Monday, 18 November 2024 08:14

አንብቢ - ሃገሬ!

Written by  ነቢል አዱኛ
Rate this item
(0 votes)

”አንባቢ ትውልድ ያላት ሃገር ኃያል ትኾናለች!“

ነቢል አዱኛ


፨ ግርማ ሞገስ የተላበሱ፣ 70ኛ ዓመታቸው’ን በቅርቡ የደፈኑ፣ ከሁለት ደርዘን በላይ መጻሕፍት የጻፉ አዛውንት ይታያሉ። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሱዳን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ፣ ሃይማኖታዊ ዕውቀታቸውን ከተለያዩ ምሁራን የቀሰሙት አባት በልጆቻቸው ተከበው ተቀምጠዋል - ዑስታዝ ሉቅማን። ማንበብን የሚስታቸው ያህል የሚወዱት እኚህ አባት፤ በእድሜ መግፋት አይናቸው እንደበፊቱ አልታዘዝ ቢላቸው ‹‹ሰው ከማንበብና ከመጻፍ ከተቋረጠ ምን ህይወት አለው?›› እያሉ ይተክዛሉ። እስራቸው ተቀምጠው ለሚያደምጧቸው ልጆቻቸው ከረዥም አመት በፊት ያነበቡትን አሁን ያነበቡት ያህል በቃላቸው ይወጡላቸዋል። የመጽሐፉ ሽታ ሲናፍቃቸው ከአምስት ሺህ በላይ መጻሕፍትን ካቀፈው የግል ቤተ-መጽሃፍታቸው ገብተው ይዳብሷቸዋል። የልጅ ልጃቸው ጓደኛውን ይዞ መጥቶ ያስተዋውቃቸዋል፤ ከዕውቀታቸው መቋደስ እንደሚፈልግ ይነግራቸዋል። እሳቸውም ‹‹በዘመናችን ያለው ችግር መነሻው መሃይምነት ነው። ይህን ለማስተካከልና ለመለወጥ መነሳት አለብን። የለውጥ ሁሉ መነሻው የአስተሳሰብ ለውጥ ነው!›› ይላሉ። ‹‹ዕውቀት የአንድ ህዝብ መለኪያ ነው!›› በልጅ ልጃቸው አስተዋዋቂነት ዑስታዙን ያወቃቸው ስሙን ያልነገረን ‹እኔ› ባዩ ገጸባህሪ፤ ከሳቸው የተማረውን ይነግረናል። ‹‹ፈጣሪ ከፈጠራቸው ፍጡሮች ውስጥ ትልቁ አዕምሮ ነው›› ይላሉ ዑስታዙ። በመጠን ትንሽ ቢኾንም በውስጡ በሚያቀናብራቸው በርካታ ነገሮች እስከ ሰማይ መምጠቅ፣ ምድረ ዓለምን ማካለል፣ በውስጡ ከ100 ሚሊዮን በላይ መጻሕፍትን መያዝ ይችላል።
‹‹በእያንዳንዱ ደቂቃ ከአንድ መቶ ሺህ እስከ አንድ ሚሊዮን ያህል የሚኾኑ የኬሚካል መብላላቶች(Chemical reactions) ይከናወናሉ።››(23).. በማለት የተሰጠን ትልቅ መኾኑን ያስታውሱናል። በዚህ በላቀው አዕምሯችን ተጠቅመን ለዓለም፣ ለሰው ዘር ጠቅላላ የሚኾን ነገር ማበርከት አለብን፤ በአዕምሯችን ተጠቅመን ፈጣሪን ስናውቅ የዕውቀት መሃል ላይ ደርሰናል፣ ፈጣሪን ካወቅንና ከተረዳን ሌላው ገር ይኾናል።›› ይሉናል። አረቦች እንደሚሉት፤ ‹‹መን አረፈ ረበሁ አረፈ ነፍሰሁ›› በርግጥም አምላኩን ያወቀ ራሱን አውቋል። ከዕውቀትም እኩል ልቦናን መግራት (Emotional Intelligence) ግዴታ ነው። ስሜትን መገደብ መቻል፣ አመዛዛኝና አስተዋይ መኾን፣ አለመቸኮል ለሰው ልጅ አስፈላጊ ነገሮች ናቸው። እናም ዕውቀትም ከእዝነት ጋር ነው፦ ‹‹ከዕዝነት የራቀ ዕውቀት የተፈጠርንበትን አላማ ያዘናጋል። ዕውቀቱም ለጥፋት ነው የሚውለው።