Sunday, 17 November 2024 00:00

“ሩብ ዓመቱ ከሕዝብ ጋር ተቀራርበን የሠራንበት፣ የሥራ ባህልን መለወጥ የተቻለበትም ነው“

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ከንቲባ አዳነች አቤቤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት አፈፃፀም ግምገማን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፤ በሩብ ዓመቱ የተከናወኑ ሥራዎች ወጪ ቆጣቢ፣ ጥራት ያላቸውና ባጠረ ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ምቹ ከማድረግ አኳያ ትልቅ ትርጉም ያላቸው ሥራዎች መከናወናቸውንም ተናግረዋል፡፡
“ሩብ ዓመቱ ከሕዝብ ጋር ተቀራርበን የሠራንበት፣ የአመራር ቅንጅት የታየበትና የሥራ ባህልን መለወጥ የተቻለበትም ነው“ ብለዋል።
የኮሪደር ልማትና ከተማዋን መልሶ የማደስ ሥራዎቻችን ውጤታማ ሆነዋል ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ በኮሪደር ልማቱ ለኑሮ ከማይመች ጎስቋላ አካባቢ ያነሣናቸው ነዋሪዎቻችንን ለኑሮ ምቹ የሆነ ንፁህ የመኖሪያ ቤትና አካባቢ እንዲያገኙ ማድረግ ችለናል ብለዋል፡፡
የኮሪደር ልማትን ጨምሮ የፕሮጀክቶች አፈፃፀም የተሻለ እንደነበርም ገልጸዋል፣ ሁሉንም ሥራ በማስተሳሰር መምራትና ለውጤት ማብቃት መቻል አንዱ ጥንካሬ መሆኑን በመጥቀስ፡፡
“ሌብነትና ብልሹ አሠራር ያልተሻገርናቸው የቤት ሥራዎቻችን ቢሆኑም፣ ነዋሪው የሚሰጠውን ጥቆማና አስተያየት መሠረት በማድረግ የተሠሩ ሥራዎች ፍሬ ማፍራት ጀምረዋል” ብለዋል፡፡
አዲስ አበባን ዓለም አቀፍ የስበት ማዕከል ለማድረግና የሀገራችንን ገፅታ ለመገንባት እመርታ የታየበት ሥራ መከናወኑንም ነው የገለጹት፡፡
“አዲስ አበባን የቱሪስት መዳረሻ፣ ዓለም አቀፍ የስበት ማዕከል ለማድረግና የሀገራችንን ገፅታ ለመገንባት የሰራናቸው የኮሪደር ልማትና ከተማዋን መልሶ የማደስ ሥራዎቻችን ውጤታማ ሆነዋል“ ያሉት ከንቲባዋ፤ “ከተማዋ በሩብ ዓመቱ ብቻ 20 የተለያዩ አህጉርና ዓለም አቀፍ ኮንፍረንሶችን በብቃት ማስተናገድ ችላለች” ብለዋል፡፡
በሩብ ዓመቱ በመሠረተ ልማት ግንባታ ላይ የተቋማት ተቀናጅቶ መሥራት ለውጥ የታየበት መሆኑን በመጠቆምም፤ በዚህ ዘርፍ አንዱ የሠራውን ሌላው የሚያፈርስበት ሁኔታ ቀርቶ በመናበብ መሰራቱን ገልጸዋል።
የበጎ ፈቃድ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉንና በርካቶች ተጠቃሚ መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡ ለአብነትም ሲጠቅሱ፤ ከ2 ሺ 780 በላይ ቤቶች በበጎ ፈቃድ መሰራታቸውንና ሕዝብና ባለሃብቱን በማስተባበር ከ5 ቢሊዮን በላይ ብር ለዚሁ ሥራ መዋሉን ተናግረዋል፡፡
ቤቶችን በማስተዳደር፣ በማስተላለፍ እንዲሁም በመንገድ ግንባታ ጥሩ ሥራ መከናወኑን ያወሱት ከንቲባዋ፤ በተለይም በሩብ ዓመቱ ከ27 ኪሎ ሜትር በላይ በራስ ኃይል የተሠራ ሲሆን፣ ከ221 ኪሎ ሜትር በላይ መንገዶች ጥገና መካሄዱን ጠቁመዋል፡፡
የስማርት ከተማ ግንባታ ሥራዎች ስኬት የተገኘባቸው መሆናቸውን የገለጹት ከንቲባ አዳነች፤ በመሬት አስተዳደርና ልማት ቢሮ በኅብረት ሥራ ኮሚሽን፣ በሲቪል ምዝገባ እና የዜግነት አገልግሎት መስኮች የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች ፍሬ ማፍራት መጀመራቸውን አመልክተዋል፡፡
በሩብ ዓመቱ የከተማ አስተዳደሩ አመራር የአስተሳሰብና የተግባር አንድነትን ፈጥሮ ሥራዎችን የመራበት፣ የአመራር ዕድገትና መረጋጋት የታየበት መሆኑንም ነው ያብራሩት፡፡
ከሩብ ዓመቱ ውጤታማ ሥራዎች በመነሣትም ችግሮችን በዘላቂነት ለማረም የሚያስችል የአመራር ቁመና ለመፍጠር፣ ግልፅነትን ለመጨመርና ነዋሪውን በማሳተፍ ለመሥራት የሚያስችል አቅጣጫም መቀመጡን አመልክተዋል፡፡
የተቋም ግንባታ፣ የሰው ተኮር ሥራዎችን ማጠናከር፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የኑሮ ውድነትን መቀነስ፣ የገቢ አሰባሰብን ማሻሻል፣ የንግድ ሥርዓቱን ማጠናከር፣ ለነዋሪዎቿ የተመቸች ከተማ መገንባት እንዲሁም የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በመጨረስ ወደ አገልግሎት ማስገባት እና የ2ኛ ዙር ኮሪደር ሥራን በጥራትና በፍጥነት ማጠናቀቅ በቀጣይ በልዩ ትኩረት የሚሠሩ ሥራዎች መሆናቸውን ከንቲባ አዳነች አስገንዝበዋል።
በማጠቃለያቸውም፤ “አገልግሎት አሰጣጣችንን ይበልጥ ቀልጣፋና ከሌብነትና ብልሹ አሠራር የፀዳ በማድረግ፣ በትጋትና በታማኝነት በማሳተፍ፣ መሥራታችንን አሁንም አጠናክረን እንቀጥላለን” ብለዋል፡፡

 

 

Read 257 times