Sunday, 17 November 2024 00:00

የሞት ማሽኑ ቪክቶር ቦት

Written by  በዮናስ ታረቀኝ
Rate this item
(0 votes)

‹‹ጦርነትን ወይም ፖለቲካን ማካሄድ ቀላል ነገር ነው፡፡ ከእርሱ ጋር በነፃነት መኖር ግን…››

በዮናስ ታረቀኝ

 

እ.ኤ.አ በ 2008 ዓ.ም ታይላንድ ውስጥ የተያዘው የዓለማችን ቁጥር አንድ የጦር መሳሪያ ነጋዴ የሆነው የቪክቶር ቦት ጉዳይ በወቅቱ አነጋጋሪ ነበር፡፡ ቪክቶር ቦት በ2010 ለአሜሪካኖች ተላልፎ ከተሰጠ በኋላ ኒውዮርክ በተሰየመው ችሎት የ25 ዓመት ፅኑ እስራት ተፈርዶበታል፡፡ ፍርዱን ተከትሎ አሜሪካና ሩሲያ ከፍተኛ እሰጥ እገባ ውስጥ ገብተው ነበር፡፡
ቪክቶር ቦት በበኩሉ፤ ‹‹ጥፋተኛ አይደለሁም፣ ማንንም ሰው ለመግደል፣ ለማንም መሳሪያ መሸጥን አቅጄው አላውቅም፣ እውነቱን የሚያውቀው እግዚአብሔር ነው፡፡›› በማለት መልስ ሰጥቷል፡፡
በጀርመን አገር እየታተመ የሚወጣው ዙዊድ ዶቸ ሳይቱንግ መጽሔት በ2003 ዓ.ም በጥቅምት ወር እትሙ ስለ ቪክቶር ቦት አንድ ጽሑፍ አስነብቦን ነበር፡፡ ጸሐፊው ፔተር ላንደስማን ጽሑፉን ‹‹ሞት አምጪው›› በሚል ርእስ እንዲህ ነበር ያሰፈረው፡፡
‹‹ለመገዳደል ምክንያቱ የጦር መሳሪያ ሳይሆን መሳሪያውን የሚጠቀሙበት ሰዎች ናቸው፡፡›› ይህን ያለው የዚያን ጊዜው የ36 ዓመቱ ቪክቶር ቦት ነበር፡፡
ሞስኮ ሬነሰንስ ሆቴል እንድንገናኝ ሃሳቡን ያቀረበልኝ እራሱ ቪክቶር ነው፡፡ ሆቴሉ አንድ ወጥ ህንፃ ያለው ሲሆን 3ኛ ደረጃ በሚባሉ ሴተኛ አዳሪዎችና ጠቆር ያለ ሙሉ ልብስ በለበሱ ወንዶች የተሞላ ነው፡፡ የተቀጣጠርንበት ሰዓት እስኪደርስ ድረስ ኮሪደሩ ላይ ከሌሎች ሁለት ሰዎች ጋር ሆኜ እየተጠባበቅኩት ነው፡፡ እነሱም ብዛት ላላቸው የወንድሙ የአየር በረራ አገልግሎት ድርጅቶች የሚሰራው የቦት ታላቅ ወንድም ሰርጌይ እና በትውልድ ሶሪያዊ የሆነው የቀድሞው የንግድ ሸሪኩና እራሱን የቪክቶር ጓደኛና ወንድም ብሎ የሰየመው ሰዎች ናቸው፡፡
እየጠበቅነው እያለ ሶሪያዊው ቦትን ስለ ንግዱ እንቅስቃሴ አጥብቄ ከመጠየቅ እንድቆጠብ ለማድረግ ሙከራ እያደረገ ቆየ፡፡ ማወቅ የማይገቡኝ ብዙ ነገሮች እንዳሉ፣ ያለበለዚያ ለእኔ አደገኛ እንደሚሆን፣ ሊገድሉኝ ሁሉ እንደሚችሉና ከመግደላቸው በፊት ደግሞ ብዙ ሊያሰቃዩኝ እንደሚችሉ ነገረኝ፡፡ ከዚያም ወደ በሩ አቅጣጫ እያመለከተ ‹‹ያው ቪክቶር መጣ›› አለኝ፡፡
ቦት ሜትር ከሰማንያ ቁመት ያለው ሲሆን፣ በጣም ወፍራም ነው፡፡ በፍጥነት ኮሪደሩን አቋረጠና ወደ እኔ በመምጣት በአንገቱ ሰላምታ ሰጥቶኝ ጨበጠኝ፡፡ እንደተቀመጠ የያዘውን ‹‹ባይንደር›› ጉልበቱ ላይ በማስቀመጥ እየደባበሰ ሰገግ ብሎ ‹‹ከመስከረም አስራ አንዱ ጥቃት በኋላ የተገነዘብኩት ነገር ቢኖር ከኦሳማን ቀጥሎ ሁለተኛው ሰው መሆኔን ነው፡፡›› አለ፡፡ እውነታው ግን የህይወት ታሪኩ ከዚህም የበለጠ ውስብስብ መሆኑ ነው፡፡ ‹‹ደንበኞቼ መንግሥታት ናቸው፡፡›› ሲል በመደነቅ አፌን ያዝኩኝ፡፡ በመቀጠልም፣ ‹‹ሁሉንም ነገር ዘርዝሬ ከነገርኩህ እዚህ ላይ በጥይት እበረቀሳለሁ፡፡›› በማለት በጣቱ ግንባሩን አመለከተኝ፡፡
