Tuesday, 19 November 2024 00:00

ባህል፣ ታሪክና የአስተዳደር ስርዓት፡- አንድነትና ልዩነት

Written by  ስንታየሁ ገ/ጊዮርጊስ
Rate this item
(1 Vote)

ባለፉት ሁለት ተከታታይ ጽሑፎቼ (አዲስ አድማስ ቅጽ 23 ቁጥር 1280 እና 1281) በታሪክ ዙሪያ አስተያየት ያቀረብኩኝ በመሆኑ የዚህ ጽሑፍ ትኩረት ታሪክና የአስተዳደር ሥርዓት አይሆኑም፡፡ ይህ ጽሑፍ ይበልጥ የሚያተኩረው በባህል ዙሪያ ነው፡፡ ባህልን አስመልክቶ ለመግለጥ የምሻው ደግሞ ስለ ባህል ምንነት ሳይሆን፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ባህሎችን እንደምን አዳብረን (ተመሳሳዮችን በአንድነት የጋራ ብለን) “የእኛ የምንለውን ጠቃሚ ባህል እናበለጽጋለን?” የሚለውን ጥያቄ በኮርኳሪነት ለማንሳት ነው፡፡ በእርግጥ የእኛ እያልን በተለምዶ በጋራ እያከናወንናቸው የሚገኙ በርካታ የተወራረሱ ባህሎች እንዳሉን አውቃለሁ፡፡ እነሱን ሁሉ መዘርዘር ድካም ነው፡፡ ከልዩነታችን አንድነታችን ይበልጣል የምንለው የተወራረሱ ባህሎቻችንን በመገንዘብም ጭምር ነው፡፡ ልዩ የሆኑት የብሔረ-ሰብ ባሕሎችም ቢሆኑ ጌጦቻችን ስለሆኑ ተከብረው ሊዳብሩና የአገር ቅርስ መሆን የሚገባቸው ናቸው ብዬም አምናለሁ፡፡
ባህል፣ የእኔ ነው በማለት ተቀብለው የሚኖሩትና ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ በመቀጠል፣ ሰዎች ተለምዷቸውንና የአኗኗር ዘይቤዎቻቸውን (የቋንቋ፣ የአለባበስ፣ የጋብቻ፣ የአመጋገብ፣ የበአል አከባበር፣ የግልና የማህበረ-ሰብ ግንኙነት፣ ማህበራዊ አኗኗር፣ የቤት ውስጥና የውጭ ሥርዓቶች (ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን ጨምሮ)፣…) የሚያንጸባርቁበት በተግባር የሚቀመር የማንነት ማሕበራዊ እሴት ነው፡፡ በእርግጥ ይህ የመዝገበ ቃላት ትርጉም አይደለም፡፡ እኔ ባህልን የማይበት የግል አመለካከቴ ነው፡፡ ባህል በድርጊት የተሞላና የሚዳሰስ/የሚታይ የኑሮ አካል በመሆኑ፣ ሁሉም እንደገባው ሊተረጉመው ይችላል፡፡ በእይታ መለያየት አያጣላም፡፡
ባህል ለጊዜው በድርጊት ሊገለጥ በማይችልባቸው ሁኔታዎች እንኳን (ለምሳሌ፣ አንድ ሰው በስደትም ይሁን በሌላ አጋጣሚ ከእሱ ባህል ልዩ ከሆነ ኅብረተሰብ ጋር የመቀላቀል ዕድል ቢገጠመውና በራሱ የአኗኗር ዘይቤ የዕለት ኑሮውን ማከናወን ባይችል) ባህሌ ብሎ በተቀበለው ሰው አእምሮ/ሃሳብ ውስጥ ባህሉና ማህበራዊ እሴቶቹ ፍጹም አይጠፉም፡፡ ባህል አእምሮ ውስጥ ሆኖ/ሰርጾ አመለካከትንና ድርጊትን የመግዛት/የመቆጣጠር ኃይል አለው፡፡
