ኤችአይቪን በተመለከተ ብዙ ልምድ አለን፡፡ ግን ሸልፍ ላይ አስቀምጠነው ነበር፡፡ እሱን መልሰን ማንሳት ነው፡፡ ለመከላከል ሌላ የተለየ እውቀት አያስፈልግም፡፡ ምርመራው አለ፡፡ ሕክምናው አለ፡፡ ትተን የነበረውን ሥራ መቀጠል ነው፡፡
በኤችአይቪ ምክንያት ሰው ሲሞት፣ ሰው ሲቀበር ያላየ ትውልድ መጥቷል፡፡ ስለዚህ ማስተማሩ ሊቋረጥ አይገባም፡፡
ዶ/ር ፍስሐ ታደሰ የጽንስና ማህፀን ሕክምና እስፔሻሊስት
ከአሁን ቀደም ከሰጡት ቃለምልልስ የተወሰደ፡፡
በኢትዮጵያ አቆጣጠር ህዳር ማብቂያ ላይ በውጭው አቆጣጠር December 1 በየአመቱ ኤች አይቪ ኤይድስን በሚመለከት ማንኛውንም መረጃ የአለም ሀገራት እርስ በእርሳቸውም ሆነ ከውጭ ኃይላት ጋር የሚለዋወጡበት ህብረተሰቡን የሚያነቁበት፤ ስርጭቱን በማስቆምም ሆነ ህክምናውን በማዳረስ በኩል ስለአለው አገልግለሎት የሚወያዩበት፤ስርጭቱ የነበረበትን እና ያለበትን ደረጃ በጥናት ይፋ የሚያደርጉበት ፤ወደፊት የተሸለ ነገር ለመስራት ምን ይደረግ ብለው የሚመክሩበት መሆኑ እሙን ነው፡፡ እኛም ከወዲሁ ርእሰ ጉዳዩን በሚመለከት አንዳንድ መረጃ ዎችን ለንባብ ብለናል፡፡
አለም አቀፍ ቀን የሚወሰነው ሰዎችን ለማስተማር፤አለም አቀፉን ችግር ለመቅረፍ ፖለቲካዊ ፈቃደኝነትን እና አቅምን ለመፍጠር እና የህብረተሰቡን ጥረት ለማጠናከር ሲባል ነው ይላል የተባበሩት መንግስታት መረጃ፡፡ የኤችአይቪ ቫይረስ መኖሩ ከታወቀበት ጊዜ ጀምሮ በአለም አቀፍ ደረጃ 88.4 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውንና ወደ 42.3 ሚሊዮን የሚሆኑት ለሞት መዳረጋቸውን አለም አቀፍ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
እንደ ውጭው አቆጣጠር እስከ 2023 ማብቂያ በአለም አቀፍ ደረጃ 39.9 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በአለም አቀፍ ደረጃ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ መሆኑ ተረጋግጦአል፡፡ ምንም እንኩዋን ስርጭቱ ከአገር አገር ቢለያይም እድሜአቸው ከ15---49 የሚደርስ ሰዎች ባብዛኛው በአለም አቀፍ ደረጃ ቫይ ረሱ በደማቸው ውስጥ ይገኛል ይላሉ አንዳንድ እማኝነቶች፡፡
በአፍሪካ የሚገኘው የአለም የጤና ድርጅት ወኪል እንደሚያስረዳው በአፍሪካ ከሰላሳ ወጣት አንዱ በሚባል ደረጃ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ሲሆን የዚህም ግምት በአለም ላይ ቫይረሱ በደማቸው ካለባቸው ሰዎች (2/3) ሁለት----ሶስተኛውን ያህል ይሆናል፡፡ አለም አቀፉን ኤችአይቪ ኤይድስ ቀን በማስመልከት በ2023 የወጣው መረጃ የሚከተለውን ይጠቁማል፡፡
በ2023/ በአለም አቀፍ ደረጃ 39.9 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ይገኛል፡፡
በ2023/ በአለም አቀፍ ደረጃ 630.000 የሚሆኑ ሰዎች ከኤችአይቪ ጋር በተያያዘ ለሞት ተዳርገዋል፡፡
በ2023/ 103 የሚሆኑ ሀገራት ባስተላለፉት ሪፖርት በድምሩ ወደ 230 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች እራሳቸውን ከቫይረሱ ለመከላከል እና ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅ በጤናቸው ላይ ምርመራ አድርገው ውጤታቸውንም ተቀብለዋል፡፡
