‹‹ይቀነሱ››፣ ‹‹አይቀነሱ›› በሚል ሙግትና ክርክር፤ ከ1917 ዓ.ም ጀምሮ የጋራ ስምምነት ሳይበጅለት አንድ ክፍለ ዘመን ያስቆጠረው የአማርኛ ሞክሼ ፊደላትን በተመለከተ፣ መቀነሳቸውን በመቃወም፣ ምክንያታዊ መከራከሪያ በማቅረብ ከሚታወቁት አንዱ ደራሲ ተሰማ ሀብተሚካኤል ናቸው፡፡ ‹‹ከሣቴ ብርሃን የአማርኛ መዝገበ ቃላት›› በሚል ርዕስ በ1951 ዓ.ም ባሳተሙት መጽሐፍ በተለየ ሁኔታ የሚታወቁት ደራሲ ተሰማ ሀብተሚካኤል፤ ‹‹ከ2ኛው የዓለም ጦርነት በፊት የኢትዮጵያን ጠረፍ መቀነስ ላገራችን ከጉዳት በቀር ጥቅም እንዳልሰጠ፤ የፊደልም መቀነስ ስሕተትና ማስነቀፍን (አያውቁም መባልን) እንጂ፤ ዕውቀት አያስገኝም›› በሚል ንጽጽር ሁለቱንም ርዕሰ ጉዳዮች (የሀገራዊ ቋንቋና ድንበርን ዋጋ) ከፍ አድርገው አሳይተዋል፡፡
በዓለም ላይ ብቸኛ ፊደል ካላቸው ቋንቋዎች አንዱ የሆነው አማርኛ፤ ታሪካዊነቱን ከፍ የሚያደርግለት ዘመን እየመጣ ስለመሆኑ በቅርቡ በአንድ መድረክ ተስፋ ሰጪ መረጃ ተላልፏል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ ለብልጽግና አመራሮች በተዘጋጀ የስልጠና መድረክ ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው ያቀረቡትን ማብራሪያ፤ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ኢቢሲ) ጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም ምሽት ላይ በልዩ ፕሮግራም አቅርቧል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገለጻቸው መሐል፤ አማርኛ ቋንቋ ከሀገር ውስጥ ባለፈ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ልዩ ሞገስና ክብር የሚያገኝበት ዘመን እየመጣ ስለመሆኑ ነበር፤ የተለያዩ ማብራሪያዎችን እያቀረቡ የገለጹት፡፡
ከዚህኛው ቀደም ብሎም፤ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ አንደበት ከሰሞኑ የሰማነው ሌላ ትኩረት ሳቢ ጉዳይም ነበር፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት መደበኛ ባልሆነ የፓርላማ ስብሰባ፣ የፓርላማ አባላትን ሰብስበው፤ ‹‹ሀገሪቱ ወደብ እንዲኖራት ፓርላማው ለምን አይጠይቅም ?›› በሚል ያወያዩት ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ ሐሙስ ጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም፤ በሦስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ተገኝተው፤ ከፓርላማው አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ በሰጡበት ወቅት፤ ኢትዮጵያ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የባሕር በር በሚያስፈልጋት ዘመን ላይ ስለመገኘቷ ‹‹ዛሬ ዓለም ይስማው›› በሚል የአጽንኦት ቃል አመልክተዋል፡፡
አማርኛ ቋንቋ ከሀገር ውስጥም ባሻገር በሌሎች ሀገራትና ሕዝቦት ዘንድ ክብርና ተቀባይነት የሚያገኝበት ዘመን መምጣቱ እንደማይቀር መገለጹም ሆነ፤ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የባህር በር እንደሚያስፈልጋቸው በመንግስት ደረጃ ታምኖበት በግልጽ መነገሩ ልብ ያሞቃል፡፡ ተስፋና ብርታትም ይሰጣል፡፡ በታሪክ፣ በዕውቀት፣ በሀብት… ሀገሪቷ፣ መንግስታቷና ሕዝቧ እንደቀልድ የጣሉትን ‹‹ክብር›› በእርግጥ ይመለስ ይሆን ? የሚል ብቻ ሳይሆን፤ መቼ፣ እንዴት፣ ከየት፣ በማን ጥረትና ትብብር…መሰል አጓጊ ጥያቄንም ያጭራል - ጥሪው፡፡
