አንድ የአይሁዶች ተረት እንዲህ ይላል፡፡
አንድ በጣም ኃይለኛ ውሸታም ነበር - ስመ ጥር ዋሾ እንዲሉ፡፡ የሃይማኖት መጽሀፍ ባያሌው ያነብባል፡፡ አንድ ቀን እንደተለመደው የፀሎት መፅሐፉን ይዞ በተመስጦ እያነበበ ሳለ፣ ከውጪ የብዙ ሰዎች የጩኸት ድምፅ ይሰማል፡፡ ወደ መስኮቱ ሄዶ ሲመለከት የሚጮሁት ትናንሽ የሰፈር ልጆች ናቸው፡፡ “እነዚህ የሰፈር ልጆች ደሞ ሌላ ተንኮል ሊሰሩ ነው! ቆይ እሰራላቸዋለሁ!” ይልና እንዲህ አላቸው፡፡
“ስሙ ልጆች፤ ወደ - ፀሎት ምኩራቡ ሂዱና እዩ፡፡ እዚያ የባህር ሰይጣን ቆሞ ታያላችሁ፡፡ ምን ዓይነት ግዙፍ ሰይጣን መሰላችሁ? 5 እግር፣ 3 ዓይኖችና እንደ ፍየል ዓይነት ጢም ያለው ነው፡፡ ደሞ አረንጓዴ ቀለም ያለው ነው!”
ልጆቹ የተባለውን ጉደኛ ፍጡር ለማየት ጓጉና እየበረሩ ሄዱ፡፡ ውሸታሙም ሰው ወደ መጽሐፉ ተመለሰ፡፡ በነዚህ ደቃቃ ልጆች እንዴት እንደቀለደባቸው እያሰበ በተንዠረገገው ረዥም ጢሙ ውስጥ ሳቀ፤
ጥቂት ቆይቶ ግን መዓት አይሁዶች ወደሱ ደጃፍ እየጮሁ ሲያልፉ ሰማና ወደ መስኮቱ ሄዶ አየ፡፡ አንገቱን ብቅ አድርጎም፤
“ወዴት እየሄዳችሁ ነው?” ብሎ ጠየቀ፡፡
“ወደ ፀሎቱ- ምኩራብ!” አሉና መለሱ፡፡
“እዚያ ምን ፍለጋ ትሄዳላችሁ?”
“አልሰማህም ወዳጄ! አንድ የባህር ሰይጣን ወጥቷል አሉ፡፡ አምስት እግር፣ ሦስት ዐይን፣ የፍየል ጢም ያለው አረንጓዴ ፍጡር ነው!”
ዋሾው አይሁድ የሰራው ዘዴ አገር እንዳታለለ ገብቶት በደስታ እየሳቀ መፅሐፍ ማንበቡን ቀጠለ፡፡ ግን ብዙም ሳያነብ ሌላ ከፍተኛ ጩኸት ሰማ፡፡ ወጥቶ ቢያይ አገር ይተራመሳል፡፡ አንዳች መንጋ ህዝብ ወደ ምኩራቡ ይነጉዳል፡፡
“ሰማችሁ ወይ ጎበዝ? ወዴት ነው፣ ይሄ ሁሉ ህዝብ የሚተምመው?” አለና ጮሆ ጠየቀ፡፡
“ምን ዓይነት የጅል ጥያቄ ነው የምትጠይቀው! ከፀሎት ምኩራቡ ፊት ለፊት የባህር ሰይጣን ቆሞ እየታየ መሆኑን አልሰማህም? አምስት እግር፣ ሦስት ዐይኖች፣ የፍየል ጢምና አረንጓዴ ሰውነት እንዳለው ተረጋግጧል” አለው ከሰዉ አንዱ፡፡ ዋሾው አይሁድ በነገሩ በመገረም ቀና ብሎ ወደ ሰዎቹ አየ፡፡ ከሚጎርፈው ህዝብ መካከል ዋናውን የቤተ-አይሁድ ሰባኪ ቄስ አያቸው፡፡
“ኧረ የፈጣሪ ያለህ! ዋናው የአይሁድ ሃይማኖት አስተማሪም ወደዚያው እየሄዱ ነው ማለት ነው? ዋናው ቄስ አምነውበት ከሄዱማ በእርግጥም አንድ ነገር አለ ማለት ነው፡፡ እሳት ካለ ጭስ አለ!”