ሲ.አይ.ኤ እና የእንግሊዝ የስለላ ድርጅት ኤም 16፣ እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ አጋማሽ ላይ የቪክቶር ቦት አውሮፕላኖች ወደ አፍሪካ መብረር ሲጀምሩ ሁኔታውን ደርሰውበት ነበር፡፡ መጀመሪያ ላይ ሲያመላልሱ የነበሩት አበቦችንና የተዘጋጁ ዶሮዎችን ነበር፡፡ በመቀጠል አልማዞችንና የማዕድን ማውጫ ማሽኖችን፣ ክላሽንኮቮችን፣ ሄሊኮፕተሮችንና ይባስ ብለው የተባበሩት መንግስታትን ሰማያዊ የብረት ቆብና የአፍሪካ አማፅያን መሪዎችን ሆነ፡፡ ቦት ሁሌ እንደ ኮንጎና ላይቤሪያ ባሉ የውጊያ ቀጠናዎች ስሙ እንደተነሳ ነው፡፡
የቪክቶር ቦት ማንነት የታወቀው በአንድ ጫካ ውስጥ በተነሳው ፎቶ አማካኝነት ነበር፡፡ ቀስ በቀስም በመሳሪያ ዝውውር ውስጥ ሰፊ ድርሻ እንዳለው በስለላ ድርጅቶች ዘንድ ታወቀ፡፡ ይሁን እንጂ የአሜሪካ የስለላ ድርጅት በትክክል ስለሁኔታው ያወቀው እ.ኤ.አ በ2000 ዓ.ም በጋ ላይ ነበር፡፡ ቦት መንግሥትን ከሚቃወሙ ድርጅቶች ጋር ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ መሳሪያ ከሚሸጡ መንግሥታት ጋር ጭምር ነው የሚሰራው፡፡
በአሜሪካ የደህንነት መስሪያ ቤት የአፍሪካ መምሪያ ኃላፊ የሆነው ጌይል ስሚዝ፤ ‹‹ቦት ብሩህ የሆነ ጭንቅላት ያለው ነው፡፡ ህጋዊ የሆኑ ንግዶችን ቢያካሂድ ኖሮ በዓለም ካሉት ምርጥ ነጋዴዎች አንዱ በሆነ ነበር፡፡ የሚደንቀው ግን አጥፊ መሆኑ ነው፡፡›› ሲል መስክሮለታል፡፡
ቦት የሚንቀሳቀሰው ከአሜሪካ ውጭ በመሆኑ የደህንነት መስሪያ ቤቱ ክስ ሊመሰርትበት ህጋዊ ፍቃድ አልነበረውም፡፡ ይሁን እንጂ ከሌሎች ሰባት አገሮች የስለላ ምንጮች ከተገኘ እገዛና በካቢኔ ደረጃ ከተደረጉ የዲፕሎማቶች ስብሰባ በመነሳት ድርጊቱን እንዲያቆም ሙከራ አድርጓል፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ ቤልጅየም በቦት ላይ የእስር ትእዛዝ አስተላለፈች፡፡
ቤልጂየም የእስር ትእዛዙን ያስተላለፈችው በመሳሪያ ሽያጭ ምክንያት ሳይሆን በመሬቷ ላይ ባካሄደው የገንዘብና የአልማዝ ዝውውር ወንጀል ነበር፡፡ ሆኖም ግን በቁጥጥሯ ስር ልታውለው አልተቻላትም፡፡ ቦት ሁሌም ከአለም አቀፍ ፍርድ እንደተሰወረ ነበር፡፡ ከኦሳማን ቢን ላደን የሚለየው ሁሉም ሰው እያየው ሞስኮ ውስጥ መኖሩና በቀድሞው የኮሚዩኒስት ስርዓት ጥበቃ የሚደረግለት መሆኑ ነው፡፡ ‹‹ይሄ ሁሉ ነገር የተጀመረው በአበባ ሽያጭ ነው፡፡›› ይላል በትውልድ ሶሪያዊ የሆነው ሪቻርድ ቺቻክሊ ስለ ቦት ሲናገር፤ ‹‹ቦት የአካባቢ ጥበቃ ምን እንደሆነ የገባው፣ ለተፈጥሮ ደን የሚቆረቆር ነው፡፡›› በማለት ያክላል፡፡
ቦት ወደ አንዱ የአፍሪካ አገር ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት ሲሄድ እዛ ያሉ የዱር እንሰሳትን ፎቶ ያነሳል፡፡ ኋላ ቀር የሆኑ ብሔረሰቦችን ያጠናል፡፡ ‹‹በእነዚህ በተረሱ ቦታዎች የሰው ልጅ እየኖርኩኝ ነው የሚል ስሜት ይሰማዋል፡፡ ይህም የተፈጥሮ አንዱ ገፅታ ነው፡፡›› ይላል ቦት፡፡
