Monday, 18 November 2024 08:10

ገብረ ክርስቶስኣዊው የሙዚቃ ዓለም

Written by  አብርሃም ገብሬ ደቢ
Rate this item
(1 Vote)

ሙዚቃ ስሜት ነው፤ለልብ የሚከየን፡፡ በሙዚቃ የደነደነ ልብ ይባባል፡፡ የተዘበራረቀው የሕይወት መስመራችን በሙዚቃ ቅጥ ይይዛል፡፡ የተበታተነው ትኩረታችን ከሙዚቃ በሚወጣ ዜማ ይሰክናል፡፡ ለዚህ ይመስላል ፈረንሳዊው ፈላስፋና የሙዚቃ ሃያሲ ጋብሬል ማርሴል፤ “ዛሬ ላይ የኪነት ዋነኛ ተግባር መሆን ያለበት የተመሰቃቀለውን የህላዌ ዑደት ቅጥ ማስያዝ ነው” (The task of art today is to bring chaos into order) ያለው፡፡
ሙዚቃን ጨምሮ ሌሎችም ኪናዊ የፈጠራ ሥራዎች ስሜታችንን እንደ እንፋሎት እያትጎለጎሉ ከውስጥ ፈንቅሎ እንዲወጣ በማድረግ በነጻነት ባህር ውስጥ ያንሳፍፉናል፡፡ ከጊዜና ከስፍራ የተቆራኘንበትን ሰንሰለት በመበጣጠስ በምናብ እሩቅ እንድንጓዝ፤ በነጻነት ወዳሻን ዓለም እንድንቀዝፍ ዕድል ይሰጡናል፡፡
በእርግጥ ኪነት ነጻነት ነች፡፡ ከያኒው በምናቡ አለም ያበጃጃትን የሕይወት ቅጥ ስጋ አልብሶ ለተደራሲያን ያቀርባል፡፡ ይህ ጥረት የተለየ ቁሳዊ ጥቅም ታስገኝልኛለች ከሚል መነሻ ሳይሆን የመንፈስ ሃሴት ለከያኒው ስለምታጎናጽፈው ነው፡፡ ሃሴት ደግሞ ነጻነትን ይወልዳል፡፡ ለዚህ ነው ከያኒው የፈጠራ ስራዎቹን ውበትና ቅርጽ አላብሶ እንካችሁ የሚለው፡፡ ይህ የፈጠራ ስራ ደግሞ የሕይወታችን ሌላኛውን ገጽታ እንድንረዳ ዕድል ይሰጠናል፡፡
በታላቁ ሰዓሊና ገጣሚ ገብረ ክርስቶስ ደስታ የግጥም ስራዎች ላይ እንደምናነበው፣ አንድን የምናውቀው የሚመስለንን ነገር ያላየነውን ሌላኛውን ገጽታ በማሳየት ያስደምመናል፡፡ የጋራ ስምምነት የፈጠረንባቸው ሃሳቦችን በመሞገት አዲስ አይነት ምልከታዎችን ያጋራናል፡፡
ገብረ ክርስቶስ ደስታ ‘መንገድ ስጡኝ ሰፊ’ በተሰኘው ተወዳጅ የግጥም መድበሉ ውስጥ ከተካተቱት ግጥሞች መካከል ስለሙዚቃ የተቀኛቸው ግጥሞች ይህንን የገጣሚውን የሰላ ምልከታ ውብ አድርጎ ያስነብበናል፡፡ ይህንን ታሳቢ በማድረግ በእነዚህ ግጥሞች ላይ ምጥን ዳሰሳ ለማድረግ ሞክሬያለሁ፡፡