በየአመቱ ዲሴምበር 1 አለም አቀፉ ህብረተሰብ የአለም ኤድስ ቀንን ምክንያት በማድረግ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ሰዎችን እና በቫይረሱ የተጎዱ ሰዎች እንዲሁም በቫይረሱ ምክንያት ለሞት የተዳረጉትን ለማሰብ፤ለመርዳት እና ለማጠናከር በሚረዳ መልኩ ጎን ለጎን መቆማቸውን የሚያሳ ዩበት ነው፡፡ ህብረተሰብ ከተሳተፈበት እና መንገዱን ከመራ አለም ኤችአይቪ ኤይድስን እንዲያበቃ ታስችላለች የሚል እምነት አለ ብሎአል የ2023/አለም አቀፍ ኤችአይቪ ኤይድስ ቀን መሪ ቃል፡፡ ቫይረሱ በደማቸው ያለ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚስተናገዱባቸው፤ ለአደጋው የተጋ ለጡ፤ወይንም በቫይረሱ ተጎጂ የሆኑ ሰዎች ኤችአይቪን በመከላከል ረገድ ከፍ ያለ እና ውጤታማ እርምጃ ሊያሳዩ ይችላሉ፡፡ ህብረተሰቡ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ያለባቸውን ሰዎች በግል ደረጃ የህብረተ ሰብ ጤና አገልግሎትን ከሚያገኙበት ጋር ማገናኘት፤እንዲያምኑበት ማድረግ፤ፖሊሲውን እና አተገባበሩን መከታተል እና አገልግሎት ሰጪዎቹን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ለማድረግ መከታ ተል አለበት፡፡ ይህ የአለም አቀፍ ኤይድስ ቀን ከአንዳንድ የህብረተሰብ የስራ ውጤቶች ወይንም ክብረበአላት የበለጠ ተደርጎ መወሰድ ያለበት ነው፡፡ ይህ እለት ለድርጊት፤ እርምጃ ለመውሰድ እና ህብረተሰቡ በራሱ አመራር ተመስርቶ ለሚተ ገብረው ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል በመሆኑ ከፍተኛ ቀን ነው ይላል የ2023/ የአለም ኤይድስ ቀን፡፡
እስከአሁን ባሉት ጊዜያት የኤችአይቪ ስርጭትን በሚመለከት የተሰበሰቡ መረጃዎች ከትክክለኛ ሰዎች፤ በትክክለኛ ቦታ እና በትክክለኛው ጊዜ የተሰራ መሆኑን አለም አቀፉ መረጃ ያረጋግጣል፡፡ ይህም በመሆኑ ወደፊት ስርጭቱን ለመግታት መሰራት ስላለባቸው ነገሮች ለመነጋገር፤ለመወሰን፤ ለመደጋገፍ፤መጠንንና ጊዜን ዓላማው ያደረገ ስራን ለመስራት ለውጥ ለማምጣትና ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚረዳ ስራ ለመስራት ያስችላል ይላል ያለፈው አመት የ2023/ የአለም ኤይድስ ቀን ዘገባ፡፡ ለዘንድሮ ማለትም ለ2024 አለምአቀፍ ኤችአይቪ ኤይድስ ቀን የተዘጋጀው አለም አቀፍ መረጃ አንዳንድ ነገሮችን እንደሚከተለው አስፍሮአል፡፡
በ2023/ 39.9 የሚሆኑ ሰዎች በአለም አቀፍ ደረጃ ቫይረሱ በደማቸው ይገኛል፡፡
በ2023 1.3 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ኢስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ተመዝግበዋል፡፡
በ2023 630.000የሚሆኑ ሰዎች ከኤይድስ ጋር በተያያዘ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
በ2023 30.7 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ፀረ ኤችአይቪ መድሀኒት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
በ2023 ወደ 5.4 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው ይገኝ እንደነበር አያውቁም ነበር፡፡
