ከተማችን አዲስ አበባ የጀመረችውን የመታደስ ጉዞ አጠናክራ ቀጥላለች፡፡ በአጭር ጊዜ በፍጥነትና በጥራት ከአለም አቻ ከተሞች ጋር ተወዳዳሪ እየሆነች እንዳለ የብዙዎች ምስክርነት ነው፡፡ ከተማዋ በርካታ የተመሰቃቀሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ስታስተናግድ ቆይታለች፡፡ የለውጥ ፍላጎት ጩኸቶች በማህበረሰቡ ሲሰሙም ነበር፡፡ ሆኖም የህብረተሰቡን መሰረታዊ ጥያቄ መነሻ በማድረግ ከተማዋ እምርታዊ በሆነ መልኩ በለውጥ ግስጋሴ ላይ በመሆኗ የማህበረሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች ለማሟላት ሌት ተቀን እየተጋች ትገኛለች፡፡
በመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት ስራ በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የዘመናዊነት ከተማ መስፈርትን በሚያሟላ ደረጃ የተዘረጉ መሰረተ ልማቶች እየተጠናቀቁ ህዝቡን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ሀሳብ አመንጪነት በተሰጠ አቅጣጫ መሰረት፣ በአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ በክብርት አዳነች አበቤ በጋዜጣዊ መግለጫ በይፋ ያስጀመሩት የሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ጅማሮ፣ አሁን ያለበት ደረጃና በቀጣይ ለነዋሪው የሚሰጠው ጠቀሜታ ምንድነው? የሚለውን ጥያቄ የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች ገልጸውታል፡፡ በአዲስ አበባ ባለፉት ስርአቶች የከተማ ማደስ ስራዎች በጥቂቱ ተከናውነው ነበር፡፡ የአሁኑ የኮሪደር ልማት ከበፊቶቹ ምን ለየት ያደርገዋል? ለሚለው መሰረታዊ ጥያቂ አቶ ጥላሁን ወርቁ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ፅ/ቤትና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ፡- ምን አሉ?
“አዲስ አበባ ከተማ የአለም አቀፍ ተቋማት፤ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ፤ የሃገራችን ርእሰ ከተማ እንዲሁም ለነዋሪዎቿም ደግሞ የሚመጥን አገልግሎት መስጠት ያለባት ከተማ ነች፡፡ እነዚህ ሁሉ ሲደመሩ የኮሪደር ልማቱ አዲስ አበባን ስሟንና ግብሯን የሚመጥን እንዲሆን ያስቻለ ነዉ፡፡
ካለፉት መንግስታት ጀምሮ ጣሊያን በ1928 ኢትዮጵያን ለመውረር ለሁለተኛ ጊዜ በመጣችበት ጊዜ የንጉሱን ክብረ በዓል አስመልክቶ፣ በደርግ ጊዜ የአፍሪካን ህብረት አስመልክቶ፣ በተለያዩ ጊዜ የእድሳት ሙከራዎች ተካሂደዋል፡፡ በወቅቱ እነዚህ ሁነት ተኮር እድሳቶች ነበሩ፡፡ አሁን እየተሰራ ያለው የአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደር ልማት ሁሉን ያማከለ የከተማ ማደስ፣ የከተማ ማዘመንና የከተማ ማላቅ ስራ ልዩ የሚያደርገው ሁሉ አቀፍና ታቅዶ ለረጅም ጊዜ ከተማን ልናድስበት የሚገባ ሞዴል አድርገን እንደ ሃገር በራሳችን ጥረት ከእቅዱ ጀምሮ የክብር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ሃሳብ ሆኖ የመጣ፣ በዘላቂነት ከተማችንን የምናዘምንበት ተግባር ነዉ፡፡