አሁን ከሆቴሉ ወጥተን ፒሳ የሚበሉና ቮድካ የሚጠጡ ሰዎች በሞሉበት አንድ የጣሊያን ሬስቶራንት ውስጥ እንገኛለን፡፡ ቦት የካሮት ጭማቂና ሰላጣ አዘዘ፡፡ የሚመገበው አትክልት ብቻ ነው፡፡ የሚያደንቃቸው ፀሐፊዎች ፓውሎ ኮልሆ እና ካርሎስ ካስታኔዳ መሆናቸውን፣ ማድረግ የሚፈልገው ነገር በአንዱ ሄሊኮፕተሩ ሰሜናዊ ሩሲያ አርክቲክ ላይ እየበረረ ተፈጥሮን በፊልም መቅረፅ እንደሆነ አወራልኝ፡፡ ለምን እኔን ማግኘት እንደፈለገ እስካሁን አልገባኝም፡፡ ባንድ በኩል ስለሱ በሚወራው ነገር ኩራት ይሰማዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ማድበስበስ ይፈልጋል፡፡
ቺቻክሊ ስለ ቦት ሙያ ማውራት ቀጠለ፡፡ ‹‹ንግዱን በ25 እጥፍ አሳድጓል፡፡ በ1992 ዓ.ም በ120›000 ዶላር ሦስት አንቶኖቭ አውሮፕላኖችን በመግዛት ሞስኮ ውስጥ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ከፈተ፡፡ በ1993 ዓ.ም የድርጅቱን ቅርንጫፍ በተባባሩት አረብ ኤምሬትስ መሠረተ፡፡ በዚያን ጊዜ አዳዲስ የሩሲያ ሃብታሞች ከቀረጥ ነፃ የሆነ ግብይት ለመፈፀም በብዛት ወደ ዱባይ ይመላለሱ ነበር፡፡
‹‹ሁሉንም ነገር መግዛት ይፈልጋሉ፡፡ ከእርሳስ ጀምሮ እስከ የኤሌክትሪክ እቃዎች ጭምር፡፡ ከቤትና የቢሮ እቃዎች እስከ መኪናዎች፡፡ በትራንስፖርት ስራ ውስጥ የቱ ጋ ክፍተት እንዳለ አውቃለሁ፡፡ እናም ለሁሉም ነገር ምላሽ እሰጣለሁ፡፡›› ይላል ቦት ስለራሱ፡፡
‹‹ቪክቶር አንድን የአበባ እስር በሁለት ዶላር ይገዛና ዱባይ ወስዶ በመቶ ዶላር ይሸጣል፡፡ በአንድ በረራ ሃያ ቶን ያህል ያጓጉዛል፡፡ ገንዘቡን ራሱን ከማተም የበለጠ የተሻለ ነበር፡፡›› ይሄን የሚለው ቺቻክሊ ነው፡፡ ቦት የአየር ማረፊያ ቁጥጥሩ የላላ ነው በሚል የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ሌላ ከተማ ወደሆነችው ሻርጂያ አዛወረ፡፡ ከቺቻክሊ ጋርም የተዋወቀው እዚያ ነበር፡፡ ቺቻክሊ በወቅቱ የሻርጂያ ነፃ የገበያ ቀጠና መሥራችና ዳይሬክተር ነበር፡፡
በ1996 ዓ.ም ቦት በኤምሬት ከሚገኙ 160 የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ሁሉ ትልቁ ሆነ፡፡ ‹‹የድርጅቴን መረብ በአፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅም መዘርጋት ፈልጌ ነበር፡፡ የእቃና የመንገደኞች ትልቅ የበረራ መስመር መሆን ይኖርበታል፡፡ ልክ እንደ ቨርጂን አትላንቲክ፡፡›› የሚለው ቦት፤ በንፅፅር ስለ ቀድሞ ድርጅቱ በግልፅ ያወራል፡፡ ግን ወሬው የግል ህይወቱን የሚመለከት ከሆነ ይቆጠባል፡፡ ‹‹የግል ሕይወት ለህዝብ በግልፅ ሲቀርብ ያማል›› የሚል እምነት አለው፡፡
ቦት የተወለደው ጃንዋሪ 13 ቀን 1967 ዓ.ም በደሻንቤ ታጃኪስታን ከአንድ ሩሲያዊ ቤተሰብ ነው፡፡ ሞስኮ ውስጥ የውጭ ቋንቋ ተናጋሪዎች ወታደራዊ ተቋም ውስጥ ተምሯል፡፡ ከወታደራዊ አካዳሚው በኢኮኖሚክስ ተመርቋል፡፡ ስድስት ቋንቋዎችን ይናገራል፡፡ እስከ 1991 ዓ.ም ድረስ በአንድ የሩሲያ አየር ኃይል ሬጅመንት ውስጥ አገልግሏል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱን ዓመት የእርስ በእርስ ጦርነቱ ማብቂያ አካባቢ ሞዛምቢክ ውስጥ ነው ያገለገለው፡፡ በመቀጠል አንጎላ ውስጥ ለኬጂቢ ሠርቷል፡፡ እሱ ግን በፍፁም ከኬጂቢ ጋር ግንኙነት ኖሮት እንደማያውቅ ነው የሚናገረው፡፡ በ1995 ዓ.