(የጋዜጣው ዜና እንደ አጭር ልብወለድ)
“ዘ ጎድ ፋዘር” የተሰኘው ፊልም ለእይታ የበቃበት ዘመን ነው፡፡ የፍልስጥኤም አሸባሪዎች በሙኒክ ኦሎምፒክ ሽብር የፈጠሩበት ጊዜ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ኒክሰን ለምስራቁና ምእራቡ ግንኙነት አዲስ ምእራፍ ከፋች ጉብኝት በቻይና ያደረጉትም በዚሁ ዘመን ነው፡፡ የሴቶች የነፃነት እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ ያየለበት ጊዜ ነበር፡፡ የሰው ልጅ ወደ ጨረቃ ላይ ከወጣ ብዙ ዘመን ተቆጥሯል፡፡ በፈረንጆቹ አቆጣጠር 1972 ዓ.ም ነው፡፡ በዚህ ዓመት ነው የሚከተለው አስገራሚ ታሪክ ከወደ ጃፓን የተሰማው፡፡
በግምት 5,000 የሚሆኑ ሰዎች በአየር ማረፍያው አካባቢ ተኮልኩለዋል፡፡ አብዛኞቹ በቀድሞው የንጉስ ዘመን በወታደርነት ያገለገሉ ናቸው፡፡ የቀድሞውን ሰራዊት የደንብ ልብስ የለበሰ አንድ ወታደር በጉልህ የሚነበብ አንድ ጽሁፍ በሁለት እጆቹ ይዞ ለአካባቢው ሰው የሚሳይ ይመስላል፡፡
“የጃፓን መንፈስ በውስጡ ያለ ብቸኛ ሰው ዮኮይ ነው!” ይላል ጽሁፉ፡፡ በደህንነት ሚኒስትሩ የተመራ ኦፌሴላዊ አቀባበል እንደሚደረግለት የአገሪቱ ጋዜጦች ለፍፈዋል፡፡ ዮኮይ ከአውሮፕላን ሲወጣ እየተንገዳገደ ነበር፡፡ የህክምና ባለሙያዎች ግራና ቀኝ ደግፈውታል፡፡ ህዝቡ ባንዲራ እያውለበለበ በከፍተኛ ጩኸት አቀባበል ማድረግ ጀመረ፡፡ ዮኮይ ደግሞ ሀምራዊ መሀረብ እያውለበለበ ለህዝቡ የሰላምታ አፀፋ ሰጠ፡፡ ህዝቡ የበለጠ እየጮኸ ስሙን ይጠራ ጀመር፡፡ በነጭ ሳጥን የታሸገ ሬሳ ከአውሮፕላን ውስጥ ወጣ፡፡ ከዮኮይ ጋር ተሰልፈው ህይወታቸውን ያጡ ጓዶች ሬሳ ነበር፡፡ ሬሳውን ለዘመድ አዝማድ የመስጠት ሥነሥርዓት ተከናወነ፡፡
ዮኮይ ጃፓን እንደገባ የተወሰደው ወደ ሆስፒታል ነበር፡፡ ስሜቱን ከገዛ በኋላ እንኳ ለጥቂት ጊዜ እዚያው እንዲቆይ ተደርጓል፡፡ ዮኮይ ጋዜጣ ማንበብ አይወድም ነበር፡፡ ቴሌቪዥን ለመመልከትም ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ “ቴሌቪዥን ማለት ጫጫታና ሁካታ ነው” እያለ ያጣጥለዋል፡፡