ባህል በየዕለቱ የሚያዘወትሩትን ተግባር/ልማድ (በዓመት አንድ ጊዜ በዙር የሚመጣውን በዓል ጨምሮ)፣ በለመዱት አሠራር (የአኗኗር ዘይቤ) መሠረት የማከናወን ጉዳይ ነው፡፡ የራስ በመሆኑ በተፈጥሮ የሚከውኑት ወይንም ሊማሩት የሚችሉት የአኗኗር ዘይቤ (“የልማድ ምህዋር”) ይመስለኛል፡፡ ባህል ዕለት በዕለት የምናከናውናቸውን የኑሮ ሂደቶች ሁሉ አንቀሳቃሽ ነው፡፡ አንድን ነገር ስናከናውን ባህላችን በአመለካከታችንና በድርጊታችን ውስጥ ይንጸባረቃል፡፡ ባህል ወደ ልማድ ተቀይሮ ገዢ የአመለካከትና የድርጊት መዘውር የመሆን እድሉም ከፍተኛ ነው፡፡ ባሕል መነሻና መጠሪያውንም እንዴት እንዳገኘ ለማወቅ ይቻል ይሆን? ይህን በጥያቄነት ይዤ ወደፊት የምመረምረው ይሆናል፡፡ ከተሳካልኝ፤ ባህልን የምመረምረው ግን ከኤኮኖሚ ተጽዕኖው አንጻር ብቻ መሆኑን እወቁልኝ፡፡ የሚቀድመኝ ወይንም አብሮኝ የሚመረምር ባገኝ/ቢኖር ደስ እሰኝ ነበር፡፡
አንድ ባህል የታሪክ አንድ አካል ተደርጎ ሊገለጽ የሚችል ቢሆንም፣ ሁሉንም የባህል አካል እንደ ታሪክ ጽፈን በመጽሐፍ በመደጎስ ያለፈ ድርጊት አድርገን ልንመለከተው የምንችል አይደለም፡፡ ባህል እጅግ በጣም ውስብስብ ነው፡፡
አንዳንዱ ባህል አብሮት የነበረውን የታሪክ ወቅት ተሻግሮ በሌላ የታሪክ ክንውንም እንደነበረ ሊቀጥል ይችላል፡፡ የተለያዩ ባህሎች ያሉት ሕዝብ አንድ ወጥ ታሪክ ሊሠራ ይችላል፤ አንድ ታሪክ ግን አንድን ባህል ብቻ ወክሎ ይከናወናል ብሎ ማመን ይከብዳል፡፡ ባህል ከታሪክ ጋር ያለው ተመሳሳይነት፣ እየተከናወነ የሚቀጥልና አብዛኛውን ጊዜ ከታሪክ ጋር አንድ ላይ ተሰናኝቶ የሚገኝ “ሕብር” መሆኑ ብቻ ነው፡፡ በማንኛውም ታሪክ ውስጥ የአድራጊዎቹ/ተሳታፊዎቹ ባህል አለበት፡፡
አንድ ታሪክ ተከናውኖ አንድ ሥፍራ ላይ ሊቆምና፣ ሌላ አዲስ ታሪክ በሌላ መልክ ተከስቶ ሊቀጥል ይችላል፡፡ ታሪክ ራሱን እንዳለ የመድገም ባህርይም አለው፡፡ ባህል ግን ባህሌ ብሎ በተቀበለው ሕዝብ ዘንድ ሳይለወጥ (መጥፎውን እየተዉ ጥሩው እንዲቀጥል የማድረግ ባሕሪው እንደተጠበቀ ሆኖ) ለረጅም ጊዜ ሊቀጥል የሚችል ነው፡፡ ያም ሆኖ፣ ታሪክ በሕዝብ መካከል ልዩነቶችን እያጎላ ደረቅ ተረኮችን ይዞ ክችች በማለት የሚዘልቅ ሲሆን፣ ባህል ግን እንደ ጊዜና ቦታው እየተቀያየጠ/እየተወራረሰ በመለስለስ የሕዝብን እሴቶች እያመሳሰለ/እያዋሀደ ይዘልቃል፡፡