ም ንግዱን ወደ ቤልጂየም፣ ከዚያም ወደ ኦዴሳ አስፋፋ፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ባለስልጣናትና የአፍሪካ አማፂያን መሪዎች የሚፈልጉትን ነገር በቀላሉና በፍጥነት ማቅረብ የጀመረው፡፡ የሚያቀርበው ግን አበቦችን ወይም ደግሞ የተዘጋጁ ዶሮዎችን አልነበረም፡፡
በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የመሳሪያ ንግድ አልፎ አልፎ ከዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች ጋር ተያያዥነት ያለው ነበር፡፡ በዚያን ወቅት መሳሪያ አዘዋዋሪዎቹ የኃያላን መንግስታቱ ዋሽንግተንና ሞስኮ ጥቅም ተካፋዮች የሆኑ የተለያዩ የጦርነት አራጋቢ ተወካዮች ነበሩ፡፡ ዛሬም ቢሆን ጥቂት ነጋዴዎች ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር በመተባባር በአይዶሎጂ ለሚመስሏቸው አገሮች መሳሪዎችን ይሸጣሉ፡፡ በእርግጥ አብዛኛዎቹ ይሉኝታም ሆነ ፖለቲካዊ ምክንያት የማያውቁ፣ ከንግዳቸው ትርፍን ማካበት ብቻ የሚፈልጉ ነፃ ኩባንያዎች ናቸው፡፡
ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃት በኋላ በሶቭየት ሕብረት ጦር ሰራዊት ውስጥ ረብሻ ነገሰ፡፡ የታላቁ የቀዩ ጦር ተምሳሌት አብዛኛው ክፍል ከሶቭየት ሕብረት የተገነጠሉ ሪፐብሊኮች ዘንድ ተሸኙ፡፡ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ጄኔራሎቹና ፖለቲከኞቹ በከፍተኛ ዋጋ መሳሪያዎቹን ቸበቸቡዋቸው፡፡ ዩክሬይን ከሩሲያ ቀጥሎ ከሁሉም ሪፐብሊኮች በላይ የጦር መሳሪያዎች ባለቤት ነበረች፡፡ በሷ ግዛት ውስጥ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ሊታጠቋቸው የሚችሉ ‹‹ኮንቬንሽናል›› መሳሪዎች ነበሩ፡፡ የአቶሚክ መሳሪዎቹን ግን የዩክሬይን መንግስት ለሩሲያ አስረክቦ ነበር፡፡
ከ1992 – 1998 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ 32 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ መሳሪያዎች ከጦር መሳሪያ ዴፖ ውስጥ ጠፍተዋል፡፡ ይህም ዩክሬይን ለመሳሪያ አቅራቢዎች መረብ አስተማማኝ የመሳሪያ አቅራቢ ምንጭ እንድትሆን አደረጋት፡፡ ስልጣን በጥቂቶች እጅ ላይ ነበር፡፡ የውጭ ንግድ ቁጥጥር፣ ነፃ ፍርድ ቤት የለም፡፡ ቁጥጥር የሌለበት ረዥም ድንበር፣ ግዙፍ ወታደራዊ ተቋሞች፣ ብዛት ያላቸው ትናንሽ አውሮፕላን ማረፊያዎች፣ ብዛት ያላቸው አውሮፕላኖች ያሉባት ነበረች፤ ዩክሬይን፡፡ የአለም አቀፍ ወንጀለኞች ማዕከልና ማንም ሰው የፈለገውን መግዛት የሚችልባት አገር፡፡