እነዚህ የገብረ ክርስቶስ ደስታ ግጥሞች ዋነኛ ጭብጣቸው ሙዚቃ ነው፡፡ ሙዚቃን በቃላት ይኩላሉ፡፡ የሙዚቃ ኪናዊ ተፈጥሮን ያደንቃሉ፡፡ ከዚያም አልፎ ከያኒው ሙዚቃ ገጽታዋና መገኛዋ ብዙ መሆኑን “የሙዚቃ ድምጽ” በተሰኘው ግጥሙ እንዲህ ሲል አውጇል፤
የዛፉ ቅርንጫፍ የበገና ቅኝት
ነፋስ ሲያውተረትር የሚጫወትበት፡፡
እያጨበጨቡ፣
ቅጠሎች በጃቸው ዜማውን ሲያደምቁ
ወፎች ድምጻቸውን እያስረቀረቁ፣
ወንዙ እየተላጋ፣
እየተጋረፈ ሲሄድ እንዳለንጋ፣
ባህር ሲገላበጥ
እየተንጠራራ ወደቡን ሲቧጥጥ፣
መብረቅ ደመናውን ሰንጥቆ ሲወጣ
እያስገመገመ ሰማዩ ሲቆጣ፣
ሙዚቃ ተወልዷል፡፡
ፍጥረት ተሰብስቦ መዝሙር ይዘምራል፡፡
በዚህ ግጥም ውስጥ ሙዚቃና ፍጥረታት ይወዳጃሉ፡፡ የተራራቁ የሚመስሉ ነገሮች ህብር ይፈጥራሉ፡፡ እንዲሁም ከያኒው ተፈጥሮን የሙዚቃ መገኛ ምንጭ ያደርጋታል፡፡ የፍጥረታት እያንዳንዱ ድምጽ ዜማ ነውም ይለናል፡፡
የሙዚቃ ድምፁ
አለ፤ ሁሉም ቦታ፣ አለ የትም ቦታ፣
በቅጠል ኮሽታ፣
በውሃ ጠብታ፣
በንጋት በሌሊት በብርሃን በማታ፣
ወይ ከባዶ ቦታ፡፡
ገብረ ክርስቶስ በዚህ ግጥሙ አረዳዳችንን ይሞግታል፡፡ ከዝንጋኤነታችን እንድንመለስ በተዘዋዋሪ ይገስፀናል፡፡ በዙርያችን ያሉ ፍጥረቶች ሲያዜሙና ሲዘምሩ ማድመጥ እንደተሳነን ይነግረናል፡፡ ጆሮ ነፍገናቸው እንጂ ፍጥረታት ድምጻቸው ሙዚቃዊ ነው ሲል ከያኒው በግጥሙ ይጣራል፡፡
ባለ ክራር
አሰማ ዜማህን
በክራሩ ጅማት የሚነደፈውን፡፡
ጣቶችህ ይዝለሉ እያሸበሸቡ
አድማጭ ይሰብሰቡ፡፡
ሙዚቃን አንስተህ ጣለው በሙዚቃ
የፈዘዘው ይንቃ፡፡
የተኛው ይቀስቀስ
ይሽከርከር ይደንስ፡፡
በሙዚቃ የቀዘዘው ስሜታችን ይነቃቃል፡፡ የሚንቀለቀለውን ትኩረታችን ያድባል፡፡ ከያኒው “ባለ ክራር” በተሰኘው ግጥሙ ላይ ባለክራሩን ጠርቶ የሚነግረው ይኸንኑ ነው፡፡ በባለክራሩ የፈዘዘው እንዲነቃ፤ የተኛው እንዲቀሰቀስ ያውጃል፡፡
ሙዚቃን አስተምር ትርጉሙን አስረዳ
የሰው ስሜት ዝረፍ ሐሳብን አስከዳ፡፡
ሒድ ወደ በረሃ ግባ ወደ ጫካ
የዱር አውሬ ስማ ሲጨፍር ሲያስካካ፡፡
ወፎች የሚሉትን ቋንቋቸውን ልቀም
ዜማቸው በክራር በድምጽህ ይተርጎም፡፡
