Sunday, 17 November 2024 00:00

ለማፍረስም ጊዜ አለው፤ ለመገንባትም ጊዜ አለው!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

“ተረጋጉ፣ ምንም ለውጥ የለም፣ ወደፊትም አይኖርም”… ይላል አንዱ። “የምሥራች ልንገራችሁ፣ ለውጥ በላይ በላዩ መጣላችሁ!” ይላል ሌላኛው። ሳምንት ሳይሞላቸው፣ ቦታ ተቀያይረው፣ ኢላማቸውን ወደ ምሽግ ለውጠው ሲተጋተጉ ትሰማላችሁ።
ጥፋት ነው። ወይም ከንቱ ስህተት። ግን አለምክንያት የሚመጣ ስህተት አይደለም።
ሰው በተፈጥሮው፣ ነባርና ቋሚ ነገሮችን ይፈልጋል። አዲስና የተሻለ ለውጥ ማየትም እንዲሁ። ለዚህም ነው፣ የጥንት ዐዋቂዎችና ጥበበኞችም፣ እነዚህን ጉዳዮች እያነሡ ሲፈላሰፉና ሲሰብኩ የነበሩት።
“ተመስጌን፤ ምንም አዲስ ነገር የለም። ምልአተ ዓለሙ ዕጹብ ድንቅ ነው፤ አሜን ለዘላለም። ሁሉም ነገር ሰላም ነው። አንዳችም የሚመጣ ለውጥ የለም” የሚል ሐሳብ ይሰጠናል - የግሪኩ ፈላስፋ ፓርሜንደስ።
ሄኖክ በዚህ የሚስማማ ይመስላል። “ዓለማትና ከዋክብት የተፈጥሮ ሥርዓታቸውን ጠብቀው፣ ምሕዋራቸውን ተከትለው፣ ከዑደታቸው ሳይዛነፉ ይጓዛሉ፤ ይሽከረከራሉ” ይለናል መጽሐፈ ሄኖክ።
“የሰው ልጆችም የተፈጥሮ ሥርዓታቸውን ዐውቀውና ጠብቀው፣ የተቃና መንገድ ይዘው ቢተጉ ይበጃቸዋል” ባይ ነው ሄኖክ። እሠዬው “የተፈጥሮ ሥርዓት ቋሚና ዘላለማዊ ነው፤ አዲስ ነገር የለውም፤ ለውጥ አይነካውም” እንደማለት ይመስላል።
የሄራክሊተስ ሐሳብ ከእነዚህ ይለያል። ምንም ቋሚ ነገር የለም ይላል። ለዘላለም የሚዘልቅ ይቅርና ለአፍታ የሚቆይ ነገር የለም። ሁሌም አዲስ ነው፤ ሁሌም ለውጥ ነው ባይ ነው ሄራክሊተስ። የተሻገርከውን ወይም የዋኘህበትን ወንዝ ደግመህ አትሻገረውም፤ አትዋኝበትም ብሎ እንደተናገረም ይተረክለታል። የሄራክሊተስ ዓለም፣ የለውጥ ዓለም ነው። ሁሌም አዲስ ነው።
እነዚህ ሐሳቦች ሁሉ ለመክብብ አይዋጡለትም። “ምንም አዲስ ነገር የለም” ይላል መክብብ። አዎ ወንዙ ይጎርፋል። ግን የሄደው ውኃ፣ ዝናብ ሆኖ ይመለሳል፤ እንደገና ዞሮ ለመጉረፍ። አዎ፣ ነፋስ ይነፍሳል። ነገር ግን፣ ዞሮ ተመልሶ ይነፍሳል። አዎ ፀሐይ ትወጣለች፤ ትገባለች። ግን ምን ለውጥ አለው? ምን አዲስ ነገር መጣ? ፀሐይዋ እንደገና ተመልሳ ትወጣለች። ከሰማያት በታች ምንም አዲስ ነገር የለም ይለናል መጽሐፈ መክብብ።
ቋሚና ዘላለማዊ ዓለም
“ሰላም ነው፤ ተመስጌን፤ ምንም አዲስ ነገር የለም” ይላል ፈላስፋው። ምልዐተ ዓለሙ ነቀፋና ጉድለት የለበትም። ሁልጊዜ በሁሉም ቦታ ሙሉ ነው። አይጨምሩለት፣ አይቀንሱበት። full, complete and perfect በማለት ይገልጸዋል።
የነበረ፣ ያለ፣ የሚኖር፣ ዘላለም የሚያምኑበትና የሚተማመኑበት ምልዓተ ዓለም… እጅግ ዕጹብ ድንቅ ነው፤ ለውጥ የሚባል ነገር ከየትም አይመጣም። መቼም አይከሰትም… ሁሉም ነገር አማን ነው ይላል ፓርሚንደስ።
አሜን እንድንል ሊጠብቅ ይችላል። አዎ ትክክል ብለሃል። “አዎ የታመነ እውነታ ነው። አዎ ትክክለኛው የእውነትና የዕውቀት መንገድ ይሄ ነው” ካላልን፣ ከዚህ ውጭ አዘንብለን ካፈነገጥን፣ ዐምጸን ከተላተምን፣ ወዮው ለኛ!