ባርኔጣውን አጠለቀ፣ ካፖርቱን አደረገ፤ ከዘራውን ያዘና እየሮጠ ከመንጋው ጋር ተቀላቀለ፡፡
“ማን ያውቃል? ያ ያልኩት ነገር ዕውነት ሆኖ፣ የባህሩ ሰይጣን’ኮ መጥቶ ቆሞ ይሆናል!” እያለ በሆዱ፤ ጭራሽ ከህዝቡ ቀድሞ ሩጫውን ተያያዘው፡፡
* * *
እራሱ በዋሸው ውሸት ውሎ አድሮ ተተብትቦ መውጫ መሸሻ የሚያጣ ብዙ መሪ፣ ኃላፊ፣ አስተዳዳሪ፣ የፖለቲካ ፓርቲ ተጠሪ ወዘተ ሞልቷል፡፡ በሀሰት የፈጠረው ሰይጣን ድንገት ህዝቡን ያሳምንና ማጣፊያው ያጥረዋል፡፡ ውሸት እንደ እርግዝና በትንሿ ጀምሮ፤ በኋላ የማይሸፈንበት ደረጃ ይደርስና ፍጥጥ ብሎ የመውጣት ባህሪ አለው፡፡ ለማስወረድ እንሞክርም ቢባል የተወሳሰበ ችግር ይፈጠራል፡፡ ወይ አድጎ የማስወረጃው ጊዜ ያልፋል፡፡ ወይ አስወርዳለሁ ሲሉ የመመረዝ፣ አንዳንዴም የሞት አደጋ ሊደርስ ይችላል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ውሸቱ ከርሞ ከርሞ ሲወለድ ፈጣሪውን ጭምር ማስደንገጡ ነው፡፡ ፈጣሪው የገዛ ፈጠራውን እንደ ጣዖት እንዲያመልክ የሚገደድበት ሁኔታ ሲመጣ ግን ጉዳዩ የአገርና የህዝብ ችግር እንደሚሆን ማስተዋል ይገባል፡፡
ለህዝብ የተዋሸ ውሸት ወሎ አድሮ መጋለጡ አይቀርምና ህዝብን ያስቆጣል፡፡ ይህም አላስተማማኝና ያልተረጋጋ ሁኔታን መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ “ዲሞክራሲን አስፋፋለሁ፣ ሰላምን አሰፍናለሁ፤ የህግ የበላይነት ከመሬት በላይ ስለሆነ እሱን ማረጋገጥ ነው ዋናው፣ ’ይህን ሁሉ መስዋዕትነት የከፈልነው የመሬት ትርፍና ኪራን ለማስላት አይደለም፣‘ ’የህግ የበላይነት በሌለበት ወፈፍ ያደረገው ሁሉ የመሰለውን እየሰራ ጦርነት መለኮሱ ሰላምም መደፍረሱ ፍፁም የማይቀር ነው፣‘ ሉአላዊነትን አስከብራለሁ፣ ልማትን አፋጥናለሁ፣ አቅም እገነባለሁ፣” ማለት፣ ማለት፣ ማለት፡፡…. ተስፋ፣ ተስፋ፣ ተስፋ…. በየዘመኑ በየወቅቱ ተስፋ ማቆር!! ተስፋው አልጨበጥ ካለ ተዓማኒነት ይጠፋል፡፡
ይህን ሁሉ ቃል ገብተን ተዘናግተን ከተገኘን ሁሉንም መስዋዕትነት የህይወትም፣ የማቴሪያልም ዋጋ መጠየቁ ግልጽ ነውና ከተጠባቂነት ወደተጠያቂነት ያሸጋግረናል፡፡
ውለን አድረንም ’ኃይል የሌለው ታጋይ፣ ስንቅ የሌለው ጎራሽ‘ ልንሆን እንደምንችል ይጠቁመናል፡፡ ይህን አውቀን ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አሁኑኑ ማሰብ አለብን፡፡ በመሰረቱ መቼም ቢሆን መች፤ ሰላም፤ የመንቀሳቀሻችን መሽከርክሪት የሚሆነውና ለግብም የሚያበቃን በሌሎች አቅጣጫዎች ሁሉ አቅምና ኃይላችን አስተማማኝ መሆኑን ለማረጋገጥ ስንችል መሆኑን በውል መረዳት ተገቢ ነው፡፡