›› (21) ..ያለ ዕዝነት ዕውቀት ለሰው ልጅ ልማት የሚጠቅምን ሳይኾን ቦንብ ያሰራል፤ እንደ ሂትለር ዶክተሮች የተጎዳን ሰው ይዞ በስመ ጥናት(Experiment)‹‹ሰውነቱ ላይ ባክቴሪያ ብንጨምር ስንት ቀን ተሰቃይቶ መቆየት ይችላል?›› አስብሎ በነፍስ ያሳልቃል። መዝሙረ ዳዊት (110:10) ላይ “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው።” እንደሚለው የጥበብና ዕውቀት መነሻ ፈጣሪን መፍራትና አዛኝ መሆን ነው።
፨ በተከታታይ ሳምንት ጓደኞቻቸውን እየጨመሩ ዑስታዙ ሥር ቁጭ ብለው ለሰው፣ ለማህበረሰብ፣ ለሃገር፣ ለሰው ዘር በጠቅላላ እንዴት መጥቀም አለብን የሚለውን ይማራሉ። ዑስታዙ ከንባብ ፍቅር በተጨማሪ ዕውቀትን ከተግባር ጋር ማጣመዳቸው እንደጠቀማቸው ይናገራሉ። ጠያቂ አዕምሮ አስፈላጊ እንደኾነ፣ ሁለገብ ዕውቀት ግዴታ እንደኾነ ‹‹በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ሁሉን አቀፍ ዕውቀት ያለው አካል ከሌለ ሙሉ ማህበረሰቡ ተጠያቂ ነው›› እያሉ ይናገራሉ። ‹‹ማህበረሰባችን ከዕውቀት በመራቁ አሁን ያለንበት ዘመን ላይ ደርሰናል። ይህን ለማስተካከል የምንነሳው አስተሳሰባችንን በመቀየር ነው።›› በማለት ሃገራችንን ከሌሎች አለማት ጋር እያነጻጸሩ የማንበብ ባህላችንን ይኮንናሉ። ሰው ከራሱ ጀምሮ አለምን መቀየር እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተው ይመክራሉ። ‹‹ይህች ሃገር ካለችበት የድህነት አረንቋ የምትወጣው በዕውቀት በጠገቡ አዕምሮዎች፣ ቅን አስተሳሰብ በተሞሉ ልቦናዎችና ለሌሎች በሚኖሩ ሰብዕናዎች ነው።››(79).. ይላሉ። በነብዩ ሙሐመድ “የከሰረ ሰው ማለት ሁለቱ ቀኖቹ አንድ አይነት የኾኑበት ነው!” በሚለው ንግግር በመነሳት ‹‹አዕምሮ አዲስ ነገር የማይቀርብለት ከኾነ ለርሱ ዛሬ እንደ ትናንት ነው፣ ትናንቱም እንደዛሬ ነው።››(26).. ይሉናል። ሌላው ለሃገራችንም ኾነ ለመላው አለም በስርዓት የተጻፈ ታሪክ እንደሚያስፈልገን በመግለጽ የታሪክ ፍልስፍናን (Philosophy of History) ፋይዳ ይናገራሉ። ወጣቶቹ በዑስታዙ በተመከሩት፣ የበፊት ሥልጣኔዎችን ልዕልና ሲሰሙ በውስጣቸው የሰረፀውን ለለውጥ አነሳሽ ሃሳብ ይዘው መከሩ - አምስት መጻህፍትን ይመርጡና (5 ናቸው) ተራ በተራ እያነበቧቸው ይወያዩባቸው ጀመር፡፡ ለስድስት ወራት ቀጠሉበትና 25 መጻሕፍትን አንብበው ተወያዩባቸው። ከጊዜ በኋላ የመጻሕፍት ዋጋ የተወደደባቸው ወጣቶች ከነሱ አንዱ በኾነው (አዩብ) ሃሳብ አመንጪነት የመጽሐፍ ዕቁብ ይጀምራሉ። የጀመሩትንና የደረሱበትን ጉዳይ ለዑስታዙ ነገሯቸው። ‹‹ጎበዞች እንዲህ ነው እንጂ!