ደንበኞቿ ከኢራቅ፣ ከሶማሊያ፣ ከኢራን፣ ከፓኪስታን የሚመጡ ነበሩ፡፡ ምናልባትም እነዚህ ሰዎች ከሰሜን ኮሪያ እንዲሁም ከአልቃይዳ መሳሪያዎችን ለታሊባን ለማቀበል የሚተጉ ይሆናሉ፡፡ የዝውውር መንገዱን ደግሞ እንደ ቪክቶር ቦት ያሉ ሰዎች ያቀላጥፉታል፡፡ ህገ ወጡ የንግድ እንቅስቃሴ ሕጋዊ በሚመስሉ ንግዶች ይሸፈናል፡፡ ብዙውን ጊዜ በሰንሰለቱ የመጀመሪያ ረድፍ የሚገኘው አንድ የጦር ሠራዊት አባል ነው፡፡ አንዱ መኮንን ያላየ እንዲመስል በጉርሻ ይደለላል፡፡ ወታደሮች በዴፖው ውስጥ የሚደረገውን ጨዋታ እንዲጫወቱ መደለያ ይወሸቅላቸዋል፡፡
ለምሳሌ የመሳሪያ መያዣ ሳጥኖቹ ትኩስ የአፕል ፍሬዎች የሚል ፅሁፍ ይለጠፍባቸዋል፡፡ ወይም ደግሞ ሆን ተብሎ በታቀደ ‹ነዳጅ መሙላት› የሚል ሰበብ ግራውንድ ቴክኒሽያኑ ጭነቱ በፍጥነት እንዲቀያየር ያደርጋል፡፡ አብዛኛዎቹ አውሮፕላኖች ሲነሱ ወይም ደግሞ ሲያርፉ ከነበራቸው ሌላ በሌላ ቁጥር እንዲመዘገቡ ይደረጋል፡፡ እንበልና ከአቴንስ ወደ ፔሩ ይበራል የተባለው አውሮፕላን ባልታወቀ የበረራ መስመር ዞሮ አፍሪካ ውስጥ ወዳለ የጦርነት ቀጠና ይበራል፡፡ ገንዘቡ በፖስታ አገልግሎት ድርጅቶች ወዲያና ወዲህ ይላካል፡፡ ወይም ደግሞ ህጋዊ ንግድ የሚያከናውኑ ወደ ሚመስሉ የአየር መጓጓዣ አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎች ይተላለፋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የመሳሪዎቹ ክፍያ በቀላሉ በጆንያ ሙሉ ጥሬ ገንዘብ ወይም ደግሞ በካልሲ ሙሉ አልማዝ ይፈፀማል፡፡
‹‹መሳሪያ መግዛትና ማጓጓዝ ሴቶችንና አደንዛዥ እፆችን ከማዘዋወር የበለጠ አስቸጋሪ ነው፡፡ በዓለም ላይ ይህንን ንግድ እንደ ቦት በብቃት የሚያካሂድ ማንም የለም፡፡›› በብሔራዊ የደህንንት ቢሮ እንደ ዳይሬክተር ሆኖ ሚስጢራዊ ክትትልን የሚያቀናጀው ሊ.ኤስ. ወሎስኪ ነው ይህን የሚለን፡፡
በሚቀጥለው ቀን ከቦትና ከወንድሙ ጋር እያለሁ ጥቂት ወረቀቶች አውጥቼ ጠረጴዛ ላይ አስቀመጥኩ፡፡ ወረቀቶቹ ለመሳሪያ ንግድ የተከፈሉ ደረሰኞችን የሚያሳይ ከአንድ የአውሮፓ የስለላ ድርጅት ያገኘኋቸው ኮፒዎች ነበሩ፡፡ ደብዳቤው በአድራሻ የተጻፈው ለሰን ኤር ጄኔራል ትሬዲንግ በሚል ሻርጂያ ለሚገኘው የቦት ኩባንያ ሲሆን፤ የተላለፈው ክፍያም ለሁለት የሩሲያ ስሪት ኤም አይ 8ቲ ሄሊኮፕተሮች፣ ለአራት የሮኬት ማስወንጨፊያዎችና ለሦስት ሞርተሮች ግዢ 1›900›000 ዶላር ነበር፡፡ በመሰረቱ ወደ አይቮሪኮስት መጓጓዝ የነበረባቸው ቢሆንም እንደ የስለላ ድርጅቶቹ ዘገባ ከሆነ የተራገፉት ላይቤሪያ ነው፡፡ ቦት ወረቀቶቹን መልከት አደረገና፣ ‹‹ውሸት ነው›› አለኝ ባጭሩ፡፡ ‹‹እርግጥ ሮኬቶችንና የተኩስ መሳሪያዎችን በማሻሻል የውጊያ ሄሊኮፕተር እንዲሆኑ አድርጎ መስራት ይቻላል›› አለ፡፡
የአሜሪካ ከፍተኛ የመንግሥታዊ መሥሪያ ቤት፣ ቦትን ከዝነኛው መሳሪያ ነጋዴ ከአሌክሳንደር ኢስላሞቭና ከዩክሬኒያዊው የንግድ ባላጋራው ሊዮኖድ ሚኒ ጋር ያመሳስለዋል፡፡ ለሁለቱ ሄሊኮፕተሮች የማጓጓዣ ሰነድ እንዳለው ጠየቅኩት፡፡ ‹‹ደንበኞቼ ናቸው፤ ማን ያገባዋል? የጉዞ ሰነዱ እንዴት እንደተዘጋጀ የሚያውቁት እነሱ ናቸው፡፡ የኔ ሥራ አይደለም! ሳጥኖቹን እየከፈቱ ውስጡ ምን እንዳለ ማየት የፓይለቶቹ ስራ እንዳልሆነ ሁሉ›› አለ፡፡