ባህልን እንደ የአኗኗር ሥርዓትም መውሰድ የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ባህላዊ አመለካከት በአስተዳደር ሥርዓትና በድርጊት (የታሪክ ክንውን) ሊተሳሰርም ይችላል፡፡ አንድ አስተዳደራዊ ሥርዓትም ሆነ ባህል ለመለወጥ (ለ ይጥበቅ) የየራሳቸውን ጊዜያት ሊወስዱ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ፣ የጋርዮሽ ሥርዓት፣ የፊውዳል አስተዳደር ሥርዓት፣ የገዳ ሥርዓት፣ …፡፡ ባህልም እንደዚያ ነው፡፡
በእርግጥ ከአንድ የአስተዳደር ሥርዓት ይልቅ ባህል ለመለወጥ (ለ ይጥበቅ) ችኮ ነው፡፡ በአንጻራዊ ሁኔታ ከአስተዳደር ይልቅ ባህልን ለመለወጥ ጊዜ ሊወስድ ይችላል ለማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ፣ በእኔ ዕድሜ እንኳን ሦስት የአስተዳደር ሥርዓቶች (የዘውድ፣ ሶሻሊዝምና አብዮታዊ ዲሞክራሲ) ተለዋውጠዋል፡፡ በአገራችን ብዙ የተወራረሱ ባህሎች የመገኘታቸውን ያህል፣ በብዙ መልክ የተለዋወጠ ባህል ግን አላስታውስም፡፡ በርካታ ባህላዊ አመለካከቶችና ክንዋኔዎች እንዲያውም እንደተቸነከሩ ያሉ ይመስለኛል፡፡ ያም ሆኖ ግን አንድ ባህል የመወራረስና አብሮ በመኖር እሴቶች ውስጥ በመናኘት አንዱ ወደ ሌላው የመጋባትና የመደባለቅ/የመቀየጥ ባህርያት አሉት፡፡ መሆን የለበትም በማለት መሟገት አይቻልም፡፡ ባህሪው ነው፡፡
ባህል በተለያዩ መልካም እሴቶቹ አማካኝነት ሰዎችን የማቀራረብና የማዋሐድ ባህርይ ቢኖረውም (ምሳሌ፣ በአመጋገብ፣ በቋንቋ፣ በጋብቻ፣ በአልባሳት፣…) ውስብስብ የሆነ የሰዎች ስስ ብልት (sensitive) ነው፡፡ ስለ ባህል መጻፍ ከባድ የሚሆነውም፣ በተለይ በአገራችን ሁኔታ፣ ከሃይማኖት፣ ከአስተዳደር ሥርዓት፣ ከዕለት ዕለት የኑሮ ክንዋኔዎችና ከሰዎች አመለካከት ጋር የተቆራኘ ሆኖ ስለምናገኘው ጭምር ነው፡፡
ባህል፣ የማንነት መግለጫ ስስ ብልት በመሆኑ ማንም ባህሌ ነው ብሎ በሚከተለው የአኗኗር ዘይቤው ሲመጡበት በቀላሉ የሚያልፈው ጉዳይ አይደለም፡፡ እንደ ታሪክ በክርክር ብቻ እየተቋሰሉ የሚቀጥሉበትን መድረክ አያመቻችም፡፡ ቶሎ ስሜታዊ ያደርጋል፡፡