በከንቱ እየተሳከርን፣ እየተሞኘን፣ እየተምታታብን ዕድሜያችንን እንጨርሳለን። ከሦስት ዐይነት ብኩኖች መካከል የትኛው ውስጥ እንደምንመደብ ተመልከቱ።
በመጀመሪያው ምድብ የምናገኘው፣ “ለውጥ አምላኪዎችን” ነው።
“የሌለ ነገር አለ። ያለ ነገር የለም”…
“ያልኖረ ነገር ይኖራል፤ የኖረ ነገር አይኖርም”…
“የሌለ ነገርና ያለ ነገር አንድ ናቸው፤ ሁለትም ናቸው” ብለው ሰውንና ራሳቸውን ያምታታሉ። የተደፈነባቸውና የተጋረደባቸው አላዋቂ “ባለሁለት ራስ ሟቾች” ናቸው ይላቸዋል - ፓርሚንደስ። two-headed mortals… “both deaf and blind… who believe that to be and not to be are the same and not the same”. ስድብ ነው። ስድቡም በሄራክሊተስ ላይ ነው ተብሎም ተጽፏል። ሄራክሊተስም ለስድብ እንደማይተናንስ እናየዋለን። ለጊዜው ግን፣ በፓርሚንደስ ሚዛን “ብኩን” የተባሉትን ምድቦች እንጨርስ።
ሁለተኛው ምድብ፣ የተራ አላዋቂዎች ምድብ ነው። ያለው እውነታ ላይ የሌለ ነገር እንጨምራለን ይላሉ። “አላዋቂ ሟቾች”ተብለው ሊጠቀሱ ይችላሉ (knowing nothing, ignorant mortals)።
የሦስተኛው ምድብ ሰፋሪዎች የባሰባቸው ናቸው። በእውን ያለውን ትተው በእውን የሌለ ነገር በቦታው ለመተካት ይፈልጋሉ። “የማይታየው ዓለም”፣ “አይደረሴ፣ አይዳሰሴ ዓለም ውስጥ፣ ሊታወቅ የማይችል ልዩ ሕይወት” ብለው ሊናገሩ ይችላሉ። እውኑ ዓለም ላይ ማመጽ የሚያምራቸው የቅዠት ዋናተኞች ናቸው - ባዶነትን የሚያመልኩ ብኩን ሟቾች ናቸው። “nihilist mortals” ይሏቸዋል - የፓርሜንደስን አገላለጽ በመከተል።
እሺ ይሁንለት። ስድቡንና ምድቡን እንቀበልለት። አላዋቂ ሞኞች፣ የቅዠት ዋናተኞችና የለውጥ አምላኪዎች… ምን አጥፍተው ነው፣ “ሟቾች” የሚል ቅጽል የተጨመረባቸው?