ከያኒው የሙዚቃ ፅንሰት መነሻው ፍጥረታት ናቸው ሲል በዚህኛውና በሌሎች ግጥሞቹ ላይ በአጽንኦት ይገልጻል፡፡ ጀርመናዊው ፈላስፋ ማርቲን ሃይዲገር፤ ኪናዊ የፈጠራ ስራዎች የሰው ልጅ እውነተኛ እሱነቱንና ኑረቱን መግለጥ (Ontological revelation of being) አለባቸው ይላል፡፡ ይህም ማለት ከዘልማዳዊው የህይወት አኗኗር በተሻገረ መልኩ የሰው ልጆችን የህይወት ገጽ የመግለጥ፤ ህይወትን በብዙ አውታሮች እንድንረዳት ዕይታዎችን መፈንጠቅ አለባት ነው፤ የሃይዲገር ክርክር፡፡
ገብረ ክርስቶስም በዚህ ግጥሙ ለባለክራሩ የሚነግረው፣ ሰው ከሌሎች ፍጥረታት ጋር ህብር እንዳለው፤ ሙዚቃውም ከእነዚህ የፍጥረታት እስትንፋስ እንዲቀዳ ያዟል፡፡ ሙዚቃ በአንድ ስቱድዮ ውስጥ ተቀርጾና ተቀናብሮ የሚወጣ ብቻም ሳይሆን ተጎራብተን ከምንኖረው ሌሎች ፍጥረታትም ዜማ ልንቀዳና ልንዋዋስ እንደምንችል አዲስ እይታ ይገልጣል፡፡
ለቡጊ
በግሬ ጣራ መርገጥ፤
ሙዚቃ ሲጋልብ መውጣት መውረድ
መፍረጥ፣
ዐይኔን ማገላበጥ፤
መርበትበት መንቀጥቀጥ፤
መላጋት መንገድገድ እንደሰከረ ሰው
የናፈቀኝ ይህ ነው፤
ተነስቼ ልዝለል፤
“ቡጊ ቡጊ” ልበል፡፡
ቡጊ! ቡጊ! ቡጊ!...
ከበሮ ሲያጋፍት ጥሩንባ ሲያናፋ
ልብሴን ጥዬ ልጥፋ፡፡
ልራቆት አብጄ
ልብረር ካለም ሄጄ፡፡
ሙዚቃው በጥላው ይምጣ ይሸፍነኝ
ሁሉንም ያስረሳኝ፡፡
ገብረ ክርስቶስ “ቡጊ” በተሰኘው በዚህ ግጥሙ ላይ በሙዚቃ ነጻነቱን ያውጃል፡፡ በሚሰማው ሙዚቃ “ቡጊ ቡጊ” ይላል፡፡ ሙዚቃው መጥቶ ሁሉንም እንዲያስረሳውም ይማፀናል፡፡ ሙዚቃና ስሜት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች መሆናቸውን በግጥሙ ያፀናል፡፡
ገብረ ክርስቶስ ደስታ ምንም እንኳን ዋነኛ ትኩረቱን ስዕል ላይ አድርጎ የሚከይን ታላቅ አርቲስት ቢሆንም፣ በዚያው ልክ ታላቅ ገጣሚ መሆኑን ስራዎቹ ሁነኛ ዕማኞች ናቸው፡፡ ከያኒው ስዕልን ያፈቅራል፡፡ ልክ እንደ ስዕል ሁሉ ግጥምን ይወዳል፡፡ ልክ እንደ ስዕልና ግጥም ሁሉ ሙዚቃንም ከልቡ ያፈቅራታል፡፡ ሥዕል፣ ግጥምና ሙዚቃ አንድም ሦስትም መሆናቸውን በስራዎቹ አሳይቷል፡፡ በግጥም መድበሉ ውስጥ ስለ ሥዕልና ሙዚቃ መቀኘቱ የዚህ አፍቅሮቱ መገለጫ አድርገን ልንወስደው እንችላለን፡፡

 

Read 163 times