ሥነ-ጽሑፍ አንድ ሥነ-ዘዴ ነው፤ እውቀት የምናካብትበት መስክ ሲሆን፣ በርካታ ትኩረት ሊደረጉባቸው የሚሹ ጉዳዮች አሉት፡፡ የአንድ ማኅበረሰብ ዕድገት ወይንም ለውጥ ከሚለካባቸው መስፈርቶች አንዱ ሥነ-ጽሑፍ ነው፤ ማኅበረሰቡ የደረሰበትን የሥልጣኔ እና የዕድገት ደረጃ ለመለካትና ለማወቅ ይረዳል…
በአሁን ወቅት፣ ሥነ-ጽሑፋችን ላይ ካጠሉ ጥላዎች መካከል ዋንኛው ዘውግኤያዊ የአተራረክ ይትባሃል ነው፤ ዘውጌአዊ/generic ደራሲዎች ገጸ-ባሕሪይ ቀርጸውና ፈጥረው፣ ለዕድገቱና ለሥነ-ልቡናው፣ ብሎም መላበስ ስላለበት የሥጋ ውቅር ስፍራን ይነፍጉና፣ ሀሳባቸውን ለተደራሲ ያደርሳሉ፤ በዚህ ምክንያት ለፈጠራ፣ ለምናባዊነት፣ ለትረካ ቴክኒክ አጠቃቀም፣ ለበይነ-ዲስፒሊናዊ አተራረክ፣ ለእንግዳ ክስተቶችና መገለጦች፣ ለእንግዳ ገጸ-ባሕሪያት፣ ለሥነ-ምርምር…ወዘተ. ዕድል አያገኙም፤ የኖሩትን በዘገባ መልክ በማቅረባቸው አዲስ ነገር የጎደለው ድርሰት ያቀርባሉ።
በአብዛኛው ጊዜ ከፈጠራ ይልቅ ዘውግ ይዘው፣ ጎራ መድበው፣ ዋልታ ታክከው ስለሚመጡ አጥኚውና አንባቢውንም ለምርምርና ለአዳዲስ ሙግቶች አይጋብዙም፤ ሥነ-ጽሑፍን የመወያያ መድረክ ከማድረግ ያቅቡታል፡፡
እንዲያ ዓይነቶቹ ደራሲዎች የተጫማኸውን የጫማ ቁጥር፣ ወላ የሱሪህን ስፋት ላንተው በመንገር ባክነው ሊያባክኑህ ሲዳዱ ዕድሜያቸውን ይባጃሉ፤ ተደራሲው የኖረውንና በወል፣ በአደባባይ የሰማውን መልሰው ስለሚነግሩ ለምርምር አይጋብዙም። ተረት፣ ተረት ከመንገር ያልተለየ ጉዳይ ይዘው ሊቀርቡም ይችላሉ፤ አዲስ ነገር አጥታ ነፍሳችን ኩም ብላ እንቅልፏን እንድትለጥጥ የሚያደርጉ ናቸው፡፡
እንዲያ ዓይነቶቹን ጸሐፍት ‹‹አትጻፉ›› ማለት ባይቻልም፣ ለአንዳንድ መሠረታዊያን ግን ትኩረት ስጡ ማለት አግባብ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ከሚስተዋሉ ዘውጌአዊ ጸሐፍት መካከል አብዛኞቹ በመቼት፣ በጭብጥ፣ በገጸ-ሰብ፣ በታሪክ… የሚመሳሰሉና የሚቀራረቡ ጽሑፎችን ሰጥተውን ያውቃሉ፤ አዲስ ወደ መፍጠር ሳይሆን፣ የጻፉትን በተወሰነ መልክ በመቀየር፣ ወይም ስምና ቦታ በመለወጥ መልሰው ያንኑ ያቀርቡልናል፡፡
