“ፍቅርዬ ሆ…”
ከዛሬ ስንትና ስንት ዓመታት በፊት… ፒያሳ እንደዛሬው ሳይኾን ባንድ ካፌ ቁጭ ብለን የባጡን የቆጡን እያወራን ነበር፡፡
“እኔ የምልሽ?”
“ወይየ?”
ቆይ ግን “ወይየ” የሚለውን ቃል የከረሜላ ያህል እሷ አፍ ላይ ለምንድን ነው የሚጣፍጠው? የምሬን እኮ ነው:: ምን አስዋሸኝ?
“ይሄ የታጠረው ሕንፃ መቼ ነው አልቆ የምናየው?”
ሁለት እጆቼን ይዛ ዐይን ዐይኔን እያየች፤ “እዚህ ጋ ወራጅ አለ” አለች:: “ጨዋታ ቀይር” ማለቷ ነው፡፡
“ወራጅ ነው ያልሽው እናቱ?”
“ውይ አዎ!” የውሸት ቁጣ፡፡
“ጫፍ ወይስ ተሻግሮ?”
“ዞሮ “
ሳቅ ሁካታ፡፡ ለቲራቲሩ ማን ብሎን? በሀገር ፍቅር ሰፈር ታድመን! ግን ግን ፍቅረኛን ቀጥሮ ስለ ሕንፃ ማውራት አሁን ምን ማለት ነው? የጤና ነው? እንኳን ወራጅ አራጅ አያስብልም?
እንደዚህ ነኝ እኔ:: ዘልዬ ቁም ነገር ላይ ጉብ አልልም፡፡ አሟሙቃለሁ፡፡ ዱብ፣ ዱብ፣ ዱብ፡፡ እንደ አበበ ቢቂላ ከፍ ዝቅ፣ አየር እንደመሳብ፣ እንደመንጠራራት፡፡ “አንድ አይቀመጥም፣ ሦስት አይጨለጥም” የሚለው የጠጪዎች ቋንቋ ለዚህ ቀን ሲኾን ‘ይለፈኝ’ እላለሁ፡፡ ሰውነትን ሳያፍታቱ መገለባበጥ መገልበጥ እንደሚያመጣ ጨዋታም እንዲያ መኾን አለበት፡፡ ‘ደርሶ ወደ ገደለው መግባት ሊገድለን ይችላል’ እላለሁ፡፡ ውሸቴን ነው፡፡ ዘጠኝ ዓመት በፍቅር ቆይተን ለምን እንደምፈራት አይገባኝም፡፡ “እውነተኛ ፍቅር ፍርሃት አያውቅም” የሚሉት ውሸተኛ ፍቅር የያዛቸው ብቻ ናቸው፡፡ አሁን ማ ይሙት የዶሮ ወጥ (ይቅርታ የሽንኩርት) ቅልጥም መጀመሪያ ይበላል?
እሷ ደግሞ ‘የአየር ሁኔታው እንዴት ነው ይወብቃል አይደል’ ብሎ ወግ ለማይተዋወቁ ሰዎች ነው ትላለች፡፡
“ፍቅር ምንድን ነው?” ለስንት ሺኛ ጊዜ ጠየቅኳት፡፡ እኔ መጠየቅ አይሰለቸኝ፤ እሷ መመለስ አይሰለቻት፡፡ መልሷ አጭር ነበር፡፡ “መላመድ”፡፡ “ትወጅኛለሽ?” ለስንት ሺኛ ጊዜ ጠየቅኳት?
“እራሴን ከምወደው በላይ!” ለስንት ሺኛ ጊዜ መለሰችልኝ:: “የምር?” ብዬ ሳልጨርስ ከንፈሬን ትስመኛለች፡፡ እየሳቀች ትስመኛለች፡፡ ስትስቅ አይደለም ፈገግ ስትል ወከክ ታደርጋለች ፡፡ አቤት ጥርሷ ሲያምር በ’የሱስ ስም! የኾነ ጠማማ ጉዳይ ጠማማ በኾነ ቢሮ አልፈጸም ካለኝ ይዣት እሔዳለሁ፡፡ ከሷ የሚጠበቀው ፈገግ ማለት ብቻ ነው፡፡ አንድ ዓመት የፈጀው የቢሮክራሲ ድር ተበጣጥሶ ቁጭ!