ሀገርና ሕዝብ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የጣሉትን ‹‹ክብር›› ለማስመለስ መንግስት የመሆን ዕድል አግኝቶ መመኘትና ማሰብ ብቻ በቂ አይሆንም፡፡ ያ በቂ ቢሆን ኖሮ አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን የዛሬ 100 ዓመት፤ እንደግለሰብ ሳይሆን እንደመንግስት ‹‹የአማርኛችንን ነገር መልክ አስይዝልን›› ብለው፤ ለአለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ በጻፉት ደብዳቤ፤ ክፍተቱ ተደፍኖ ነገር ዓለሙ በተቋጨ ነበር፡፡
አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ ከአማርኛ በፊት አባቱ ግዕዝ የሚከበርበት ሥራ መቅደም አለበት ብለው የጀመሩት ጥረት እውን ሆኖ ‹‹መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ›› ለሕትመት የበቃው፣ ዝግጅቱ ከተጀመረ ከ30 ዓመት በኋላ በ1948 ዓ.ም ነበር፡፡ ያም ምኞት ተሳክቶ፣ የተጠናቀቀው መዝገበ ቃላት ለህትመት እንዲበቃ፣ የአለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ ደቀ- መዝሙር የነበሩት የደራሲ ደስታ ተክለወልድ፤ መምህር አክባሪነት፣ አደራ ጠባቂነት፣ ቀናነትና አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነበር፡፡
በአማርኛ ቋንቋ የሞክሼ ሆሄያት መቀነስና አለመቀነስን በተመለከተ፣ መግባባት ሳይቻል አንድ ክፍለ ዘመን ያስቆጠረው ጉዳይ፤ የውስጥ ችግራችንን በመግባባትና በፍጥነት መፍታት ያለመቻላችን አንዱ ማሳያ ሆኖ ሊቀርብ የሚችል ነው፡፡ በዚህ መልኩ ከዘመን ዘመን እየተንከባለሉ ለዛሬ የደረሱ ችግሮቻችን ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡ የቤታችን (የውስጣችን) ችግር የደጁን እያባባበሰብን፤ ሀገሪቱንና ሕዝቧን ለብዙ መከራና እንግልት ስለዳረጉ ጉዳዮች መናገር ቀባሪን ማርዳት ነው፡፡ ‹‹ዛሬ ዓለም ይስማው›› የተባለለት ችግራችን፤ የውስጥ ሽንቁር ሰፍቶ የተፈጠረ ነው፡፡ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ወደብ አልባ ለሆኑበት ምክንያቱ፤ ከጎረቤት ሀገራትና ከውጭ ኃይሎች የተለያየ ፍላጎት ጋር መያያዙ እንዳለ ሆኖ፤ በውስጥ የተፈጠሩ ክፍተቶችን መድፈኛ ሁነኛ ብልሐት መታጣቱም ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡
በሀገረ መንግስት ታሪካችን፤ እርስ በእርስ ካልሆነ በስተቀር፤ ከጎረቤት ሀገራትና መንግሥታት ጋር አለመግባባት በመፍጠር ብዙ አንታወቅም፡፡ እንዲህም ሆኖ ሀገሪቱና ሕዝቧ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በተያያዘ ስጋት ከሚፈጥሩ ችግሮች ነጻ የሆኑበት ዘመን ጥቂት ነው፡፡ ዛሬም ይህንን ከመሳሰሉ ስጋትና ጭንቀቶች ነጻ አይደለንም፡፡ ከቅርቡ ዘመን ታሪካችን የኢትዮ-ሶማሌ ጦርነት እና ኤርትራ ከእናት ሀገሯ እንድትገነጠል የተደረገበት ‹‹ሴራ›› ሁነኛ ማሳያዎች ናቸው፡፡
በ1969 ዓ.ም የተቀሰቀሰው የኢትዮ-ሶማሌ ጦርነትን በተመለከተ በቅርብ ያዩትን (ያለፉበትን) ታሪክ በመጽሐፍ ሰንደው ካቀረቡልን መሐል ኮ/ል ዱሬሳ ዋማ ‹‹እንዴት ሊሆን ቻለ? መልሱን ከዓይን ምስክሩ›› በሚል ርዕስ አዘጋጅተው፤ በ2015 ዓ.ም በሳተሙት መጽሐፍ፤ ከወራሪው የዚያድባሬ መንግሥት የመውረር ፍላጎት ባልተናነሰ ሁኔታ፤ ከወራሪው ጎን የቆሙ ‹‹የውስጥ ኃይሎች ሴራ››፤ ኢትዮጵያ እንድትደፈር፣ ዜጎቿ ለበዛ እንግልት እንዲዳረጉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገው እንደነበር ምስክርነታቸውን በሚከተለው መልኩ አኑረዋል፡-