ከብዙ ባህሎች የተወራረሰ/የተቀየጠ አንድ የጋራ ባህልን ማበልጸግ፣ ወይንስ እያንዳንዱ ባህል በራሱ መንገድ የባህሉ ባለቤት የሆነው ሕዝብ እስከፈለገው ድረስ እየበለጸገ ወይንም እየጠፋ ይሂድ የሚል አመለካከት እየተነሳ ሰዎችን “ሲያፈላስፍ” እንደነበረ አውቃለሁ፡፡ እኛ በሆነው ባልሆነው መከራከርና፣ አዋቂ/ምሁር እንድንባልም መፈላሰፍ የምንወድ ነን፡፡ አይጣል ነው፡፡
በመሠረቱ፣ ሁለቱም (አንድ ባህል በመወራረስ እየበለጸገ ወይንም እየጠፋ የመሄዱ ጉዳይ) ተወራራሽነት አላቸው፡፡ ውይይቱ የሚያስፈልገው የልዩነት/ቅራኔ መነሻ ምንጭ በሆኑትና ሊሆኑ በሚችሉት ላይ ብቻ ቢሆን መልካም ነው፡፡
በኢትዮጵያ የልዩነት/ቅራኔ መነሻ/ምንጭ የሆኑ ባህሎች አሉ? ባህሌ “ተናቀብኝ”፣ “እንዳያድግ ታፈነብኝ” የሚል ቅሬታ ሲስተጋባ እሰማለሁ፡፡ በእርግጥ በአብዛኛው ቅሬታው የሚስተጋባው በፖለቲካ ኤሊቶች (“ምሁራን”) መካከል ነው፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በወሳኝ ሁኔታ በባህል ምክንያት የተነሳ ግጭት ለመኖሩ ማንበቤን አላስታውስም፡፡ በባህል ምክንያት የተነሳ ግጭት ከነበረም ዘንግቼው ሊሆን ይችላል፡፡ ለነገሩ የታሪክ ተማሪ አልነበርኩምና ብዙ ባላውቅ አትፍረዱብኝ፡፡ የምታውቁ አስረዱኝ፡፡
ባህል በሃይማኖት፣ በሥራ፣ በአመጋገብ፣ በጋብቻ፣ በቋንቋ፣ በዘፈን፣ በአለባበስ፣ በምግብ ዝግጅት፣ በአኗኗር፣ … ሊገለጥ የሚችል እንደሆነ ግን ግንዛቤው አለኝ፡፡ አመጋገብና የጋብቻ ባህሎች በምንም መልኩ በተለያዩ ብሔረሰቦች መካከል የቅራኔ ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ አይመስለኝም፡፡ ሆነው አይቼም ሰምቼም አላውቅም፡፡ አልኖርኩበትም፡፡ ከእኛ ውጪ ካሉ ብሔረሰቦች ጋር ወድደንና ፈቅደን (ሰው ሁሉ ሰው ነውና) መጋባትና የተለያዩ ምግቦችን መመገብ በግለሰቦች ፍላጎት ላይ የሚመሰረቱ ናቸው፡፡
የሰው ፍላጎት በዘረኛ ፖለቲካ ሲቃኝ ወይንም እንደ ባህል አብዮት (በቻይና እና በሌሎች ሥፍራዎች እንደታየው) አንዱን ባህል ደፍጥጦ በሌላ ለመተካት በሚደረግ የፖለቲካ ጡንቻ ነው ባህል ለግጭት መነሻ እንዲሆን ዝግጅቱን የሚሰንቀው ብዬም አምናለሁ፡፡ ካየሁትና ጥቂት ካነበብኩት የተገነዘብኩት ያንን ሁኔታ ነው፡፡
