Saturday, 23 November 2024 20:05

በ2030 የጨርቃጨርቅና አልባሳት ንግድ ገቢን 1ቢ.ዶላር ለማድረስ ግብ ተቀምጧል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እ.ኤ.አ. በ2030 የጨርቃጨርቅና አልባሳት ንግድ ገቢን 1 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ግብ ማስቀመጡ ተገለጸ፡፡ ይህ ግብ ይፋ የተደረገው በአዲስ አበባ በተካሄደው የ2024 ዓለም አቀፍ የጨርቃጨርቅ ፎረም ላይ ነው፡፡
ኮሚሽኑ ዓለማቀፍ ኹነቱን ያዘጋጀው ከኪንግ ዴም ግሩፕ ሆልዲንግ ጋር በመተባበር ሲሆን፤ ፎረሙ የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ እድገት ለማሳየትና በጨርቃ ጨርቅ ዘርፉ ያሉ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለማስተዋወቅ ቁልፍ መድረክ ሆኖ እንደሚያገለግል ተነግሯል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዘለቀ ተመስገን፤ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ንግድ ገቢ እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል። ይህ እድገት የመጣው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመጨመርና በጨርቃ ጨርቅ ማምረቻ ላይ ያተኮሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማቋቋም ነው ተብሏል።
መንግሥት ሰፊ የኢኮኖሚ ግቦቹን ለማሳካት የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪውን ማጠናከሩን እንደሚቀጥል የተገለጸ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ምርትን በማስተዋወቅና አለም አቀፍ ኢንቨስትመንቶችን በመሳብ የጨርቃጨርቅ ዘርፉን ለሀገራዊ ገቢ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዲያበረክት ለማድረግ አቅዳለች። እንደ አለም አቀፉ የጨርቃጨርቅ ፎረም ያሉ ዝግጅቶች ደግሞ ኢትዮጵያ የጨርቃጨርቅ ኢንቨስትመንቶች ዋነኛ መዳረሻ መሆኗን ለማሳየት ወሳኝ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

Read 535 times