የተሳሳተ ሐሳባቸውና ጭፍን እምነታቸው አይዘልቅም። ቢዘልቅም ዘላለማዊ እውነታ ላይ ለውጥ አያመጣበትም። ከምልዐተ ዓለሙ ላይ ምንም አያጎድልበትም ለማለት ነው - “ሟቾች” የሚል ማዕርግ የተመረቀላቸው።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ የተሳሳተ ሐሳብ… ከየትኛውም ሰው ቢመጣ ለውጥ አያመጣም ለማለት ነው። እውነት ያልሆነ ሐሳብ፣ በጦረኞችም ሆነ በነገሥታት ቢታወጅ፣ በፈላስፎችም ሆነ በሰባክያን አንደበት ቢስተጋባ፣ በሙዚቀኞች ቢዘመርለት እንኳ… ስህተት መሆኑ አይቀርለትም። እንደ ዘላለማዊ የተፈጥሮ ሕግ ልናየው ወይም እንደ ዘላለማዊ የአምላክ ቃል ልንቆጥረውና አሜን ብለን ልንቀበለው አይገባም። ለዚህም ነው “ሟቾች” የሚል የሕልፈትና የስንብት ቅጽል የተለጠፈላቸው።
ወደ ቁም ነገሩ ተመልሰን በዐጭሩ ብንቋጨው ይሻላል።
አንዳንዶቹ የፓርሜንደስ ሐሳቦች፣ ብዙም መፈላስፍ የሚያስፈልጋቸው አይመስሉም። እሱ እንደሚለን ከሆነ፣ ከባዶ… አንዳች ነገር አይፈጠርም። ከየት ይመጣል? ከየትም ሊመጣ አይችልም። በእውን ያሉ ነገሮች ተጠራቅመው አዲስ ቅርጽ ሊይዙ፣ ተቀላቅለውና ተብላልተው አዲስ ጣዕም ሊሰጡ፣ ተገጣጥመውና ተዋሕደው አዲስ ዐይነት ይዘት ሊፈጥሩ ይችላሉ። ከባዶ አንዳች ነገር ይመጣል ብሎ ማሰብ ግን፣ “የሌለ ነገር አለ” ብሎ እንደማሰብ ነው። ከምንም ነገር ምንም አይመጣም (out of nothing comes nothing)።
በእውን ያለ አንዳች ነገር፣ ምንም ነገር ቢሆን… መልክንና ዐይነቱን ይቀይር እንደሆነ እንጂ፣ ድምጥማጡ ብን ብሎ አይሰወርም። ከነፍጥረቱ እልም ብሎ አይጠፋም። ወዴት ይሄዳል? የትም ሊሄድ አይችልም።። ከምልዐተ ዓለሙ ውጭ ሌላ ነገር ሌላ ቦታ የለም።
ፓርሜንደስ በዚህ መልክ ሐሳቡን ሲገልጽልን አሳማኝ ይመስላል። “
ምልአተ ዓለሙ አስተማማኝ ነው፤ … የነበረ፣ ያለ፣ የሚኖር ነው ይለናል። አሜን። “ሁሉም ሰላም ነው፤ ምንም አዲስ ነገር የለም” ያስብላል። አሳማኝ ይመስላል ብንልም፣ ሙሉ ለሙሉ እውነት ነው ማለታችን አይደለም። በዚያ ላይ…
እንዲህ ዐይነት ዓለም ለመክብብ ግን ያንገሸግሸዋል።
አዲስ ነገር የማይታይበት፣ ለውጥ የማይከሰትበት ዓለም፣ ለፓርሜንደስ… ነቀፋና ጉድለት የሌለበት፣ እንከን አልባ ዕጹብ ድንቅ ምልአተ ዓለም ነው። ለመክብብ ግን፣ አታካችና ከንቱ ልፋት ነው። የነፋስ እረኛ እንደመሆን ነው። ለውጥ የሌለበት ዓለም፣ የጣር የመከራ ዓለም ነው።
ምናልባት የሄራክሊተስ ዓለም ለመክብብ ይመቸው ይሆን?
ምልዓተ ዓለሙ ሁሉ፣ የለውጥ ዓለም ነው ይላሉ የሄራክሊተስ አድናቂዎች። እንዲያውም እስከ ጥግ ድረስ ይወስዱታል። እንዲህም ይሉለታል።
ለዘላለም የሚዘልቅ ይቅርና ለጊዜው የሚቆይ ምንም ቋሚ ነገር የለም - የትም።
ለአፍታ ሳይለወጥ የሚቀር ምንም ቋሚ ነገር አይኖርም - ለዘላለም።
እዚህ ላይ ከሄራክሊተስ ጋር ተያይዞ የሚነሳውን የተለመደ አባባል ሳንጠቅስ ማለፍ አንችልም።
“it is not possible to step twice into the same river.”