ባህሎችን ከመወራረስ ማቆም እንደማይቻል ሁሉ፣ የእኔ ባህል ይበልጣል በማለት የሌላውን በቀጥታ ወይንም በተዘዋዋሪ መግፋት (ማቃለል) ትክክል እንዳልሆነ ማወቅም መልካም ይመስለኛል፡፡ የአንዱን በሌላው ላይ ካለውዴታው መጫንም እንዲሁ ከባድ ይሆናል፡፡ አንድን ባህል ማሳደግ የሚቻለው የሌላውን አጥፍቶ/ሰርዞ የራስን በመጫን እንዳልሆነ ማወቅ ብልህነት ነው፡፡ ስለሆነም የእያንዳንዱ ብሔረሰብ ባህል ለራሱ ሊተውለት እንደሚገባ ማመን የማስፈለጉን ያህል፤ ለልማት እንቅፋት የሚሆን፣ በአብሮነት ላይ ችግር የሚፈጥር፣ እንደ ታሪክ የሚያቆራቁስና “ጎታች” አመለካከትን ሊፈጥር የሚችል ባህል/አሠራር ሲገኝ ደግሞ የሚገደብበትን በጋራ መሻት ተገቢ ሊሆን ይችላል (ይሄ ይሆን የባህል አብዮት የሚባለውን ያስከተለው?)፡፡
አንድን ባህል እንዳይሰፋ መገደብም በራሱ ችግር አለው፡፡ ገዳቢውስ ማነው? የቤተሰብና የአካባቢ አስተዳደር ሥርዓቶች እንኳን የባህል አንድ አካል በመሆን ያገለግሉ እንደነበረ ከታሪክ መረዳት ይቻላል፡፡ ባህል በራሱ የአስተሳሰብ መስመርን ሊያመነጭ የሚችል ኃይል አለው፡፡ አስተሳሰብ/አመለካከት ደግሞ ጥሩም መጥፎም ጎኖች አሉት፡፡ እነኚህ ሁሉ በታሪክ አጻጻፍ/ቅንብር ውስጥ የመንጸባረቅ ዕድል ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚያን ለታሪክ እርቅ/ግንዛቤ መተው ካልሆነ ዛሬ ላይ ሌላ ምን አማራጭ ይኖራል?
መልካም ባህሎችን ሁሉም በቀላሉ ሊገነዘባቸው የሚችል ይመስለኛል፡፡ ጎጂዎቹ ባህሎች ግን ጎጂ ናቸው ተብለው መቅረብ የሚገባቸው የባህሉ መነሻ ከሆነው ሕዝብ ውጪ ባለ ሌላ አካል ወይንም ሕዝብ ባይሆን ይመረጣል፡፡ የባህሎቹ ባለቤቶች ናቸው የባህሎቻቸውን ጥቅም የሚያውቁት፡፡ አለያ እንደ ታሪክ ያለያያል፡፡ ሁሉም በንጽጽር የሚታይ ነው፡፡ እይታውም ከዘመንና የዓለም ስልጣኔ ከደረሰበት አድማስ አንጻር ሊሆን ይችላል፡፡ ጎጂ ባህሎቹ የትኞቹ ናቸው? ለምን ጎጂ ተባሉ?... የሚሉትን በውል ማጤን ግን ተገቢ ነው፡፡ ሰው ሁሉ ቢጠይቅና ቢመራመር ክፋት የለውም፡፡
ባህል የሰዎችን ስስ የአኗኗር እሴቶችና ዘይቤዎች በጥምር ሰብስቦ የሚከወን ጭምር ስለሆነ ውስብስብ ነው፡፡ ውስብስብ ማለትን አበዛሁ? የአንድ ሕዝብ ባህል የማንነቱ መግለጫ ስለሆነ ሕዝቡ እስካለ ድረስ ያ ባህል ይኖራል ብሎ ማመን ይቻላል፡፡
ለምሳሌ፣ ቋንቋ የባህል አንዱ ዘርፍ ነው፡፡ ቋንቋ ባህልን ማሰናኛ አንድ ወሳኝ የመገናኛ ድልድይ ይመስለኛል፡፡ ካለ ቋንቋ የሚቀናበር ባህል/የአኗኗር ዘይቤ የለም በማለት በማመኔ ነው ይህንን ማለቴ፡፡ ግን ደግሞ፣ አንድ ቋንቋ እንደሚያድግና እንደሚሞት አውቃለሁ፡፡ ቋንቋ ያድጋል፣ ይሞታል