›› ይሏቸውና ‹‹ሁልጊዜ አንብቦ መወያየት ብቻ ሳይኾን ሃሳብ አምጥታችሁ በሃሳቡ ላይ በርካታ መጻሕፍት አንብባችሁ ተወያዩ። ለምትፈልጉት መጻሕፍት የኔ ቤተ-መጽሃፍ ክፍት ነው።›› ብለው ሃሳብ ይነግሯቸዋል። <<የእምነት ነጻነት በእስልምና ዕይታ እና ለውጥ፦ ተግዳሮቱና መፍትሄው>> በሚሉ ሃሳቦች ላይ ይወያያሉ። እንዲህ እያለ ይቀጥልና ከገጽ 177 - 199 ድረስ የዋና ገጸባህሪውን አስተማሪ ማስታወሻዎች እናነባለን። በመጨረሻም ከገጽ 246 - 254 ድረስ ዑስታዙ ለወጣቶቹ “ለምን አጫጭር ጽሁፎች እየጻፍኩ አልሰጣቸውም?” በሚል ሃሳብ ተነስተው የጻፏቸውን 70 ሃሳቦች አንብበን መጽሐፉን እንጨርሳለን። እነዚህ 70 ሃሳቦች የመጽሐፉን ጭብጥ ጠቅለል አድገው የሚያሳዩ ናቸው።
፨ በዑስታዝ በድሩ ሁሴን (ኢንጂነር) በ2009 ዓ.ም የታተመው <ለውጥ> የተሰኘው ይህ መጽሐፍ፤ የሚተረክልን በአንደኛ መደብ ወይም በ‹እኔ› ባይ ገጸባህሪ ነው። ደራሲው መጽሐፉን ሲጽፍ ለሃሳቦቹ እንጂ ለአተራረኩ ብዙም የተጨነቀ አይመስልም። በመጽሐፉ ውስጥ የሚነሱት ጠንካራ ሃሳቦች ለአተራረኩ ትኩረት እንዳንሰጥ ቢያደርጉንም ትረካው በሦስተኛ መደብ ወይም በ‹ሁሉን አወቅ› ተራኪ ቢኾን የተሻለ ነበር። ይህ ‹እኔ› ባይ ተራኪም ለአንደኛ መደብ ገጸባህሪ ምስጢር የኾኑ ጉዳዮችን ሲነግረን እንመለከታለን። መጽሐፉ ሲጀምር እንኳ በዚህ ገጸ-ባህሪ የሚተረክ አይመስልም። አተራረኩና አሳሳሉ ለአንደኛ መደብ የሚኾን አይደለም። ለምሳሌ፦ከገጽ 201-208 ያለው ሙሉ ታሪክ፣ ከ241 እስከ መጨረሻው፣ ገጽ 118 ላይ ጓደኛቸው አዩብ “ዕውነተኛ ታሪክ ላጫውታችሁ” ብሎ ገና ታሪኩን ሳይጀምር ዋና ገጸባህሪው በመሃል መጥቶ ‹‹አዩብ ከ’ይቻላል’ መንፈስ ጋር የተገናኘ ታሪክ ሊያወጋን በማሰብ በዚህ ሰአት የሚጠቅመንን ታሪክ ሊነግረን ነው›› ይለናል። ሌሎችም መጥቀስ ይቻላል።
፨ ሌላው የምናስተውለው ነገር ገጸባህሪያቱ በራሳቸው መስመር እንዲጓዙ ደራሲው አይፈቅድላቸውም - ወደ ራሱ ሃሳብ ስቦ ያመጣቸዋል። ዋና ገጸባህሪው ሌሎች ገጸባህሪያት ሲናገሩ በየመሃሉ እየመጣ “እንዲህ ማለታቸው ነው” ይላል። ይህም መኾን ያልነበረበት ነው።
፨ በመጨረሻም መጽሐፉ ለሰው ልጆችም ኾነ ለሃገር የሚጠቅሙ፣ እያንዳንዳቸው ሊጻፍባቸው የሚችሉ ብዙ ጠቃሚ ሃሳቦችን የያዘ በመኾኑም ሁሉም ማንበብ የሚችል ሰው እንዲያነበው የምመኘው ነው።
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በቴሌግራም አድራሻው፡- @NEBILADU ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 174 times