ነዋሪዎች ከሚያገኗቸው ፋይዳዎች ወሳኝ የሆኑ የመሰረተ ልማት ጥቅም ባሻገር በዋናነት የሰው ልጆችን ህይወት መቀየር ነው፡፡ በዚህ ለውጥ የመንግስት ዋናው የትኩረት አጀንዳ ሰው ተኮር መሆን ነው፡፡ በተለይ በዚህ የኮሪደር ልማት ህንፃዎች የሚታደሱት እንዴት ነው፣ በርካታ ሰዎች በልማቱ ምክንያት እየተነሱ ነው እንዴት እየተስተናገዱ ነው የሚለው ዋናዉ ጉዳይ ነዉ፡፡
እንደ አዲስ አበባ የስኬታችንም ሚስጥር ተብሎ የሚታሰበው እነዚህን በጣም በተጎሳቆሉ ለአደጋዎች የተጋለጡ የሰዉን ልጅ የማይመጥኑ የመኖሪያ ቤቶች የነበሩትን ዜጎች አንስቶ ለኑሮ አመቺ በሆኑ ቤቶች ውስጥ እንዲኖሩ ማስቻል ነው፡፡
ክቡር ጠ/ሚሩ ከመጀመሪያዉ ኦረንቴሽን ቀን ጀምሮ “ማንም ዜጋ በዚህ ልማት ምክንያት መጎዳት የለበትም፤አንድም እናት በዚህ ማልቀስ የለባትም” የሚል አቅጣጫ አስቀምጠዋል፤ በማለት ዜጎች ሳይጉላሉ ከነበረባቸው ያልተመቸ የአኗኗር ዘይቤ ተላቀው ወደተሻለ ህይወት መሸጋገራቸውን የሚያብራሩት አቶ ጥላሁን አክለውም፡-
“በሁለተኛዉ ኮሪደር የተነሳው የወንዝ ዳርቻ ልማት ነው፡፡ ይህም በአዲስ አበባ ከተማ ወደ 607 ኪሎ.ሜ ኔትዎርክ የሚሸፍን ነዉ፡፡ ቦታው ባክኖ፤የቆሻሻ መጣያ ሆኖ ለከተማ ማስዋብ ለአረንጓዴ ምንጭ፤ለዓሳ ማስገሪያ ሊሆኑ የሚችሉ ከተማን ማስዋብ የሚለውን አባባል በጣሰ መልኩ ባለፉት ዘመናት ወንዞቻችን በአካባቢዉ ያሉትን ሰዎች መጥፎ ሽታ የሚበክል የነበረበት ነዉ፡፡ ብዙ ሰዎች የሚቸገሩበትና ለህመም መንስዔ የሚሆኑበት ሁኔታ ነበር፡፤
ታዲያ ይሄን ታሪክ ለመቀየር ከእንጦጦ ፒኮክ የሚዘልቀዉ አንደኛዉ የኮሪደሩ አካል ሆኖ የወንዝ ዳርቻዉ እንዲለማ እንዲሁም የቀበናና የግንፍሌ ወንዝም ተይዞ እንዲለማ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በኮሪደር ልማቱ ላይ የወንዞች ዳርቻ ልማት ሲጨመር በአጠቃላይ የከተማችንን ተወዳዳሪነት እንደ ሃገር የጀመርናቸዉን እነዚህን የልማት ዶቶች ያልናቸዉ የፓርኮች ልማት እርስ በእርስ አገናኝቶ የከተማችንን ከፍታ የሚያልቅ ይሆናል፡፡ መንግስታችን ዜጋ ተኮር መርህን ስለሚከተል በመጀመሪያ ዙር ብቻ ከ4300 በላይ በማይመች ሁኔታ ሲኖሩ ለነበሩ ዜጎች ባለሃብቱን አስተባብረን ባስገነባናቸዉ ቤቶች እንዲገቡ አድርገናል፤በዚህም የህይወት ለውጥ አምጥተናል፡፡ በርካታ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የስራ እድል ተፈጥሮላቸዉ በሚሊዮኖች ገንዘብ አግኝተዉበታል፡፡ የከተማችን ኢንዱስትሪዎች ተነቃቅተዋል፤በተለይ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪዉ በከፍተኛ ሁኔታ ተነቃቅቷል፡፡ በፍጥነት ልምድ የተወሰደበት ነዉ፤ስለዚህ ስኬት የተመዘገበበት ሰባት ሀያ አራት በሚል የስራ ባህል የተተካበት ለቀጣይ ክልሎች እንደሃገርም ልምድና ባህል አድርገን እንድንቀጥልበት የሚያስችለን ነዉ፡፡ በመጀመሪያው ዙር ከ50 ሺህ በላይ የጊዜያዊና ቋሚ የስራ እድል የተፈጠረበት ተጨማሪ ስኬት ነው፡፡