ተብዬ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የኒቨርስቲ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ በነበርኩበት ወቅት ነፍሱን ይማረውና ዮሐንስ አድማሱ አስተምሮኛል፡፡ አቤት ይሄ ጊዜ የሚሉት ነገር እንዴት ይሮጣል? በእርግጥ ጊዜ የሚሮጠው በሕይወት ላለ ሰው ብቻ ነው፡፡ ብዙዎች የሚያውቁትን ይዘው በጊዜያት መካከል ማለፋቸው የተፈጥሮ ሕግ ነው፡፡
አንድን ቋንቋ የሚናገር ሕዝብ በተለያየ ምክንያት ባይኖር/ቢጠፋ (ከመኖር ወደ አለመኖር ቢለወጥ) ሌላ ቋንቋውን የሚናገረው ሕዝብ ስለሌለ ቋንቋውም ይሞታል (ሞተ ይባላል)፡፡ ይህ በትምህርት ክፍለ ጊዜ ስማር የተረዳሁት ነው፡፡ እኔ ደግሞ ስለ ቋንቋ መሞት በራሴ ያረጋገጥኩት አለ፡፡ ለምሳሌ፣ በደንብ መናገርና ለሌላ ሰው እስከ ማስተርጎም ድረስ አውቀው የነበረ የሲዳምኛ የቋንቋ ችሎታዬ ከአርባ ዓመታት በላይ ልናገረው ባለመቻሌ ዛሬ ላይ አላውቀውም፡፡ ልማረው ብል ጊዜ ላይወስድብኝ ይችላል፣ ለአሁኑ ግን ከውስጤ ሞቷል፡፡ በእርግጥ እኔ ገና አልሞትኩም፡፡ ቋንቋው ግን ተናጋሪ ሕዝቦች ስላሉት ሕያው ሆኖ ያለና የሚቀጥልም ቋንቋ ነው፡፡ ቋንቋን ካልተናገሩት ሙት ነው (ለማይናገረው ሰው) ከተናገሩት ግን ሕያው ነው ለማለት ነው፡፡
እንደ ቋንቋ ሁሉ ባህልም የሚያድግና የሚሞት መሆኑን ከዚህ እውነታ ለመረዳት አያዳግትም፡፡ አንድን ባህል ዕለት ከዕለት የሚከተለው/የሚከውነው ሰው ከሌለ (ኖሮም ካልተጠቀመበት) ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? በድርጊት የሚፈጽመው ባለመኖሩ ሳቢያ ይሞታል/ይጠፋል፡፡ ቃዠሁ? ግን ራሴን አያየሁት እንዴት እቃዣለሁ? አልቃዠሁም፡፡
ሰዎች ለባህላቸው መቆርቆራቸውና እንዳይጠፋ መሥራታቸው፣ የእኔ የሚሉትን እሴት እንዳያጡትና በሌሎች ተውጠው እንዳይኖሩ ከመስጋት አንጻር ሲሆን እውነት አላቸው፡፡ ሆኖም፤ ማንኛውንም ባህል ከመወራረስና ከመቀየጥ ማዳን ይከብዳል፤ ለምን ሆነ ብሎ መሟገትም ምንም ፋይዳ የለውም፡፡ የባህሎችን የመወራረስ ባህርይ ከዚህ አንጻር ስመለከት፣ ጠፍተው እንዳይቀሩ መወራረሳቸው በራሱ፣ እየተገበሩ እንዲኖሩ አንድ ዕድል የሚያበረክትላቸው መሆኑን እረዳለሁ፡፡ ከተቀየጠው መካከልም የእኔ የቱ ነው በማለት መፈለግም ፋይዳ የለውም፡፡ ጎጂ እስካልሆነ ድረስ ተቀብሎ መኖር ነው፡፡