ስለ ሰላም መደረግ ያለበትን ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ሁሉ ጥርጊያውን ማስተካከል ተገቢ የመሆኑን ያህል፤ ራሳችንን ለወረራና ለባላንጣ አመቻችተን መስጠትም ፍፁም አደጋ ውስጥ ሊጥለን እንደሚችል በጊዜ ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ ምነው ቢሉ “ሀይለኛ መትቶ ካልደገመ ይንጠራራል፤ ሰነፍ እንዲደገም ይለመጣል” ይሏልና፡፡
ከህዝቡ ጋር ሆኜ ስለህዝብ እሰራለሁ የሚል ወገን ሁሉ፤ የህዝብን የልብ ትርታ ማዳመጥ ይጠበቅበታል፡፡ የህዝብ የልብ ትርታ፣ የሀገር እስትንፋስ ነውና፣ በተለይም ለስልጣን ያበቃኝ ህዝቡ ነው የሚል፣ ባለስልጣን የመቆየት አቅሙም ያው ህዝቡ መሆኑን መገንዘብ ምርጫው ብቻ ሳይሆን ግዴታውም ነው፡፡ ምንም ዓይነት የውጪ ጫና የሀገር ህልውናን ከማጣት ጋር ሊተካከል አይገባም፡፡ የህዝብንና የሀገርን ህልውና ለመጠበቅ የምንተገብረውን ነገር በተመለከተ ያለመሸፋፈንና ያለማድበስበስ አቋምን ለይቶ መሄድ ኋላ ውዥንብር ውስጥ ከመግባት ያድናል፡፡ አበው “ወይ ታጥቀህ ተዋጋ፣ ወይ ርቀህ ሽሽ” የሚሉት ለዚህ ነው፡፡
የገዛ ውሸቱን እውነት ይሆን እንዴ? ብሎ ከህዝቡ ፊት እንደሮጠው ይሁዳ የገዛ ንግግራችንና ንድፈ - ሀሳባችን ቁራኛና ሰለባ ሆነን ተጠላልፈን መውደቅ የለብንም፡፡ ኋላ ነገር ሲከፋ፤
“…እሸሸግበት ጥግ አጣሁ”
እምፀናበት ልብ አጣሁ”
እንዳንል መጠንቀቅ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ያ ሳይሆን ቀርቶ በተደጋጋሚና አንድ ነገር እንደበቀቀን የምንለፍፍ ከሆነ፤ “ሀጢያት ሲደጋገም ፅድቅ ይመስላል” ማለት ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ ታዋቂው ያገራችን ገጣሚ ያለውንም አለመርሳት ነው፡-
“ትቻቸዋለሁ ይተውኝ
አልነካቸውም አይንኩኝ
ብለህ ተገልለህ ርቀህ፤
ዕውነት ይተውኛል ብለህ፣ እንዴት ተስፋ ታደርጋለህ?
…የተወጋ በቅቶት ቢተ’ኛ፣ የወጋ መች እንቅልፍ አለው
የጅምሩን ካልጨረሰው፡፡
እና በእኔ ይሁንብህ
እንቅልፍ ነው እሚያስወስድህ”
Published in
ርዕሰ አንቀፅ