ዐይኔን ትስመኛለች፡፡ እጄን ትስመኛለች፡፡ መላ ፊቴ በሃፍረት ሲቀላ ይብስባታል፡፡ አፍንጫዬ በሀፍረት ሲወዛ ይብስባታል፡፡ ዐይኔን በሃፍረት የት ልጣለው ብዬ ስርበተበት ይብስባታል፡፡ …ትስመኛለች፡፡ ትስመኛለች፡፡ ትስመኛለች፡፡ ከጎን ያሉት ጥንዶች በቅናት ጉሮሮአቸውን ሲያፀዱ ከእብደቷ ትመለሳለች ሲባል ይብስባታል፡፡ ከፊቷ ያለውን ስፕራይት ፉት ትልና እንደ ርግብ አፏን አሞጥሙጣ ትቀርበኛለች፡፡ ትን እንዳይለኝ እየተጠነቀቅኩ አፌን እከፍታለሁ፡፡ ታጠጣኛለች፡፡ ስትሮው አያስፈልገኝም፡፡ እብድ ነበረች፡፡ እብድ ነበርን፡፡ ፒያሳ ትጠበን ነበር፡፡ ባንድ ካፌ ቁጭ ብለን ፒያሳን በክንፎቻችን ከልለን እንሞላት ነበር፡፡ ከእብደታችን የምንመለሰው ጀንበር ስታዘቀዝቅ ነበር፡፡ እንዲህ ነን እኛ፣ እንዲህ ነበርን እኛ! ‘ፍቅርስ እንደነሱ’ ግን የምንባል አይመስለኝም፡፡ ‘ዕዩኝ ዕዩኝ’ አላልንማ፡፡ በልባቸው የሚፋቀሩ ታይታን አይወዱም፡፡ በዚህ ካፌስ ቢኾን ማን ዕዩኝ አለ?
እወድሃለሁ ስትል አመንኳት፡፡ እሞትልሃለሁ ስትል አመንኳት፡፡ አዳም ሔዋንን እንዳመነው፤ አምኖም የተከለከለውን እንደበላው ገደል ብትገባ አብሬ ለመግባት ዐይኔን አላሽም ነበር፡፡ ትናፋሽዋ በዱር ጽጌረዳ አይመሰልም፡፡ ይልቃል፡፡ በፍቅሯ ናላዬን አዞረችው፡፡ በዓሉ ግርማ ፒያሳን ባያውቅ እንጂ ‘ትንፋሽዋ ፒያሳ ፒያሳ ይላል’ ይል ነበር እስከማለት ደረስኩ፡፡ ሔዋን ከምር የወደዳትን አዳም ለማሳመን አትቸገርም፡፡ “እንዲህ በተናጠል አጉል ካረጉን በጅምላማ እንዴት?” ብሎ ይመስለኛል ጳውሎስ “ሴት በማኅበር መካከል አትናገር” ያለው፡፡ ለዚህ ሳይኾን አይቀርም የዘመኑ የሽያጭ ሊቆች፣ ቆንጆ ሴቶችን ለማስታወቂያ ሥራ የሚመርጡት፡፡
ያች የምናውቃት ካፌ በነበረበት ስፍራ ከፍራሽ በተአምር የተረፈ ‘ኮለን’ ተደግፌ ፡-
“…
በውልውል መኪና
በፋሽን መጫሚያ
ወይም በባዶ እግሩ
ሽው እልም የሚለው፣
ይሄ ሁሉ ምሁር ይሄ ሁሉ ማይም፣
መንገዱን የሞላው ከታችም ከላይም፣
ሲመላለስ አንጂ ሲደርስ ዐይታይም፡፡” የሚለውን ግጥም በሆዴ እየዘመርሁ ወጪ ወራጁን እመለከታለሁ፡፡ ቆመጥ የያዙ ሰዎች እንዳያይዋት እየተገላመጠች በቆሎ የምትጠብሰዋን ሴት ዐያለሁ፡፡ በቅርብ ርቀት የሚጫወቱትን ሕፃናት እመለከታለሁ፡፡ ‘ስታድግ ምን መኾን ትፈልጋለህ?’ እያሉ ሲጠያየቁ እሰማለሁ፡፡ ፈገግ እያልኩ፣ኮስተር እያልኩ የሚነጋገሩትን እንደዘበት እሰማለሁ፡፡
“ስታድግ ምን መኾን ትፈልጋለህ?” ሲል ከፍ ያለው ልጅ ይጠይቃል፡፡
“እኔ ዶክተር”
“አንተስ?”