ባህልን ልክ እንደ ባለቤቱ (ይህ ባህል የእኔ ነው ብሎ እንደያዘው ሕዝብ ሆኖ ለማለት ነው) ማየት የግድ ያስፈልጋል፡፡ ስለ ባህል ለመጻፍም ሆነ ለመተቸት ከባድ የሚሆነው የባህሉ ባለቤት ራሱ ተዋናይ በመሆን መሳተፍ ስላለበት ነው፡፡ ባህል እንደ ታሪክ የተፈጸመና ያለፈ ክንዋኔን ሁሉ የሚጨምር መድብል አይመስለኝም፡፡ እንደ ተዋናዮቹ ጥንካሬ እየጎለበተ ወይም እየተቀየረ በእለታዊ ድርጊት ውስጥ የሚንጸባረቅ ውህድ የአኗኗር ዘይቤ ነው፡፡ ከውህዱ አንዱን ወይም ብዙውን የድርጊቱ ማያያዣና የአመለካከቱ መነሻ ለማድረግ ባይፈልግ፣ የፈለገውን ውህድ በሚፈልገው ዓይነት የሚያቀናብረው ራሱ የባህሉ ባለቤት የሆነው ሕዝብ ብቻ ነው፡፡ ከውጭ መጥቶ ይህ ባህል ደህና ነው፤ ይህኛው ደካማ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡
ጥሩ ነው ወይንም አይደለም ለማለት መለኪያውስ ምን ሊሆን ነው? የሌላ ህዝብ ባህልና ሥልጣኔ? የየትኛው ሕዝብ? ለምን? ሰፊ ውይይት የሚሻ ስስ ብልት መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ የትኛው ባህል ከየት መነጨ በሚሉ መዳረቆች ጊዜ ማጥፋት ሳይሆን፣ የተወራረሱትን አክብሮ መጠቀምና ያልተቀየጡትን ደግሞ አክብሮ በመያዝ አዳብሮ የልዩነታችን ኅብረ-ቀለም እንዲሆኑ ማጎልበትና ማስጌጥ መልካም ይመስለኛል፡፡ በፍጹም መቀየጥ የለባቸውም በማለት አጥሮ ማኖርም ዓለም አሁን በደረሰበት ሁኔታ የሚከብድ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ አንጻር እኔ የምመኘው በቅድሚያ የእያንዳንዱን ህዝብ ባህል ማጥናትና ማወቅ ላይ ነው፡፡ የተጠናም ካለ፣ በቅጡ በመጽሐፍ ተደጉሶ ሁሉም እንዲያውቀው ቢደረግ ይጠቅማል፡፡ በሂደቱ የጋራና የብቻ የሆኑትን ባህሎች ከጥናቱ በመነሳት መለየት የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ከዚያም ባህልን አስመልክቶ ውይይቶችን የባህሉ ባለቤት ከሆነው ሕዝብ ጋር ጠቃሚውንና ጎጂውን በመለየት አንጥሮ ማውጣት ነው፡፡ ከተነጋገሩ ሁሉም ነገር ይቻላል፡፡ ባህልን አስመልክቶ፣ ለምክክር ኮሚሽኑ በአጀንዳ መልክ ይቅረብ የሚል ምኞት ግን የለኝም፡፡
“ጎጂ” ተብለው የሚፈረጁት ባህሎችም ቢሆኑ በግልና በጋራ እድገት፣ “በሞራላዊ አስተሳሰብ”፣ በአብሮነት፣ … ላይ ጉዳት የሚያመጡ ሲሆኑ ብቻ ሊታዩ የሚገባቸው ይመስለኛል፡፡ በአጠቃላይ፣ የባህል ጉዳይ ከላይ በጠቀስኳቸው ውስብስብ ምክንያቶች ጠለቅ ያለ እይታን የሚሻ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ክብደቱ የሚመነጨው በውስጡ ከያዛቸው በርካታ እሴቶችና የሰዎች ስስ ብልት ከመሆኑ አንጻር መሆኑንም ማየት የሚቻል ነው፡፡