እውነታው ግን ፓይለቶች የሚያጓጓዙትን ዕቃ የማወቅ የውዴታ ግዴታ ያለባቸው መሆኑ ነው፡፡ በመቀጠል ‹‹ጥያቄው መሆን ያለበት መሳሪያ አጓጉዘሃል አላጓጓዝክም ሳይሆን መሳሪያ ማጓጓዝ ስህተቱ ምኑ ላይ ነው የሚለው መሆን አለበት፡፡ ህገወጥ መሳሪዎች ማለት ምን ማለት ነው? አማፂያን አንድን አውሮፕላን ማረፊያ፣ አንድን ከተማ ተቆጣጥረው ወደ እዛ እንድትገባ ፈቃድ የሚሰጡህ ከሆነ ህገ ወጥነቱ ምኑ ላይ ነው? ቀጥሎ ደግሞ አማፂያኑ መንግስት ይሆናሉ፡፡›› በማለት ይሞግታል፡፡ ይሁን እንጂ መሳሪያ የሚያቀብላቸው አገሮች በተባበሩት መንግሥታት መሳሪያ እንዳያስገቡ እገዳ የተጣለባቸው መሆናቸውን አያነሳም፡፡ ወይም አማፂያኑ ወደ ስልጣን ለመምጣት ሲሉ ሕዝብ እንደሚፈጁ፡፡
‹‹ችግሩ ያለው ሲስተሙ ላይ ነው፡፡›› ይላል ቦት፤ ‹‹የጦር መሳሪያዎች ልክ እንደ መድኃኒቶች ናቸው፡፡ በትክክል ካሰብነው መድኃኒቶችም አደገኛ ሊሆኑ ይችላሉና፡፡ ስለመግደሉ መጠየቅ ያለበት መሳሪያው አይደለም፡፡ የሚጠቀሙበት ሰዎች እንጂ፡፡››
ቦት ይህን ተናግሮ ሲያበቃ ፀጥ አለ፡፡ ራሱን የሚያየው ሸቀጡን ለገበያ እንደሚያቀርብ ነጋዴ ብቻ ነው፡፡ በደንብ ላጤነው በእርግጥም አውነት አለው፡፡ ከአደንዛዥ እፅ ነጋዴዎች ራሱን በአንድ መሰረታዊ ነገር ይለያል፡፡ የሚሰራው ስራ የማያስደስት ነገር ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ የግድ ወንጀል ነው ብሎ ማለት አያስደፍርም፡፡ ለምን ቢሉ ስለመሳሪያ ሽያጭ የሚደነግጉ ብዙ ሕጎች የሉም፡፡
ከ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሳሪያ አቀብለሃል በሚል የከሰሰው አንድም የመሳሪያ ነጋዴ የለም፡፡ የሚገርመው ነገር አሜሪካኖች በዓለም ጠንካራውን ሕግ የደነገጉ ቢሆንም አንድንም የመሳሪያ ነጋዴ ለፍርድ አቅርበው አያውቁም፡፡ (ቦት የመጀመሪያው ይሆንን?)
‹‹ደንቦችን እያወጡ የመሳሪያ ሽያጩን የሚያመቻቹት በተወሰነ መልኩ ሆን ብለው ይመስላል፡፡›› ይለናል የሰብአዊ መብት ጠባቂ የሆነው ሊዛ ሚሲል፡፡ ከሌላ፣ ከሆነ ቦታ የሚመጣ እስከሆነ ድረስ መሳሪያ ማስተላለፍን እያንዳንዱ አገር እንደ ችግር እንደማያየው ነጋዴዎቹ እርግጠኞች ናቸው፡፡ ነጋዴው እስካልተከለከለ ድረስ እንዴት አድርጎ መከላከል ይቻላል? ለምንስ የሰው ልጅ እንዳይገዛ ይከለከላል?
የላይቤሪያውያን ህፃናት ወታደሮችን ለተመለከተ ጥያቄው የተማረ ሳይሆን ትምህርት የጎደለው ሰው የሰነዘረው ሊመስል ይችላል፡፡ ስለ መሳሪያዎች ሲነሳ ከሰብዓዊ መብት የበለጠ ሌሎች ፍላጎቶች ወሳኝ ሆነው ይገኛሉ፡፡ አሜሪካ ሌላው የዓለም ክፍል አንድ ላይ ሆኖ ከሚሸጠው የበለጠ የጦር መሳሪያዎችን ትሸጣለች፡፡ ፋብሪካዎቹ ሕገ ወጥም ይሁን ሕጋዊ ምርቶቻቸው ገበያውን እንዲቆጣጠርላቸው ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው፡፡ በተጨማሪም የጦር መሳሪያ ነጋዴዎች የሚንቀሳቀሱት ከመንግሥታት ጂኦ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አኳያ ነው፡፡ ስለዚህ ሁኔታውን ለመከላከል ግፊት የማድረጋቸው ነገር አጠራጣሪ ነው፡፡