ከፊት ለፊትህ ያለው ወንዝ፣ አሁን የዋኘህበት ወይም አሁን የተሻገርከው ወንዝ አይደለም። የቅድሙ ውኃ አሁን የለም፤ ሄዷል። በጎርፍ ደፍርሷል። ዳርቻዎቹ ተሸርሽረዋል። ወለሉ በጎርፍ ተጠርጎ፣ አሸዋውና ደለሉ ተወስዷል። ሌላ አሸዋና ደለል እየተኛበት ነው።
በዐጭሩ፣ ቆሞ የሚጠብቃችሁ ነገር የለም ለማለት ነው። እናንተም ቆማችሁ አትጠብቁም። በሐሳብ፣ በአካል፣ በባሕርይ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተለውጣችኋል።
ምናለፋችሁ? ቀድሞ በነበረበት ሁኔታ የሚዘልቅ ይቅርና ለአፍታ የሚቆይ ነገር የለም። እናም…
“ምንድነው ነገሩ? ምን ነገር አለ? ምን ነገር ተከሰተ? ምን ተደረገ?” ብለን ከመጠየቅ ይልቅ…
“ምን እየሆነና እየተሆነ ነው? ምን እየተከሰተ፣ ምን እየተደረገ፣ ምን እየተካሄደ ነው?” ብለን ማሰብና መጠየቅ አለብን ባይ ናቸው - የሄራክሊተስ አድናቂዎች።
ምንም ቋሚ ነገር የለም፤ ይህን እውነታ የማይገነዘቡ ሰዎች… ከእንስሳት የማይሻሉ ሟቾች ናቸው ብሎ ሄራክሊተስ ለፓርሚንደስ የአጸፋ መልስ አይሰጥም። በዘመን ይቀድመዋል። ቢሆንም ግን “ምልአተ ዓለሙ የለውጥ ዓለም” እንደሆነ የማያምኑ ፈላስፎችን ከማናናቅ ወደኋላ አይልም።
አብዛኛው ሰው አላዋቂ እንደሆነ ያምናል ተብሎ የሚነገርለት ሄራክሊተስ፣ የብዙ ሰው ሐሳብ እንደ ሕጻናት ጨዋታ ሆኖ ቢታየው አይገርመውም። ይልቅስ፣ ብዙ ፈላስፎች ከግዑዝ አለት ጋር ሊመሳሰሉበት ይችላሉ። በትምህርት ዓመታት ብዛት፣ ወይም በመጻሕፍትና በንባብ ብዛት ብቻ ዐዋቂ መሆን ቢቻል ኖሮ፣ ብዙዎቹ ፈላስፎች ዐዋቂ ይሆኑ ነበር ብሎ በስም ይዘረዝራቸዋል - የዘመኑና የቀድሞ ታዋቂ ፈላስፎችን።
“Much learning does not teach insight. Otherwise it would have taught Hesiod and Pythagoras and moreover Xenophanes…” ብሎ ጽፏል ሰውየው።
ሌሎች ፈላስፎች በፊናቸው፣ “የሄራክሊተስ ንግግርና ጽሑፍ ለግንዛቤ ያስቸግራል። ቅኔና ምሳሌ ያበዛል። የስብከት ምስጢር፣ የትንቢት እንቆቅልሽ ያስመስለዋል” ብለው ያማርሩታል። ጨለማው ፈላስፋ፣ ድብቁ ፈላስፋ ይሉታል።
እንግዲህ ስንቴ ይንገራቸው። “መቼም አይገባቸውም፤ አንዴ አይደለም ዐሥሬ እየተወለዱ ዕድሜያቸውን በትምህርት ቢጨርሱ ምንም አይገለጥላቸውም” እያለ እስኪያማርር ነው የሚጠብቁት?
“የሚያነባ ፈላስፋ” ብለው የሰየሙት ምሬቱ ሲበዛባቸው ይሆን?
አይ፣ የሚያነባው የሰዎች መከራ ስለሚያሳዝነው ነው ብለው የጻፉ አሉ። ብዙ ሰው አይገባውም። የሌሎችን ስቃይ አለመረዳቱ ብቻ ሳይሆን የራሱንም ችግር በቅጡ አይገነዘብም ብዙ ሰው? ለሄራክሊተስ የአብዛኛው ሰው ሐሳብ የልጆች ጨዋታ ነው ተብሎ የለ?
ሄራክሊተስ ግን የሰዎችን ችግር ይገነዘባል። በየመንገዱ በሚያስተውለው የሰዎች መከራ እያዘነ ያለቅስ ስለነበር የሚያነባ ፈላስፋ ተብሎ ተጠራ ብለው ተርከውለታል።
ግን፣ ስለየትኛው ሄራክሊተስ ነው የሚያወሩት? ምንም ቋሚ ነገር ከሌለ፣ ቋሚ ሄራክሊተስ እንዴት ይኖራል? ትናንት ያያችሁት ሰው ሌላ፣ ዛሬ ስታዩት ሌላ!