ከዚህ አንጻር፣ ቢቻል፣ ታሪክንና ባሕልን አስመልክቶ ለምክክር ኮሚሽኑ የሚቀርብ አጀንዳ ባይኖር እመኛለሁ፡፡ ተወያዮች ሲጨቃጨቁ ተቋስለው ከሚለያዩ፣ አብሮ የመኖር ሂደት በራሱ ሁለቱንም (ባህልንና ታሪክን) እንዲያጠራቸው በአብሮነት ለሚደረግ ኢትዮጵያዊ የጋራ ሕይወት መተው ጥሩ አማራጭ ይመስለኛል፡፡ ሲያስፈልግ የታሪክና የባህል ምሁራን ነን የሚሉት በአንድ ላይ ተሰብስበው ይነጋገሩና ተስማምተው አገርንም ያስማሙ፡፡ አገሪቱ በበርካታ የሀሰት ተረኮች የታጨቀች ናት፡፡ ለፖለቲካ ጥቅም ሲባል የተሳሳተ አዲስ ተረክ ላለመፈብረክ ጥንቃቄ ይሻል፡፡ የተሳሳቱ ካሉም ማስተካከል መልካም ነው፡፡
ከጥናት ውጪ፣ ማንም በዘፈቀደ ተነስቶ ይህ “ጎጂ” ባህል ነው፤ ይህኛው ደግሞ “ኋላ ቀር ባህል” ነው ብሎ ከመፈረጅ በመቆጠብ፣ ለእድገትና ለምክንያታዊ አስተሳሰብ ለውጥ መነሻ በሚሆኑት ላይ ውል ያለው ትኩረት በመስጠት መሥራት የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ የተለያዩ የአገራችን ባሕሎች ጌጦቻችን ናቸው፡፡ ጌጥ እንደ ቀልድ አይጣልም፡፡ በክብር ያስቀምጡታል፡፡ በክብር የተያዘ ነገር ደግሞ ጊዜያትን ሁሉ ተሻግሮ አኩሪ የታሪክ መረጃ በመሆን ቱሪስቶችን ከዓለም ዙሪያ ሊስብ የሚችል እንቁ ይሆናል፡፡ ለሁሉም ጉዳይ ባህልና ታሪክ አብረውን ያሉና የሚቀጥሉ ጥላዎቻችን ናቸውና በጥንቃቄ መያዝ (ያ ይጠብቃል) የሚገባቸው ናቸው፡፡ እንደ አስተዳደር ስርዓቶቻችን አይደሉም፡፡ የኢትዮጵያን የአስተዳደር ሥርዓት በተመለከተ ብዙ የሚባል ጉዳይ የለውም፡፡ የአስተዳደር ስርዓት ፖለቲካ በመሆኑ ተለዋዋጭ ነው፡፡ ፖለቲከኞቹም ተለዋዋጭ ናቸው፡፡ ፖለቲካው፣በፖለቲካ ኤሊቶች የአፈር ዓይነት መረጣ የሚሠራና (ሠ ይጠብቃል)፣ እናውቃለን የሚሉ ፖለቲከኞች ሁሉ የሚያቦኩት የሸክላ ጭቃን ይመስላል - እየፈረሰ የሚሠራ፡፡ የጋራ ባህልንና ታሪክን ተንተርሶ በእኩልነት የሚከዉን ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ አስተዳደር ስርዓትን እየናፈቁ መኖር እንዴት ይከብዳል መሰላችሁ? በናፍቆቴ መካከል የአኩሪ ታሪክና ባህል ባለቤት መሆኔ ግን ያጽናናኛል፡፡ ያ ባይሆን ምንኛ በተከፋሁ! ሰላም፡፡

 

Read 572 times