“እኔ ፓይለት”
“አንቺስ?”
“እኔ ኢንጂነር”
“አንተስ?”
“እኔ ጳጳስ “
“ምን?… ጳጳስ?” እኔ አላምንም! የወዳጄን አገላለጽ ልጠቀምና you know what? … I can’t believe this እያልሁ የነገውን ጳጳስ ሕፃን ቀርቤ በሕፃንኛ interview ላደርገው ፈለግሁ፡፡
ማሙሽዬ ”ለምን ጳጳስ ለመኾን ፈለግህ?” ስለው ፈጠን ብሎ “በሥጋም በነፍስም ለማትረፍ!” ጉድ በል ! ደግሞ ፍጥነቱ! ሸምድዶ ይዞታል ማለት ነው? በቆሎ የምትጠብሰዋ ሴት እጇን አፏ ላይ ጭና ለወትሮው ልጆች ያለዕድሜያቸው የኾነ ሲመኙ (ለምሳሌ እኔ ሳድግ ራሔልን አግብቼ… ዓይነት ምኞት) ስትሰማ መታገስ አትችልም ነበር፡፡ እናትነት በሰጣት የመደመጥ ጸጋ “እናንተ.. ዋ!...ሒዱ ከዚህ!... ሳይሞቅ ፈላ…” ብላ ታባርራቸው ነበር፡፡
ዛሬስ? ዛሬ ለመገሰጽ አልሞከረችም ሳይኾን አልቻለችም፡፡ ለመቆጣትም አልደፈረችም፡፡ ደንግጣለች፡፡ ከአፏ የወጣው ብቸኛ ቃል “ወይ ዘመን!” ነበር ፡፡
አላልኳችሁም? ዘመን ነው ፍቅር! ዘመን ነው ሰላም! ዘመን ነው ዳኛ! ዘመን ነው ጌታ! ዘመን ነው ጠላት! ዘመን ነው ወዳጅ! የለም፡፡ ፍቅር መላመድ አይደለም፡፡ ፍቅር ዘመን ነው፡፡ ዘመንን ማን ይጨብጠዋል? ዘመን አሁን ያዝኩት ስንል የሚከዳ፣ እንደ ሳሙና አይደለምን? ለዛ ሳይኾን አይቀርም ሀብታሞች በቃኝን የማያውቁት፡፡ ዛሬ ያገኘሁትን ነገ ባጣውስ በሚል ዘመንን ያለማመን! ፍቅርማ ዘመን ነው፡፡ ትዝታ፡፡ ጣፋጭ ወይም መሪር ትዝታ በጉያው ያቀፈ፡፡ ውብ ፈገግታሽ ታወሰኝ፡፡ ፍቅር ናፍቆት ነው፡፡ ሳቅሽ ናፈቀኝ፡፡ ‘ነይልኝ’ የኔ አበባ፡፡ ልቤ እስኪጠፋ ሳሚኝና መብራት ካልጠፋ መሳሳም የሚፈሩትን ቀንድ አስበቅይልኝ፡፡ ነይ ባቅላባ እንብላ፣ ነይ ስፕራይት እንጠጣ፣ ነይ ሲኒማ እንግባ፣ እነ…ዛ ካፌ ውስጥ የሚሳሳሙት አብረው ሞቱ ይባል፣ ነይ አብረን እንሙት፡፡ ፒያሳ ነንና ቀባሪ አናጣም፡፡ ‘እሞትልሃለሁ’ ብለሺኝ አልነበር? ነይ አብረን እንሙት! መስዋዕትነት ቀጠሮ ከማክበር ይጀምራል ትይ አልነበር? ነይ እዚያው ነኝ፡፡ እጠብቃሻለሁ፡፡ እምባዬ ሳላስበው ዐይኔን ከደነው፡፡ ‘እወድሻለሁ፡፡’
‘ምን? ማነው ይሄን የተናገረው? ለካ በዘጠኝ ዓመት ውስጥ አንድም ቀን ‘እወድሻለሁ’ ብያት አላውቅም?!!! ምን ዓይነት ሰገጤ ኖሬያለሁ? የኾነ ውለታ ተውሎለት ‘አመሰግናለሁ ‘በል እንጂ ሲሉት ‘ሆድ ያመስግን’ ከሚለው አርሶ አደር አጎቴ በምን ተሻልሁ? የሆድን ካንድዬ በቀር ማ ያውቃል? የምር የኾንኩ ማቶ ነገር ነኝ እሽ፡፡
ፍቅርዬ ጠላታችሁ ይጥፋ ‘እዚህም ነኝ፣እዛም ነኝ’ ሳትል ጠፋች፡፡ ጠፋች ጠፋች፡፡ በቃ፡፡ ‘አድራሻሽ ጠፋብኝ’ የሚለውን ዜማውን ባህታ ገ/ሕይወትን በአካል ለምኜ ባይሳካልኝ፣ ኤፍ ኤም ራዲዮ ላይ ስንት ጊዜ አስዘፈንኩት?!