መነበብ አለባቸው፤ ነገር ግን ብዙ ሺ/ሚሊዮን ቅጂ ስለተሸጠላቸው ‹‹ከእነርሱ ወዲያ ከየት መጥቶ!›› ሊባሉ አይገባም፤ ብዙ ቅጂ ተነበበ ማለት መልካም ጎኑ በዛ ማለት ላይሆንም ይችላል፤ እውቀት ለማግኘት፣ የውይይት መነሾ ለመያዝና ሀሳቡን ለማዳበር የሚያነብብ እንዳለ ሁሉ ለፌዝ፣ ለትችት፣ ለማብጠልጠል (በርግጥ ልክ ባይሆንም) የሚያነብም እንዳለ መዘንጋት የለብንም፡፡ ይኼ ጉዳይ ሙዚቃችን ላይም ይስተዋላል፤ ግጥምና ዜማ ብሎም ቅንብር የሌለው የሚመስል ነገር ግን ምስሉ ብቻ ጥሩ የሆነ ዘፈን በዚህ ዘመን ወጣት አድማጮች እየገነነ መምጣቱን አንዘንጋ፤ ብዙ ስለታየ ልከኛ ዘፈን ነው ማለት ዘበት ነው…
…ስለሆነም፣ ብዙ ቅጂዎች የተሸጡ ዘውጌአዊ መጻሕፍትን ከማናፈሳችን በፊት መጠንቀቅ ያለብን ጉዳይ ሊኖር ይገባል፤ ከመነበባቸው በላይ የሚይዙት መልእክት፣ የሚያመጡት አዲስ ሀሳብ፣ በይነ-ንባብ፣ ፈጠራ፣ የማመራመር እድል… ከግምት ሊገቡ ይገባል።
ሥነ-ጽሑፋዊ/literary ተራኪዎች ደግሞ፣ ገጸ-ባሕሪይ ቀርጸው የሚያደርሱ ናቸው፤ እነዚህ ወገኖች፣ ለገጸ-ባሕሪይው ውልደትና ዕድገት፣ ቅርጽና ሰብዕና፣ ሥምና ሥራ፣ ሥጋና ሥሜት፣ ግንባታና ግብረ-መልስ ልዩ ትኩረትን ይሰጣሉ፤ በመሆኑም፣ ለፈጠራ ምቹ ዕድልን ያገኛሉ፤ በይነ-ዲስፒሊናዊ ድርሰት መገለጫቸው ነው፤ ድርሰቶቻቸው የገጸ-ባሕሪይውን ሥሜት በታከኩና ዐውዱን ባማከሉ አዳዲስ ክስተቶች የተሞላ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የቀረጹት ገጸ-ባሕሪይ ሥሙን የሚመስል ሥራን ሲያከናውን ይስተዋላል፤ በላይኞቹ ጎራ (በዘውጌዎቹ) ሥነ-ልቡናዊ ዘውግ ያለው መጻሕፍት ደርሶ ዋናውን ገጸ-ባሕሪይ ራሱን እንዲያጠፋ የሚያደርጉ አሉ፤ ከዐውዱ ያፈነገጡ እንደማለት ነው፡፡
ዘውጌ ደራሲዎች ሥነ-ጽሑፋችንን ሞልተውታል፤ ዓለማየሁ ዋሴ፣ ምሕረት ደበበ እና ዳዊት ወንድማገኝ ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡ በእርግጥ በእነዚህ ‹ደራሲዎች› አነሳሽነት ብዙ ወጣቶች ወደ ንባብ ዓለሙ መግባታቸው ባይካድም፣ ‹ደራሲዎቹ› ተረት፣ተረት ከማቅረብ የዘለለ ነገር አላመጡም፤ የሣይንስንና የዕምነትን ጎራ አልለዩም፤ ዕምነትና ሥነ-ጽሑፍ ተምታቶባቸዋል፤ በእርግጥ ተቀባይነት አግኝተዋል፤ ብዙ ኮፒ ሸጠዋል፤ ዕውነታው ብዙ ኮፒ መሸጥ ሳይሆን የመጻሕፍቶቹ ዋጋ ወይም ጥራታቸው ነው፤ ቁጥር ዕውነትን ሲተካ አላየንም፡፡
Every big victory is not won by war እንዲል ቻይና፣ ጋጋታና ኳኳታ የሚያመጡት ለውጥ የለም፤ አንደኛ ኮፒያቸው ያላለቀላቸው ጉምቱ ደራሲዎችንም በወዲህ በኩል እናውቃቸዋለን…
