማሁት ሸገር ሬዲዮ ላይ ከመአዛ ብሩ ጋር ያደረገቺውን ቃለ መጠይቅ ነው፡፡ የጂጂን ማንነት መዘንሁ፡፡ ጂጂ ጎበዝ አርቲስት ብቻ ሳትሆን ማራኪ ሰብዕና ያላት ሴት ሆና አገኘኋት፡፡ ጂጂ ትሁት ናት፣ ምርጥ ምርጥ ስራዎችን ብትከይንም ራሷን ከፍ ከፍ አድርጋ አትኩራራም፡፡ ራሷን ከሌሎች ብቁ አርቲስቶች አንፃር ዝቅ አድርጋ ነው የምታቀርበው፡፡ አስቴር አወቀን ታደንቃለች፡፡ ከማሪቱ ለገሰ ጋር ብትዘፍኝስ ስትባል፤ “ውይ ድምጥማጤን ነው የምታጠፋው!” አለች፡፡ ይሄን ይሄን ስሰማ ጂጂን በዘፈኗ ብቻ ሳይሆን በሰብዕናዋም ወደድኳት፡፡
ጂጂ አሁን መዝፈን ከተወች ረጅም ጊዜ ሆኗታል፡፡ ጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳልሆነች ሰዎች ሲናገሩ እንሰማለን፡፡ አንዳንዶች ደግሞ አሜሪካ ቤቷ ድረስ እየሄዱ እያገኟት ቆይታቸውን በምስል ቀርፀው ዩቲዩብ ላይ ሲለቁ አያለሁ፡፡ የእውነት ለጂጂ አስበውላት ይሆን ወይስ አጋጣሚውን ተጠቅመው ራሳቸውን ለማሳወቅ? ወይም ለመሸቀል? እሷስ በዚህ ደስተኛ ናት? እድሜ የማይድጠው፣ ጊዜና ሁኔታ የማያነሳውና የማይጥለው ሰው የለም፡፡ የጂጂም ነገር ከዚህ የተለየ ትንግርት የለውም፡፡ ጥሩ ሁኔታ ላይ አይደለቺም ምናምን እያሉ፣ ጂጂን እየፈለጉ እየቀረፁ አደባባይ ላይ ማስጣት የግል ህይወቷን መጋፋት ነው፡፡ መረዳት ካስፈለጋትና ቅን ልብ ያለው ካለ፣ ያለምንም የፎቶና የምስል ጋጋታ እገዛውን በፀጥታ ማድረግ ይችላል፡፡ ምናልባት እሷ ምንም አትፈልግም፡፡ ምናልባት ጂጂ ስለ እሷ ደህና አለመሆን ከምናወራው ከብዙዎቻችን በተሻለ መረጋጋትና የአእምሮ ሰላም ውስጥ ይሆናል ያለቺው፡፡
በቅርብ ጊዜ አንድ ሰው ቤቷ ሄዶ አግኝቷት ቀርፆ የለቀቀውን ምስል አይቻለሁ፣ ጤነኛ ናት፣ ከለዛዋና ከትህትናዋ ጋር ናት፡፡ ከዚህ ጀርባ ያለውን ገመናዋን ደግሞ ለራሷና ለቅርብ ቤተሰቦቿ መተው ነው ያለብን፡፡  ቀሪ ዘመኗን በሰላም ልትኖር ይገባታል፣ የግል ህይወቷን ለራሷ ልንተውላት ይገባል፡፡ ደግሞስ ጂጂ በሙዚቃ ስራዋ የግድ መመለስ አለባት? በህይወት እስካለች ድረስ ሁልጊዜም የግድ መዝፈን አለባት? የህይወት ግቧን በጊዜ አጠናቃ ከሆነስ? ከበቃትስ? ሁላችንም በየተሰማራንበት ስራ በየአመቱ ብንመነደግ እንወዳለን፡፡ ነጋዴ ሁልጊዜ ትርፍ ቢያፍስ ደስ ይለዋል፡፡ ደራሲ በየአመቱ ቢያሳትም፣ ሙዚቀኛ በየአመት በአሉ ዘፈን ቢለቅ አይጠላም፡፡ ግን ሁልጊዜ እንደምኞታችን አይሆንም፡፡ ሁኔታዎች መሻታችንንና ጥረታችንን አግዘው አብረውን የሚፈሱበት ጊዜ አለ፡፡ በዙሪያችን ያለው ሁሉ ለእኛ ስኬት የሚያደላበት ወቅት አለ፡፡ የተገላቢጦሽ የሚሆንበት ወቅትም አለ፡፡ የሚሰራበት ጊዜ አለ፣ ዝም ተብሎ የሚኖርበት ጊዜ አለ፡፡ ጂጂ ምርጥ ምርጥ ዘመን ተሻጋሪ ዘፈኖችን አበርክታልናለች፡፡ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ የራሷን መልካም አሻራ አሳርፋለች፡፡ አሁን ዝም ብላ በሰላምና በዕረፍት ኑሮዋን የምትኖርበት ጊዜ ይመስለኛል፡፡ ይሄም ለእሷ ይገባታል፡፡ ሰላም ለጂጂ ባለችበት እመኝላታለሁ፡፡
(ሚያዚያ 2013 ዓ.ም. ባህር ዳር)

Read 578 times