ትዝ ይለኛል..ከአንድ ዓመት ከሦስት ወር በኋላ ከጠፋችበት ብቅ አለች፡፡ የኾነ ካፌ ቀጠረችኝ፡፡ የጥንት የጥዋቱን ካፌ ያልመረጠችው ለመርዶ መኾኑ ቀልቤ ነግሮኛል፡፡ ወንበር ይዘን ቁጭ እንዳልን ወደ ገደለው መግባት የምትወደው ፍቅሬ፤ ዛሬ ዝም ብላ ካስተዋለችኝ በኋላ ‘ሸሚዝህ ያምራል’ አለችኝ፡፡ እርጋታዋ አስፈራኝ፡፡ ጠባይ ተቀያይረናል ልበል? የባጡን የቆጡን በመቀባጠር ወደ ዋናው ጉዳይ መግባት የምፈራው እኔ፣ ያበጠው ይፈንዳ ብዬ ለክት ጊዜ ያስቀመጥኩትን ልቤን እንዳትሰብረው እየፈራሁ የሞት ሞቴን “አግብተሻል አይደል?” አልኳት፡፡ ፊቷን ቅጭም አድርጋ ምን ብትል ጥሩ ነው? “እንዴት ዐወቅህ? ይሄን ብላ ጣቷን ለመደበቅ ሞከረች፡፡ “ስሔድ አገኘኋት ስመለስ አጣኋት” ለሚለው እንቆቅልሽ ሰበቡ እኔ፣ ፍቺው ፍቅርዬ ናት፡፡ “ነበር ለካ እንዲህ ቅርብ ኖሯል” አለች እቴጌ ጣይቱ፡፡ ዘጠኝ ዓመት እንዲህ ቀላል ኖሯል? ‘ግን ለምን? ብዬ ሳፈጥባት፤ ምላሽዋ “ዘጠኝ ዓመትና ዘጠኝ ቀን አንድ ነው፡፡” ይሄን ስትናገር እምባ ጠብቄ ነበር፡፡ እንድያውም ፈገግ ያለች መሰለኝ ወይስ ዐይኔ ነው? How could these numbers be equal? እንዴት 9(365) እና 9(1) እኩል (=) ሊኾኑ ይችላሉ? የለም የሒሳብ ሊቆች አሳስተውናል፡፡ የኾነ የደበቁን ነገርማ አለ! ወይም ከቁጥሮች ዐቅም በላይ የኾነ ነገር አለ፡፡ ቁጥሮቹን እያጣቀሰ ደቡብ አፍሪካ በአፓርታይድ ጊዜ ትሻል ነበር ብሎ ለማሳመን ሲጋጋጥ የነበረው ሰው (የኔልሰን ማንዴላ ሚስት ትመስለኛለች) ምላሽዋ አጭር ነበር:- “…you are right but we don’t want be fattened slaves.” ፕሌቶ “I have hardly ever known a mathematician who was capable of reasoning” ማለቱ እንደኔ ፍቅረኛው ከድታው መኾን አለበት፡፡ ፕሌቶ ልክ ነው፡፡ ፍቅርዬም ልክ ነበረች፡፡ ዘጠኝ ዓመትና ዘጠኝ ቀን አንድ የሚኾነው በፍልስፍና ብቻ ሳይኾን ይቀራል? ‘ፍልስፍና የትምህርቶች ሁሉ እናት’ መባሉ ለዚህ ይኾን? ፍቅርዬን ሳላውቃት ፈላስፋ ኖራለች ለካ?! ምናለ ከሌላ ሰው ብሰማ የምለውን “አግብቼ አማሪካ መሄዴ ነው” ስትል አከለችበት፡፡ ነገሩ ሁሉ ፍጥንጥን ሲልብኝ ዐይኔን ዐይታ ልቤን የምታነበው ፍቅርዬ፣ ከረዥም ጸጥታ በኋላ “ሆድዬ ፍቅር መላመድ አይደለም፤ ትዳር ነው መላመድ” ስትል ተነፈሰች፡፡ ‘ሆድዬ አትበይኝ’ ብዬ ለምን አልተቆጣሁም? ‘ሆድዬ አትበይኝ! አንቺ ይሁዳ በሴት’ ብዬ ለምን እፊቴ ያለውን ስፕራይት አልደፋሁባትም? እውነትም እውነታን ለመጋፈጥ ፈሪ ነኝ፡፡ ደንዝዤ ቀረሁ፡፡ ሁሉ ነገር ዞረብኝ፡፡ እነዛ ስንሳሳም ይቀኑ የነበሩት ጥንዶች ዛሬ በተራቸው ከጣራ በላይ ሲስቁ ተሰማኝ፡፡ ሃሃሃሃሃሃሃሃ…. ሃሃሃሃ… ይህ ድምፅ ለኔ እንግዳ አይደለም፡፡ የት ነው የሰማሁት? የኾነ ቦታ፣ በኾነ ጊዜ ሰምቸዋለሁ፡፡ ማርያምን ሰምቸዋለሁ፡፡ yes yes yes… አዎ፡፡ ትሪለር (thriller) የሚባለው የማይክል ጃክሰን ‘ክሊፕ’ ላይ!፡፡ አዎ ይህን ድምፅ አሳምሬ ዐውቀዋለሁ፡፡ ሃሃሃሃሃሃሃሃ…. ሃሃሃሃ…እንደዚህ የሚስቀው ሳጥናኤል ብቻ ነው፡፡ አዎ እራሱ ነው! ወለሉ ጣራ፣ ጣራው ወለል ኾነብኝ፡፡ በካፌው ያሉት ሰዎቹ ሁሉ እንደ በረዶ ማሙተው ጥርሳቸው ብቻ ይታየኝ ጀመር፡፡ ሃሃሃሃሃሃሃሃ…. ሃሃሃሃ… እንደ ደጋን እየታጠፉ፣ እንደ እብድ ተክለ አቋቋም ወዲያ ወዲህ እየተዛመሙ…ሃሃሃሃ…
ከጥቂት ወራት በኋላ እራሴን ስቼ ‘የተሳተኝ ነገር ካለ’ ብዬ የኾነውን ትነግረኝ ዘንድ በጊዜው የነበረችውን አስተናጋጅ ጠየቄያት ነበር፡፡ “አልነግርህም፤ ምን ያደርግልሃል? ያለፈ አልፏል የፈሰሰ ውኃ ላይታፈስ!” ብላ ልትመክረኝ ተንደፋደፈች፡፡ አይ መሬት ያለ ሰው! ካልነገርሽኝ ብዬ ስጨቀጭቃት ፊቷን በሐዘን ከስክሳ “ትዝ ይለኛል..የት ነኝ?’ ነበር ያልከው … የምትወድህ ግን አይመስለኝም” አለችና እምባዋን ለመደበቅ ወደ ጓዳ ሮጣ ገባች፡፡ ‘የምትወድህ ግን አይመስለኝም’ ማለት በተግባር የታየ ሐቅ ነው፡፡ ‘ምን ለማለት ነው?’ እያልኩ በዐይኔ ተከተልኳት፡፡ ’እኔ ነኝ የምወድህ ማለት ነው? እሷ እንደኔ አትወድህም ማለት ነው?’ ካልኾነ ማልቀስን ምን አመጣው? ወንድሟን ስለመሰልኳት ነው? አለቃዋ ሆድ አስብሷት ነው ወይስ ተመሳሳይ ቁስል ስላለን? ዘመን የሚፈታው ይኾናል::
ፍቅርማ መላመድ አይደለም፤ዘመን እንጂ፡፡ ዘመንም አይደለም፤ መላመድ ያለዘመን ይኾናል? ዘመን የሰጠው ፍቅር ተራራ ያሳክላል፤ ዘንበል ሲል ደግሞ ጓዳ ስርም ያስደብቃል? እንዲህ እንደኔ! የት ልደበቅ? የኔ ጤዛ የሌላ ሰው ገላ መላመድን አንቺ ከቻልሽበት፣ እኔ ያልቻልኩበት የቱ ጋ ተሳስቼ ነው?