ዮኮይ እዚህ ሀገር ከመጣ ለጥቂት ደቂቃዎች ከማሸለብ በቀር ጥሩ እንቅልፍ እንኳ ወስዶት አያውቅም፡፡ ያም ሆኖ አስተኛኘቱም እንደ ቀድሞው ግድግዳ ደገፍ ብሎ ነበር፡፡ ከአዲሱ የአኗኗር ሥርዓት ጋር የተላመደ አይመስልም፡፡ ቀን ቀን ጭንቅላቱን በእጁ ይዞ ይተክዛል፡፡ ድንገት ከመኝታው ላይ ጮሆ ይባንንና፤ “ፃዕረ-ሞት እያስፈራራኝ ነው!” ይላል በላብ ተዘፍቆ፡፡ “ጓዶችህን ጥለህ እዚህ ለምን መጣህ? ይለኛል” እያለ በማለክለክ ይናገራል፡፡ ሀኪሞች የአእምሮውን ሁኔታ የተረዱ ይመስላሉ፡፡
ዮኮይ ፂሙ በጣም ጎፍሮ ነበር፡፡ ከዛፍ ልጥ የሰራውን ጃኬትና ሱሪ ለብሷል፡፡ ለውትድርና ከመቀጠሩ በፊት ልብስ ሰፊ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ይጠቀምበት የነበረውን መቀስ ይዞ ነበር የዘመተው፡፡ በጦርነቱ ዓመታት ሁሉ መቀሱ ባለውለታው ነበር፡፡ ፀጉሩን ለማስተካከልና የሚሰፋቸውን ነገሮች ለመቆራረጥ መቀሱ በአያሌው ረድቶታል፡፡ ጦርነቱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ የለውዝ ፍሬ፣ ማንጎ፣ ፓፓያ፣ ቀንድ አውጣ፣ አይጥና እንቁራሪት ቀለቡ ነበር፡፡ ዮኮይ ከዚህ ኑሮ ተላቆ ከ28 ዓመት በኋላ ወደ ጃፓን እንዴት ሊመጣ ቻለ?
ሃምሳ አለቃ ሾይቺ ዮኮይ አሁን 56 ዓመቱ ነው፡፡ አንድ አመሻሽ ላይ በታሎፍ ወንዝ አካባቢ ባለው ጥቅጥቅ ያለ ደን ውስጥ ሁለት አዳኞች ከበቡት፡፡ ዓሳ ለማጥመድ ወደ ወንዙ እየሄደ ነበር፡፡ አዳኞቹ ጠብመንጃ ደግነው ማረኩት፡፡ ወደ ፖሊስ ጣቢያም ወሰዱት፡፡
ከየአቅጣጫው ስለ ዮኮይ የሚደመጠው ታሪክ በጃፓናውያን ምናብ ውስጥ የሚረብሽ ስሜት መፍጠሩ አልቀረም፡፡ የተረሱ ማህበረሰባዊ ዕሴቶች በእያንዳንዱ ጃፓናዊ ጆሮ ውስጥ ማስተጋባት ጀምረዋል፡፡ ለንጉሱ የነበረው ፍፁም ታዛዥነት፤ እጅ የመስጠት አሳፋሪነትና የሥነ ምግባር ዋጋ በጃፓን ማህበረሰብ ዘንድ እንዲታወስ አድርጓል፡፡ ዓለም አቀፋዊ አቋሟ በጦር ሃይል ሳይሆን በኢንዱስትሪው እድገት የሚወሰነው የዛሬይቱ ጃፓን፣ እነዚህ የቀድሞ እሴቶች የሚፈይዱላት አንዳች ነገር ይኖር ይሆን? በእያንዳንዱ ጃፓናዊ ዜጋ ህሊና ውስጥ የሚንቀለቀል ጥያቄ ነበር፡፡
በርካታ ጋዜጠኞች በአደባባይ ተሰብስበው እየተጠባበቁ ነው፡፡ ዮኮይ ጋዜጣዊ መግለጫ የሚሰጥበት ዕለት ነው፡፡ የጃፓን ጋዜጠኞች ጥያቄዎችን በልዩ ጥንቃቄ አዘጋጅተው ይዘዋል፡፡ አብዛኞቹ ጥያቄዎች ወደ አገሩ በመመለሱ የተሰማውን ደስታ፣ በጦርነቱ ጊዜ የነበረውን አስፈሪና አስቸጋሪ ሁኔታ እንዲገልጽ የሚጋብዙ ነበሩ፡፡ የዮኮይ መልስ ግን አስደንጋጭ ነበር፡፡ ብዙም ሰው ያልጠበቀውን መልስ ነበር የሰጠው፡፡ ዮኮይ ወደ አገሩ በመመለሱ ደስተኛ አልነበረም፡፡