ከምር ግን፣ ይሄን ሐሳብ መረን ከለቀቅነው ያስፈራል። ምልአተ ዓለሙ ሁሉ “የለየለት የለውጥ ዓለም” ቢሆን ኖሮ፣ ሁሉም ነገር መያዣ መጨበጫ የሌለው ተለዋዋጭ ነገር ቢሆን ኖሮ፣ የማይነጋለት አስፈሪ ቅዠት፣ ወይም ማለቂያ የሌለው “የሆረር ቅዠት” ይሆን ነበር።
ቢሆንም ግን፣ የሄራክሊተስ ሐሳብ ትልቅ ቁም ነገር መያዙን እንዴት መካድ ይቻላል? ለውጥ የዘወትር እውነታ ነው። የብዙ ሰው ባሕርይ፣ በማይጨበጥ ተለዋዋጭ ስሜት የተሞላ ስለሆነ ብቻ አይደለም። ይሄማ የሰዎች ጉድለትና ድክመት ነው።
ይልቅስ እናስበው። “በአእምሮና በአካል፣ በዕውቀትና በሙያ፣ በጥበብና በባሕርይ ማደግ” የሚባል ነገር ባይኖር ኖሮ፣ ሕይወት ምን ትርጉም ምን ጣዕም ይኖረዋል። ጣዕም ሊኖር ይቅርና፣ ከነጭራሹስ ሕይወት የሚሉት ነገር ይኖር ነበር?
ሕይወት ቢኖር እንኳ፣ ለውጥ የማይመጣ ከሆነ፣ ማሰብና መሥራት፣ ማወቅና መምረጥ ለምን ያስፈልጋል?
የለየለት የለውጥ ዓለም እውነትም ሆረር ነው።
ግን፣ ዘላለማዊና ቋሚ ዓለምስ?
ምንም ለውጥ የሌለበት “ቋሚና ዘላለማዊ ዓለም” እንዲሁ ላይ ላዩን ማራኪ ይመስላል። ነገር ግን፣ ራሱን የቻለ ሌላ አስፈሪ ቅዠት ነው።
እንደ ሰዓት እጀታ፣ ቀን ከሌት ሳያቋርጡ፣ የውኃ ጠብታ የእሥረኞች አናት ላይ ማንጠባጠብ፣ እጅግ አስፈሪ የማሰቃያ ዘዴ እንደነበር የሚነገረው አለምክንያት አይደለም። ሕመሙ ብቻ አይደለም ችግሩ። ለውጥ የለሽ ድግግሞሹም ናላ ያዞራል።
ጨለማ ውስጥ የተዘጋበት እሥረኛም፣ ለብዙ ቀናት በጤና አይቆይም። ጨለማ በመሆኑ ብቻ አይደለም አእምሮ የሚበጠበጠው። በነጭ ወለል፣ በነጭ ግድግዳና በነጭ ኮርኒስ የተከበበ፣ በብርሀን የተጥለቀለቀ ባዶ ክፍል ውስጥ የተዘጋበት እሥረኛም የአእምሮ ሰላም አያገኝም።
በዚያ ላይ ሁሉም ነገር፣ ዝም፣ ጸጥ፣ ረጭ ያለ ባዶ ሕዋ ላይ የተጣለ ይመስላል።
ይሄም ሆረር ነው።
ቢሆንም ግን፣ ቋሚና ዘላለማዊ ነገሮች ከሌሉ፣ “መያዣ መጨበጫ የሌለው የሆረር ዓለም” እንደሚሆንብንም ተነጋግረናል።
እና ምን ይሻላል? መክብብ መፍትሔ ይኖረው ይሆን?
ቋሚና ዘላለማዊ ነገሮች አሉ። ለውጦችና አዳዲስ ክስተቶችም አሉ። እና ምንድነው ችግሩ? ሁለቱን ማስታረቁ ላይ ነው ችግሩ?
መክብብ፣ በራሱ መንገድ ሁለቱንም ያስታረቃቸው ይመስላል። ውጤቱን ግን አልወደደውም። ሁሉም ነገር ከንቱ ነው ይለናል። ከከንቱም ከንቱ ብሎም ይጨምርልናል። የነፋስ እረኛ እንደመሆን ነው ብሎም እርማችንን እንድናወጣ ይነግረናል። ምክንያቱን እንሰማለታለን። በሃይማኖታዊው የኦሪት መጽሐፍ ውስጥ የመክብብ ትረካን የመሰለ ነገር የለም። እናየዋለና።

Read 554 times Last modified on Monday, 18 November 2024 08:40