የባንግላዲሽ 10ኛዋ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ሼኪ ሀሲና ምን አሉ? “Poverty is the root of all evil.” ያ የዳስ ካፒታል ደራሲ ካርል ማርክስ ምን አለ? “The stronger the power of my money, the stronger I am.” ቅዱስ ጳውሎስ ለደቀ መዝሙሩ ቲቶ ምን ብሎ ይኾን? “ገንዘብ የክፋት ሁሉ ስር ነው፡፡”
እና ምን ይጠበስ!! እኔን ምን አድርግ ነው የምትሉኝ? ለሷ አትነግሯትምን?
ከመፍረስ በተአምር የተረፈውን ‘ኮለን’ ተደግፌ፣ ትናንት የኾነ ያህል ‘ፍቅር አይደለም፤ ትዳር ነው መላመድ’ የሚለው ቃሏ ጆሮዬ ላይ እያቃጨለብኝ… ከዛሬ ምናምን ዓመት በኋላ… ያ ካፌ የነበረበትን ስፍራ ሰዎች ሲመለከቱት ከንፈራቸውን እየመጠጡ ‘ፍቅር እዚያ ግድም ፈገግ ብሎ ነበር’ ማለታቸው አይቀርም እያልሁ… ይሄን ክፉ ትዝታ ለመርሳት የመጀመሪያ ልጄን ‘አልፎ ዐይቼው’ ብዬ ነው ስም የማወጣለት እያልሁ፣ ‘አይረጭም፣ አይቀባም’ የሚለውን የበረሮ መድኃኒት ማስታወቂያ፣ ትናንትን የሚያስታውስ ፍቅር ለሞት የቀረበ ነውና ‘አይወሳም፣ አይነሣም’ ብዬ ለእራሴ እየነገርኩ፣ ሠራተኛ ሰፈር ስደርስ ‘ሂትለር አይሁድ ጠል የኾነው ከአንዲት አይሁዳዊት ሴተኛ አዳሪ ጋር ተኝቶ በደዌ ተለክፎ ነው’ የሚለውን ታሪክ ‘እውነት ነው ግን?’ እያልሁ እያሰላሰልሁ፣…ከርቀት ከአራዳ ጊዮርጊስ የሚሰማውን ‘ዘመኑ አልቋል፣ ንስሐ ግቡ’ የሚለውን ሰባኪ ‘መቼ?’ ስል እየጠየቅኩ፣ ሀገር ፍቅር ቴአትር ጋ ስደርስ ዓለምን ያህል ሰፊ ቴአትር ቤት ታቅፎ መድረክ ብሎ ‘በአጭር ቁመት፣ በጠባብ ደረት ተወስኖ’ ቴአትር መሥራት ኤዲያ ምን ሊረባ! ደሞ ‘ሀገር ፍቅር’ ብሎ ስም፣ ‘ሀገር ሰላም?!’ መባል አለበት እያልሁ፣ ‘ፍቅርዬ ሆ! ፍቅርዬ ሆ!...’ የሚለውን የቆየ ዜማ ለብቻዬ እያንጎራጎርኩ …ቁልቁል ወደ ‘አጥቢያ’ ዋና ከተማ፣ አራት ኪሎ ተንደረደርኩ፡፡