ዲሴምበር 2023 መጨረሻ ላይ በአለም አቀፍ ደረጃ 30.7 ሚሊዮን የሚሆኑ ፀረ ኤችአይቪ ተጠቃሚዎች ተመዝግበዋል፡፡
ምንጭ UNAIDS /2024
ኤችአይቪ ኤይድስን በሚመለከት ከአሁን ቀደም በተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር የሰራናቸውን ስራዎች በመጠኑ ቀነጫጭበን ለዚህ እትም ብለናል፡፡
‹‹…እኔ የሚገርመኝ ነገር ሰው በዚህ ዘመን የሚያሳየው አካሄድ ነው፡፡ ሳይንስ በረቀቀበት ስንት ነገር በሚሠራበት ዘመን ላይ ሆነን እንዴት ወደኋላ እንመለሳለን? ለምሳሌ… ኤችአይቪ ቫይረስ በጸበል ወይንም በባህል ሕክምና ይድናል…. የምን ኪኒን መዋጥ ነው? ሲሉ የሚስተዋሉ ሰዎች አጋጥመውኛል፡፡ እንዲያውም አንዲት ዘመዴ ሞታብኛለች፡፡ የሕክምና ዘዴውም ሆነ ጸበሉ ወይንም ባህላዊ ሕክምናው አንድን ሰው የሚያድነው እኮ እግዚአብሔር ሲፈቅድ ነው፡፡ ኤችአይቪን በተመለከተ መዘናጋት አይገባም፡፡››
ዘመዴ አንተነህ ከደብረብርሃን
‹‹……እኔ የኤችአይቪ ቫይረስ በደሜ ውስጥ ይገኛል፡፡ ኑሮዬ እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ በየሰው ቤት እየዞርኩ ልብስ አጥብ ነበር፡፡ እንጀራም እጋግር ነበር፡፡ ነገር ግን ቫይረሱ በደሜ ውስጥ እንዳለ ሲታወቅ ሰዎቹ አናስጋግርም ፤አናሳጥብም አሉኝ፡፡ እኔም ተውኩት፡፡ ታዲያ መድሃኒቱን ሲመቸኝ እየወሰድኩ ሳይመቸኝ ሲቀር እየተውኩት ነበር፡፡ ለካንስ ማቋረጥ አይገባም ነበርና እጅግ በጣም ታመምኩኝ፡፡ ሰዎች ወደ ሆስፒታሉ አድርሰውኝ በከባድ ሁኔታ ታክሜ ዳንኩኝ፡፡ ለመዳን ግን ብዙ ጊዜ ነበር የወሰደብኝ፡፡
ውብ እስከዳር መንግስቱ ከደብረብርሃን
ከላይ ያነበባችሁት ስለ ኤችአይቪ አንዳንድ ነገሮችን ለመነጋገር በደብረብርሃን ሪፈሆስፒታል በተገኘንበት ጊዜ ያነጋገርናቸው ታካሚዎች እማኝነት ነው፡፡ የደብረብርሀን ሆስፒታል ቆይታችንን ስንፈትሽ ያገኘነው ቁም ነገር ከህብረተሰቡ ጋር በቫይረሱ ዙሪያ ምክክር ማድረግ የሚል ይገኝበታል፡፡ ይህ ሀሳብ በ2023/ አለም አቀፍ ኤችአይቪ ቀንን በሚመለከት የወጣውን መሪ ቃል (Community lead) ከሚለው ጋር ይመሳሰላል፡፡ በጊዜው ከደብረብርሀን ያገኘነው መልስ ፡- የምክክር መድረኩ ያስፈለገበት ምክንያት የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት ከማኅበረሰቡ ጋር ከመምከር የተሻለ መፍትሔ ይገኛል የሚል እምነት ስለሌለ ነው፡፡ መድሃቱን እየጀመሩ የሚያቋርጡ፤ መድሃኒቱን ጊዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የሚጠቀሙ እንዲሁም እያቋረጡ የሚመለሱ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ጭርሱንም አቋርጠው ወደ ባህላዊው መንገድ የሚሄዱ አሉ፡፡ መድሃኒቱን ባለመውሰዳቸው ወይንም ጀምረው በማቋረጣቸው ምክንያት በጣም ከታመሙ በኋላ ወደ ሆስፒታል ቢያመጡዋቸውም እንኳን ማዳን ከማይቻለበት ደረጃ ላይ ደርሰው ሊሆን ስለሚችል ሞት የማይቀር ይሆናል፡፡ ስለዚህም ህብረተሰቡ እርስ በእርሱ እንዲማማር ማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡
Monday, 18 November 2024 08:01
ኤችአይቪን በተመለከተ መዘናጋት አይገባም፡፡
Written by ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Published in
ላንተና ላንቺ