በተጨማሪም በኮሪደር ልማት ወቅት ከተለያዩ አከባቢዎች የሚነሱ አሉና በተጨባጭ በሚኖሩበት አካባቢ የመሰረቱት ማህበራዊ ህይወት ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ሲነሱ ቀድሞ የነበራቸው ማህበራዊ ህይወት ሊናድ ይችላል፣ ይህንን ከማስጠበቅ አንፃር የዜጎች አብሮነትና ማህበራዊ አንድነት መስተጋብርን ከመጠበቅ አንፃር ምን ያህል እየተሰራ ነው ? ለሚለው ጥያቄ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ስራ አስከያጅ ኢንጅነር ወንደሰን ሴታ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት 8 ቦታዎችን ያካተተ ሲሆን፤ ሁለቱ የወንዝ ዳርቻ ቦታዎች ናቸው፡፡ በተጀመረበት ፍጥነት በሰባት ሃያ አራት የስራ ባህል እየተከናወነ ሲሆን፤ አንዳንድ ከልማት ተነሺዎች ጋር የሚሰነዘሩ ሀሳቦች በመሰረታዊነት መመለስ ስለሚገባቸው ኢንጅነር ወንድሙ ኬታ የሚሉት አለ፡- “የሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ከተጀመረ በኋላ ተነሺዎችን በምናስተናግድበት ወቅት ከአንድ አካባቢ የተነሱ ሰዎችን ወደ አንድ አካባቢ እንዲሄዱ አድርገናል፡፡ የነበራቸውም ማህበራዊ መስተጋብር ሳይጠፋ የተሻለ መሰረተ ልማት ወደ ተሟላበት ንጹህና ፅዱ ወደ ሆነ ቦታ ነው እንዲሄዱ የተደረገው፡፡ በዚህ ሂደት በዋናነት ታሳቢ የተደረገው አቅመ ደካሞች፣ አካል ጉዳተኞችና የተለያዩ የጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች ካሉ ቅድሚያ በመስጠት ነው፡፡ በድልድሉ ሂደት የተለያየ አድልኦ እንዳይኖር በእጣ የሚስተናገዱበትና የሚደመጡበት ስራ ተሰርቷል፡፡ ይህ በመሆኑ ምክንያት ነው የአዲስ አበባ ነዋሪ በልማቱ ከጎናችን መቆሙን ያሳየን፡፡
ህዝቡ ካሳ ሳይገመትለት መተማመኛ ደብዳቤ ሳይሰጠው የግል አጥሩን አስጠግቷል፣ ቤቱን አፍርሷል ይህ የሆነበት ምክንያት ወደ ህዝብ ቀረብ ብለን ያለውን ችግር ለመረዳት በመጣራችን ነው፤ በቀጣይም በምንሰራቸው ስራዎች ከህዝቡ ጋር አብረን የምንሰራ ይሆናል፡፡
በመጀመሪያ ዙር የነበሩ ክፍተቶችን ትምህርት ወስደን በ2ኛው ዙር የኮሪደር ልማት በመሙላት የገባንበትን በበቂ ዝግጅት በሚባል መልኩ መስራት እንችላለን፡፡” በማለት ገልጸውታል፡፡
በመነሻችን እንደጠቀስነው ይህ የኮሪደር ልማት ቀጣይነት ያለው፣ የበርካታ ዜጎችን ህይወት በመለወጥ ከተማዋን ዘመናዊ ከተባሉ አቻ ከተሞች ተርታ የሚያሰልፍ መሆኑንም በርካቶች ተስማምተውበታል፤መስክረውለታልም፡፡
Published in
ባህል