ማንም ከሚሰማው በላይ መክፈል ለሚችሉት ሁሉ ቦት አፍሪካ ውስጥ ለእያንዳንዱ አገር መሳሪያ ሸጧል፡፡ የአፍጋኒስታኑ ግን የተለየ ነበር፡፡ እዚያ በ19ኛው መቶ አጋማሽ ከታሊባኖች ጋር ስልጣን ለመያዝ ሲዋጋ የነበረውንና የመንግሥት ወታደሮች ቡድን የሆነውን ራባኒን ነው ያስታጠቀው፡፡
‹‹ራባኒን ነበር የምደግፈው፡፡ ታሊባን ማን እንደነበረ በደንብ ስለማላውቅ ለኔ ራባኒ ብቸኛው የዚያች አገር ተስፋ ነበር፡፡›› ይላል ቦት፡፡ ቦት እንደሚለው በቀን አራት ጊዜ የጦር መሣሪያዎችን፣ የግንኙነትና ኤሌክትሮኒክስ መሣሪዎችን፣ የመንግሥት መቀመጫ ወደ ሆነው ጃላላባድ ያመላልስ ነበር፡፡ በኦገስት 1995 ዓ.ም ካቡል በታሊባኖች ቁጥጥር ስር ከመውደቋ 12 ወራት ቀደም ብሎ አንዱ አውሮፕላኑ ተያዘበት፡፡ የማጓጓዣ አውሮፕላኑን አስገድደው በታሊባኖች ይዞታ ስር ወደነበረው ካንዳሃር እንዲያርፍ ያደረጉት የውጊያ ጀቶች ናቸው፡፡ አውሮፕላኑና ጭነቱ ተወረሱ፡፡ ሰባቱ የአውሮፕላኑ አባላት ከአንድ ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ ታሰሩ፡፡
ቦት እንደነገረኝ፤ ስለታሰሩ አባላቱ ለመደራደር ብዙ ጊዜ ወደ ካንዳሃር በሯል፡፡ ግን ብቻውን አልነበረም፡፡ ከሩሲያ መንግሥት የተወከሉ ሰዎችም አብረውት ነበሩ፡፡ ድርድሩ ውጤት አልባ ነበር፡፡ በመጨረሻ ግን እስካሁን ግልፅ ባልሆነ ሁኔታ ሰዎቹ በነፃ ተለቀቁ፡፡
‹‹እንዴት?››
‹‹ሰዎች አስመለጧቸው›› አለ ቦት፡፡
‹‹የሩሲያ መንግሥት ነው እስረኞቹን የማስመለጥ ዘመቻ ያካሄደው?›› ጠየቅኩ፡፡ በመጀመሪያ ቦት ምንም አልመለሰም፡፡ በመቀጠል ግን ቁጣ ያዘለ በሚመስል መልኩ፣ ‹‹እስካሁን ከትልቅ ባህር ውስጥ በማንኪያ ስትጨልፍ ነበር፡፡ ኃያላን አሉ…›› ቃላቱን ሳይጨርሰው አቆመ፡፡
በእርሱ፣ በመንግሥታትና በደንበኞቹ መካካል ስላለው የሦስትዮሽ ግንኙነት ይፋ እንዲያወጣ ግፊቴ ብዙ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ መልሱ ሁለታችንንም ለአደጋ ሊያጋልጥ ስለሚችል ከመናገር ተቆጠበ፡፡
በሦስተኛው ቀን ማታ ባረፍኩበት የሞስኮ ከተማ ሆቴል የክፍሌ ስልክ ጮኸ፡፡ አንድ የወንድ ድምፅ፣ ‹‹እንደማስበው ከሆነ አንዳንድ ነገሮችን መነጋገር ያለብን ይመስለኛል›› አለ፡፡ ግራ ገባኝ፤ ቀዝቃዛ ድምፁ አስፈሪ ነው፤ ‹‹ነገ 11 ሰዓት ፑሽኪን አደባባይ ወዳለው ማክዶናልድ ትሄዳለህ፡፡ ሁለት ቡና ትገዛና ትቀመጣለህ፡፡ እኔም አገኝሃለሁ›› አለና ስልኩን ዘጋው፡፡
ከሰዓት በኋላ 11 ሰዓት ላይ እቦታው ደርሻለሁ፡፡ ቤቱ እድሜያቸው በአስራዎቹ ባሉ ሩሲያኖች ተሞልቷል፡፡ ቴክኖ ፖፕ ሙዚቃ በክፍሉ ውስጥ ይሰማል፡፡ ሳይረበሹ ለማውራት ምርጥና አመቺ ቦታ ነው፡፡ ቡናውን ጠረጴዛ ላይ አስቀምጬ መጠበቅ ጀመርኩኝ፡፡ ልክ 11፡02 ሰዓት ሲሆን ለቅፅበት ከእኔ በስተግራ አቅጣጫ መልከት አደረግኩና መልሼ ጠረጴዛዬ ላይ አቀረቀርኩ፡፡ ከእኔ ፊት ለፊት በአርባዎቹ መጀመሪያ የእድሜ ክልል የሚገኝ ሰው ተቀምጧል፡፡ ‹‹ስለ ቡናው አመሰግናለሁ፡፡›› አለኝ፡፡