‹‹… የሶማሊያ ጦር የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ በብዙ ኪሎ ሜትሮች ወደ ውስጥ እንዲገባ አስተዋጽኦ ካደረጉ ነገሮች መሐል፤ ኢህአፓ የጦሩን አባላት ለሁለት የሚከፍል አመለካከት ማሰራጨቱ አንዱ ነበር፡፡ በዚያ የሀሰት ወዥንብር በየቦታው ያለው ጦር ይዞታውን እየለቀቀ ወደኋላ እንዲሸሽ ተደርጓል፡፡ ኢህአፓ፤ ሬዲዮ ኦኘሬተር፣ ሹፌር፣ ከባድ መሣሪያ ተኳሽ የመሳሰሉትን መልምሎ፤ ‹የሶማሊያ ጦር ካቅማችን በላይ ነው› እያለ ጦሩ እንዲሸሽ የሚያደርግ ደባ ሠርቶ ነበር፡፡ ኢህአፓ ልክ እንደ ህወሓት (TPLF) ሴረኛና እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል እንዳለችው እንስሳ የሚያስብ ነበር፡፡ የኢህአፓ አባላት ሀገር የወረረው ሶማሊያን ያግዙ ነበር፡፡ ህወሓትም (TPLF) እንደዚያው የሶማሌ ጦርነት የነጻነት ጦርነት ስለሆነ ወራሪው ትክክል ነው ይል ነበር›› በሚል በቅርበት ያዩት ምስክርነታቸውን አስፍረዋል፡፡
ብዙ ሕይወት፣ ሀብትና ንብረት ከወደመ በኋላ የዚያድባሬ ወረራ ቢቀለበስም ከጥቂት ዓመታት በኋላ ‹‹ሽንቁር አስፊው የውስጥ ችግር›› በሌላ ገጽ ተከስቶ ሀገሪቷን ወደብ አልባ አደረጋት፡፡ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ በ‹‹ፍልስምና 6›› መጽሐፉ፤ በሀገራዊ፣ ሕዝባዊና ፖለቲካዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ልምድና ዕውቀታቸውን እንዲያካፍሉት ከጋበዛቸው 8 አንጋፋ የሀገራችን ሰዎች አንዱ የሆኑት አቶ ሌንጮ ለታ፤ ኢትዮጵያውያን ወንድም ሕዝባቸው ኤርትራውያንን ያጡበት ብቻ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያም ወደብ አልባ የተደረገችበት ‹‹ደባ›› የመጨረሻው ትዕይንት ምን ይመስል እንደነበር በሚከተለው መልኩ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡-
‹‹‹የለንደን ኮንፈረንስ የሚባለው› (በግንቦት/1983 በእንግሊዝ ደርግ፣ ኢሕአዴግ፣ ኦነግና ሻቢያ፣ የተሳተፉበት) በዘልማድ ኮንፈረንስ ይባል እንጂ ምንም ኮንፈረንስ አልነበረም፡፡ ኸርማን ኮህን ሁላችንም የተለያየ ክፍል ሆነን አንዳንዴ የደርግ ልዑካንን ያነጋግራል፤ ኢሳያስን ያነጋግራል፤ መለስን ያነጋግራል፡፡ አልፎ አልፎ እኛንም ያስታውሰን ነበር እንጂ ለአንድም ጊዜ በሁላችንም መሀል በጠረጴዛ ዙሪያ የተደረገ ኮንፈረንስ አልነበረም፡፡ ፕሮግራሙ ሲያልቅ ማታ ላይ ለንደን የሚገኘው የወያኔ መ/ቤት ተገናኘን፡፡ ኢሳያስ አዘዘን፡፡ ‹ ከዚህ ስንወጣ ኤርትራ እንገናኝና የኢትዮጵያን መጪ ዕድል እንወስን፤ የኤርትራንም› ብሎ ነገረን፡፡ በዚሁ መሰረትም መለስ ከአዲስ አበባ፣ እኔ ከሱዳን፣ ኤርትራ/ሰንአፌ ላይ ማታ ተገናኘን፡፡ ኢሳያስ የኤርትራን ጉዳይ በሚመለከት ግልጽ የሆነው ሀሳብ፤ ኮንፈረንሱ የኤርትራን ነጻነት እንዲቀበል ነው የተፈለገው…› ››
ሀገሪቱ፣ መንግስታቷና ሕዝቧ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ እየጣሉ የመጡት ነገር ብዙ ነው፡፡ የወደቀውን እያነሱ ያጌጡበትም ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ገጣሚ በዕውቀቱ ስዩም፤ በ1995 ዓ.ም ‹‹ኗሪ አልባ ጎጆዎች›› በሚል ርዕስ ባሳተመው የመጀመሪያ የግጥም መጽሐፉ፣ በገጽ 28 ‹‹ጣይና አንሺ›› ባለው ግጥሙ፤ የላብ ዋጋን፣ ክብርን፣ ማንነት መገለጫን፣ መመርኮዣን… መጣል ራስን ለውርደት እንደሚያጋልጥ እነዚህን ስንኞች አስፍሯል፡-
ደሞዙን ቢጥል - አንስተው ጠጡበት
ባርኔጣውን ቢጥል - ወስደው ደመቁበት
ከዘራውን ቢጥል - ተመረኮዙበት
በሄደበት ሁሉ - እየተከተሉ
በጣለው ሲያጌጡ - በጣለው ሲያተርፉ
ራሱን ሲጥል ግን - አይተውት አለፉ
ከወደብ ችግራችን ጋር በተያያዘ ‹‹ዛሬ ዓለም ይስማው›› በሚል በግልጽ ለቀረበው ጥሪ፤ ከዓለም ይልቅ ኢትዮጵያውያን ጆሮ ካልሰጠነው፤ ያለንንም አስጥለው፣ የተቀረ ክብራችንን ለመቀማት ያሰፈሰፉ አካላት ሰለባ ከመሆን የምንድንበት ዕድል አይኖርም፡፡ በድንበር፣ በወደብ፣ በቋንቋ… ያለፈው ታሪካችን እያረጋገጠልን ያለው እውነታ ይኸው ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡-
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ማግኘት ይቻላል፡፡