“ሆኖም አንድ ዓላማ አለኝ፡፡ ምናልባት አገሬ ጃፓን በሌላ ጦርነት ላይ የመካፈል እቅድ ካላት የእኔን የውትድርና ልምድ ማካፈል፡፡… አለዚያ ምን ልሰራ መጣሁ?” አለ ዮኮይ ለተሰበሰበው ጋዜጠኛ፡፡
ጋዜጠኞች ተራ በተራ ጥያቄዎች መወርወር ቀጥለዋል፡፡ ዮኮይ ንግግሩ ሁሉ ደረቅና ለዛቢስ ነበር፡፡ ብዙዎቹ ጥያቄዎች ያስደሰቱት አይመስልም፡፡ በተለይ የንጉሱ ስም በአደባባይ መነሳቱ በጣም አስገርሞታል፡፡ “የፈጣሪ ያለህ! የንጉስ ስም በተራ ሰዎች በአደባባይ!” አለ ዮኮይ፡፡ ዮኮይ እውነት አለው፡፡ ከጦርነቱ በፊት በነበረው የወጣትነት ህይወቱ መመዘኛ አንፃር ሲታይ፣ በእርግጥ የንጉሱን ስም በአደባባይ መጥራት ነውር ነው፡፡ ክብራቸውንም ስማቸውንም ማርከስ ይሆናላ!
ጋዜጠኞች ጥያቄዎችን እያከታተሉ መጠየቅ ጀመሩ፡፡
“28 ዓመት ሙሉ የት ነበር የተደበቅኸው?”
“ፓስፊክ ደሴት ጉአም ጫካ ውስጥ”
“ለምንድነው እዚያ የተደበቅኸው?”
“ለጠላት እጃችንን ከሰጠን እንገደላለን ብለን በመፍራት”
“ስንት ነበራችሁ?”
“ሌሎች ሁለት ጓደኞች ነበሩኝ፡፡”
“ታዲያ እነርሱ የት ገቡ?”
“በ1944 የአሜሪካ ወታደሮች ዳግም ደሴቲቱን ሲይዟት እኔና ጓደኞቼ ጉአም ጫካ ውስጥ ዋሻ ቆፍረን ተደበቅን፡፡ ከጥቂት ወራት በኋላ ግን ምግባችን አለቀ፡፡ ሁለቱ ምግብ ፍለጋ ወደ ሌላ ቦታ ሄዱ፡፡ በየጊዜው በድብቅ እንገናኝ ነበር፡፡ የዛሬ ስምንት ዓመት ሞተው አገኘኋቸው”
“በምን ምክንያት የሞቱ ይመስልሃል?”
“በረሃብ ነዋ! ሌላ ምን ሊሆን ይችላል”
“ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃቱን አታውቁም ነበር?”
“በፍፁም! አብቅቷል እንዴ?”
“አቶሚክ ቦምብና ቴሌቪዥን መሰራቱን አታውቁም እንዴ?”
“ምንድናቸው? ዛሬ ገና መስማቴ ነው”
***
የካቲት 5 ቀን 1972 ዓ.ም ለንባብ የበቃው “ዘ ታይምስ” ጋዜጣ፣ እግሩ ውሃ ከመቋጠሩ በስተቀር በተሟላ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ዘግቦ ነበር፡፡ የሚርመው ነገር በአገራችንም እቴጌ በሞቱ (1954) በሁለት ዓመታቸው ከጫካ ወጥቶ “እቴጌ ሞቱ እንዴ?” ያለም ሰው እንደነበር ልብ ይሏል፡፡
(ምንጭ፡- ዘ ዎርልድስ ዊርደስት ኒውስፔፐር ስቶሪስ፤ሃምሌ 20 ቀን 1994 አዲስ አድማስ ላይ የወጣ)