ሰውዬው ራሱን አላስተዋወቀኝም፡፡ ስለመሳሪያ ንግድና እነማን ንግዱን እንደሚያንቀሳቅሱት ያለው እውቀት ግን ባለሙያ እንደሆነ ይመሰክራሉ፡፡ ከታላላቅ ነጋዴዎች መካከል በግልፅ የሚያውቀው ቦትን ብቻ መሆኑን ገለፀልኝ፡፡ ላይ ላዩን ነው እንጂ ወደ ውስጥ ገብቶ መቦርቦሩ አደገኛ እንደሆነ ወዲያው ግልፅ ሆነልኝ፡፡ የሩሲያውያንን የመሳሪያ ንግድ መቁጠር ያለብኝ ልክ እንደ አንድ እንከብል (ፒልስ) ነው፡፡ ቦት ደግሞ ከሚታየው የእንክብሉ መሸፈኛዎች አንዱ ነው፡፡ ሩሲያ ውስጥ ክሩን የሚመዙት ሰዎች ያሉት ቀለበት ውስጥ ነው፡፡ ‹‹እነሱን ታዲያ በፍፁም አታያቸውም፡፡›› አለኝ፡፡
ቦት በአንድ በኩል ለምን ማውራት እንደሚፈልግ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለምን ምላሱን እንደሚነክስ አሁን ይገባኝ ጀምሯል፡፡ በአንድ የወንጀል መዋቅር ውስጥ ከብዙዎቹ ጎማዎች አንዱ ሆኖ ሳለ ጥፋቶቹ ሁሉ እሱ ላይ የሚላከከብት መሆኑ ያሳዝነዋል፡፡ ቦት ስለዚህ መዋቅር ብዙ ማውራት አይችልም፡፡ ራሱ ብዙ ጊዜ እንደሚናገረው በጣም አደገኛ ነው፡፡
በሞስኮ የመጨረሻዬ በሆነው ምሽት፣ ቦት ከከተማ ወጣ ወዳለ አንድ ሬስቶራንት ጋበዘኝ፡፡ ጥቂት ቮድካ ከወሳሰደ በኋላ እንደ መፈላሰፍ አደረገው፡፡ ትንሽ ከተከዘ በኋላ፣ ‹‹ጦርነትን ወይም ፖለቲካን ማካሄድ ቀላል ነገር ነው፡፡ ከእርሱ ጋር በነፃነት መኖር ግን…›› አለ፡፡
ምግብ ከተመገብን በኋላ በጫካ ውስጥ አቋርጠን ወደ አንድ ምርጥ የተባለ የሩሲያ ባህላዊ ሳውና ባዝ አገልገሎት ወደሚሰጥ የግል ክለብ ተጓዝን፡፡ የሩሲያ ሰዎች ስለሆነ ነገር መወያየት ሲፈልጉ ወይም ስለሆነ ከባድ ነገር ለመነጋገር ዝግጀት ሲያደርጉ ወደ እዚህ ይመጣሉ፡፡ በእንፋሎቱ ከታጠቡ በኋላ ብቸኝነት ይሰማቸዋል፤ እናም ምንም ነገር አይደብቁም፡፡ ትዳራቸው ላይ ችግር ካለባቸው ወይም ወሲብ ከፈለጉ አንዲት ሴት ትላክላቸዋለች፡፡
ሳውና ውስጥ ያለው ሙቀት 75 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ነው፡፡ አንድ ሠራተኛ በባህር ዛፍ ቅጠል አሸት አሸት እያደረገን ነው፡፡ ሁለት ጊዜ በእንፋሎት ከታጠብን በኋላ ሶፋ ላይ ተቀመጥን፡፡
ቦት ስለ ሥነጽሑፍ እንዲሁም በአፍሪካ ውስጥ ስላሉ አነስተኛ ዝርያ ያላቸው እንሰሳት አወራልኝ፡፡ በጥግ በኩል የተሰቀለው ቴሌቪዥን ስለ ተፈጥሮ አንድ ፊልም እያሳየ ነበር፡፡ ለአንድ ሰዓት ያህል የጫካዎቹ አውሬዎች በአፍሪካ ሳቫና ውስጥ እንዴት እርስ በእርሳቸው እንደሚበላሉ ተመለከትን፡፡
ወገቡ ላይ ፎጣውን አሸርጦ ሲታይ ቦት ዓለምን ከጥፋት ማቆም የማይችል ሳይሆን ማቆም የማይፈልግ መስሎ ይታያል፡፡ ከሚሰራበት ከግዙፉ መዋቅር ጋር ሲነፃፀር ደግሞ በድንገት ትንሽና የማይታይ መስሎ ይታያል፡፡ በትክክል ከመሳሪያ ነጋዴዎቹ መካካል አንዱ እርሱ ከሆነና ሊያዝም ሆነ ሊቆም ካልቻለ፣ ትልቁ ዓለም አቀፍና ኢ-ሞራላዊ የሆነው የንግድ ዝውውር ምን ይነግረናል? ጨዋታው ውስጥ ስላሉት ነጋዴዎችም ሆነ መንግሥታት ኪስ ስለሚገባው ስፍር ቁጥር የሌለው ትርፍስ?
ሪቻርድ ቺቻክሊ ስለ ቦት የተናገረው ትዝ አለኝ፤ ‹‹እንደ ቦት ብዙ የፖለቲካ የግንኙነት መረብ ያለው ሰው የለም፡፡ ይሁን እንጂ እርሱ ዓለምን ለመለወጥ የሚፈልግ ሰው አይደለም፡፡››

Read 288 times