ዓለማየሁ ዋሴ ሣይንስና ዕምነትን አባርዟል፤ ገጸ-ባሕሪይ ቀርጾ ከመተረክ ይልቅ ያንን ከርታታ ሢሳይ እያነሳ አንዴ ግዑዝ አንዴ ሕያው ሲያደርገው ይኖራል፤ ሕልዮቶችን፣ የተለያዩ መስኮችንና ጥናቶችን ከገጸ-ባሕሪይ ሥሜትና ሁኔታ ጋር አዋህዶ ከመተረክ ይልቅ፣ እግሩ ስር ቁጭ አድርጎ የቸከ ምክሩን ጆሮአችን ላይ ይደነባብናል፤ ገጸ-ባሕሪይውና ዐውዱ በሚፈቅደው መልክ ቴክኒክን ማዕከል አድርጎ ማቅረብ ሲገባው፣ በአነቃቂ ንግግሩ ያንቀናል፤ ቋንቋውም ቢሆን ሥነ-ጽሑፍን የሚመጥን አይደለም…
…ጓድ ዓለማየሁ ዋሴ የሚሳሳተው የማይፈተሸውን፣ እምነት እፈትሻለሁ ሲል ነው፤ ሐይማኖት ውስጥ የማይፈተሽ ሲባል ካላየሁ አላምንም ዓይነት ስህተትን እንደማለትም ሊሆን ይችላል። ሐይማኖት የሚፈተሽ፣ የሚጨበጥ አለመሆኑ ልብ ይባል…
በእንግዳ ሁኔታ ደግሞ፣ ዳዊት ወንድማገኝ ሥነ-ልቡናዊ ይዘት ባለው መጽሐፍ ዋናውን ገጸ-ባሕሪይ ራሱን እንዲያጠፋ የሚያነሳሳበት ሂደት አለ፤ ይኼ የተነሱበትን ዓላማ መሳት ነው…
…አንድ የማያከራክር ነገር አለ፤ እነዚህ ሰዎች ‹ሥነ-ጽሑፍ ነው› ብለው ማቅረባቸው ነው ኪሳራ ውስጥ የዶላቸው፡፡ ሥነ-ጽሑፍ እንዳሻህ የምታፌዝበት መስክ ሳይሆን፣ ጥናት ነው፤ የዕውቀት መስክ ነው፡፡ ጥናትና ምርምር የተለያዩ መስፈርቶችን እንደሚሻ ሁሉ፣ ሥነ-ጽሑፍም ሀሳብ መለፍለፊያ ሳይሆን፣ መስፈርት አሟልተህ የምትተርክበት አንድ ሥነ-ዘዴ ነው፤ ችግራቸው የተለያዩ ሂልዮቶችን በቁም በውርዳቸው መዘገባቸው ነው፤ ሂልዮቶችን በተለያዩ መንገዶች እናነባቸዋለን፤ ሥነ-ጽሑፍ ላይ የሚቀርብ ሂልዮት ግን የሚዘከዘክ ሳይሆን፣ በዐውድ ውስጥ፣ በገጸ-ባሕሪይ ሥሜት መካከል፣ በክስተቶች እየተመሩ የሚተረክ ነው፤ ዝብዝብ ማቅረብ አይደለም ቁምነገር፤ ያንን ከቦታውና ከሁኔታው ጋር ማዋሃድ ነው ትልቁ የቤት ሥራ፤ በመሆኑም፣ የአማርኛን ሥነ-ጽሑፍ ከኸዲዱ በማንሸራተታችሁ ወደ ኋላ ተመልሳችሁ ጥናት አድርጉና ሙከራችሁን አስተካክሉ።
ከአዘጋጁ
ዮናስ ታምሩ ገብሬ በእንግልዚኛ ቋንቋ ማስተማር /ELT/ የፒ.ኤች.ዲ. ተማሪ ሲሆን፣ በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የእንግልዚኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ መምህር ነው፤ ሁለት ሥነ-ጽሑፋዊ መጻሕፍትን በግል፣ አንድ ደግሞ በጋራ ለማሳተም በቅቷል፤ ከዚህ በተጨማሪ የአንደኛና የስምንተኛ ክፍል የእንግልዚኛ ቋንቋ አጋዥ መጻሕፍትን አዘጋጅቷል፡፡ እነዚህን መጻሕፍት የምትፈልጉ በ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
በኩል ማግኘት ትችላላችሁ።